በአስቴር ኤልያስ
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኢንቫይሮሜንታል አንትሮፖሊጂ ሠርተዋል – ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡፡ በትግራይ ክልል ከወረዳ እስከ ክልል ባሉ መዋቅሮች ውስጥ ከ1995 ጀምሮ በባለሙያነትና በኃላፊነት ደረጃም አገልግለዋል፡፡ በክልል ደረጃ የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በድርጅትም የገጠር ዘርፍ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ወይዘሮ ኬሪያ ከወራት በፊት ደግሞ በፌዴራል ደረጃ የቀድሞው አፈ ጉባኤ አቶ ያለው አባተ ለምክር ቤቱ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተከትሎ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ሆነው መሾማቸው ይታወቃል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከወይዘሮ ኬሪያ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ሲከሰቱ ቆይተዋል፡፡ የባንዲራ ቀንም ግጭት እንዳይቀሰቀስ በሚል የተከበረው በአደባባይ እንዳልሆነ ይታወቃል፤ የዘንድሮውን 13ኛውን የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ችግሩ ተፈትቶ ነው በዓሉን በአዳባባይ ለማክበር የታሰበው?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- በእርግጥም እንዳልሽው በሁሉም አካባቢ ባይባልም በውስጡ ጥላቻ፣ መጠራጠርና ቅሬታ መኖሩ አይታበልም፡፡ መተማመን የተሸረሸረበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ ከዚህም አልፎ በተቀሰቀሱ ግጭቶች የዜጎች ህይወት አልፏል፤ በመቶ ሺዎችም የተፈናቀሉበት አካባቢ አለ፡፡ በማንነታቸውና በብሄራቸው ምክንያት የተጠቁም በጣም ብዙ ናቸው፡፡
ስለዚህ እነዚህ አካላት በማንነታቸው ምክንያት ተጠቅተው እያለ ማንነታችሁን ከፍ አድርጋችሁ የምታሳዩበት በዓል ነው ብሎ ለመናገርም በራሱ ይከብዳል፡፡ እኛም ይህን አስበንበታል፡፡ በዚህ ጉዳይ በቁርጠኝነት መሥራት የሚያስፈልገው ቀደም ሲል እንጂ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ‹‹በዓል አለና ፤ እንደለመድከው በማንነትህ ተደስተህና ኮርተህ አክብር›› ለማለት ይከብዳል፤ በቅድሚያ ያለውን ቁርሾ መፍታት ያለብን እንዴት ነው በሚል በሁሉም አካባቢ ተንቀሳቅሰናል፤ እየተንቀሳቀስንም ነው፡፡
የመንቀሳቀሳችን ዋና ግቡም ሰላምና መረጋጋትን እንፍጠር፤ ብዝሃነት ስጋት አይደለም፡፡ ማንነት ወደግጭት የሚመራ አይደለም ለማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ማንነትን ማንም ሊያጠፋው አይችልም፤ አብሮ የሚኖርና ትውልድ የሚቀባበለው ጉዳይ ነው፡፡
የመቻቻላችን የመሸርሸሩ ምክንያት ምንድን ነው በሚል በመቻቻል ዙሪያ ጽሑፍ አዘጋጅተናል፡፡ ለምሳሌ ቀደም ሲል ስልጠና ይሰጥ የነበረው ይበልጥ በህገ መንግሥቱና በፌዴራል ስርዓት ላይ ነበር፡፡ ይህን ቀየር በማድረግ በብዙህነት ላይ የተመሰረተው መቻቻላችን እንዴት ነበር ? አሁንስ እንዴት ነው የምናስቀጥለው? ባህላዊም ሆኑ የኃይማኖት ተቋማት ግጭት ሲፈጠር በራሳቸው የሚዳኙት እንዴት ነበር? እነዚህ ባህላዊ እሴቶቻችን ግጭት ሲፈጠር በቀላሉ የሚያመክንቡት የየራሳቸው ስልት አላቸውና ይህን ተጠቅመን በውስጣችን ያለውን ችግር እንዴት ነው መፍታት የምንችለው? በሚሉት ዙሪያ በተለያዩ አካባቢዎች እየዞርን መድረክ አዘጋጅተናል፡፡
