ልዩነት ያልገደበው የፅዳት ዘመቻ

የክርስትና እምነት ተከታዮች በተለይ የሕማማት ሳምንትን በፆም፣ በጸሎት እና በስግደት የክርስቶስን ስቃይ እና ሞት እያሰበ ይገኛል፡፡ በእለተ እሁድም ‹‹ትንሣዔከ ለእነ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲበነ›› ትንሣዔህን ላመንን ለእኛ ብርሃንህን ላክልን እያሉ በዝማሬ ያከብሩታል፡፡

ኢትዮጵያ የብዙ ሃይማኖቶች እና ባህሎች ባለቤት ብትሆንም ሕዝቦቿ በመዋደድ እና በመተሳሰብ ለዘመናት ተከባብረው ኖረዋል፡፡ ይህም ለዘመናት የኖረ የእኛነታችን መታወቂያ ነው፡፡

በኮልፌ ቀራኒዮ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ለበዓሉ ታዳሚያን ቦታውን ዝግጁ ለማድረግ ትናንት በተካሄደው የፅዳት ዘመቻ ላይ ማልደን ተገኝተናል፡፡ በዘመቻውም የሃይማኖት ልዩነት ያልበገረው፤ ተቻችሎ ሳይሆን ተዋዶ የሚኖረውን ማኅበረሰብ አንድነቱንና መተሳሰቡን በተግባር ተመልክተናል፡፡

ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የእስልምና እምነት ተከታዩ አቶ ብርሃኑ ተማም የወረዳ 8 ቀራኒዮ መድኃኒዓለም አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ ዛሬ በቤተክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ማልደው የተገኙት የክርስትና እምነት ተከታዮች ለሚያከብሩት የትንሣዔ በዓል አካባቢውን ፅዱ ለማድረግ ነው ይላሉ፡፡

አቶ ብርሃኑ ክርስቲያን እና ሙስሊም በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ጊዜ አብረው ተዋደው የሚኖሩ ናቸው ይላሉ፡፡ በአካባቢውም የሙስሊም በዓል ሲሆን የክርስትና እምነት ተከታዮች ማድረግ የሚገቧቸውን ሥራዎች በጋራ ይከውናሉ፡፡ የክርስቲያን በዓል ሲሆንም ሙስሊሞች ማገዝ የሚገባቸውን ያግዛሉ፡፡ በአዘቦት ቀናትም ማኅበራዊ ኑሯቸውን በጋራ እንደሚከውኑም ይናገራሉ፡፡ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወረዳ 8 ቀራኒዮ መድኃኒዓለም ነዋሪ የሆነችው ወይዘሮ አበበች ተምትሜ የክርስትና እምነት ተከታይ ነች፡፡ በፅዳት ዘመቻው ላይ እንድትገኝ ሲነገራት በደስታ እንደወጣችም ትገልጻለች፡፡ ሙስሊም ወንድሞች እና እህቶች የቤተክርስቲያኗን ቅጥር ግቢ ሲያፀዱ ስታይ የተፈጠረባት የወንድማማችነት እና የመዋደድ ስሜት ‹‹ሀገር እንደዚህ ያለችው ነች›› እንድትልም አድርጓታል፡፡

የክፍለ ከተማው አመራሮች እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከሕዝቡ ጎን በመሆን አካባቢውን ማፅዳታቸው ከሕዝቡ ጋር ተቀራርበው እንደሚሠሩ ማሳያ ነውም ትላለች፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ከተማዋን ፅዱ ለማድረግ የበዓላት ቀናትን ጠብቀው ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቀናት የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርባለች፡፡

በእለቱ ተገኝተው ፅዳት ዘመቻው ላይ የተሳተፉት የአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙላት ተገኝ ሃይማኖታዊ በዓላት ሲኖሩ የሃይማኖት ልዩነት ሳይኖር ተቋማትን ማዕከል ያደረገ የሕዝብ ንቅናቄ በማድረግ ከተማዋን እንደሚያፀዱ ተናግረዋል፡፡

የፅዳት ንቅናቄው ዓላማም የተለያየ እምነት የሚከተሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች አብሮነታቸውን የሚያሳዩበት እና የሃይማኖቱ ተከታዮች ደግሞ ፅዱ በሆነ አካባቢ ሃይማኖታዊ ክንውኖቻቸውን እንዲያካሂዱ ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ንቅናቄውም በከተማዋ ባሉ 119 ወረዳዎች ላይ ያሉትን አድባራት ለማፅዳት እቅድ ወጥቶ እየተከወነ የሚገኝ መሆኑን የሚገልጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ እንደእነዚህ ያሉ የፅዳት ዘመቻ ሥራዎች የፅዳት ባህልን የሚያሳድጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የኮልፌ ክፍለ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ሐረግ አብረሃ የከተማ ፅዳት በየእለቱ የሚደረግ መሆኑን ገልጸው፤ በትላንትናው እለት የተካሄደው የፅዳት ዘመቻ ዓላማው የትንሣዔን በዓል በፅዱ ስፍራ እንዲከበር በማሰብ የተደረገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ዘመቻውም የአካባቢው ነዋሪዎች የሃይማኖት ልዩነትን መሠረት ሳያደርጉ ያላቸውን መዋደድ እና አንድነት ያረጋገጡበት መሆኑን ተናግረው፤ ከአንድ ሺህ እስከ አንድ ሺህ 200 የሚሆኑ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በፅዳት ዘመቻው ላይ እንደተሳተፉም ጠቁመዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You