የአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት ታሪፉን በመቃወም ክስ መሠረተች

ከአሜሪካ ግዛቶች ሁሉ ከፍተኛ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅሰው እንዲሁም የግዙፍ ፋብሪካዎች እና እርሻዎች መገኛ የሆነችው የካሊፎርኒያ ግዛት፤ የዶናልድ ትራምፕን ታሪፍ በመቃወም ክስ መሠረተች። የካሊፎርኒያ ግዛት አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ታሪፍ በመቃወም ክስ መመሥረታቸውን ይፋ አድርገዋል። ዶናልድ ትራምፕ በዓለም አቀፍ ሀገራት ላይ የጣሉትን ታሪፍ በመቃወም ለመጀመሪያ ጊዜ በተመሠረተው የግዛቲቱ ክስ፤ ትራምፕ ይህንን ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ለማስተላለፍ የተጠቀሙትን ሕግ ተቃውሟል።

ካሊፎርኒያ ከየትኛውም የአሜሪካ ግዛቶች በመቅደም በዓለም አምስተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ግዛት ነች። በግዛቲቱ ውስጥ ግዙፍ የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች እና ሰፋፊ እርሻዎች ይገኛሉ። ታሪፉ በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ የሚስተዋለውን አለመመጣጠን ይፈታል ሲል የሚከራከረው ኋይት ሐውስ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጎ “የአሜሪካን ኢንዱስትሪዎችን እየጎዳ ያለውን ብሔራዊ ድንገተኛ አደጋ” መፍትሔ ለመስጠት መሥራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የኋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ኩሽ ዴሳይ “ጋቪን ኒውሶም በካሊፎርኒያ የተንሰራፋውን ወንጀል፣ የቤት እጦት እና አልቀመስ ያለ ኑሮ ላይ ከማተኮር ይልቅ ሀገራችንን እየጎዳ ያለውን የንግድ ጉድለት. . . ለመፍታት ፕሬዚዳንት ትራምፕን የሚያደርጉትን ታሪካዊ ጥረት ለመግታት ጊዜውን እያጠፋ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ኒውሶም እና የግዛቲቱ ዓቃቤ ሕግ ሮብ ቦንታ ክስ መመሥረታቸውን ይፋ ያደረጉት በካሊፎርኒያ የአልሞንድ እርሻ መካከል ተገኝተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

የዓለማችን 82 በመቶ አልሞንድን የምታመርተው የካሊፎርኒያ ግዛት፣ አርቲኮክ፣ የወይራ ፍሬ፣ ዋልነት እና የዘቢብ ብቸኛ አምራች ነች። የካሊፎርኒያ ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑት ኒውሶም፣ ዶናልድ ትራምፕ በጣሉት ታሪፍ የተነሳ ግዛቲቱ “ፍትሐዊ ባልሆነ መልኩ ተጎድታለች” በማለት ተከራክረዋል።

ከጥር ወር ጀምሮ በዶናልድ ትራምፕ ላይ 15 ክሶችን የመሠረተችው የካሊፎርኒያ ግዛት፣ አሁን ደግሞ በአብዛኛዎቹ የዓለም ሀገራት ላይ 10 በመቶ እና በቻይና ላይ 145 በመቶ የተጣለውን ታሪፍ ተቃውማ ክስ በመመሥረት የመጀመሪያዋ ሆናለች። አስተዳዳሪው “ይህ የእኛ መረዳት ነው። ለዚህም ነው በ40 ሚሊዮን አሜሪካውያን ስም በመሆን ራሳችንን ከፊት ያስቀደምነው” ብለዋል።

የካሊፎርኒያ ግዛት የመሠረተችው ክስ ትራምፕ በዓለም ሀገራት ላይ ታሪፍ ለመጣል የተጠቀሙት ‘ኢንተርናሽናል ኢመርጀንሲ ኢኮኖሚክ ፖወርስ አክት’ የተሰኘ ሕግ፣ ለእንዲህ ዓይነት ታሪፍ ጥቅም ላይ ውሎ አያውቅም፣ ሥልጣኑም የአሜሪካ ኮንግረስ ነው በሚል ይሞግታል። የክሱ ዝርዝር ላይ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባይደን አስተዳደር የተማሪዎችን ዕዳ ለመሰረዝ የሚያደርገውን እርምጃ ለማገድ የባይደንን ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣን ይለጥጣል በሚል ያሳለፈውን ውሳኔ በተደጋጋሚ ጠቅሷል። ኒውሶም ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ወጥነት ያለው አሠራር ካለ ይህ ክስ [ለግዛቲቱ] መቋጫ ነው” ብለዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ ሕግ በየትኛውም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ታሪፍ ለመጣል ጥቅም ላይ ውሎ አያውቅም። ካሊፎርኒያ በትራምፕ አስተዳደር የተጣለውን ታሪፍ በመቃወም ክስ የመሠረተች የመጀመሪያዋ ግዛት ሆናለች። ከዚህ በፊት በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ እንዲሁም የሲቪል መብቶች እንዲከበሩ የሚሟገቱ ቡድኖች በተመሳሳይ የትራምፕን እርምጃ በመቃወም ክስ መሥርተዋል።

ትራምፕ በጥር ወር ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በዓለም ሀገራት ላይ የተለያየ ታሪፍ ጥለዋል። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ላይ የተጣለው ታሪፍ ሸማቾች የአሜሪካ ምርቶችን እንዲገዙ ያበረታታል፤ የሚሰበሰበውን የታክስ መጠን እንዲጨምር እንዲሁም በሀገሪቱ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል።

ተቺዎቻቸው ግን ፋብሪካዎችን ወደ አሜሪካ ማምጣት ከባድ እና አሥርተ ዓመታትን ሊወስድ እንደሚችል በመጥቀስ፣ እስከዚያው ድረስ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚወድቅ ጠቅሰው ተከራክረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ርምጃ ለመውሰድ ይፋ ካደረጉ በኋላ ውሳኔያቸውን ሲያዘገዩ ታይተዋል። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ወደ 60 በሚጠጉ የአሜሪካ የንግድ አጋሮች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ከጣሉ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ፣ ከፖለቲከኞች ከፍተኛ ተቃውሞን ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ከቻይና ውጪ በሌሎቹ ሀገራት ላይ ርምጃው ለ90 ቀናት እንዲዘገይ ወስነዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You