መቋደሻ

ሦስት ወንደላጤ ጓደኛሞች መኝታ ለየብቻ ሆኖ ሳሎኑን በጋራ ልንጠቀም ተስማምተን ኮንዶሚኒየም ተከራየን። ወቅቱ ዓውዳ ዓመት ቢሆንም ሐና መሐላችን በመኖሯ አላሳሰበንም። የእሷ መኖር ከገመትነው በላይ ኑሮን በማቅለል ፋንታ እንዳከበደብን የተረዳነው ዘግይተን ነበር።

ሐና “በዓልን ለምን ቤት አታከብሩም?” በማለት ሃሳብ አመጣ ብላ ለእንቁላልና ለዶሮ ብልት ክፍፍል አሳመፀችን። ፈረሰኛውን ማን ይወስዳል? የመቋደሻውስ ነገር እንዴት ይሆናል? እያልን ደረጃ ስንለካካ ቶማስና የሽዋስ በሐና የይገባኛል ጥያቄ ያረገዘ ኩርፊያቸው ሰበብ አግኝቶ ፈነዳ።

ማዕድ ከመቅረቡ በፊት ሁለቱ ጩልሌዎች ያበረከቱላትን ስጦታ ጠረጴዛ ላይ አስቀመጠችው። “ይከፈት? ይከፈት?” አልኩ ለብቻዬ የብሽሽቅ ጨዋታው ይበልጥ እየናፈቀኝ፤ እነሱ ግን አፍረው ነበር።

የየሽዋስን ብትከፍተው ፓንትና ጡት ማስያዣ ነው። ቶማስ በሳቅ እየተንፈራፈረ “ኧረ በተሰቀለው! ኋላ ቀር ጅንጀና ነው አባቴ ይሙት፤ ዘለህ ፊጥ ትላለህ?” በማለት አሸማቀቀው። “ዝም በለው የሹዬ፤ ገበናሽን እጠብቅልሻለሁ ማለትህ እንደሆነ ይገባኛል” ስትለው ጊዜ ከነፍሷ ያቀረበችው መስሎ ስለተረዳው ሐሴት አደረገ። ቀጠለችና የቶማስን ብትከፍተው ጌምፓሪስ ሽቶ ነው። የሽዋስ በተራው “ምነው ብብት ስር ተወሸክ?” አለና አጸፋውን መለሰ።

እርግጥ ነው ሐኒቾ መልክን ከፀባይ አሟልቶ የሰጣት ደመ ግቡ ስትሆን የጀመረችውን የኮሌጅ ትምህርቷን ለመጨረስ የወላጆቿን ደሳሳ ጎጆ ይበልጥ ላለማጉበጥ እኛ ዘንድ ባብሳይነት ተቀጥራ ብትሠራም የየሽዋስና የቶማስ ድብብቆሽ ቁንጥጫ እረፍት ነስቷታል። “አንተ ግን አልሰጠኸኝም” አለች ለኩርፊያ ከንፈሯን አሞጥሙጣ።

“ለጋዜጣ የሚሆን ሃሳብ አላዋጣው ብለሽ ይሆናላ” አለ ቶማስ የጎሪጥ እያየኝ። የተንዠረገገ ጺሙ ካርል ማርክስን አስመስሎታል። የዛየን ትሪብልን “ትሩ ሪቮሊውሽን” ሙዚቃን አብዝቶ ያደምጣል። የፍራንሲስኮ አልቫሬስን “ዘ ፖርቹጊዝ ሚሽን ኢን አቢሲኒያ” መጽሐፍንም ከእጁ አይለይም። “ታውቃለህ? እኔኮ ስሜቴ እንጂ ሆዴ ተርቦ አያውቅም” ይላል። ይህ አባባሉ “እኔ መሆን የነበረብኝ ደራሲ ነው” ለሚለው ዲስኩሩ ጉዝጓዝ ነው።

የሽዋስ “ኤዲፐስ ኮንፕሌክስን” ባነሳ ቁጥር ለሁለት ሺህ ዓመታት ያህል ያለማቋረጥ በዕይታ የዘለቀውን “አንቲገን” የመድረክ ቲያትርን ያስታውሳልና “ቲያትር ልጋብዝሽ ሐኒዬ?” አለ እጇን ስቦ ከደረቱ እያስጠጋ። ቶማስ በቅንድቡ ስር ቅናት እያለፈ “በረሃብ ቀቀልሽን ምግብ አቅርቢ እንጂ?” አለ ሁኔታቸው ባይጥመው።

ምግብ ቀርቦ መብላት ተጀመረና የሽዋስ “ብይልኝ የኔ ቆንጆ” እያለ ባፍ ባፏ ሲያጎርሳት “ያዋጣኸው ብቻህን መሰለህ እንዴ? ብይልኝ ሳይሆን ብይልን ነው የሚባለው” አለ ቶማስ ቀልድ አስመስሎ ቁጭቱን እየገለጸ። ተጀመረ! አልኩ ነቆራቸው ሳይከር እንዲያጫውተኝ ፈልጌ። “ምኑ?” አለች አትኩራ እያየችኝ። በምን እንደሚጣሉ ታውቃለችና ለምን አፍርጬው አንገላገልም? አልኩና ፈረሰኛውን በእድሜ ትልቅ የሆነ ይወስዳል፤ መቋደሻውን ግን ከሐኒቾ ጋር ማን ነው የሚቆርሰው? ስል ዙሩን አከረርኩት።

“ትልቅ ብሎ ነገር የለም፤ ሁሉም በዕጣ ነው” አለ ቶማስ ወረቀት እየጠቀለለ። ፈረሰኛውስ ይሁን፤ አበው ሲናገሩ እንደሰማሁትና እኔም እንደማውቀው ዶሮ ታርዶ መቋደሻውን ብቻውን የበላ ሰው እድሜ ልኩን ሳያገባ ይኖራል፤ ደግሞምኮ ባልና ሚስት መቋደሻውን የሚካፈሉት ክርስቶስ ለሐዋሪያቱ ቆርሶ የሰጣቸው የሥጋው ምሳሌ ስለሆነ ነው። መቼስ አንድ አካል አንድ አምሳል አይደሉ? ብዬ የፈጠርኩትን ታሪክ ሳጫውታቸው ሁለቱም ሃሳብ ገባቸው።

የሽዋስም ቶማስም ብቻዬን ስሆን እየጠበቁ ሐናን እንደሚያፈቅሯት አዋይተውኛል፤ እሷም በበኩሏ ሁለቱም ምርጫዋ እንዳልሆኑ ነግራኛለች።

ለማውራት አጋጣሚ እንዲሆናቸው አስበው መሰለኝ “ማን ለማን ይሰጣል” ተባብለው የወርሐዊ አስቤዛ መዋጮን እንኳን በእጇ ነው የሚሰጧት። እኔ ግን ቋሚ ምልክት አበጀሁና “ያስቤዛ ብር ስጠኝ” በሚል ሰበብ ከሚመጣ ቅርርብ ራሴን አሸሸሁና ድንበር ተከልኩ። ከዚህም የተነሳ ግንኙነታቸው የት እንደደረሰ አላውቅም። እንቁላሉን እየቆጠረች እኩል ስታዳርሰን በሉ ጎበዝ ተፈራራችሁኮ አልኳቸው ያቦን ግብር እንደበላ ልክፍተኛ ደንዝዘው ባይ።

“ሐና እኩል አታዳምጠንም፤ ዛሬ እንኳን በዓሉን ቤት ለማክበር የሽዋስ እሺ ባይላት ኖሮ አትመጣም ነበር” አለ ቶማስ የምሩን ተናዶ። “ስለምን መቅረትና መደመጥ ነው የምታወራው? ለኔ እንደሆነ ሁላችሁም ወንድሞቼ ናችሁ፤ እና ምን የተለየ ነገር አይተህብኝ ነው የምታሳጣኝ?” አለች ልትጎርስ ያለችውን ጉርሻ መልሳ። “ምነው ጃል ቀናችንን አካፋህበት? ቅሬታ ካለህ ራስህን ችለህ ጠይቅ፤ ደግሞስ ለማን ነው አቤት የምትለው?” አለ የሽዋስ የነገራቸው አያያዝ ቅፍፍ እያለው ተሸማቆ። “ያም ሆነ ይህ መከባበር በሌለበት ቤት መቋደሻውም ቢሆን ሥርዓተ ክብሩ አይፈጸምምና በዕጣ ይሆናል” አለ ቶማስ ከስሜቱ ሸሽቶ ልቡን እያራቀ።

“ለነገሩ ዶሮውን ያረደው እኮ ነው ፈረሰኛውንም መቋደሻውንም መውሰድ ያለበት?” አለ ቶማስ ደንግጦ ከእንቅልፉ የነቃ ይመስል። የሽዋስም ቀበል አድርጎ “በቤቱ ውስጥ አባወራ ከሌለ ለባህሉ ክዋኔ ሲባል ወንድ ሕጻን ልጅም ሊያርድ ይችላል” በማለት አፉን አሲያዘው። “ምነው ዝም አልክ አንድ ነገር በል እንጂ?” አለች ሐና መላ እንዳመጣ ሽታ።

ሁለታችሁም ልትስማሙ አልቻላችሁምና መቋደሻውን ከማን ጋር እንደምትቆርሰው ራሷ ትምረጥ ስል ብልሃት ዘየድኩ። “ይሻላል” “አዎ ይሻላል” አሉ ደግ ነገር ለዕድላቸው እየተመኙ።

አለበለዚያ ግን የሚዳቆዋ ተረት እናንተ ላይ እውን ይሆንና የመቋደሻው ዕድል ወደኔ እንዳይመጣ ብላቸው “አታደርገውም” ሲሉ “ምን አለበት? እንዳውም ከሱ ጋር ነው የምቆርሰው” ከማለቷ “ምን?” አሉ ባንድነት በጥፊ የተመቱ ያህል ክው ብለው። ያላሰብኩት ነበርና እውነቱን ለመናገር እኔም ደነገጥኩ…።

ሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You