
አዲስ አበባ፡- የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል የሀገር ውስጥ የቆዳ ምርት ተጠቃሚነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
በ2014/15 በጀት ዓመት በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ልማት ማእከል የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን መነሻ በማድረግ ከትናንት በስቲያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጓል።
በወቅቱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ እንዳስታወቁት፤ የሀገር ውስጥ የቆዳ ምርቶችን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንጻር ማእከሉ በትኩረት ሊሠራ ይገባል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ አምራችነት ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ ከመሥራት ጎን ለጎን፤ በሀገር ውስጥ የተመረተ ምርት ዜጎች ፈልገው እንዲጠቀሙ የንቅናቄ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ አመልክተው፤ አስፈላጊ ከሆነ የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም እንደ ሕግ ሊደነገግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በሀገር ውስጥ በስፋት ምርቶች እየተመረቱ ቢሆንም፤ የመጠቀም ሁኔታ ዝቅተኛ ነው ያሉት ምክትል ሰብሳቢዋ፤ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አንጻር እንደ ሀገር የጥራት ችግር የለም። ነገር ግን አዳዲስ ፋሽኖችን ተከታትሎ እንደ ተጠቃሚው ፍላጎት የማቅረብ ክፍተት አለ፤ ክፍተቱን ለመሙላት መሥራት ይገባል ብለዋል ማእከሉ ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጀት መሥራት እንደሚገባው፤ የአዋጭነት ጥናት በተመለከተ በኦዲት ግኝቱ የተቀመጠውን ግኝት መሠረት በማድረግ እንዲሠራ አሳስበዋል። ተቋሙ በካይዘን የሥራ አመራር እንደመመራቱ መጠን ለሌሎች ተቋማት አርአያ ለመሆን በአግባቡ መሥራት እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው፤ በማእከሉ በቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ላይ ለተሠማሩ ኢንዱስትሪዎች በሚሰጠው የአቅም ግንባታ ፣ ለኢንዱስትሪ የሚያደርገውን የግብዓት ቅብብሎሽ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የተሠሩ የቅንጅት ሥራዎችን ትኩረት በማድረግ የኦዲት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በኦዲት ወቅት የሚሰጡ ሥልጠናዎች ክፍተቶችን መሠረት ያደረጉ እንዳልሆነ ተለይቶ አቅጣጫ ተቀምጧል። ከተሠጠው አቅጣጫ በኋላ ሥልጠናዎች መሰጠታቸው ከማእከሉ በኩል የተገለጸ ቢሆንም፤ በሥልጠናው የተገኘው ውጤት አልተገለጸም። ስለዚህ በዘርፉ የሚሰጡ ሥልጠናዎች በጥናት መደገፍ አለባቸው ብለዋል።
ለጥሬ ቆዳ እና ለሌጦ ምርት የሚሆኑ የኬሚካል ግብዓቶች በምንዛሪ እጥረት ምክንያት ስላልተሟሉ የማምረት ሂደቱን ለማቆም የተደረሰበት አጋጣሚ መኖሩን በማንሳት፤ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን በበቂ ሁኔታ ማሟላት አስቸጋሪ ስለሆነ እነዚህን ግብዓቶች በሀገር ውስጥ የማምረት ሥራ መጀመር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከጫፍ እንደደረሰች ጠቅሰው፤ ከእዚህ አንጻር የሚመረቱ የቆዳ ምርቶች በጥራት እና በዲዛይን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ካልሆኑ፤ የሌሎች ሀገራት ምርት ተቀባይ ብቻ ሆነን ስለምንቀር ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችሉ ምርቶች ላይ እንዲሠራ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት የሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ሁኔታ እያደገ መሆኑን የጠቆሙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፤ ከቆዳ ምርት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሱቆች ከፍተው ምርቶችን በዶላር እየሸጡ ያሉ አምራቾች እንዳሉ እና በአሜሪካም ምርቶቹ እየተሸጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የሀገር ውስጥ ምርት መጠቀም እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ተጠቃሚዎች ከጥራት አንጻር ምንም ጥርጣሬ ባይኖራቸውም፤ የዋጋ ውድነት ግን እንዳለ ያነሳሉ ብለዋል። የተቋማት የግዢ ሁኔታ አሁንም እንዳልተስተካከለ እና በርካታ ተቋማት ምርቶችን የሚያስገቡት ከውጭ ሀገራት እንደሆነ ጠቅሰዋል። የተሰጡትን የማስተካከያ አቅጣጫዎች በመከተል ይህን ባሕል መቀየር እንደሚቻል ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም