
ባሕላዊ የአስተዳደር ስርዓቶች የባሕል ሃብቶች በመጠበቅ፣ ማሕበረሰቦችን በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። በባሕላዊ ስርዓት እና በሕዝብ ተሳትፎ መካከል ያለውን ልዩነት ያስተካክላል፣ ባሕል ሕያው፣ ተለዋዋጭ ኃይል ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል። በዚህ በያዝነው የግሎባላይዜሽንና ፈጣን ለውጥ ባለበት ዓለም ላይ የባሕል አስተዳደር ቢሮክራሲያዊ ተግባር ብቻ ሳይሆን የማንነት፣ የኢኮኖሚ ሕያውነት እና የማሕበራዊ ትስስር የማዕዘን ድንጋይ ነው።
ባሕላዊ አስተዳደር ቅርሶችን በመጠበቅ፡ የጋራ የትውስታን ማሕደር ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት የሶሾሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ምሁራን ይናገራሉ። የባሕል አስተዳዳሪዎች የአንድን ሕዝብ፣ ሀገር ወይም አካባቢ የቅርስ ጠባቂዎች ሆነው ይሠራሉ፣ የሚዳሰሱ ቅርሶችን (ሙዚየሞችን፣ ታሪካዊ ቦታዎችን) እና የማይዳሰሱ ወጎችን (ሙዚቃን፣ ቋንቋዎችን፣ የአምልኮ ሥርዓቶችን) ለመጪው ትውልድ ያቆያሉ። ለምሳሌ፣ የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ፕሮግራሞች እንደ ጌዲዮ ባሕላዊ መልከዓምድር የመሰሉ የዓለማችን የቅርስ ቦታዎችን ሁለንተናዊ ጠቀሜታቸውን በመገንዘብ ለመጠበቅ ውጤታማ በሆነ የባሕል አስተዳደር ላይ ያተኩራል። አንድ ማሕበረሰብ ባሕላዊ የአስተዳደር ስርዓት ከሌለው መሰል ሀብቶችን ለማቆየት አንደሚቸገር ጥናቶች ያመለክታሉ።
ባሕላዊ አስተዳደር የማሕበረሰብ ማንነት እና ማሕበራዊ ትስስርን ለማጎልበት ይረዳል። ባሕል ማሕበረሰቦችን የሚያስተሳስረው ሙጫ ነው። የባሕል አስተዳዳሪዎች ሁሉን አቀፍነትን በሚያጎለብቱበት ወቅት የአካባቢ ወጎችን የሚያከብሩ ፕሮግራሞችን በዓላትን፣ አውደ ርዕዮች፣ ወርክሾፖችን ያዘጋጃሉ። ለምሳሌ በባሕል አስተዳዳሪዎች የሚዘጋጀው እንደ ፊቼ ጫምባላላ ያለ ፌስቲቫል ማሕበረሰብን የሚያቀራርብ ፀጋዎችን በውስጡ የያዘ ነው። በተለይ ማሕበራዊ መከፋፈልን በመቀነስ፤ ትስስርን በማጠናከር ትልቅ አስተዋፆ አለው።
ባሕላዊ ስርዓት አሊያም አስተዳደር ዓለም አቀፍ የጎብኚዎችን ትኩረት በመሳብ የኢኮኖሚ ምንጭም ይሆናል። ለአንድ ሀገር ቱሪዝም አድገት መሰል እሴቶች ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክቱ የዘርፉ ምሁራን አበክረው ይገልፃሉ። ከዚህ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር በዓለማችን ላይ ልዩ የቱሪስት ትኩረት የሚያገኙ አገራት ባሕላዊ እሴቶቻቸውን በማልማት፣ በማስተዋወቅ እና በመጠበቅ ግዙፍ ትርፍን ያጋብሳሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የቱሪዝም ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው የባሕል ተቋማት ሙዚየሞች፣ ቤተ-መጻህፍት፣ ቲያትር ቤቶች እና መደበኛ ያልሆኑ የመማሪያ ቦታዎች ሆነው ያገለግላሉ። በተጨማሪ ባሕላዊ አስተዳደር የባሕል ግንዛቤን ያዳብራል። ታሪክን ማንነትን እና የሰው ልጆችን ዘርፈ ብዙ ክህሎት አጉልቶ የማሳየት አቅም አለው። ለዚህ ነው ባሕላዊ ሰርዓት፣ አስተዳደር እና እሴቶች የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት መሰረት፣ የሕዝቦች ሀብትና የማንነት መገለጫ ተደርገው የሚቆጠሩት።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ ባሕላዊ ሀብቶች እና የባሕል አስተዳደራዊ ስርዓቶች ያሉባት ሀገር ነች። አነዚህ ባሕላዊ ሀብቶች የእያንዳንዱ ማሕበረሰብ ማንነት መገለጫ፣ እሴትና የኩራት ምንጭ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግሥትም እነዚህ ሀብቶች እሴታቸው ሳይሸረሸር ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ አንዲተላለፉ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ጎልቶ አንዲወጣ እየሰራ ይገኛል። ከእነዚሀ ባሕላዊ ሀብቶች መካከል የሀዲያ ባሕላዊ ስርዓት አንዱ ነው። የዝግጅት ክፍላችንም በመግቢያችን ላይ ለማንሳት አንደሞከረው የዚህን ባሕላዊ እሴት ፋይዳዎች በዛሬው ሀገርኛ ዓምድ ላይ በዝርዝር ለመቃኘት ይወዳል።
የሀዲያ ባሕላዊ አስተዳደራዊ ሥርዓትን እሴቶቸ በሚመለከት የብሔሩ ተወላጅ የሆነ እና የብሄረሰቡን ማንነት የሚገልጽ በጎ ባሕል፤ ቋንቋና ታሪክ አጠናክሮ በማስቀጠል፤ ብሎም ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ረገድ በትኩረት እየሰሩ የሚገኙትን ሕባ ዮሴፍ (ዶ/ር) በማነጋገር የሚከተለውን ዳሰሳ እነሆ ብለናል።
ሕባ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ በሀዲያ ውስጥ ባዳዋቾ ሀዲያ የሚተዳደርበት ራሱን የቻለ የአንጃቾ (ገዳ) ባሕላዊ አስተዳደር ሥርዓት አለው። ይሄ የባሕላዊ የአንጃቾ (ገዳ) አስተዳደር ስርዓት በሀዲያ ውስጥ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከ12ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲሆን ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ መጥቶ ዛሬ ላይ ለመድረስ በቅቷል። የአንጃቾ (ገዳ) ባሕላዊ አሰተዳደር ሥርዓት የሀዲያ ብሄረሰብ ተወላጅ በተናጠልም በጋራም ማንነቱ የሚገልጽበት፤ ባሕሉን የአብሮነት መስተጋብሩን የሚያንጸባርቅበት፤ በአብሮነት የተገመደ አንድነቱን አጠናክሮ የሚያስቀጥልበት ውብ፣ ሳቢና ማራኪ ገጽታ ያለው ነው።
‹‹ውሸትን መጥላት ወንጀልን መጥላት ነው›› የሚሉት ሕባ (ዶ/ር) ይሄ ብቻም ሳይሆን የሀዲያ ብሄረሰብ በአንጃቾ ባሕላዊ አስተዳደር ሥርዓት ማሕበራዊ ፍትህ እንዲመጣም አጥብቆ እንደሚሰራም ይናገራሉ። ‹‹በአንጃቾ ባሕላዊ አስተዳደር ሥርዓት ውሸትን የሚፀየፍ ዜጋ እንዲፈጠር የምንሰራበት መሳርያችን ነውም›› ሲሉ ይገልፁታል።
እንደ ሕባ (ዶ/ር) ገለፃ ከ12ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረው የአንጃቾ (ገዳ) ባሕላዊ አሰተዳደር ሥርዓት የሰው ዘር ሁሉ በእኩልነት በነፃነትና በመተማመን በጋራ እንዲኖሩ ከፍተኛ አሰተዋጽኦ የሚያደርግ የራሱ የሆነ ውብና ድንቅ እሴቶች አሉት።
እርሳቸውም አሁን ላይ ይሄ የአንጀንቾ ባሕላዊ እሴት በባዳዋቾ በሀዲያ ክልል እንዳይወሰን እየሰሩ ከሚገኙት የዘመኑ ትውልድ ወጣቶች አንዱም ናቸው። ዛሬ ወንድም ወንድሙን በሚገድልበት፤ ምድራችን ፍቅር በናፈቀችበት እና በሰው ክፋት በተማረችበት ዘመን ወጣቱ (ዶ/ር) ሕባ የአንጀንቾ ባሕላዊ እሴት በባዳዋቾ በሀዲያ ክልል ሳይወሰን በሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፋ በተለያየ መንገድ እየሰሩ ይገኛሉ። በጎረቤት ዞኖችና ክልሎች መካከል ችግር ስፈጠር ሰው በሰው እጅ ሲሞትና የጎሳና የድንበር ግጭቾች ሲከሰቱ መፍቻ መሳርያ ሆኖ በማገልገሉ ረገድ የጎላ ነው። ችግርን የመፍቻውን፤ እውነትን ፈልፍሎ የማውጫውን የስልጠና ቁልፍ በመስጠት ጭምር እየሰሩ የሚገኙበትም ዋነኛው የድርሻቸውን እየተወጡ የሚገኙበት ተግባር ማሳያ ነው።
በዚሁ ጉዳይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከሌሎች በርካታ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተጨማሪም ከግል ድርጅቶች ጋር የግንኙነት መረባቸውን በመዘርጋት ይሰራሉ። ለዓመታት ይሄንኑ ያካተተ መረጃ እንደ ኢትዮጵያ ተደራሽ በማድረግ መርፌ የተሰኘ የራሳቸውን መጽሔትም በማሳተም ይታወቃሉ። በተለይ መጽሔቷ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ኢንዳስትሪ ውስጥ የባዳዋቾ ሀዲያ የአንጃንቾ ባሕላዊ አሰተዳደር ሥርዓት እና መሰል እሴቶች ያሉት ስርዓት ናኝቶ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ፍትህ እንዲመጣ አበክረው ሲሰሩ የቆዩባት ነች።
በሀዲያ ብሄረሰብ ማሕበረሰቡ ውስጥ ጎልፋ የሚሰኝ ስርቆትን የመዳኛም ባሕል አለ። ስርቆት ሲፈፀም አንጀንቾ ጋር በመምጣት ሀላንጋን (ሌጋን) ይዘው ይቆሙና እውነትና ውሸቱን እንዲያምን ይደረጋል። አንጀንቾ ሀላንጋን (ሌጋን) እንዲሻገርም ይጠየቃል። ሌባው የተባለውን ንብረት ከሰረቀ በዚህ እውነቱ ይወጣል። በማመኑ የባዳዋቾ ሀዲያ የአንጃንቾ ባሕላዊ አሰተዳደር ሥርዓት የሚደረግለት ምህረት አለ።
ሆኖም በሀዲያ ብሄረሰብ የባዳዋቾ ሀዲያ የአንጃንቾ ባሕላዊ አስተዳደር ሥርዓት ሴት ልጅን ለደፈረ ግለሰብ በምንም ታምር ምህረት አያደርግም። ይሄን ፍራቻ ሴት ከደፈረ በኋላም ደፋሪው ከዛ አካባቢ ርቆ ይሄድና ይደበቃል። ሆኖም የተደፋሪዋ ሴት ቤተሰቦች ልጃቸውን እንደደፈረባቸው የአንጃንቾ ባሕላዊ አስተዳደር ሥርዓት ከነገሩ በኋላ አባቶች ይመረጡና ደፋሪውን ልጅ ከተደበቀበት ቦታ ይዘውት እንዲመጡ ይደረጋል፡፡
ሲመጣ እውነቱን እንዲያወጣ ይደረጋል። ያችን አለንጋም እንዲሻገር ይጠየቃል። አንደበቱ ከመዘጋት ጀምሮ እስከ ሞት የሚያደርስ መቅሰፍት የሚያስከትል የመሆኑ እምነት በመላ ብሄረሰቡም ሆነ በሱ ውስጥ ስላለ ለመሻገር አይደፍርም። ሴት ስለመድፈሩም ያምናል። አመነ ተብሎ በይቅርታ አይታለፍም፤ ሴት በብሄረሰቡ በሀገርም በእናትም ምትመሰልና የምትታይ ክቨብር ናት እና ከባድ ነው የተባለ ቅጣት እንዲቀጣ ይደረጋል።
እንደ ሕባ (ዶ/ር) ማብራሪያ የአንጀንቾ ባሕላዊ እሴት በባዳዋቾ በሀዲያ ክልል ሳይወሰን በጓሮቤት ዞኖችና ክልሎች መካከል ችግር ሲፈጠር፤ ሰው በሰው እጅ ሲሞትና የጎሳና የድንበር ግጭቾች ሲከሰቱ አንጀንቾ ጣልቃ በመግባት ይሰራል። አንጀንቾ ጉዳዩን የማብረድና የማስቆም ስልጣን ያለውም ነው። አንጀንቾ ሀላንጋን (ሌጋን) ይዘው ሲቆም እምቢ ያለው ወገን በክፉ መቅሰፍት ይቀሰፋል ተብሎ ስለሚታመን ሁለቱ ተቃራኒ ወገን ከግጭቱ በመመለስ ለአንጃንቾ እርቅ ሰላም ይታዘዛሉ። አንጃንቾም የባሕል ጉዳይ ከሚመለከታቸው ብሔር ወይም ጎሳ ባሕል መሪዎች ጋር በመሆን ግጭቱን በእርቅ በመጨረስ የሰው ልጅ ሁሉ ባለበት አካባቢ በሰላም፣ በአንድነት፣ በአብሮነት፣ በእኩልነት፣ ተከባብሮ፣ ተማምኖ በፍቅር እንዲኖሩ ቃለ መሐላ (ጉዳ) በሚደረግ ጥላቻ ደግሞ እንዳይፈጠር አድርጎ ያስታርቃል።
ይህ የአንጃንቾ (ገዳ ) ሥርዓት ለዜጎች፣ ድህነትን፣ ጥበቃና ለመኖር ዋስትና ሆኖ ለዘመናት የቆየ ባሕላዊ እሴት ነው። የአንጃንቾ ባሕላዊ ሥርዓት ግጭትን የሚፈታ ሰላምና ፍቅርን የሚያጠናክር ባሕላዊ እሴት ይዘት ያለውም ነው።
‹‹አንጃንቾ ማለት ገዳ ማለት ነው›› የሚሉት የዮብ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር ባለቤትና መሥራች ሕባ ዮሴፍ (ዶ/ር) የባዳዋቾ አንጃንቾ ባሕላዊ ስርዓት ከጥንት ጀምሮ ያለ በመሆኑ በብሄረሰቡ ዘንድ ተቀባይነትና ተሰሚነት አትርፏል። እኛም የታሪክ መዛግብት አገላብጠን እንዳየነው የአንጃንቾ ታሪክ ከ12ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረ ታሪክ እንደሆነ የታሪክ ፀሀፊዎች አስፍረውለታል።
ሕባ ዮሴፍ (ዶ/ር) እንደሚሉትም በዚህ መሰረት ከ12ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከባሌ እስከ ደንበል፣ ዶዩ ዶዲቻ ዝዋይ እስከ ባዳዋቾ ሀዲያ የነበረ ታሪክን የሚያንፀባርቅ እሴት አለው። በዚህ ታሪክ መሰረት አንጀንቾ በሀዲያ በባደዋቾ አካባቢ የአንጃንቾ ስርዓትን እያራመደ ይገኛል።
እንደሳቸው ገለፃ አንድ ሰው ወይም ብሔር በግልም ሆነ ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር ትርጉም ያለው ማሕበራዊ ሕይወት ሊያጋራ የሚችለው ባለፉት ዘመናት እና ትውልድ ላይ ስለነበረው የታሪክ እውቀት ሲኖረው ነው። የታሪክ እውቀት የሌለውና የታሪክን ጠቀሜታ ያልተገነዘበ ማንኛውም ግለሰብ የማንነት ስሜት ሊኖረው አይችልም ከትክክለኛው ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያቅማማል። በመሆኑም እሳቸው በሀገራችን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትህ እንዲመጣ መገናኛ ብዙሃንን እንደመፍትሄ አማራጭ በመጠቀም እየሠራ የሚገኝ የግል ድርጅት መስርተው ‹‹አንጃንቾ ወይም ገዳ›› ላይ በተለያየ መልኩ የድርሻቸውን አስተዋጾ እያበረከቱ ይገኛሉ። መልካም ሳምንት !
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም