በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ታላቁ የቦስተን ማራቶን ዛሬ ለ127ኛ ጊዜ ይካሄዳል። ከመቶ በላይ አገራት የተውጣጡ ከሠላሳ ሺ በላይ ተወዳዳሪዎች በሚፋለሙበት በዚህ ውድድር እንደተለመደው የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ለድል ይጠበቃሉ፡፡ በተለየ መልኩ ግን ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአትሌቲክስ አፍቃሪዎችን ትኩረት መሳብ ችለዋል።
የ2022 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዩጂን ኦሬጎን ላይ በድንቅ አጨራረስ የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያውን ያጠለቀችው ጎይተቶም ገብረሥላሴ በዛሬው የቦስተን ማራቶን ትኩረት መሆኗ የተጠበቀ ነው። የሃያ ስምንት ዓመቷ የወቅቱ የማራቶን ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው አርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩን 2:18:11 በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ እንደነበረ ይታወሳል። ጎይተቶም በ2021 የበርሊን ማራቶን ማሸነፏ የሚታወስ ሲሆን ከዓመት በኋላም በ2022 የኒውዮርክ ማራቶን ሦስተኛ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች። ይህም የማራቶን ስኬቷ በዛሬው የቦስተን ማራቶን በርካቶች ዓይናቸውን እንዲጥሉባት አድርጓል።
በማራቶን የኢትዮጵያ የሴቶች ክብረወሰን በመስበር 2፡14.58 ሰዓት ያስመዘገበችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አማኔ በሪሶ በዛሬው የቦስተን ማራቶን ትኩረት የተሰጣት ሆናለች። ይህች የሠላሳ ስድስት ዓመት አትሌት እኤአ በ2016 ይህንኑ የቦስተን ማራቶን ማሸነፍ የቻለች ሲሆን፣ እኤአ በ2012 እንዲሁም በ2016 የቺካጎ ማራቶንን በድል ፈጽማለች። በተጨማሪም እኤአ በ2009 እና 2010 የፓሪስ ማራቶንን አከታትላ ማሸነፍ የቻለች ሲሆን በርቀቱ ያላት ደማቅ ስኬት ዛሬ ለድል እንድትጠበቅ ምክንያት ሆኗል። ሕይወት ገብረማርያምና አባብል የሻነህም በዛሬው ቦስተን ማራቶን ድል ለመጎናፀፍ ትግል የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ የ5ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችው ኬንያዊቷ ሄለን ኦብሪ በዚህ መድረክ እንደምትሳተፍ ማረጋገጫ መስጠቷን ተከትሎ በኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን መካከል የሚደረገውን ፉክክር በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ ኦብሪ በ12 ዓመት የፕሮፌሽናል አትሌትነት ሕይወቷ ይህ ሁለተኛ የሙሉ ማራቶን ውድድሯ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በኒውዮርክ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፋ በ6ኛነት ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡ ከሦስት ሳምንታት በፊት ደግሞ ዛሬ በምትፎካከርበት ቦስተን በግማሽ ማራቶን ተወዳድራ የቦታውን ክብረወሰን 1፡07.21 በማሻሻል ጭምር ማሸነፏ ይታወሳል፡፡
በወንዶች መካከል በሚደረገው ፉክክር የሠላሳ ሶስት አመቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት የአሸናፊነት ቅድመ ግምቶችን ማግኘት ችሏል። ይህ አትሌት ለቦስተን እንግዳ አይደለም፣ሌሊሳ ዴሲሳ ይህን ውድድር ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ቦስተን ላይ ትልቅ ዝና አለው። የመጀመሪያ ድሉን እኤአ 2013 ላይ ማሳካቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በኋላም 2015 ላይ ተመሳሳይ ድል በእጁ አስገብቷል። ሌሊሳ የመጀመሪያ ድሉን ቦስተን ላይ ባስመዘገበበት ውድድር መጨረሻ የደረሰው የቦንብ አደጋ የሚታወስ ሲሆን እሱም ሜዳሊያውን ቦንብ ፍንዳታ ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች መታሰቢያ እንዲሆን ማበርከቱ አይዘነጋም። ይህም አትሌቱን በቦስተን ከተማ እጅግ ታዋቂና በርካታ ደጋፊዎች እንዲኖሩት አድርጓል። ሌሊሳ እኤአ በ2018 የኒውዮርክ ማራቶንን ከማሸነፉ ባሻገር 2019 ላይ በኳታር ዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወርቅ ማጥለቁ ይታወሳል። ይህ ከብዙ ጥቂት የማራቶን ስኬቱ ሲሆን ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ በቦስተን ማራቶን አሸንፎ የማይረሳ ታሪክ ይፅፋል ተብሎ ተጠብቋል።
በሁለቱም ፆታዎች በቀዳሚነት ያሸነፉ አትሌቶች በነብስ ወከፍ 150 ሺ ዶላር ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ክብረወሰን ያሻሻሉ አትሌቶች ደግሞ ተጨማሪ 50 ሺ ዶላር ጉርሻ የሚያገኙ ይሆናል። ከ2ኛ-10ኛ ባለው ደረጃ የሚያጠናቅቁ አትሌቶችም ከ75 ሺ እስከ 5,500 ዶላር ሽልማት እንደሚያገኙ ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 9 ቀን 2015 ዓ.ም