ይህ ርዕሰ ጉዳይ እንደ ባህር የሰፋ፣ እንደ ውቅያኖስ የጠለቀ ባህርይ እንዳለው ይገባኛል:: ርዕሰ ጉዳዩን ከባህሩ ወይንም ከውቅያኖሱ በማንኪያ መስፈሪያ ጨልፌ ለማንሸራሸር መፈተኑ አይቀርም:: ቢሆንም መጽናኛ አለ:: ለምሳሌ፤ የአንድ ውቅያኖስ ጨዋማ ባህርይ ወይንም የአንድን የባህር ውሃ ይዘት ለማጥናትና ለምርምር ለማዋል ወደ ቤተ ሙከራ የሚወሰደው በማንኪያ ስፍር የተመጠነ ናሙና እንጂ ውቅያኖሱ ራሱ ወይንም ባህሩ ለጥናቱ ዓላማ ወደ ቤተ ሙከራው እንዲፈስ አይጠበቅም::
ብዙ ሳይንሳዊ ምርምሮች የሚደረጉት በናሙና ጥናት ላይ በመመሥረት መሆኑን ልብ ይሏል:: ሌላው ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር የሚነሳው ተግዳሮት የስያሜ ጉዳይ ነው:: ለመሆኑ የጥበባቱ የወል መጠሪያ ኪነ ጥበብ ነው ወይንስ ሥነ ጥበብ? ሁለቱን የወል ስያሜዎች የሚለዩአቸው አላባዎች (elementes) ምንድን ናቸው? ለዚህ ለሁለተኛው መሠረታዊ ጥያቄም የጠለለ ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ አልተቻለም::
ከዛሬ ሦስት አስርት ዓመታት በፊት በሳምንታዊዋ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ “ኪነ ጥበብ ወይንስ ሥነ ጥበብ” በሚል ርዕስ የውይይት ሃሳብ ማቅረቤን አስታውሳለሁ:: በዘመነ ወጣትነት ያነሳሁት ርዕስ በጉልምስናና በእርጅና ዕድሜያችንም ምላሽ አጥቶ ከሽበት ጋር ጋልቦ እየደረሰብን ነው:: ለጊዜው በተግዳሮትነት የጠቀስኳቸውን ስጋቶች ወደ ጎን አድርጌ ኪነ ጥበቡ በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እየተወጣው ስላለው ድርሻና መወጣት ስለተሳነው ጉዳይ ጥቂት ሃሳቦችን ልሰንዝር:: ኪነ ጥበብ አልነውም ሥነ ጥበብ ለማንኛውም የወል ስሙ ጉዳይ ለጊዜው በይደር ይተላለፍና ጥበቡ አቅፎ የያዛቸው ቤተሰቦች ግን በርካታ ስለመሆናቸው ጠቁሞ ማለፉ አግባብ ይሆናል:: ስለ ሙዚቃ ለመጻፍ ተፈልጎ ደጃፉ ቢንኳኳ የሚከፈቱልን በሮች በርካቶች ናቸው::
ሥነ ጽሑፍን እንጥራ ብንል “አቤት ባይ ቅርንጫፎቹ” ዝርዝራቸው በርካታ ነው:: በስዕል፣ በቴአትር፣ በፊልም፣ በቅርጻ ቅርጽ እያልን የጥበብ ዓይነቶቹን ለመፈታታትና ለማፍታታት ብንሞክርም የተገጣጠመ አንዳች አርኪ ምስል ለመፍጠር በጥራዝ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር በጋዜጣ እንጎቻ ጽሑፍ የሚሞከር አይሆንም:: ይህም ተግዳሮት በራሱ ፈታኝ ቢሆንም በተቻለ መጠን የሀገራችንን ወቅታዊ የኪነ ጥበባት ውሎ አምሽቶ በዝርዝር ጥናትነት ሳይሆን በአጠቃላይ ዳሰሳ መልክ ለመቃኘት ይሞከራል:: በግል እምነቴ የሀገራችንን የጥበባት አቅም በሚገባ የተጠቀመበት የደርግ ሥርዓት እንደነበር አስባለሁ:: ሥርዓቱ ጥበባቱን ለመልካምነትም ሆነ በተቃራኒው የበዘበዘው አምራቹን ጠቢብ አግልሎ፤ የጥበብ ምርቱን ብቻ በማክበር አልነበረም::
ሁለቱንም መሳ ለመሳ አቅፎና አክብሮ ዓላማውን አስፈጽሞበታል:: ጥቂት ማስረጃ ልጥቀስ:: የደርግ አስተዳደር በኪነ ጥበባቱ ዙሪያ ሳንሱር የሚባል በብረት የታጠረ በረት ከገነባ በኋላ ጠቢባኑንም ሆነ ጥበቡን በዚያ ማዕቀፍ ውስጥ በማጠር ለሥርዓቱ ዘብ አድርጎ ሰየማቸው:: በማስከተልም የጥበብ ማኅበራቱን በአይዲዮሎጂው ካጠመቀ በኋላ የየጥበባቱን ብሔራዊ ማኅበራት ሊቃነመናብርት የፖለቲካ ድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አድርጎ ሾማቸው፤ ለያቸው:: ማኅበራቱ በገንዘብና በቢሮ ችግር እጅግም እንዳያጉረመርሙም ለሁሉም ሀገራዊ የሙያ ማኅበራት (የድርሰት፣ የቴአትር፣ የሙዚቃ፣ የስዕል ወዘተ.) ዓመታዊ የአስር ሺህ ብር ዳረጎትና የተመቻቸ የቢሮ ቁልፍ አስረከባቸው::
ከዚያማ ምን ይጠየቃል “ፈረሱም ሜዳውም ይሄው” ብሎ ከሳንሱር በረት ሾልከው እንዳይወጡ እያገዳቸው ለግልቢያ ለቀቃቸው:: በእውነትም የሶሻሊዝምን አይዲዮሎጂና ተያያዥ የወቅቱን ማኅበራዊ ሕይወትና የአብዮቱን ታላቅነት የሚያወድሱ የብዕርና የጥበብ ትንታጎች ከቀበሌ አዳራሽ እስከ ብሔራዊ ቴአትር ተንበለበሉ:: የሙዚቃው ዘርፍም የሶሻሊዝምን ብጽእና እየሰበከ አየሩን በስፋት አጠነው:: የቴአትር መድረኮችም በርዕዮተ ዓለሙ “ቀይ ባንዲራና ቀይ ጭብጥ” አሸበረቁ::
ከወቅቱ የቴአትር ዘርፍ ይዘት በማንኪያ መስፈሪያ ያህል ጥቂት አብነት የምጨልፈው የወዳጄን፣ የታላቁንና የማከብረውን የደራሲ አያልነህ ሙላቱን ሶሻሊዝም ለበስ የሆኑ የመድረክ ሥራዎችን ይሆናል:: ቴአትሮቹ ከ1968 – 1977 ዓ.ም በነበሩት አፍለኛ የአብዮቱ ዓመታት ለመድረክ የበቁ ነበሩ:: እነሆ ዝርዝራቸው፤ እሳት ሲነድ፣ ሻጥር በየፈርጁ፣ የገጠሯ ፋና፣ የፊት ዕድፍ፣ የመንታ እናት፣ ዱባና ቅል፣ ጥልቅ ዓይን . . . ለምሳሌነት አያንሱም:: በሙዚቃው ዘርፍም እንዲሁ በሥርዓቱ የተተገበሩ በርካታ ሀገራዊ ግዙፍ ተግባራት ተዚሞላቸዋል:: ተዘምሮላቸዋል::
ተዘፍኖላቸዋል:: ለዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ፣ ለአረንጓዴ ዘመቻ፣ ለሶማሊያ ወረራ ዘመቻ፣ ለሰሜኑ ዘመቻ፣ ለመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ወዘተ ለሁሉም ዘመቻዎችና ለሥርዓቱ አዝማቾች ጭምር የሙዚቃ ጠል ተንዠቅዥቆላቸዋል:: አንጋፋው ደራሲና ጸሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ በአንድ ጉባዔ ላይ በቀልድ እያዋዙ የተናገሩት ንግግር እዚህ ቢጠቀስ ወጉ ያምራል:: አረንጓዴ ቅጽል የተሰጠው የወቅቱ የልማት ዘመቻ እንደታወጀ የደርግ ሹሞች የኪነ ጥበባቱን ባለሙያዎች ሰብስበው በሙያቸው ዘመቻውን እንዲያግዙ መመሪያ ሲሰጣቸው እኚህ ጎምቱ አባት ለአስተያየት እጃቸውን በማውጣት “ምን ችግር አለና ቀይ ዘመቻ ሲታወጅ ቀይ ጽሑፍ እንጽፋለን፣ አረንጓዴ ዘመቻም ሲታወጅ አረንጓዴ ጽሑፍ ለመጻፍ አንቸገርም::”
ዘመኑን በጥሩ ቋንቋ ገልጸውታል:: በድርሰቱ ዘርፍም እንዲሁ “ለቀይ አበባ” (ታደለ ገ/ሕይወት)፣ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” (በዓሉ ግርማ)፣ “ጽጌሬዳ ብዕር” (የበርካታ ደራስያን ግጥም ሥራዎች)ን የመሳሰሉ የዘመኑ ምስክር ሥራዎች ለንባብ ቀርበዋል:: ስዕሉና ቅርጻ ቅርጹማ አደባባዮችንና አዳራሾችን አጥለቅልቆ እንደነበር ያልመሸበት ታሪካችን ይመሰክራል:: የማርክስ፣ የኤንግልስና የሌኒን ሦስት በአንድ ስዕሎች፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ተጎራብቶ የቆመው ትግላችን፣ ግዙፉ የሌኒን እና የማርክስ ከወገብ በላይ ሐውልቶች በመዲናችን አዲስ አበባ ገዝፈው ተሰይመው ነበር:: በየክፍለ ሀገሩም ምስላቸው ብርቅ አልነበረም:: ዘመኑ ካዘመራቸው ዜማዎች መካከል ለዕድገት በኅብረት ዘመቻ የተዜሙትን የጥላዬ ጨዋቃ፣ የታምራት ሞላና በኋለኛው የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ወቅትም የጸሐዬ ዮሐንስና የሌሎቹን እና የወታደራዊ ክፍሎች ዜማዎች ዛሬም ድረስ በህሊናችን ውስጥ የህያውነት ሐውልት ተክለው አልፈዋል::
የሶማሊያ ወራሪ በደፈረን ጊዜም የተዘመሩትና የተዜሙት “ወደፊት በሉለት እና ግፋ በለው”ን መሰል ይዘት ያላቸው የጥበብ ሥራዎች አይዘነጉም:: ጥላሁን ገሠሠን፣ ሂሩት በቀለንና የተባ ብዕር ባለቤቱን የወዳጄን የሻለቃ ክፍሌ አቦቸር አብዮታዊ የዜማ ግጥሞች አስታውሼ ብቻ የማልፈው የጋዜጣ ጽሑፉን የቆነጠርኩበት የማንኪያ ስፍር አላፈናፍን ስለሚለኝ ነው:: አጠቃላይ ትውስታው በመልካም ትዝታዎች ላይ አተኮረ እንጂ ስለ ዘመን ደርግ ሥርዓት ገና ተጽፎ አላለቀም:: እንዳው በድፍኑ የዘመኑ የሳንሱር የሰላ ጥርስ ብዙዎችን ነክሷል:: ብዙዎችን አስነክሷል:: ለብዙዎች ሕይወት መጥፋትም ዋና ሰበብ ሆኗል::
እንዲዚያም ቢሆን ግን የሳንሱሩን የብረት ሳንቃ ሾልከው የወጡና አምባገነኑን ሥርዓት እና የሥርዓቱን ዘዋሪዎች በድፍረት በመሞገት ዘመናቸውን ዋጅተው ያለፉና ዛሬም ለምስክርነት የሚቆሙ ብዙዎች ናቸው:: በታሪክ ፊት ሊወደሱና ሊመሰገኑ ይገባል:: “ከታሪክ መሰዊያ ላይ አመዱን ሳይሆን እሳቱን ጭረን” ከተንደረደርን ዘንዳ ወደ ዛሬው እውነታችን ተመልሰን በወቅታዊው የኪነ ጥበባችን ዙሪያ መጠነኛ ቅኝት እናድርግ:: የሀገራችን ሳንሱር ተቀብሮ አረም ከበቀለበት ዓመታት ተቆጥረዋል:: የደራስያን ብዕሮች፣ የሙዚቀኞቻችን ኖታዎች፣ የሰዓሊያን ብሩሾች፣ የቀራፂያን መሮና መዶሻዎች ከሳንሱር እስረኝነት ከተፈቱም ሰነባብቷል:: እስራቱ ሳይፈታለት ኖሮ በቅርቡ ከቁራኛው ነፃ የሆነውን የጥበብ ዘርፍ እንጥቀስ ብንል ቶሎ ወደ አእምሯችን የሚመጣው የፊልም ጥበብ ነው::
ይህ የጥበብ አቡጀዲ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በስውርና በእጅ አዙር አጥቂነት “ልዩ የጥበብ ደንብ አስከባሪዎች” አቁሞ እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ ጥበቡን ሲያቀጭጭ መኖሩ አይዘነጋም:: ይህም ጉዳይ ቢሆን በዘመነ ነብዩ ባዬ የቢሮ ኃላፊነት ዘመን አቡጀዲዎቹ ከከፈን ጨርቅነት ነፃ መውጣታቸው ተበስሯል:: ነብዩ እናመሰግናለን:: ስለሆነም፤ የወቅታዊ ሀገራችን ኪነ ጥበባት ከሳንሱር የፀዳ ነፃ አየር እየተነፈሱ ብዕራቸውን ቀለም እንዲያጠቅሱ፣ ዜማቸውን በነፃነት እንዲቀምሩ፣ ብሩሻቸውን ያለስቅቅ እንዲያጫውቱ፣ ፊልሞቻቸውን እንዳሻቸው ለትዕይንት እንዲያቀርቡ፣ ቴአትራቸውን ያለገደብ እንዲተውኑ ዘመኑ የፈቀደ ቢሆንም እንደ ብዙኃኑ ሕዝብ ፍላጎት ለመራመድ ግን ልምሻው ገና የለቀቃቸው አይመስልም::
በእኔ የግል ምልከታ ጥበባቱ ከመቼውም ዘመናት በከፋ ሁኔታ የኢትዮጵያዊነት ክብር ሲጎድፍ እያስተዋሉ፣ የሕዝባችን ፍቅር ነፋስ ሲገባው እየተመለከቱ፣ አብሮነታችን ሲሸረሸር ከሩቅ እየተመለከቱ ዝምታ መምረጣቸው ግራ ያጋባል:: ደግሜ እላለሁ፤ ሀገራችንና ሕዝባችን የፍቅር ርሃብተኛ በሆኑበት በዚህ የዘመን ክፉ “እንደ ረሃብ ቀን ሰብል” አብዛኞቹ ጠቢባን በትልቅ ጉጉት እየተጠበቁ ሳለ ምላሽ ያለመስጠታቸውን ስናስተውል የህሊና ቅጣትና የዜግነት ተጠያቂነት ብቻ ሳይሆን የታሪክ በትርም ሳያርፍባቸው እንደማይቀር ይሰማናል:: በሀገሪቱ ብልጭ ያለው የለውጥ ኮከብ በጥቁር ደመና እንዳይከደን፣ ተነቃቅቶ የነበረው የሕዝብ መንፈስ ወደ ድብርት እንዳይመለስ፣ ሀገራዊ ተስፋችን በንኖና ተንኖ እንዳይጠፋና በመሪዎቻችን የተሰበከልን የአብሮነት ርዕይ ወደ ቅዠትነት እንዳይለወጥ ኪነ ጥበባቱ ተግተው መሥራት ሲገባቸው ተግተው እየሸሹ በሚመስል ሁኔታ ሽልብታን መርጠዋል::
ተቃቅፎ፣ ተከባብሮ፣ ተጋብቶና ተዋልዶ ለዘመናት በኖረው ሕዝባችን መካከል ፖለቲካው የፈለፈላቸው የክፋት አረሞች “እንደ ጣናው እምቦጭ” በአንድ ሌሊት ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በፈጣን ሁኔታ ሲስፋፉ የጥበባቸውን ጋሻ መክተው የዘረኝነቱ አረም እንዲመክንና ተነቅሎ እንዲወገድ በብዕራቸው፣ በበገናቸው፣ በቡርሻቸው፣ በመድረካቸው፣ በአቡጀዲያቸው መፋለም ሲገባቸው የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብለው ማሸለባቸው ደግ አይደለም:: ማን እንዳደረገው ያድርጉ ተብሎ ቢጠየቅ፤ እጅጋየሁ ሺባባውን (ጂጂ) እና ቴዎድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮን) ለመልካም አበርክቶታቸው መጥቀስ ይቻላል:: ቀደም ሲል ምሳሌዎቼን በማንኪያ ስፍር መመጠኔን አበክሬ ስለገለጽኩ “እነ እከሌን ለምን ዘነጋህ?” እንደማልባል ተስፋ አደርጋለሁ:: የሁሉም ለሁሉም የሆነው የሀገራችን የወቅቱ ባህላዊ የዜማ ይትባህል እየተናደ ክፉ የዘረኝነት የፖለቲካ ሥርዓት ወደ ክልል ደረጃ አውርዶት “የእኛ ብቻ!” መባሉ ሊመከርበት ይገባል:: እርግጥ ነው ትናንትም ሆነ ዛሬ የባህል ዘፈኖች ነበሩ፤ ዛሬም መኖራቸው እውነት ነው:: ችግሩ የትናንቱ ዜማ በሕዝብ ስሜት ውስጥ የሚንሸራሸረው ውበትና ፍቅርን ለማቀጣጠል እንጂ እንደዛሬው ባለ ባህሉ ሕዝብ የተዋለደውንና የተጋመደውን ሌላኛውን ወንድም ሕዝብ ቂምና ጥላቻውን በመግለጽ “እንዲያው ዘራፌዋ” እንዲያንጎራጉርበት አልነበረም::
ብዙዎቹ ባህላዊ ዘፈኖች ለማዝናናትና የባለ ባህሉን የከበረ ዕሴት ለማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ የማያንፁ ደባል መልዕክቶችም ሲሰነቀሩበት ይስተዋላል:: የተከበረውን ወግ ወደ ጎን ገፍቶ ጠመንጃ እያነጣጠረ፣ ጦርና ጋሻ ታጥቆ ጥላቻ ባግተረተረው ፊት “ኑና ሞክሩን!” በወራሪ ጠላት ላይ ካልሆነ በስተቀር በራስ ወንድምና እህት ላይ ሊተገበር የሚገባው አይመስለኝም:: በሁሉም ዘርፍ ለረጅም ዘመናት የጋራ ሀገራዊ ጀግኖቻችን እያልን ስናከብራቸውና ስናደንቃቸው የኖሩ አብነቶቻችንም በየክልሉና በየጎጡ ተነጥቀውብን “የእኛ ብቻ ናቸው” ሲባሉ መስማት ያማል:: የእከሌም፣ የእነ እንትናም፤ የእኛም ናቸው:: የጋራ ጀግኖቻችን በፍጹም የጎጥ “ነፃ አውጭዎች!” ተደርገው ሊሳሉልን አይገባም::
አልፎም ተርፎ ከአሁን ቀደም በጋራ አክብረን በጋራ የዘመርንላቸው ምሳሌዎቻችን “የእከሌ ክልል ጀግኖች” ናቸው እየተባለ የልዩነት ቀለም ሲቀቡ ማስተዋል እኛን ለጉድ የጎለተንንም ሆነ ለታሪክ ለራሱ የራስ ምታት የሚሆን ይመስለኛል:: የአንዳንድ ምግባረ መልካም (Role Model) ኢትዮጵያዊ ጀግና ስም በአንዳንድ አካባቢዎች ከነጭራሹ ስሙ እንዳይነሳ ገደብ ተጥሏል መባልንም እየሰማን ነው:: ይህም ያማል:: የሥነ ጽሑፋችን ጉዳይም በእርጋታ ቢፈተሽ አይከፋም:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግጥምን ከሙዚቃ ጋር እያዋሃዱ ማቅረብ የተለመደ ሆኗል:: ይህ አዲስ ባህል ማበቡ መልካም ነው:: የዘመኑ ትውልድ ያተመው አሻራ ተደርጎም ሊቆጠር ይችላል::
ቢሆንም ግን በየመድረኩ የሚቀርቡት የብዙ ወጣቶቻችን ግጥሞች ከፌዝና ከቀቢፀ ተስፋ አዋጅ ነጋሪነት ቢታቀቡ መልካም ይሆናል:: መድረኩ ከዚህን መሰል ችግር እንዲነፃ ብዙ ሊሠራበት ይገባል:: ሀገርን ከል ከማልበስ ይልቅ የተስፋ ጥበብ እያለበሱ ህፀፆችንም በአግባቡና በጨዋነት እየተቹ የራስን ክብር ጠብቆ፣ ለአድማጩም ክብር መስጠት አግባብነቱ ሊረሳ አይገባም:: ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርከት ተደርገው እየታተሙ ያሉት መጻሕፍት በዋነኛነት በግለ ታሪክ ይዘት ላይ ያተኮሩ ናቸው:: በርካታ መጻሕፍትም ነገሮችን የሚያጋግሉና በይድረስ ይድረስና በገበያ ሽሚያ በቀናት ዕድሜ ተጽፈው ለአንባቢው ሲቀርቡ እያስተዋልን ነው:: እነዚህን መሰል መጻሕፍት ለንባብ መቅረባቸው ክፋት የለውም:: በተለይም ግለ ታሪኮቹ በእጅጉ የኋሊት ዞረን ከባለታሪኩ ሕይወት ጋር የተጋመዱ እውነታዎችን ልንመለከትበትና ለአንኳር ሀገራዊ ታሪኮቻችን እንደ ማመሳከሪያ ልንጠቀምባቸው እንችል ይሆናል:: ነገር ግን በተለያዩ ወጀቦች እየተላጋ ያለውን ዘመናችንን የሚሄሱ ተነባቢ የድርሰት ሥራዎች የምንፈልገውን ያህል ማግኘት አልቻልንም:: የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ”፣ የሀዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር”፣ የብርሃኑ ዘርይሁን “ሦስት ቅጽ ማዕበሎች”፣የበዓሉ ግርማ “የቀይ ኮከብ ጥሪና ኦሮማይ” ዘመናቸውን በድርሰታቸው የሄሱትና ከታሪካዊ ሰነድ በማይተናነስ ሁኔታ የሥርዓቱን ገበና ያጋለጡት ደራሲዎቹ የነፃነት ዓየር እየተነፈሱ አልነበረም::
በዚህ ዘመን ብዕር የጨበጡ ደራሲያንም የሕዝባዊ አደራቸው ክብደት ግድ ሊላቸው ይገባል:: ታዳጊውና ገና በጋሜነት ደረጃ ያለው የሀገራችን የፊልም ጥበብም ተንጋዶና ተወላግዶ እንዳያድግ ብዙ ሊሠራ ይገባል:: የፊልሞቹ ይዘትና መቼትም ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ሀገሪቱን በስፋት መቃኘት ይገባዋል:: በዘርፉ የተሰማሩት የስም፣ የክብርና የዝና በረኞችም አዳዲስና ተተኪ ወጣቶች ወደ ጥበቡ እንዳይገቡ የብረት አጥር ሠርተው በመከላከል መጋፋታቸውን አቁመው ወጣቶቻችንን ሊያሳትፉ ይገባል:: አንዳንዶችም በአንድና በተመሳሳይ አልባሳትና ሜክ አፕ፣ በድምፅ ቅላፄና በእንቅስቃሴበየፊልሙ ላይ እየተሰለፉ “እኔ ብቻ ካልታየሁ” እያሉ ፊት ቀደም ሆኖ ለመታየት መሞከር እጅግም ፋይዳ አይኖረውም:: የሀገራችን የቴአትር ጥበብ “ተከድኖ ይብሰል” ብለን ብቻ የምናልፈው አይደለም::
ወደ ኋላ እያፈገፈገ የዱሮ ናፋቂ የሆነው የመድረክ ጥበብ በእጅጉ የባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ያገባኛል ባይ ተቋማትንም ጭምር ሊያሳስብ ይገባል:: ተመሳሳይ ሙያተኞች፣ አሰልቺ ጭብጥ፣ ከመድረክ የወረዱና አንድ ሰሞን ሆይ ሆይ የተባለላቸውን ዕድሜ ጠገብ የገቢ ማስገኛ ቴአትር እያቀረቡልን ሊጓዙ አይገባም:: “አንጋፋ ነን” እያሉ በዕድሜያቸው ሽበት ብቻ የሚኮሩ ቴአትር ቤቶቻችንና “ሙያውን ተክነናል” የሚሉት ቀዳሚ አንጋፎች በቅንነትና በፍቅር መድረካቸውን ለውይይትና ለክርክር ክፍት አድርገው ጥበቡን ሊታደጉ ይገባል:: ወቅቱ በሚፈቅደው ጭብጥ ላይ የተደረሱ ሥራዎችን ብንቆጥር አንድ፣ ሁለት ብለን ሦስትን አንደግምም:: ደራሲ ጠፋ? ሀገራዊና ወቅታዊ ጭብጥ መከነ? ታዳጊና ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣቶች ጠፉ? ሊመከርበት ይገባል::
እንደ ውቅያኖስ የሰፋውን፤ ነገር ግን በማንኪያ ስፍር ያህል የመጠንኩትን ርዕሰ ጉዳይ የማጠቃልለው ለውይይት ይረዳሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ሃሳቦች በመፈነጣጠቅ ነው:: የሀገራችን የእስከ ዛሬዎቹ የጥበብ ሥራዎች ከፋም ለማም የየዘመናቸውን ሥርዓቶች ገበና ሞግተው ወይንም ለዘመናቸው ገብረው እንደ ኖሩት ኖረዋል:: አሻራቸው የሚመረመረው እንዲህ በቁንጽል ቅኝት ሳይሆን ወግና ደርዝ ባለው ጥናት ነው::
ቢሆንም ግን፤ “ቡናው እስኪፈላ በአሹቁ አዝግም” እንዲሉ ዝርዝር ሥራዎች እስኪቀርቡ ድረስ ከወዲሁ “እኮ ምን ይደረግ?” ለሚለው ጥያቄ ሃሳቤን ሰንዝሬ ጉዳዬን ላጠቃልል:: ሀገራችን በለውጥና በወጀብ እየተላጋች መልህቋ እንደተበጠሰ መርከብ ከወዲያ ወዲህ እየተንገላታች እንዳለች ሀገር ራሷ በእንባ፣ ሕዝብ በስቅቅ፣ በፀሎትና በምህላ እያማጡ ነው:: በአንጻሩ ደግሞ ጥበበኞችና ጥበቡ በዝምታ አሸልበውና ደብቷቸው ሊያንጎላጅጁ ስለማይገባ ነቅተው ለሚሞግታቸው ወቅት ወለድ ሀገራዊ ጉዳዮች መልስ ሊሰጡ ይገባል:: በግትርነት፣ በክፋትና በምን ግዴ መለያ የሚታወቁት አንዳንድ የፖለቲካ “እንጀራ ፈላጊዎች” ሀገርና ሕዝብ በጤና ውሎ እንዳያድር በሰላማዊ እንቅልፉ ላይ ቅንቅን መንዛታቸውን እንዲያቆሙ እያዝናኑ ሊያቃኗቸው ይገባል::
ሸፍጠኛና መርዘኛ “ምላስ አደር” አክቲቪስቶችም በሕዝቡ መካከል የመለያየት እንክርዳድ እንዳይዘሩ አጥብቀው ሊሞግቷቸው ይገባል:: ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጫርሱ ጦስ ጠሪዎች ንፁኃን ዜጎችን የሚያፈናቅሉበትን ሴራና ከፋፋይ መርዝ አጥብቀው ሊያረክሱ ይገባል – በባለሁለቱ አፍ ስለታም የጥበብ ሥራዎቻቸው:: መሪዎቻችን ያበጁ መስሏቸው ሲስቱ፣ አወቅን ብለው ሲንሸራተቱ፣ እንበልጣለን ብለው ሲያንሱ፣አተረፍን ብለው ከስረው ሲያከስሩን “በአራት ዓይናማ” የጥበብ ምልከታቸው “ስማ ላልሰማ አሰማ!” እያሉ ጠቢባኑ በረቂቅ የጥበብ ጉልበታቸው ሊያቃኗቸው ግድ ይላል:: የፈንጣጣ በሽታ የሚታከመው በራሱ ከፈንጣጣ ተህዋሲያ በተቀመመ መድኃኒት መሆኑ ይታወቃል::
ለብዙ በሽታዎች መፈወሻነት የሚያገለግሉ መድኃኒቶችም የሚሠሩት ከዚያው ከበሽታው ከተወሰደ ናሙና መሆኑ ይታወቃል:: ጥበብም እንዲሁ ለራሷ ህመም ጓሮ በቀል መድኃኒትና የጥበብ ቤተሰቦች ስላላት “ጠቢባን ሆይ!” የታመመውን ኪነ ጥበባችንን ለማከም ተቀዳሚ ባለድርሻዎች እናንተ ናችሁና “ልብ ያለው ልብ ይበል::” “ሚዲያ አራተኛው መንግሥት” እየተባለ እንደሚንቆላጰስ ከሳምንታት በፊት በዚሁ ጋዜጣ ላይ ሃሳቤን መግለጤ ይታወሳል:: ለኪነ ጥበቡስ “የአምስተኛ መንግሥት” ሥልጣን ሰጥተነው “መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ቢወጣ” ሕጋችን “በሕግ አምላክ!” እያለ ይከሰን ይሆን? አይመስለኝም::
እንግዲያውስ “ጠቢባን ሆይ!” የታመመውን ኪነ ጥበብ በማከም ሀገራዊውን ተስፋ ከመደነቃቀፍ ታደጉት፤ እፀፆችን ለማረም በርቱ:: እናስ? እውነትን በድፍረትና በቅንነት ለመግለጽ መንጎላችሁን ቀለም ጥቀሱ:: መድረካችሁን ፈውሱ:: መሰንቋችሁን ቃኙ:: የፊልም አቡጀዲያችሁን አጽዱ:: ታሪክ ባስቀመጣችሁ የዛሬ ወንበር ላይ ታሪክ ሠርታችሁ እለፉ:: ሀገር ራሷ አፍ አውጥታ “ስሜን መልሱ ወይንም ጥበባችሁን በግብር ግለጡ” ብላ “የኢትዮጵያን ስም” ከፊት ላስቀደሙ የጥበብ ማኅበራት ጥያቄ ብታቀርብ ምን መልስ መስጠት ይቻላል? ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19/2011