
አዲስ አበባ፡- በበጀት ዓመቱ በሀገር ደረጃ 17 ሚሊዮን ሕዝብ የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። የተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ፤ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ተደራሽነት ችግር መኖሩን አመለከተ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 32ተኛ መደበኛ ስብሰባ፤ አባላቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በዋና ዋና ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ተደራሽነት ችግር መኖሩን አመልክተዋል።
የውሃ አካላት ደህንነትን ከመጠበቅ ፣ ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ዘላቂ የውሃ አማራጭ እንዲኖር ከመሥራት አኳያ ምን ሥራዎች እየተሠሩ ነው፤ እንደ ሀገር የንጹህ ውሃ አቅርቦት መቶ በመቶ የሚረጋገጠው መቼ ነው?
የውሃ አካላት ደህንነትን በመጠበቅ ረገድ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚገኙ ወንዞች እና ሀይቆች በእንቦጭ መጤ ወራሪ አረም እየተጠቁ ነው፤ ችግሩ በገጸ ምድር የውሃ ሽፋን ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት አንጻር ችግሩን በሰው ኃይልና በዘመቻ ብቻ ሊቀረፍ ይችላል ወይ የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ ዶ/ር ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው፤ በበጀት ዓመቱ በሀገር ደረጃ 17 ሚሊዮን ሕዝብ የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ያለው ሀገራዊ የውሃ ተደራሽነት 76 በመቶ መድረሱን አመልክተው፤ እ.አ.አ በ2030 ውሃ ተደራሽነትን መቶ በመቶ ለማሳካት ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
በከተሞች የሚታየውን የውሃ ችግር ለመፍታት የውሃ ሀብት የሌላቸው ከተሞች በዙሪያቸው ካሉ አካባቢዎች አቅርቦት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እንደ አንድ መፍትሔ ተደርጎ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሌሎች አካባቢዎች የሚታዩ የአቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት የሚጠይቀውን የበጀት ፍላጎት ለማሟላት እየሠራ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፤ የውሃ እጥረት በሚታይባቸው አካባቢዎች ዜጎች በራሳቸው አቅም የዝናብ ውሃን የማሰባሰብ ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባም አስታውቋል፡፡
የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማረጋገጥ የገጸ-ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ መረጃ አያያዝን በማጠናከር ለማዘመን እና ተዓማኒ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሀገር የውሃ አካላቶች ትልቅ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ጠቁመው ፤ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በጥናት የተደገፉ ሥራዎች ከመሥራት ባሻገር በወንዞች ዳርቻ ላይ የሚገኙ ተቋማት ኃላፊነት ወስደው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በትብብር እንዲሠሩ ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም፤ የውሃ ሀብት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ከፍተኛ በጀትን የሚጠይቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ለሌሎች የልማት ሥራዎች የሚሰጠውን ትኩረት ያክል ይህም ቅድሚያ ተሰጥቶት የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁ በየክልላቸው ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማረጋገጥ የባለቤነት ድርሻውን በመውሰድ በጋራ ሊሠራበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው 32ተኛ መደበኛ ጉባኤ የሥርዓተ-ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ አዋጅ 18/2017 እና የባለ ብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ 19/2017 ለውይይት ቀርበዋል፤ የምክር ቤቱ አባላትም በአዋጁ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየት በመስጠት፤ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡
በሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም