ዘንድሮ የመጅሊስ ምርጫ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ይደረጋል

አዲስ አበባ፦ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለቀጣይ አምስት ዓመታት መጅሊስን የሚመሩ አካላትን ለመምረጥ በሚያካሂደው ምርጫ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ አስታወቀ።

“ምርጫ ለፅኑ ተቋም” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለምርጫ አስፈጻሚዎች የግንዛቤ ማስጨበጫና የምርጫ ማስመዝገቢያ ሂደት ጅማሮ በሚሊኒየም አዳራሽ ትናንት ተካሂዷል።

የመጅሊስ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ሰብሳቢ ዶክተር አብዱልአዚዝ ኢብራሂም በወቅቱ እንዳስታወቁት፤ ጠቅላይ ምክር ቤቱ የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ እንዲቋቋም እና የምርጫ አፈጻጸም መመሪያ እንዲዘጋጅ አድርጓል። በእዚህ መሠረት ቀጣዩ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ምርጫ በሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደሮች የሚካሄድበት አሠራር ተዘርግቷል።

ምርጫው በአራት ክላስተር እንደሚከናወን እና የቅድመ ምርጫ ሥራዎች እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አብዱልአዚዝ፤ በዘንድሮ የመጅሊስ ምርጫ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረግ የምርጫ ሂደቱን ተዓማኒነት ይበልጥ የማጠናከር ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

የቀድሞ የእስልምና ጉዳዮች ምርጫ ሂደት ወጥ የሆነ መዋቅር እና አሠራር እንዳልነበረው እንዲሁም ወረቀት ተኮር እንደነበር የገለጹት ዶክተር አብዱልአዚዝ፤ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ባለባቸው አካባቢዎች የሚደረገው የመጅሊስ ምርጫ ዲጂታል እንደሆነ አስታውቀዋል።

የቴሌኮም መሠረተ ልማት ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች ደግሞ ምርጫው በወረቀት እንደሚከናወን ገልጸው፤ የዘንድሮ ምርጫ መጅሊሱ በአዋጅ ሕጋዊ እውቅና ካገኘ በኋላ የሚደረግ በመሆኑ እና ወጥ የምርጫ ሂደት ያለው በመሆኑ ምርጫው ታሪካዊ ነው ብለዋል።

ይህም በኢትዮጵያ እስልምና ታሪክ የተደራጀ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊና አካታች ምርጫ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው፤ ምርጫውን ውጤታማ ለማድረግ ከሰባት ሺህ በላይ ለሚሆኑ የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መካሄዱን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልል ተወካዮች የምርጫ ሰነድ ርክክብ አድርገዋል፤ ምርጫውን ለሚዘግቡ መገናኛ ብዙኃን የዘገባ ፍቃድ ተሰጥቷል ያሉት ዶክተር አብዱልአዚዝ፤ የምርጫ አስፈጻሚዎች የኡማውን(የአማኙን) አንድነት በመጠበቅ ረገድ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለቀጣይ አምስት ዓመታት መጅሊስን የሚመሩ አካላትን ለመምረጥ በሚያካሂደው ምርጫ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ያቀረቡት ዶክተር አብዱልአዚዝ፤ ሕዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን፣ መከባበሩ እና ትብብሩን ጠብቆ የጋራ ተቋሙን በጋራ ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የቦርዱ አባላትና አመራሮች፣ የመጅሊሱ አመራሮች፣ ዑለሞች የማህበረሰብ መሪዎችና በየደረጃው ያሉ የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ተገኝተዋል። ምርጫው በሐምሌ ወር እንደሚካሄድም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

በሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You