ክልል ከክልል ጋር በአጎራባች ህብረተሰብ አማካይነት ተገናኝቶ እንዲሁም አመራር ከአመራር ጋር ተገናኝቶና አወያይቶ እርቀ ሰላም መፈጠር አለበት፡፡ እርቅና ሰላም ከተፈጠረ በኋላ የተወሰነ መረጋጋት ሲታይ በዓሉን እናከብረዋለን፡፡ እንደሚታወቀው ቀደም ሲልም የበዓሉን መከበር የወሰነው ህዝብ ነው፤ይቅር ከተባለም የሚያስቀረው ህዝብ ነው፡፡ በዓሉ መከበር አለበትም ከተባለ ያው የህዝብ ውሳኔ ስለሆነ ይከበራል ማለት ነው፡፡
መድረኮቹን ለማካሄድ በተንቀሳቀስንበት ወቅት በስብስቡ ውስጥ የተካተቱት የሲቪክ ማህበራት አመራር፣ የሴቶችና የወጣቶች አደረጃጀቶች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትና እውቅና ያላቸው አካላት ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የተወያዩ ህዝብ ግብረ መልስ ምን ይመስል ነበር?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- በአብዛኛው ዘግይታችኋል የሚል ነበር፡፡ ችግር ከተፈጠርና ይህን ያህል ርቀት ከሄድን በኋላ ነው የመጣችሁት ብለውናል፡፡ አሁንም በዚህ ብቻ የሚፈታ ሳይሆን የህግ የበላይነት መከበር አለበት ሲሉም የጠየቁም እንዲሁም ህግ የተላለፉትንም አጋልጠው እንደሚሰጡም የሚናገሩ አሉ፡፡
ተወያዮቹ ‹‹ህዝብ ለህዝብ አልተጋጨንም›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህም በእኛ አታመካኙ ብለዋል፡፡ አመራር ነን የምትሉት እናንተ ራሳችሁ መጀመሪያ መስተካከል አለባችሁ ፤እያጣላችሁን ያላችሁት እናንተው ናችሁ ሲሉን ነበር፡፡ ስለዚህ መድረክ ፍጠሩልን፤ እናንተ መደረኩን ከፈጠራችሁልን ችግሩን ለቅመን እንነግራችኋለን፡፡ በህግ የሚጠየቅ በህግ፤ በእርቅ መንገድ የሚሄደውም በእርቅ ኢንዲፈጸም እናደርጋለን የሚል ተስፋ ሰጪ የሆነ አስተያየት ሰጥተውናል፡፡ በዚህም መልካም ተስፋ በመታገዝ ነው በዓሉን ለማክበር የተዘጋጀነው፡፡ ውይይቱን ከበዓሉ በኋላም እንቀጥልበታለን፡፡
በበዓሉ ላይ ችግር እንዳይፈጠር የጸጥታ አካላት ይሰማራሉ፤ አብይ ኮሚቴም አለ፡፡ ለጸጥታ አካላቱ እቅዶቻችንን አሳይተናቸዋል፡፡ ስለዚህም እነርሱ በራሳቸው ይዘጋጃሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በዓሉን ለማክበር ሙሉ በራስ መተማመን አለ ወይ የሚል ጥያቄ መነሳቱ ግን አግባብ ነው፡፡ ክልሎች በእርግጥ እንዴት ነው በዓሉን ማክበር የምንችለው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ አሁንም ቢሆን በአገሪቱ መረጋጋት በተፈለገው መጠን የለም የሚለው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ በዓሉን በሙሉ ልብ ያለምንም ችግር በመግባባት ማክበር የሚያስችል ሁኔታ አለ ማለት ይቻላል?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- አሁንም በእርግጥ ብዙ ያልፈታናቸው ነገሮች አሉ፡፡ ሁሉንም ህዝብ አሰባስበን የሆነ ችግርስ ቢፈጠር የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡ ነገር ግን ከጸጥታ አካሉ ጋር መወያየት ያስፈልጋል፡፡ አይ አያስፈልግም ስጋት ነው የሚባል ከሆነ ደግሞ ክልሉ ራሱ ይወስናል፡፡ ምክንያቱም የብሄር ብሄረሰቦች በዓል የሚከበረው ሰላም ስር እንዲሰድ፣ መቻቻል ይበልጥ እንዲጎለብት፣ አብሮነትና ፍቅር እንዲዳብር ለማድረግ ነው እንጂ ወደ ግጭት የሚመራ መሆን የለበትምና የሚወስነው ክልሉ ራሱ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምናልባት አንድም ሆነ ሁለት ያህል ክልል ስጋት አለብኝና አልመጣም ቢል በዓሉ ይከበራል?