
አዲስ አበባ፡– በትግራይ ክልል የሚስተዋለው የግል ጥቅም አሳዳጅነትና ሥልጣን ወዳድነት በክልሉ አስከፊ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጉን ፖለቲከኛው አቶ ጠዓመ አርዓዶም አመለከቱ። በክልሉ ዳግም ጦርነት ከተጀመረ እጅግ አውዳሚ እና የሕልውና ስጋት የሚፈጥር እንደሆነ አስታወቁ።
አቶ ጠዓመ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የግል ጥቅም እና ሥልጣን ወዳድነትን ተከትሎ በሚፈጠሩ ግጭቶች ክልሉ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት በማወክ ሰሞኑን የተፈጠረው የችሎት ብጥብጥ የክልሉ ሁለንተናዊ ውድቀት ማሳያ ነው። ትግራይ ከገባችበት ችግር እንድትወጣ በክልሉ ብሔራዊ ዕርቅ እና አንድነት በአፋጣኝ መደረግ አለበት ብለዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ለብሔራዊ ዕርቅ እና አንድነት ጥሪ ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም በፍጥነት ተግባራዊ መሆን እንዳልቻለና ከጉዳዩ ክብደት አንጻር ጊዜ የሚሰጠው ሊሆን እንደማይገባ አመልክተዋል።
የትግራይ ሕዝብ ከጦርነቱ ወዲህ በከባድ ጭንቀት እና ጫና ውስጥ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ ጠዓመ፤ በመሆኑም የማያግባቡ አጀንዳዎችን ወደ ጎን በመተው አንድነትን በሚፈጥሩ ጉዳዮች እና የሕዝብን ጥቅም በማስከበር ላይ ትኩረት በማድረግ የጦርነት ወሬ እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ማስቆም ይቻላል ብለዋል።
በፖለቲካው ዙሪያ ውስጣዊ ልዩነት በአግባቡ ማስተናገድ ባለመቻሉ፤ ለግል ጥቅምና ሥልጣን ሲባል በተፈጠረው ግጭት እያደገ በክልሉ አሁን ያለው አስከፊ ገፅታ ሊፈጠር መቻሉን ገልጸዋል።
ትግራይ አሁን በተያዘው መንገድ ከቀጠለች ወደ ከፋ ጦርነት ትገባለች ያሉት አቶ ጠዓመ፤ ምናልባትም ከእዚህ ቀደም አይታው የማታውቀው በዞን ደረጃ የመከፋፈል እጣ ፈንታ ሊገጥማት ይችላል ብለዋል። በደቡባዊ ዞን እየታየ ያለው የፖለቲካ ለውጥ የእዚህ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በክልሉ ዳግም ጦርነት ከተጀመረ እጅግ አውዳሚ እና የሕልውና ስጋት የሚፈጥር በመሆኑ ከወዲሁ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ነው ያሉት።
የክልሉ አሁናዊ ሁኔታ እና አሁን የሚስተዋሉት የተለያዩ ችግሮች መከሰት ዋና መነሻው ፖለቲካዊ ውድቀት እንደሆነ ጠቅሰው፤ የእዚህ መነሻም ሕወሓት (በቅርቡ በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ፓርቲ) በውስጡ ያጋጠመው የመምራት ችግር እንደሆነ ተናግረዋል።
በመሆኑም ሁኔታውን በማጤን በአፋጣኝ ወደ ብሔራዊ ዕርቅ ካልተገባ፤ ጦርነቱ በትግራይ ጀምሮ የሚያቆም ሳይሆን ወደ ኤርትራ እንዲሁም ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እና ሱዳንን ጨምሮ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ተስፋፍቶ ሌላ ጂኦግራፊካል ኮንፌዴሬሽን ሊፈጥር ይችላል ብለዋል፤ ትግራይ ለራስዋ እና ለሌሎች ስጋት እንዳትሆን እርስ በርስ መነጋገር እና በክልሉ ብሔራዊ ዕርቅ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም