በክልሉ 75 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል

  • 60 በመቶ የሚሆኑት ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው

አዲስ አበባ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 52ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 75 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡ 60 በመቶ የሚሆነውም ችግኝ ኢኮኖሚክ ጠቀሜታ ያላቸው ወይም የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ባባከር ኃሊፋ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በዘንድሮ ዓመት በክልሉ ከ75 ሚሊዮን ችግኝ በላይ ለማፍላት ታቅዶ እስካሁን 45 ሚሊዮን ችግኝ ማፍላት ተችሏል፡፡ 60 በመቶ የሚሆኑት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ወይም የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ለማፍላት የታቀደውን የችግኝ ቁጥር ለማሳካት እስከ ሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ በሦስት ወራት ሊደርሱ የሚችሉ ችግኞችን የማፍላት ሥራ ይሠራል፡፡ 52ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ችግኞቹን ለመትከል በመታቀዱ እስካሁን 42ሺህ ሄክታሩ ላይ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ቀሪው 10ሺህ ሄክታር መሬት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ እሚከወንበት ቀን ድረስ ይዘጋጃል፡፡ ችግኞቹ የሚተከሉባቸው ቦታዎች ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በማናበብ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት በክልሉ በየዓመቱ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ችግኝ ሲተከል መቆየቱን የተናገሩት አቶ ባባከር፤ ከተተከሉት 350 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ፀድቋል፡፡ በዚህም የደን ሽፋንን መጨመር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የአረጓዴ ዐሻራ በክልሉም የዝናብ መጠን ጨምሯል፡፡ ለምግብነት መዋል የሚችሉ ፍራፍሬዎችም ለምተዋል፡፡ ሕዝቡም በዚህ ተጠቃሚ መሆን መቻሉን አብራርተዋል፡፡

ቢሮውም የተተከሉ ችግኞች እንዳይደርቁ ክትትል የማድረግ ሥራ እየሠራ መሆኑንም ተናግረው፤ የተደራጁ ወጣቶችም ችግኞቹን እንስሳት እንዳያጠፏቸው እና በእሳት እንዳይወድሙ ችግኞቹ የተተከሉባቸው አካባቢዎችን ጥበቃ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡

ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አብዛኛው ችግኞች የሚፈሉት በማኅበር በመሆኑ ወጣቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You