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ለምሳሌ ክልሎች ወደዚህ እንደሚመጡ ተረጋግጧል፤ በዚህ በኩል ችግር የለም፡፡ ችግሩ በዓሉን በዚያው በክልሉም አክበሩ በማለታችን ነው፡፡ እንደሚታወቀው በዓሉ የመከበሩ ምስጢር አንድ ነን፤ አንለያይም ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ ግጭት በተፈጠረበት አካባቢ እርቅና ሰላም ፈጥረን በጋራ በዓላችንን እናክብር የሚል ነው፡፡ እርቅ ከተፈጸመ በኋላ ህዝቡ ለምሳሌ በሁለት ክልል መካከል አጎራባች ያሉ የተኳረፉ ህዝቦች ካሉ ታርቀው ደስታቸውን በጋራ እንዲገልጹ ለማድረግ አስበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከየክልሎቹ ያገኛችሁት ግብረ መልስ ታድያ ምን ይመስላል?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ገና ነው፤ ክልሎቹ ምላሽ አልሰጡንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የማንነት ጉዳይ ዛሬም ድረስ ጥያቄ ሆኖ እየቀረበ ነው፤ ችግሩ የሚፈታበት አግባብ እንዴት ነው?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- የማንነት ጥያቄዎች የህዝብ አንድነትን ሊሸረሽሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ስለሚያስከትል እንዲሁም አብዛኛዎቹ ግጭቶች የማንነት መልክ እየያዙም ስለሆነ በዚህ ዙሪያ በስፋት መወያየቱ መልካም ነው፡፡ በማንነት ጥያቄ ላይ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግም ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህን የምንመለከተው የፌዴሬሽን ስልጣን ወይም ህግ ሲባል ምን ማለት ነው ከሚለው አንጻር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በፊት የነበሩ ጥያቄዎች በምን አግባብ ነበር ሲመለሱ የነበረው? ምንስ ያህል ርቀት ሄደዋል? የሚለውንም አንስተን ህዝቡ እንዲያውቃቸው ማድረጉ በጣም ይጠቅማል፡፡
እንደሚታወቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገ መንግሥቱ የተሠጠው ስልጣን አለው፤ በተለይ በአንቀጽ 61 መሰረት በፌዴራል መንግሥት አባል ክልሎች የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በወከሏቸው አባላት ነው ምክር ቤቱ የሚወስነው፡፡ ስለዚህ ከማንነት አንጻር ደግሞ በተለይ በህገ መንግሥቱ በዝርዝር የተቀመጡ ስልጣኖች አሉ፡፡ በዚህ ተግባርና ስልጣን ከተሰጠው መካከል አንዱ ደግሞ ለማንነት ጉዳይ ምላሽ መስጠት ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ህገ መንግሥቱ ያስቀመጠው ማንኛውም ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ወይም ማንኛውም ማህበረሰብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቴን በአግባቡ አልተጠቀምኩም፤ ወይም ደግሞ ቋንቋዬን የማሳደግ አሊያም በቋንቋዬ የመጻፍ መብት አልተሰጠኝም፤ ባህሌን የማሳደግ ዕድል ተነፍጌያለሁ የሚል ጥያቄ ካደረበት ፌዴሬሽኑ በህገ መንግሥቱ መሰረት ይወስናል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንጻር የማንነት ጥያቄ ህገ መንግሥታዊ መብቱ ነው ማለት ነው፡፡ መጠየቁ ኃጢዓት አይደለም፤ የሚያሸማቅቅም አይሆንም፡፡
እዚህ ላይ ግን ሁሌም ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ ምክር ቤቱ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን ሁሉ በቅድሚያ ምላሽ የመስጠት ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ከአንድ አካባቢ ቀጥታ ወደዚህ የመጣ ጥያቄ የመመለስ ህጋዊ መብት የለውም፡፡ ምክንያቱም የራሱ የሆነ ሂደት ስላለው ጥያቄው ያንን ተከትሎ እስካልመጣ ድረስ ጉዳዩን የመመለስ ስልጣን አልተሰጠውም፡፡
ሌላው ደግሞ የሚቀርቡት ጥያቄዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ማለትም ቀበሌ ከነበረ ወደ ወረዳ፣ ወረዳ ከነበረ የዞን አሊያም በእገሌ ዞን ውስጥ ያሉ እገሌ እገሌ ቀበሌዎች ወደኔ ነው መምጣት ያለባቸው የሚሉ ዓይነት ጥያቄዎች ሊሆኑ ይችላሉ ወደ ምክር ቤቱ የሚመጡት፡፡ ይሁንና ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሳይሆን የክልል ስልጣን ነው፡፡ መመለስም ያለበት ክልል ነው፡፡
ታድያ ፌዴሬሽኑ የሚመልሰው እንዴት ነው የተባለ እንደሆነ በህገ መንግሥቱ የተሰጠው ስልጣንና ተግባር እሱን ለመዘርዘር የወጣ አዋጅ ቁጥር 251/93 አማካይነት ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ የሚመለሰው እሱን መሰረት አድርጎ ነው፡፡ እዚህ አዋጅ ላይ የማንነት ጥያቄ መጠየቅ መብት እንደሆነ ሁሉ መስፈርት የማሟላት ግዴታ እንዳለም ያመለክታል፡፡ እነዚህ መብትና ግዴታዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ከተፈጸሙ ፌዴሬሽኑ ወዲያውኑ ጥቄውን ይመልሳል፡፡ ሁለቱ ካልተጣጣሙ ግን ፌዴሬሽኑም ሆነ ክልል ሊመልሰው አይችልም፡፡ ከዚያ በኋላ ጉዳዩ የግጭት መንስዔ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ በክልሉ የሚነሱ ማንኛቸውንም ጥያቄዎች የየክልሉን የመስተዳድር እርከኖች አሟጠው መመልክት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በቀበሌ አሊያም በወረዳ ደረጃ ከሆነ እዚያ ያለው ህዝብ ምክር ቤትም ሆነ የመስተዳድር እርከን ስላለው እዚያው ሂደቱን ጨርሶ ወደ ክልል ማድረስ ይኖርበታል፡፡ ክልል ደግሞ የመጣለትን የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ አጥንቶ መልስ ይሰጣል፡፡ በመልሱ እርካታ የሚገኝ ከሆነ እሰየው፤ እርካታ ካልተቻለ ግን በይግባኝ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይመጣል፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ይህን ሂደት አልፎ ሲመጣ ነው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ወደ ውሳኔ የሚገባው፡፡ ይህም አንደኛው አካሄድ ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ክልሉ አቤቱታው ቀርቦለት ከሁለት ዓመት በላይ ካሳለፈ ቀጥታ ጥያቄው ወደ እኛ ይመጣና ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ ምላሽ የሚሰጥበት አካሄድ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ጣልቃ ሲገባ ምላሽ ከመስጠቱ በፊት የሚያረጋግጠው መስፈርት አለ፡፡ ይኸውም የመጀመሪያው ነገር ጥያቄው የህዝብ መሆኑን የሚያረጋገግጥ ማስረጃ ማለትም ከማህበረሰቡ አምስት በመቶ ያህሉ ጥያቄ አለን በማለት የተፈራረመበት ወረቀት ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ በሻገር ትክክለኛ አድራሻና የመስተዳድሩ ማህተም ያለበትን ማስረጃ ያካተተ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
ተወካዮች በትክክል ከህዝብ መወከላቸውን የሚያመላክት ማስረጃ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ካልተሟላ ጉዳዩ ውድቅ ይደረግና አሟልተው እንዲያመጡ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህም ፌዴሬሽኑ ለዚህ አሠራር አዲስ አይደለም፤ እስከአሁንም ይህንን መሰረት በማድረግ የማንነት ጥያቄዎችን ሲመልስ ቆይቷል፡፡
ለምሳሌ በመጀመሪያው ፓርላማ የነበሩት ብሄር ብሄረሰቦች 56 ናቸው፡፡ ከእነሱ የተወከሉ ደግሞ 108 የፌዴሬሽን ምክር አባላት ነበሩ፡፡ የማንነት ጥያቄዎች ህግና ስርዓትን ተከትለው እየመጡ ምላሽ ማግኘት በመቻላቸው ግን የብሄር ብሄረሰቦች ቁጥር ወደ 76 ከፍ ብሏል፡፡ ይገባችኋል ተብሎም ጥያቄያቸው ምለሽ በማግኘቱም በዚያው ልክ ተወካዮቻቸውን ስለሚልኩ የተወካዮቹ ቁጥር ደግሞ 153 ደርሷል፡፡
ስለዚህም ፌዴሬሽኑ በዚህ ዓይነት ሁኔታ በርካታ የማንነት ጥያቃዎችን ሲመልስ ከርሟል፡፡ ሲመልስ ግን አፋጣኝ በሆነ መልኩ ነበር ወይ ቢባል፤ አይደለም ነው መልሱ፡፡ ብዙ ግጭት ከተከስተ እና ደም ከፈሰሰ በኋላ ነበር ምላሽ ሲሰጥ የቆየው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለእዚህ እንደ ማሳያ ሊጠቅሱ የሚችሉት ይኖር ይሆን?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ለምሳሌ የስልጤ፣ የቅማንት እንዲሁም ሌሎችም አሉ፡፡ ከብዙ ደም መፍሰስና ግጭት በኋላ ምላሽ የተሰጣቸው አሉ፡፡ ስለዚህ ችግር አልነበረበትም ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ ችግር ግን ፈጥነን መውጣት አለብን፡፡
ደም አፋሶ መልስ የተሰጣቸው ቢኖሩም፣ መልስ ያልተሰጣቸው ደግሞ በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የደንጣ ማህበረሰብ ከብዙ ዓመት በኋላ ቆይቶ የማንነት መስፈርቱን አላሟላችሁም በሚል ከብዙ እንግልት በኋላ አይገባችሁም የሚል መልስ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተመሳሳይ አሁንም ያልተመለሱ አሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ እስከ አሁን ድረስ ሃያ የማንነት ጥያቄዎች መመለሳቸውን ልብ ይሏል፡፡
አሁንም ክልል ያልመለሳቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ብዙዎቹ ትክክለኛ አካሄድ ተከትለውና ስርዓቱን ይዘው ያቀረቡ ቢሆንም በክልል ላይ ምላሽ ያልተሰጣቸው አሉና በዚህ ጉዳይ ላይ ፌዴሬሽኑ አጥንቶ ምላሽ ሊሰጥ ተዘጋጅቷል፡፡ እነዚህ ምላሽ ያልተሰጠባቸው ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙ ክልል ላይ ለአስር ዓመት ያህሉ የተቀመጡ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳዩ ክልሉ እስካልፈቀደ ድረስ ፌዴሬሽኑ ጣልቃ ገብቶ መልስ መስጠት አለመቻሉን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአብዛኛው እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ተደጋግሞ የሚነሳው ከየትኛው ክልል ነው?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- በአብዛኛው ከደቡብ ክልል ሲሆን፣ አሁንም በርካታ ጥያቄዎች በእንጥልጥል ላይ ይገኛሉ፡፡ ሁሉንም ጥያቄዎች አሁን እንመልሳለን ማለት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የአድልዎና መገለል እንዲሁም ፍትሐዊ ተጠቃሚ ያለመሆን ችግር የደረሰባቸው አሉ፡፡ የመጣው ጥያቄ ሁሉ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጠዋል ማለት ሳይሆን ቁርጥ ያለው ምላሽም አሉታዊ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡ እንዲህም ሲባል ‹‹ይገባሃል›› መልስ እንደሆነ ሁሉ ‹‹አይገባምም›› ማለትም መልስ ነው፡፡ ከደቡብ ቀጥሎ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ጥያቄው ይበዛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ከማንነት ጋር በተያየዘ እየተከሰቱ ግጭቶችን እንዴት ማስቆም ይቻላል? ችግሩ በዘላቂነትስ እንዴት ይፈታል ይላሉ?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- በሁሉም አለመግባባቶች ፌዴሬሽን ይወቀሳል፡፡ የሚወቀስበትም ምክንያት አለ፡፡ ለምሳሌ ክልል ብቻውን የሚፈታው ችግር እንዳለ ሁሉ ብቻውን መፍታት የማይችለውን ጉዳይ ደግሞ ከአጎራባች ክልል ጋር በመሆን በጋራ የሚፈታው ይኖራል፡፡ ይህን ማመቻቸት ያለበት ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ በሁለቱም ክልል አለመግባባት ሲፈጠር ፌዴሬሽን ምክር ቤት ገብቶ ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡ የየክልሎቹን ፈቃደኝነት እየጠየቀም ነው ጣልቃ የሚገባው፡፡ ለምሳሌ ጉዳዩ የወሰን አከላለል ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና አስከአሁን በእንዲህ ዓይነት ሂደት የመጣ ነገር የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ክልሎቹ ችግሩን የሚፈቱት በራሳቸው ነው ማለት ነው?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- አዎ! ለምሳሌ አንዴ የሱማሌና የኦሮሚያ ጉዳይ መጥቶ ፌዴሬሽን ጣልቃ በመግባት የፈታው አካሄድ አለ፡፡ ያ ውሳኔ እስከ መጨረሻ ተግባራዊ ሆኗል ወይ የሚለው ነገር ጥያቄ ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ተግባራዊ ያልሆነ ነገር ስላለ፡፡
በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች መካከል ወንዶ ገነት አካባቢ ተከስቶ የነበረው አለመግባባት የተፈታው በዚህ ሂደት ነው፡፡ ስለዚህ እንዲዚህ ዓይነት አለመግባባቶች ሲመጡና የክልሎቹ ፈቃደኝነት ሲኖር የሚመለስበት አግባብ አለ፡፡ ይህም በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 48ም ሆነ በአዋጃችንም የተቀመጠ አካሄድ አለ፡፡
ዋናው ነገር ችግር ከተፈጠረ በኋላ ሳይሆን ከመፈጠሩ በፊት ፌዴሬሽኑ መሥራት ያለበት መሆኑ ነው፡፡ በተለይ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን፣ አንድነትንና እኩልነትን የሚሸረሽሩ አመለካከቶች ምንድን ናቸው? ተብሎ ይጠናል፡፡ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ እሳት የማጥፋት ሥራ ብቻ ሳይሆን የአቀጣጣዩም ማንነት ይጠናል፤ ማለትም ህዝብን የሚያቃቅር ነገር ምን እንደሆነ ይጠናል፡፡ ወደ ትክክለኛ አመለካከት እንዲመጣም ይሠራል፡፡
ለምሳሌ እንደጠቀስኩልሽ ‹‹የመንግ ሥታት ግንኙነት›› በሚል እያዘጋጀነው ያለ አዋጅ አለ፡፡ ምክንያቱም ፌዴራልና ክልሎች በጋራ የምንሠራቸው በርካታ ሥራዎች አሉና፡፡ ከግጭት አንጻር ግን አሁን እያጠናን ነው፡፡ ለምሳሌ የብሄራዊ የግጭት ጥንቅር ካርታ በሁሉም አካባቢ እየተጠና ነው፡፡ በተለይ የግጭት ትኩሳት የሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ መነሻ ምክንያቱ ምንድን ነው? የግጭቱ ዋና ተዋናያን እነማን ናቸው? ተባባሪዎቹስ የትኞቹ ናቸው? ለቀጣዩስ እንዴት ነው የሚፈታው? በአጭር፣ በመካከለኛ ወይስ በረጅም ጊዜ ውስጥ ነው የሚፈታው? የሚለውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ሆነንና ኮሚቴ አዋቅረን እያጠናን ነው፡፡ በጥናቱ ክልሎችም ይሳተፉበታ ል፡፡ በዚህም አማካይነት ነው ዘላቂ መፍትሄ ይገኛል ብለን በመሥራት ላይ የምንገኘው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈጠረው አለመግባባት በእናንተ በኩል እንዴት ይታይል? ጉዳዩንስ ይዛችሁታል?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- እኛ ጉዳዩን ለማጥናም ሞክረናል፡፡ ለምሳሌ በቤኒሻንጉል አሶሳ ዙሪያ የተፈጠረው ችግር ምንድን ነው ብለን አጥንተናል፡፡ ችግሩ ይበልጥ የሚያያዘው ከአመራር ጋር ነው፡፡ ችግሩ የህዝቡ አይደለም፡፡ ህዝብና ህዝብን የሚያጋጩ ዋና ተዋናይ በአካባቢው አሉ፡፡ ይህ በውይይትም ብቻ የሚፈታ ዓይነት አይደለም፡፡ የጠቀስኩት ጥናት ከተካሄደ በኋላ እንሄድበታለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፌዴሬሽኑ በራሱ መንገድ ችግሮችን ለመፍታ የሚሄድበት አሠራር አለ ወይ?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- በተለይ እንዳልኩሽ የህዝቦችን አመለካከት የሚሸረሽሩ ነገሮች ምንድን ናቸው ብለን እያጠናን ነው፡፡ ጥናቱ ውስጥ ብዙ ምክንያቶች ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ምንጩ ምን እንደሆነ የሚያመላክት በርከታ ነገር ሊመጣ ይችላል፡፡ አንዱ አካባቢ ከሌላው አካባቢም ሊለያይ ይችላል፡፡ እንደነገርኩሽ ጥናቱ ላይ ክልሎችም የተሳተፉበት እንደመሆኑ ከየክልል አመራር ጋር በመሆን እንወያይበታለን፡፡ በዘላቂነትም ይፈታልናል ብለን የምናስበው ይሄ ነው፡፡ ፖለቲካዊ በሆነ መንገድም ሊፈታ የሚችል ጉዳይም በጥናቱ ሊኖር ስለሚችል ለፖለቲካ አመራሩም የድርሻውን እንዲወጣ ጉዳዩን እናመላክተዋለን፡፡
በአስተዳደራዊም በኩል የሚፈታ ነገር ካለ ደግሞ ጉዳዩን ለአስተዳደራዊ አካል የሚሰጠው ይሆናል ማለት ነው፡፡ በህግ የሚፈታ ነገር ካለ ደግሞ ፌዴሬሽኑ የሚፈታው ይሆናል፡፡ ቶሎ ተብሎ ካልተፈታ ጉዳዩ ወደሌላ ያመራል የሚል አመለካከትም ካለ እኛን ይመለከታል፤ አሊያም ሌላ ተጨማሪ የህግ ማሻሻያ የሚያስፈልግ ከሆነ ለምሳሌ አሁን ያለው ህግ አሊያም አሁን ያለው የፌዴሬሽን አዋጅ ላይመልሰው ይችላል የሚባል ነገርም ካለ በተመሳሳይ ማሻሻያ ማቅረብ ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ መንገድ ነው አሁን ላይ እዚህም እዚያም ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተዘጋጀነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሎችና ክልሎች እንዲሁም በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት መቀዛቀዝ እንደሚታይበትና ያለመተማመንም እንደሚስተዋልበት ይነገራልና ይህን እንዴት ያዩታል?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- የኢፌዴሪ የመንግሥታት ስርዓት ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኳል፡፡ እነሱ አስተያየት ከሰጡበት በኋላ የተወካዮች ምክር ቤት ያጸድቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚባለው ፌዴራል አቅም የለውም፤ ክልልም ፌዴራልን አያዳምጥም፤ መተማመንና መደጋገፍ የለም እየተባለ በመሆኑ ይህ መንግሥታት ለመንግሥታት ግንኙነት የሚለው አዋጅ ይህንን የሚፈታ ይሆናል፡፡ ይህን ረቂቅ አዋጅ ለማጥናት የፈጀው ጊዜ አራት ዓመት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ወይዘሮ ኬሪያ፡- እኔም አመሰግናሁ፡፡