‹‹ሙሉ የለቅሶ አልበም ላሳትም ነው›› – ድምጻዊ እንዳለ ስጦታው

ርዕሱን ስታነቡ ሳትገረሙ አልቀራችሁም። እኔም ነገሩ አስደንቆኝ እና ጥያቄም ፈጥሮብኝ ድምጻዊ እንዳለ ስጦታው ምን አስበህ ነው አልኩት። ያልተለመደ በመሆኑ በማሕበረሰቡ ዘንድ የሚኖረው ቅቡልነት አላሳሰበህም ወይ? የሚል ጥያቄ በማከል ሃሳቡን በዝርዝር እንዲያጫውተኝና የቆይታችን መጀመሪያ እንዲሆን በማሰብ የልቡን በር አንኳኳሁና ከትዝታው ፈረስ አብሬው ተቆናጠጥኩ፡፡

ከዚያም ንፋሰድምጹን ለማስቀረት መቅረጸድምጼን በማሰናዳት ከምናቡ እልፍኝ ዘለልኩና እያንዳንዳቸውን የሕይወቱን ገጾች ስበረብራቸው እንዲህ አስነብበውኛልና እናንተ ውድ አንባቢያንም ከቋጠርኩት የወግ አገልግል ብዕር ያሞናሞነውን እንጎቻ ትቋደሱ ዘንድ እንካችሁ ብያለሁ።

“እንደ ጆፌ አሞራ ትረባለች ዓለም፣

የጀመራት እንጂ የጨረሳት የለም።”

ሲል ባስለቃሽነቱ መባቻ አፍ የፈታበትን ስንኝ አስቀደመና አባቱም አጎቱም ሀገር ያወቃቸው ጸሃይ የሞቃቸው አስለቃሾች በመሆናቸው ሞያውን በቅብብሎሽ እንዳገኘው ገልጦ እሱም በተራው አንገት የለየ አስለቃሽ ለመሆን በቅቶ ይህ ችሎታው ከቤተመንግሥት ደጃፍ ደርሶ ኖሮ ጉድ ትንግርት አስብሏል። የቀድሞ ጠቅላይ ምኒስትር መለስ ዜናዊ ስራተቀብራቸው ሲፈጸም

“አልቅሺ ኢትዮጵያ አልቅሺ ሀገሬ፣

መመኪያ ጋሻሽን ተነጥቀሻል ዛሬ።”

በማለት ሕዝቡን እንባ ሲያራጨው “ወጣቱ የልጅ አስለቃሽ” ተብሎ እንደትልቆቹ ቤትና ክላሽ ባይሸለምም የመለስ ዜናዊ ፎቶና የምስጋና ወረቀት እንደሰጡት በፈገግታ አዋዝቶ ሲያጫውተኝ ጥሪው በምን መንገድ ደረሰህ? አልኩት ሌላ ጥያቄ በማስከተል። “እንደኛ አቆጣጠር በ2001 ዓ.ም በኢትዮጵያ ደጋሽነት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የባሕል ፌስቲቫል ተዘጋጅቶ እንደክልል እኔ ያለሁበት መረዋ የባሕል ቡድን ሸንጎ በተሰኘ ቲያትር አሸንፎ ሀገር ፍቅር ከተመ፡፡

በተውኔቱም እኔ የምጫወተው ገጸባህሪ አስለቃሽ ስለነበር ይህን የሚያውቁ የክልልና የዞን ባለስልጣናት ታድጋለች ሀገሬ የሚለውን ነጠላ ዜማዬን ለቱቲ ሙዚቃ ቤት ለመሸጥ አዲስ አበባ መሆኔን ሲሰሙ አጋጣሚውን ተጠቅመው መለስ በሞተበት በዚያን ወቅት ወደ ጎጃም ልመለስ የነበረውን ጉዞዬን አሰርዘው ቤተመንግሥት ወሰዱኝና ስመጥር አስለቃሽ ለመሆን በቃሁ” አለ ለወግ ማድመቂያነት ከሰየምነው የእህል ደም ተጎንጭቶ ጉሮሮውን አረጠበና። ያግራሞት ድባብ ጸዳሉን አፍክቶት “ያ ዘመን ይደንቀኛል” አለ ቀጠለና፤ በምኑ? አልኩት የሚነግረኝን ወግ ለመቅለብ ጆሮዬንም ብዕሬንም አስልቼ። “ከተፈጠርኩ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በመኪና የሄድኩት በውድድሩ ሰበብ ነው፤ አዲስ አበባንም፤-

አዲስ አበባ ላይ ወድቄ ብነሳ፣

የሰራ አካላቴ ወርቅ ይዞ ተነሳ።

ከሚለው ዘፈን በቀር ከዛ በፊት አላውቃትም ነበር” ሲል አጫወተኝ። ለሁሉም ነገር እንግዳ የመሆንና ሃፍረት የተጫነው ሳቅ ወባ እንደያዘው ሰው እያንዘረዘረው። እባክህን ምንም ሳታስቀር ትዝታህን አውጋኝ እንዴት ነበር? አልኩት በሃሳቤ የጉዞ ማስታወሻውን ስበረብር ሊኖረው የሚችለው ድንጋጤ በምናቤ እየታየኝ። “ብርሃን ቦታውን ለቆ የምሽቷ ጨረቃ ከቀኗ ጸሃይ ፈረቃውን ተረክባ ምድር የጨለማ ካባ ስትደርብ እንጦጦ አፋፉ ላይ ደርሰን ቁልቁል ስመለከት የሚንቀለቀለው ኮረንቲ ከጠራራ ጸሃይ እጅግ ይልቃል፤ ይህን ጊዜ መገረሜ በዝቶ ዋ መብራቱ! ብል መኪናውን የሞሉት ሁሉም የቡድኑ አባላት ሳቁብኝና ለከተማ አዲስ መሆኔን አጋለጡብኝ።

ከዚህም የከፋው ነገር ደግሞ በመስታወት የነደደው ያረፍንበት ሆቴል ሁሉም ክፍል ተመሳሳይ ከመሆኑ የተነሳ መውጫ መውረጃው ጠፍቶኝ ኩሽና ቤት ገብቼ ጓደኞቼን አስተርቦብኛል” አለ አሁን የሆነ ያህል ገጹ ተሸብሽቦ እየተሽኮረመመ። ”ሌላም ስጨምርልህ” አለኝ በፍጹም ቅንነት ልምዱን እያካፈለኝ። “ቲያትሩ ላይ በመጀመሪያው ትይንት ጓዴ አወይ አያሌው ይሞትና ገዳዩን በሽመል የምመታበት ክፍል አለ፤ እኔ ግን ደንዝዤ ቀረሁ። ለምን? ብትል ከመድረክ ጀርባ እኔ የለመድኩት አፉፋና ርችት ሲተኮስ እንጂ አርቴፊሻል ጥይት እንደሚተኮስ አልነገሩኝማ” አለ በስህተቱ ታዳሚው እንዴት እንደሳቀ እየታወሰው። ወዳጆቹ እንደነገሩኝ ድምጻዊ እንዳለ ስጦታው ጨዋታ ከጀመረ ጥርስ አያስከድንምና

“እሽም ማሻ፣

የቀኑ ማማሻ።”

ይሉታል ልክ እንደቡናው፤ ይኸው እኔ ጋርም እየሰለቅነው ነው። መቼም አያልቅበት ነውና ፋታ ወስዶ ወጉን ቀጠለ እንዲህ ሲል። “ይህ እንዳለ ይሁን እንጂ 1ኛ በመውጣት ውድድሩን አሸንፈናል። ይግረምህና በዝግጅቱ ማብቂያ አንዲት ጋዜጠኛ ስለውድድሩ እየጠየቀችኝ ከዚህ በኋላስ ምን እንጠብቅ? ስትለኝ እኔ ምን አውቃለሁ ያልኩት ዛሬም ድረስ ያሳፍረኛል” አለ የሚዲያ ገጠመኙን በትዝታ ሲያጫውተኝ። “እና ይኸውልህ በዕጀጥበብ አድጌ በዕጀጥበብ የነገስኩባት አዲስ አበባ ይህን ሁሉ ጉድ ትንግርት አሳየችኝ” አለ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ቢሮ ተቀምጠን በትዝታ ፈረስ የኋሊት ሽምጥ ጋልቦ በንስር ከፍታ ከናፍቆት ሰማይ ስር መራዊን እየዞረ። ለመሆኑ እትብትህን የት ነው የቀበርከው? የጥበብ ጅማሬህስ ምን ይመስላል? በማለት ትናንትን አሻጋሪ ትዝታን ኮርኳሪ ጥያቄ አቀበልኩት።

ድምጻዊ እንዳለ ስጦታው ከአባቱ አቶ ስጦታው ደም መላሽና ከናቱ ከወይዘሮ ሻሼ መኮንን በወርሃ መጋቢት 1986 ዓ.ም በቀድሞ አጠራሩ ምዕራብ ጎጃም ሜጫ ወረዳ በኩድሚ የገበሬ ማሕበር ተወለደ። እድሜው ላቅመ ትምህርት ደርሶ አባቱ ሊያስመዘግበው ከትምህርት ቤት ደጃፍ ቢያደርሰውም እሱ ግን “አሻፈረኝ” ብሎ የእረኝነቱን ኃላፊነት ከታናሾቹ ጫንቃ ተቀበለና የገዛ እድሉን አሳልፎ ሰጣቸው፤ ዳሩ ምን ይደረጋል? ከታሰበለት ዓላማ ባይውል ከተጻፈለት እጣ ፈንታ አልጎደለምና የእርሻ መሬታቸው በመንግሥት ለልማት ተፈልጎ ካሳ ተከፍሏቸው ሲነሱ ቤተሰቡ “መሬቱም ሄዷል ምኑን አርሶ እየበላ ይኖራል? እዚያው ትምህርት ይግባና እድሉን ይሞክር እንጂ?” ሲል መከረ፡፡

እሱም ቢሆን ተጸጽቶ ኖሮ እድሉን ዳግመኛ ሲያገኝ ፈጣሪውን በማመስገን ደስ ተሰኝቶ በመራዊ ከተማ ሽንብራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ተቀላቀለ። 3ኛ ክፍል ሳለ መረዋ የባሕል ቡድን ባሕላዊ ዘፋኝ ፈልጎ ማስታወቂያ ሲያወጣ ከወሬ ወሬ የሰማው ይህ ወጣት ድምጻዊ እንዳለ ስጦታው እንዲቀናው ጥበብን ተማጽኖ ቀረበና “አለሁ” አለ። በማሕበረሰቡ ዘንድ “የኔ ልጅ አዝማሪ አይሆንም” የሚል ነቀፌታ አለና ያንተ ወላጆችስ በዚህ ጉዳይ ምን አሉህ? ስል ጥያቄ ሰነዘርኩለት። “የድሮ ነገሥታት የሕዝቡን ትርታ ለማወቅ እረኛ ምን አለ? አዝማሪ ምን አለ? እያሉ ይጠይቁ ነበር፤ እርግጥ ነው በደርግ ጊዜ ኪነተኞችንና አዝማሪዎችን ያቢዮቱ እሳት ከማንም በበለጠ ፈጅቷቸዋል፤ ይህን ያየ ማሕበረሰብም ጥላቻ ቢያድርበት አይፈረድበትም፤ የኔ ቤተሰቦች ግን በመረዋ የባሕል ቡድን ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲከናወኑ ከሚሰጠን ክፍያ ውጪ ቤሳ ቤስቲን ቋሚ የወርሃዊ ደሞዝ አልነበረንምና ይህን እያወቁ እንኳን በሙዚቃው ጥረቴን እንድገፋበት ሞራል ይሆኑኝ ነበር” ሲል የወላጆቹን ቀናኢነት አስገነዘበኝ።

ይህ በንዲህ እንዳለ ሰባተኛ ክፍል ሲሆን በፍኖተሰላም የተቋቋመው ዋሸራ የባሕል ቡድን ማስታወቂያ አውጥቶ ተወዳደረና በጥሩ ብቃት አለፈ። በልጅነት አቅም ከቤተሰብ ጉያ ወጥቶ ራስን መቻል እንዴት አደረገህ? አልኩት። “ታናሾቼ ሲማሩ የማደርስላቸው ስንቅ የበሰለ እህል ሳይሆን ዱቄቱን ወስጄ እንጀራ የምጋግርላቸው እኔ ነበርኩ፤ ይህም በመሆኑ ፍኖተሰላም መጥቼ ብቻዬን ስኖር በግሬ ለመቆም አልተቸገርኩም” አለ በራስ መተማመኑን ሁኔታው እያሳበቀ።

የቡድኑ ድምጻዊያን መሪ ነበርና ባልደረቦቹ አልባሌ ቦታ ሲውሉ ተመልክቶ “ጥበብ ህያው ብትሆንም ተቋማቱ ግን እክል ሊያጋጥማቸው ይችላልና ጎበዝ እንቆጥብ” በማለት ሲመክራቸው “በኛ ሕይወት ጣልቃ አትግባ” አሉት፤ ያለው አልቀረም በበጀት እጥረትና በሌላም ምክንያት የባሕል ቡድኑ ፈረሰ። ስለ ባሕሪው ትንሽ እንዲያጫውተኝም ጋበዝኩት ፤“በባህሪዬ “ሁሉ አማረኝን” አይደለሁም። ነገን አስቤ ባልቆጥብ ኖሮ የባሕል ቡድኑ ሲፈርስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴ ይቋረጥ ነበር፤ ደግሞምኮ ደሞዝ በልተህ ራስን ከመቻል በኋላ ወደቤተሰብ ጥገኛነት ስትወርድ ያሳፍራል” ሲል መቆም የነገን ሕይወት ለማሳመር እንደሚረዳ ጠቆመኝ፡፡

ማትሪክ ተፈትኖ ውጤት በመጠባበቅ ላይ ሳለ ባሕር ዳር የሚገኘው የምዕራብ እዝ ኦርኬስትራ ባንድ ባሕላዊ የሙዚቃ ተጫዋች ፈልጎ ማስታወቂያ ስላወጣ ተወዳድሮ ለተሻለ እድገትና አዲስ ሕይወት ልምምድ ራሱን አዘጋጀ። ቅጥሩ በሚሊተሪ መልክ ስለነበር ቢያቅማማም ከስንት ሙግት በኋላ ራሱን አሸንፎ ለስልጠና ብርሸለቆ ገባ። ሁለተኛ ሬጅመንት አምስተኛ ሻንበል አራተኛ ጋንታን ተቀላቅሎ ስልጠናው አሀዱ ሲባል “እናቴ ጥሪኝ” ብሎ ደም ቢያነባም “አይመልሰኝ” ብሎ ድንጋይ ቢወረውርም ሃምሳ አለቃ ደሳለኝ፣ መቶ አለቃ አበባውና ሺህ አለቃ መብራቱ እንደወንድም አቅርበው ሲገስጹት ልቡ ረግቶ የውትድርና ሕይወቱን አሳለጠ።

አራት ወር በፈጀ የስልጠና ቆይታቸው ያገኘውን ተሞክሮ እንዲያወጋኝ በጠየኩት ጊዜ “መልካም ስብዕናን ለመላበስ፣ በሀገር ፍቅር ለመታደስ፣ ከገጠሙን ችግሮች ለመውጣትና በጠንካራ ሞራል ለመገንባት ውትድርና ሁነኛ ብልሃት ስለሆነ ሁሉም ያገሬ ወጣት በውትድርና ሕይወት ቢያልፍ” አለ። ወታደርና ኪነጥበብ ያላቸውን ቁርኝት እንዴት ትገልጸዋለህ? ስል ጥያቄ አስከተልኩ። “ሀገርና ጥበብ የተጋመዱትን ያህል ነው” አለ ፍልቅልቅ ገጹ እያበራ። በመድረክስ ምን ገጠመኝ አለህ? አልኩት ቀልድ መሰል የቁምነገር ለዛው ተጠምተው ሲጠጡት ጥም እንደሚቆርጠው የሕይወት ውሃ መልሱ አርክቶኝ።

“መድረክ ላይ የከፋ ገጠመኝ የለኝም ግን ለይኩን ጫኔ ጋር የልበኩሩን ክሊፕ ስንቀርጽ ዓባይ ማዶ በቤዛዊት ተራራ ሽፍታ ሃያ ሺህ የሚጠጋ ገንዘብ ቀምቶናል” አለ የዛን ጊዜውን ሁነት እያሰበ። ድምጻዊ እንዳለ ስጦታው ‹‹ልበኩሩ፣ ታድጋለች ሀገሬ፣ ይወደስ ጀግና፣ ግፋ በለው፣ ሁሉን የታደለው፣ ቼ በለው፣ አመለኛው ጎጄና አንቺ ልጅ ተውበሽ የተሰኙ ስምንት የሙዚቃ ሥራዎችን ላድማጭ ተመልካቹ ያደረሰ ሲሆን ምነው በነጠላ? በጋቢስ የምናይህ መቼ ነው? ስል ላነሳሁለት ጥያቄ ሙሉ አልበም መጨረሱን ነግሮኛል። ሥራውን ለማሳተም አቅም ያላቸው ሰዎች እንዲያግዙት መልክቱ እንዳለ ሆኖ።

የለቅሶ ነው? አልኩት መነሻ ወጋችንን አስታውሼ። “አይደለም ግን እሱም ቢሆን አንዱ የጥበብ ዘርፍ ነው” አለ እየሳቀ። “የሙሾ ግጥሞች የተሰነዱት በመመረቂያ ጥናታዊ ጽሁፎች ነውና ለወደፊቱ በካሴት መልክ የማወጣው ይመስለኛል” አለ ሃሳቡን ሲቀጥል። ጉልቻ መስርቶ የአንድ ልጅ አባት መሆኑን ሰምቻለሁና ከባለቤቱ ጋር ስለነበረው ትውውቅ ጠየኩት። “አዳሜ እጁ ላይ ባለው ስልክ ሲነቋቆር እኔ ግን ሚስቴን ታደልኩበት” በማለት አያይዞ ማሕበራዊ ሚዲያን በተመለከተ ወጣቱ ልብ እንዲገዛ ምክሩን ለግሷል። ጥበብ ምን ከፈለችህ? ስል ላነሳሁለት የማብቂያ ጥያቄ ይህን አለኝ። “ከሰው ፍቅር በላይ ምን አለ ብለህ ነው? የቱንም ያህል በሃብት መክበር ብሻ እንኳን የነፍስ ጥሪዬን እንዳልበድል ስል የገንዘብ ፍላጎቴ እንብዛም ነው” አለ የድሮ አርቲስቶቻችንን አብዝቶ በማድነቅ። ባሁኑ ሰዓት በባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ የባሕል ማእከል ውስጥ እየሰራ ይገኛልና ሕልሙ ለምልሞ የልቦና መሻቱ ተፈጽሞ እንዳይ መልካም ምኞቴን በመግለጥ ጽሁፌን ቋጨሁ።

ሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You