ምዕመናን ከሰሞነ ሕማማት ትሕትና እና ፍቅር ሊማሩ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ

አዲስ አበባ፡- ምዕመናኑ ከሰሞነ ሕማማት ትሕትና፣ ፍቅርና ጽናትን ሊማሩ እንደሚገባ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

የሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የትምህርት ክፍል ኃላፊና የግዕዝ ቋንቋ መምህር መጋቤ ምስጢር አዕመረ ፀሐዩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰሞነ ሕማማት፤ ጸልዮ ምዕመናን እንዲጸልዩ፣ ፆሞ ምዕመናን እንዲፆሙ እና የሐዋሪያትን እግር አጥቦ ምዕመናን የወዳጆቻቸውን እግር እንዲያጥቡ አርዓያ ሆኗል፡፡

ሰማይና ምድርን የፈጠረ አምላክ ዝቅ ብሎ እግር እንዳጠበው ሁሉ ምዕመናንም የክርስቶስ ተከታይ ስለሆኑ፤ ትሕትናና አክብሮት ሊማሩና በሕይወታቸው ሊተረጉሙት ያስፈልጋል፡፡ ማንኛውንም ሰው በሰብዓዊነት ሊያከብሩ እና ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማምና ሞቱን፤ ለሰው ልጅ ሲል ክቡር ነፍሱን እንደሰጠ ምንግዜም እያሰቡ፤ ለወንድሞቻቸው እና ለወገኖቻቸው በአገልግሎት ሆነ ድህነትን በማሸነፍ መስዋዕትነት ሊከፍሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የታሰሩትን መጎብኘት፤ የተራቡትን ማብላት፤ የተጠሙትን ማጠጣት፤ የታረዙትን ማልበስ እንደሚገባ አስቀምጧል ያሉት መምህሩ፤ የትንሣዔን በዓል ምዕመናን ሲያከብሩ የተራቡትን በማብላት፤ የታሰሩትንና የታመሙትን በመጠየቅ እና የአዘኑትን በማጽናናት ሊሆን እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህን እና የኢትዮጵያ ካህናት ማኅበር ሰብሳቢ አባ ፍሰሐ ታፈሰ በበኩላቸው፤ ሰሞነ ሕማማት ጌታ የደቀመዛሙርቱን እግር ማጠቡ ምዕመናን ፍቅርን፤ ሰላምን በመሐላቸው እንዲያወርዱ፤ የመተባበር እና የመከባበር ስሜት በመሐላቸው እንዲኖር የመቻቻል ምልክት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ መከራዎችን በመቀበል እና በመስቀል ላይ በመሞት ጌታ ከባዱን ቀንበር ለሕዝቡ ተሸክሟል፡፡ ምዕመናኑም ቀላሉን ቀንበር በመሸከም የተለያዩ የኃጥያት ፈተናዎችን ማሸነፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ይቅር የመባባል መንፈስ በሁሉም ዘንድ ሊኖር ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በፆም ወቅት ከተለያዩ ነገሮች በመራቅ የሥጋ ተጋድሎ አድርገናል የሚሉት አባ ፍሰሐ፤ ፆም በሚፈታበት ጊዜ ደግሞ ለራሳችን ብቻ በመብላት ሳይሆን ለሌላቸው ማካፍል ይገባል፡፡ ወንጌልን በመከተል የታረዘን በማልበስ፤ የተጠማን በማጠጣት እና የተራበን በማብላት የትንሣዔን በዓል ማክበር እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የአዲስ አበባ ክልል ዋና ፀሐፊ ፓስተር ሙላቱ ኤርሚያስ እንደገለጹት፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰሞነ ሕማማት በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ እየሩሳሌም በመግባት፤ የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ፤ በመስቀል ላይ በመሰቀል ተከታዮቹ ማድረግ የሚገባቸው ነገር በተግባር አሳይቷል፡፡

ክርስቲያኖች የእሱ ፈለግ ተከታዮች እንደመሆናችን፤ በትክክል አስተምሕሮቱን ሊከተሉ ይገባል፡፡ ክርስቶስ ከእኔ ተማሩ ባለው መሠረት እራስን መግዛት፤ ትሕትናን፤ መልካምነትን እና ብልህነትን በሰሞነ ሕማማት መማር ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፓስተር ሙላቱ እንደገለጹት፤ ምዕመናኑ የፋሲካ በዓልን በሚያከብርበት ወቅት፤ የተቸገሩትን መደገፍ፣ ለደካሞች አለኝታ በመሆን፤ ፍቅር በማሳየት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You