
የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም መካሄዳቸውን ቀጥለዋል። ሊጉ ወደ መገባደድ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር ከሳምንት ሳምንት የሚታየው ፉክክርም ጠንክሯል። ዋንጫውን ለማንሳትና ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር በየሳምንቱ የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ለውጦች መታየታቸውን ቀጥለዋል።
በዚያኛው ሳምንት ለዋንጫ ፉክክሩ የቀረበ ክለብ በዚህኛው ሳምንት ደረጃውን ለሌላ ክለብ ያስረክባል። ላለመውረድ በሚደረገው ትግልም በተመሳሳይ። በሊጉ ለረጅም ሳምንታት ደረጃውን ሳይለቅ መቆየት የቻለ ብቸኛ ክለብ ቢኖር መሪው ኢትዮጵያ መድን ነው።
የሊጉ 25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ጨዋታዎች ከትናንት በስቲያ ሲጠናቀቁም የአሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ስብስብ መሪነቱን ይበልጥ ያጠናከረበትን ውጤት በማስመዝገብ የሻምፒዮንነት ጉዞውን አሳምሯል። ባለፈው ረቡዕ አዳማ ከተማን የገጠመው መድን 3ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ግቦቹን መሐመድ አበራ፣ ሀይደር ሸረፋ እና ያሬድ ካሳዬ ከመረብ ሲያስቆጥሩ ለአዳማ ከተማ ብቸኛዋን ግብ ስንታየሁ መንግሥቱ አስቆጥሯል። አዳማ በ21 ነጥብ ወራጅ ቀጣና ውስጥ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በመጪው እሁድም መቻልን ይገጥማል።
ኢትዮጵያ መድን ማሸነፉን ተከትሎ በደረጃ ሰንጠረዡ ከተከታዩ ክለብ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ ማስፋት ችሏል። በ48 ነጥብ እየመራም ሰኞ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማል።
የ25ኛው ሳምንት የመጨረሻው ጨዋታ ከትናንት በስቲያ ድሬዳዋ ከተማን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘ ቢሆንም በሐዋሳ ከተማ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የጨዋታ ዳኞች ሜዳው እንደማያጫውት በመወሰናቸው ሳይካሄድ ቀርቷል።
የጨዋታ ቀን/ሰዓት የሊጉ የውድድርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ በቀጣይ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።
የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የትግራይ ደርቢን ሲያገናኝ መውረዱን ቀደም ብሎ ያረጋገጠው ወልዋሎ አዲግራት ከስሁል ሽረ 1ለ1 በመለያየት ነጥብ ተጋርቷል። ቃሲም ረዛቅ የወልዋሎን ግብ ሲያስቆጥር ጥዑመልሳን ኃ/ሚካኤል የስሁል ሽረን ግብ ከመረብ አሳርፏል። ወልዋሎ በ11 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ሲገኝ ስሁል ሽረ በ17 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዟል።
አርባ ምንጭ ከተማን የገጠመው መቻል በሽመልስ በቀለ ብቸኛ ግብ አሸንፎ ነጥቡን ወደ 35 በማሳደግ አምስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠውን ውጤት አስመዝግቧል። አዞዎቹ ሽንፈት በማስተናገዳቸው ከነበሩበት ደረጃ ተንሸራተው በ34 ነጥብ 7ኛ ደረጃን ይዘዋል።
በባሕርዳር ከተማ ሽንፈት ገጥሞት የነበረው ኢትዮጵያ ቡና በኮንኮኒ ሀፊዝ ብቸኛ ግብ ፋሲል ከነማን ረቶ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል። በዚህም በ39 ነጥብ ለአንድ ሳምንት ለቆት ወደ ነበረው 2ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል። ቡናማዎቹ ነገ ሲዳማ ቡናን ሲገጥሙ በ33 ነጥብ ዘጠነኛ ላይ የሚገኙት አፄዎቹ እሁድ ድሬዳዋን ይገጥማሉ።
በዚህ የውድድር ዓመት ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር በተመዘገበበት የደቡብ ደርቢ ጨዋታ ሐዋሳ ከተማ በዓሊ ሱሌማን ብቸኛ ግብ ወላይታ ዲቻን አሸንፏል። ሲዳማ ቡና ደግሞ በፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ብቸኛ ግብ ባሕርዳር ከተማን ሲረታ፣ የአምናው ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሳይመን ፒተር ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፏል። ሀድያ ሆሳዕና በመቐለ 70 እንደርታ 2ለ0 በተሸነፈበት ጨዋታ ሸሪፍ መሐመድና ብሩክ ሙሉጌታ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
የ26ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ሲቀጥሉ የዋንጫው ተፎካካሪዎችና 25ኛ ሳምንት ላይ ሽንፈት የገጠማቸው ወላይታ ዲቻና ሀድያ ሆሳዕና 9:00 ሰዓት ላይ ይገናኛሉ። በተመሳሳይ ዛሬ 12:00 ላይ መውረዱን ቀደም ብሎ ያረጋገጠው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በውጤት ቀውስ ውስጥ ከሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም