ኢትዮጵያ እኤአ በ2025 ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ 10 የአፍሪካ ሀገራት ግንባር ቀደም መሆኗ ተገለጸ

አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ በ2025 ፈጣን ዕድገት ከሚያሳዩ 10 የአፍሪካ ሀገራት ግንባር ቀደም መሆኗን የዓለም የገንዘብ ፈንድ መረጃ (IMF) አስታወቀ። በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በወሰዷቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ በተፈጥሮ ሀብት አቅምና ባላቸው የወጣት ብዛት ምክንያት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያሳዩ መሆኑን አመለከተ።

የዓለም የገንዘብ ፈንድ መረጃ (IMF) ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ 10 የአፍሪካ ሀገራት ከዓመት ዓመት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) አፈጻጸም አንፃር የአፍሪካን ዕድገት እየመሩ ነው። ከሀገሪቱ መካከልም ኢትዮጵያ 8 ነጥብ 1 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት (GDP) በማስመዝገብ እየመራች ትገኛለች።

ይህ ዕድገት በመሠረተ ልማት፣ ኢንቨስትመንት፣ በግብርና ምርታማነትና መሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ በመሥራት የተገኘ መሆኑን ያመለከተው የዓለም የገንዘብ ፈንድ፤ከ108 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ የእዳና የዋጋ ንረት ስጋቶች ቢኖሩባትም በመንግሥት የሚመራውን የልማት ሥራዎችን ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል።

ሴኔጋል 6 ነጥብ 7 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት በማስመዝገብ ተስፋ ከተጣለባቸው ሀገራት መካከል መሆኗን ጠቁሞ ፤በቅርቡ በሚጀመረው የነዳጅ እና ጋዝ ምርት ምክንያት የሴኔጋል ኢኮኖሚ የሀገር ውስጥ ምርት ወደ 8 ነጥብ 4 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል ብሏል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፣ 6 ነጥብ 5 በመቶ፣ ኡጋንዳ 6 ነጥብ 3 የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ማስመዝገባቸውንም አመልክቷል ። በአገልግሎት እና በወርቅ ምርት የሚመራው የኡጋንዳ ኢኮኖሚ በ2024 የዋጋ ንረት ወደ 3 ነጥብ 2 በመቶ ዝቅ መድረጉንም ጠቁሟል።

ኮትዲቯር የካሼው እና የካካዋ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ኢኮኖሚዋን 6 በመቶ ማሳደጓን አስታውቋል። ዕድገቱ በ2025 ወደ 6 ነጥብ 3 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል።

ጋና በግንባታ፣ ማዕድን በማውጣትና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ባስመዘገበችው እድገት ፣ 5 ነጥብ 7 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት አስመዝግባለች ፤በእዚህም አጋጥሟት ከነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ ማገገሟን አስታውቋል።

ታንዛኒያ 5 ነጥብ 4 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት በማስመዝገብ ኢኮኖሚዋ የተረጋጋና ሁለገብ ሆና ቀጥላለች።

ኬንያ 4 ነጥብ 5 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት በማስመዝገብ ጥሩ የሚባል ዕድገት አስመዝግባለች ብሏል።

ኬንያ በብድር አቅርቦትና በዝቅተኛ የዋጋ ንረት አማካኝነት ኢኮኖሚዋ የማገገም ተስፋ ያሳየ ከመሆን ባለፈ በአህጉሪቱ ቁልፍ የቴክኖሎጂ እና የንግድ ማዕከል ሆና መቀጠሏን አመልክቷል።

አንጎላ 4 ነጥብ 5 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት አስመዝግባ ከነዳጅ ምርት ባለፈ ኢኮኖሚዋን መዘወር ችላለች ያለው መረጃው፤ ማሊ 4 ነጥብ 4 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ማስመዝገቧን አስታውቋል። ምንም እንኳን የማሊ ኢኮኖሚ በመዋቅራዊ ችግሮች ቢገደብም፤ ተስፋ ካላቸው ሀገራት መካከል ሆናለች ብሏል ።

የማዕድን ሀብትና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ቀጣይነት ያለው ትግበራ በመላው አህጉሪቱ ዕድገትን እያመጣ መሆኑን አመልክቶ፤ የዋጋ ንረት፣ ከፍተኛ ዕዳ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችና የፖለቲካ አለመረጋጋት ያሉ ችግሮች አሁንም ለዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን አመልክቷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You