
የገበያውን ስፍራ በጥዑም ሽታ ያወደው የዕጣን ጭስ በርቀት እየታየ ነው። የጭሱ አብዝቶ ማወድ ዓውደ ዓመት ስለ መድረሱ አስቀድሞ ይጠቁማል። ዛሬ የዕጣን ነጋዴዋ ከወትሮው በተለየ በሰው አጀብ ተከባለች። ዙሪያዋን የቆሙት ሴቶች ለአፍንጫቸው ያመቸውን መዓዛ እየለዩ በአቅማቸው መገብየት ይዘዋል።
ባለዕጣኗ ወይዘሮ ዓውደ ዓመት በመጣ ቁጥር መርጣ የምትይዘውን የዕጣን በረከት ‹‹እነሆ›› እያለች ነው። ደንበኞቿ የእሷን መኖር የሚለዩት በርቀት በሚሸታቸው የዕጣን መዓዛ መሆኑን ታውቃለች። ሁሌም ዓውደ ዓመት በመጣ ቁጥር ደንበኞቿ እሷን ምርጫ አድርገው ይገበይዋታል።
የሾላ ገበያ በዓውደ ዓመት ግርግር ተይዟል። የቡናውና የቅቤው መሸጫ ከወትሮው ትኩረት አግኝቶ በበርካቶች እየተጎበኘ ነው። አለፍ ሲሉ ከዓይን የሚገባው የቅመም ገበያ ጠያቂው በርክቷል። ሁሉም እንዲገዛ የታዘዘ ይመስል ቦታው ላይ የሚጋፋው ብዙ ነው።
ወይዘሮ ጥሩነሽ አስፋው ቀናት ለቀሩት የፋሲካ በዓል መዘጋጀት ከጀመረች ሰንብታለች። ጥሩነሽን ያገኘኋት ሾላ ገበያ ከቅመማቅመሙ መንደር ስትወጣ ነው። የዘንድሮ የኮረሪማ ዋጋ ከምታነጥረው ቅቤ በላይ የመሆኑ ጉዳይ እንዳሳሰባት ትናገራለች። እንዲያም ሆኖ የአቅሟን ከመግዛት አልተወችም።
እንደ ጥሩነሽ አባባል፤ ፋሲካ ከወራት ፆም በኋላ የሚከበር በመሆኑ ከልምዱ ሊጓደል አይገባውም። እጅ አጥሮ ኪስ ቢሳሳም እንደአቅም አክብሮ መዋል ግድ ይላል። ወይዘሮዋ ዓውደ ዓመቱን ከቤተሰቦቿ ጋር ተደስታ ለማሳለፍ ለቤት ለጓዳዋ ያሻትን እየሸመተች ነው።
ገበያው በአዳዲስ ዕቃዎች ደምቋል። ለዓውደ ዓመቱ ውብ መጋረጃና ምንጣፍ ያስገቡ ባለሱቆች መንገደኞች ጠይቀው እንዲገዟቸው እየወተወቱ ነው። የአገር ልብስ፣ የሽፎን ቀሚስና የጫማ መሸጫዎች ለዓይን በሚስብ እይታ ተሰቅለዋል። ስፍራው ዓውደ ዓመቱን በሚያደምቁ ሙዚቃዎች እንደታጀበ አርፍዶ ያመሻል።
ከአራዳ ጊዮርጊስ ባሻገር ዋና መንገዱን ይዘው የተተከሉት ነጫጭ ድንኳኖች ዓውደ ዓመቱ በሚፈልጋቸው ግብዓቶች ተሞልተዋል። በስፍራው አላፊ አግዳሚው ኪሱን እየጠበቀ ገበያውን ሲታደመው ይውላል። በዚህ አካባቢም ጆሮ ገብ የሚባሉ ባህላዊ ዘፈኖች ጊዜውን እያስታወሱ መድመቃቸው ቀጥሏል።
ከሚታዩት ድንኳኖች በአንደኛው በየዕቃው የተሞላ ጠጅ፤ በሊትር መጠን ተዘጋጅቶ ገዢውን ይጠብቃል። ማርና ቅቤው በየአቁማዳው ሞልቶ በየመልኩ ቀርቧል። በዚህ ስፍራ የሚገዛውም፣ የማይገዛውም ቆም እያለ መጠየቁ እንደልምድ ነው።
አንዳንድ ገዢዎች ከእጃቸው መሐል ጣል የሚልላቸውን ጠብታ ማር ቀምሰው እንዲገዙ ማስታወቂያው ደርቷል። አብዛኞቹ ከቀመሱ በኋላ ዝም አይሉም። እንደፍላጎታቸው አስመዝነው ከማርና ቅቤው ይወስዳሉ። ለአላፊ አግዳሚው የሥራ ካርዱን የሚያድለው ወጣት በየቦታው ቅቤና ማር በመሸጥ ይታወቃል። እንዲህ ለበዓል በሚዘጋጁ የባዛር ገበያዎች ደግሞ ብዙ ደንበኞችን አፍርቷል።
ስሙን በለጠ ሲሳይ ሲል ያስተዋወቀን ነጋዴ በዘንድሮው ገበያ ቅቤ፣ ማርና ጠጅ በርከት አድርጎ መያዙን ይናገራል። ጊዜው ፋሲካ በመሆኑ ተጠቃሚው ወደ ምግብ ያደላል የሚለው በለጠ፤ በዘንድሮው የበዓል ገበያ ዋጋ መጨመሩ ቢታወቅም አብዛኛው ተጠቃሚ እንደአቅሙ እየገዛው መሆኑን አልሸሸገም።
የቅቤና ማሩን ድንኳን አለፍ ሲሉ የተፈጨ ቡና፣ የተቆላ ገብስ፣ አዋዜ፣ ዕጣን፣ ቅመማቅመምና የጠላ ግብዓቶችን ያገኛሉ። ሁሉም ዓውደ ዓመቱን ታሳቢ በማድረግ ለገበያ የቀረቡ ናቸው። አብዛኞቹን ያለቀላቸው ግብዓቶች ስትገዛ ያገኘኋትን ወጣት ስለግዢ ምርጫዋ ጠየቅኳት። ኑሮዋ በጋራ መኖሪያቤት /ኮንዶሚኒየም/ በመሆኑ እነዚህ ግብዓቶች ድካሟን እንደሚቀንሱላት አወጋችኝ።
በደማቅ ሙዚቃ የታጀበውን ስፍራ ራቅ እንዳሉ በርቀት ከሚታየው የቅመማ ቅመም መሸጫ ዘንድ ይደርሳሉ። ታዋቂዋ ‹‹እምሻው ቅመማ ቅመም›› ዛሬም እንደልማዷ በዓይነትና በብዛት የምትታወቅባቸውን የእጆቿን ሙያ ይዛ ቀርባለች። ዓመታትን በደንበኝነት አብረዋት የዘለቁ ደንበኞቿ ሁሌም ካለችበት ፈልገው አያጧትም። በደንበኛ ክቡርነት የምታምነው እምሻው፤ ሁሌም ደንበኞቿን በፈገግታ ተቀብላ ታስተናግዳለች። በእሷ እጅ የሚፈለጉ ቅመሞች ደግሞ ተጠይቀው አይጠፉም። በተለያያ መጠን ያዘጋጀችውን ግብዓቶች ከታላቅ ምስጋና ጋር ለገዢዎቿ ታስረክባለች።
ፒያሳ አራዳ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት በተዘጋጀው የፋሲካ ባዛር ላይ በሥራ የምትታትረው ወይዘሮ፤ ሰሞኑን ለበዓሉ የሚያስፈልጉትን ሁሉ እንዳሟላች ትናገራለች። የእምሻው በርበሬ፣ ሚጥሚጣና ቅመማ ቅመም ዛሬም ገበያው ደርቷል። ስሟን ጠይቀው አድራሻዋን ፈልገው የሚመጡ ሁሉ ሙያዋን አጣጥመው በምስጋና ያከብሯታል። እጀ-መልካሟ ወይዘሮም ፋሲካን እንደትርጉሙ የሚያደርጉትን ተፈላጊ ቅመሞች እያዘጋጀች ለደንበኞቿ ማቅረቧ እንደሚያኮራት ትናገራለች።
በጀሞና አካባቢው ገበያ መሐል ተገኝተናል። ይህ ስፍራ በከተማዋ ከሚገኙ ደማቅ ቦታዎች አንዱ መሆኑ ይነገርለታል። እንኳን በዓል ደርሶ ለወትሮም ግርግር የማያጣው አካባቢ ከሰሞኑም በሰዎች አጀብ ደምቆ ይተራመስ ይዟል። የስፍራው ላይ ሥጋ ቤቶች ከቆዩበት ዝምታ ነቅተው በነጭ ቀለም ተውበዋል። ከቀናት በኋላ የሰንጋ አምሮታቸውን ሊወጡ ዝግጁ ናቸው። ምግብ ቤቶች፣ ሆቴሎችና መዝኛኛዎችም በዓሉን ለመቀበል ከወዲሁ ሽርጉድ ይዘዋል።
የአገር ልብሶች መደብር፣ የባህላዊ ዕቃዎች ሱቅ፣ የቆጮና ቡላ መሸጫዎች ሁሉ በዓሉን በሚገልጹ መሰናዶዎች ራሳቸውን አንቅተው ደንበኞችን ይጠብቃሉ። በእነዚህ ስፍራዎች የሚመላለሰው ገበያተኛም ከቀድሞው በላቀ ቁጥር በርክቷል። የአካባቢው ታዋቂ የገበያ ማዕከሎች /ሱፐር ማርኬቶች/ ለበዓሉ ተዘጋጅተው በወጉ የተሰነዱ ምርቶችን አዘጋጅተዋል። ጊዜው ሲደርስ የተበለተ ዶሮ፤ ሥጋ፤ አይብና ቆጮ በማቅረብ ለደንበኞቻቸው ይደርሳሉ።
የአካባቢው የቅዳሜና ዕሁድ የድንኳን ገበያዎች ለበዓሉ ከከተሙ ከሳምንት በላይ ቆጥረዋል። ለዚሁ ዓላማ ያቀረቧቸውን የሽንኩርት፣ አትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦቶች በብዛት እየሸጡ ነው። ይህንኑ ስፍራ የሚጋሩት የጠጅና፣ ቅቤና ማር ነጋዴዎችም የበዓል ደንበኞቻቸውን በወጉ ማስተናገድ ይዘዋል።
በመሐል ጀሞ ከሚታዩ የዓውደ ዓመት ገበያዎች መሐል ጀበና፣ የሸክላ ድስት ምድጃ፣ ማጨሻና የቡና ማቅረቢያዎችን የያዙት ወይዘሮ አስናቀች ድረስ፤ ደንበኞቻቸውን በጉጉት እየጠበቁ ስለመሆናቸው ይናገራሉ።
ዓመት በዓል በደረሰ ጊዜ እነዚህን ዕቃዎች የሚፈልጉ ተጠቃሚዎች እንደሚበረክቱ የሚገልጹት ወይዘሮዋ፤ ለውጥን በማሰብ ጭምር ዕቃዎችን ደግመው የሚገዙ ጥቂት አለመሆናቸውን ታዝቤያለሁ ይላሉ።
እነሆ! በሕዝበ ክርስቲያን ዘንድ በታላቅ አክብሮት የሚጠበቀው ዕለተ ፋሲካ በድምቀት ይከበር ዘንድ ሁሉም እንደየአቅሙ ዝግጅቱን ቀጥሏል። ቤትን አድምቆ ጎጆን ለመሙላት ያሰቡ በርካቶችም ከዶሮና በጉ፣ ከቅርጫና ሥጋው በረከት ተካፍለው ‹‹ዓውደ ዓመቱ ሲመጣልን በዓመቱ›› የበዓላት ቀኑን ለማድመቅ መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም