ጥበብ እንደምን ሰነበተች?

እንደምን ነሽ ዛሬ… እንዴት ነበርሽ ትናንት? ማለት ሊያስፈልገን ነው። ወደፊት በመገስገስ ውስጥ አንዳንዴም መለስ ቀለስ እያሉ ወደኋላ መመልከትን የመሰለ ነገር የለም። ብዙ ያወራ ሰው ኋላ ላይ ስለምን እያወራ እንደነበር መልሶ ለራሱ ቢሰማው ትምህርትም ትውስታም ጭምር ነው።

ዓመቱን ሙሉ ሁለትና ሦስት ምዕራፎችን እያጠና የተፈተነ ተማሪ በዓመቱ መጨረሻ ለማትሪክ ሙሉ መጽሐፉን፣ ሙሉውን ደብተሩን ያገላብጣል። የማያውቀውን አውቆ፣ የሚያውቀውንም ያስታውሳል። እኛም ለፈተናው ባይሆንም ለማወቅና ለማስታወሱ እንደምን ሰነበትሽ ትናንት ማለታችን ግድ ነው።

365 ቀናትን ይዛ ስትመጣ አዲስ ዓመት፣ አውዳመት ብለን የተቀበልናት 2016 ዓ.ም፤ የያዘቻቸውን ቀናት በሙሉ አንድ በአንድ ስትጥል… ስንቀበላት ከርማ አሁን የቀራት የለም። እኛም ዝምድናዋን ጨርሰን አሮጌ ስንል ወዲያ ግድም ልናስፈነጥራት ነው። የምንወዳትም ያልወደድናትም ሳንወድ በግድ ተለያይተን ከሌላ አዲስ ዓመት ጋር እፍ ጥብስ! ልንል ነው። 2016 ዓ.ም በይ ደህና ሰንብቺ! መንገዱን ጨርቅ ያድርግልሽ! እያልን ሌላ የ2017 ዓ.ም ወርቅ ግን እንጠብቃለን።

ይሁንና ክፉም ይሁን ደግ ትዝታ መልካም ነው። ትውስታም ስንቅ ነው። የሸኘነውን ሸኝተን የመጣውን ስንቀበል፤ ነገ የሚያጓጓን ያህል ትናንትም ሊናፍቀን ይገባል። ዛሬ ያለ ትናንት፣ ነገም ያለዛሬ አይገነባምና ሁሉንም ከትናንት መጀመር መልካም ነው።

ብዙ ትናንትናዎች ግዙፍ ኪነ ጥበብ ከዚህ 2016 ዓ.ም ጉበን ላይ በነጭና በጥቁር፣ በወርቃማና በግራጫ ቀለማት የተጻፉ፣ ተጽፈው የተነበቡ ጉዳዮች እልፍ ናቸው። እልፍ እያሉ ከእልፍኙ እልፍ ቢሉ ሳሎን ጓዳ፣ ደጅና ማጀቱ ሁሉ የሚነገር የሚዘከር የጥበብ ውበት አለ። ጋራ ሸንተረሩን አቋርጠው፣ ከአውድማው በጎን፣ ከማሳው ከመሃል ሰንጥቀው ቢያልፉ ከ2016 የጥበብ መንደር ላይ ያሸተ አዝመራ፣ የጎመራ ፍሬ ነው። የጎመራን ፍሬ እላይ ሆኖ ባይበሉትም ሲያዩት ምራቅን ያስውጣል። የአዝመራ እሸትም ታይቶ አይታለፍምና ቀንጠስ! ቆንጠር! እያደረጉ ለአምሮት ታህል መብላቱ የወግ ነው።

እንግዲህ ብዙ እያሸን ብዙ ለመብላቱ ባንችልም ከ2016 ዓ.ም የኪነ ጥበብ ማሳ ላይ እልፍ እያልን የበላነውን የጥበብ አዝመራ እየቀመሰን እናስታውሰው። በዚህ 2016 ዓመት ውስጥ ምን ተሠርቶ፣ እንደምን ታለፈ?

አስቀድመን ጠቅለል ካለው እየጠቀለልን እንሂድና በ2016 ዓ.ም በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ከተከናወኑ አበይቶች መካከል አንዱ ወደ ስነ ጥበብ ቤት ያመራናል። እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ በስነ ጥበቡ ዘርፍ ከዓለም ቀደምት ብትሆንም ዘርፉ እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ሚያዚያ 7 ቀን (አፕሪል 15) የሚከበር ቢሆንም በሀገራችን ግን ይህን ዕድል ሳያገኝም ከርሟል። በዘንድሮው ዓመት የሆነው አዲስ ነገር፤ በሀገራችን የመጀመሪያው የዓለም የሥነ ጥበብ ቀን እና የኢትዮጵያ ጃዝ ሙዚቃ ቀን መከበር መጀመሩ ነው።

ሌላው በወርሃ ህዳር ለኪነ ጥበብ አዲስ የሀይል ምንጭ የሆነ ጅማሮ ነበር። አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ለረዥም ዘመናት የቆየ የጥበብ አሻራ ባለቤት ነው። ባህል ማዕከሉ በተለይ ደግሞ ቀደም ባሉት ዘመናት ስመ ጥር ገናና ነበር። ከጊዜያት በኋላ ግን ከደበዘዙና መኖር አለመኖራቸውም ከማይታወቁት እስከመሆን ደርሷል። በ2016 ግን ከጣላቸው ነገሮች አንኳር የሆነውን አንደኛውን ነገር ቀስቅሶ ዳግም አስጀምሯል። ይታወቅበት የነበረውንና በመሃል የተወውን የኪነ ጥበብ ምሽቶችን መሰናዶ ዳግም በሕዳር ወር አስጀምሯል። ቀደም ሲል ከዚህ የተገኘው ፍሬ ብዙ እንደመሆኑ አሁንም ለ2017 ዓ.ም እና ቀጥሎ ብዙ ፍሬዎች ከዚሁ ይፈሩም ይሆናል።

ከዚሁ ጥቅልል ርዕሰ ጉዳይ ሳንወጣ…የሁል ጊዜም የኪነ የኪነ ጥበብ ጎጆ ጩኸት አንደኛው በመንግሥት ዘንድ የሚሰጠው ትኩረት በቂ አይደለም የሚል ነበር። ታዲያ ጩኸቱ ተደምጦ ጥያቄው ተመልሶ ይሆን? አሁንም በሚገባና በበቂ ሁኔታ ትኩረት አግኝቷል ለማለት ባይቻልም ከሌላው ጊዜ በተለየ ግን ጥሩ ጅምሮችን የተመለከትንበት ዓመት ነበር። ስለዚህ ጉዳይ ስናነሳ በመጀመሪያ የቀስቱ ጫፍ ወደ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ይጠቁመናል። ለኪነ ጥበቡ ከተደረጉ ከመልካም ግብሮች አንደኛው የ”ክብር ለጥበብ” ሽልማት ነበር። ሽልማቱ ለሦስተኛ ጊዜ ቢሆንም ብዙ አዳዲስ ነገሮችን አካቶ የመጣው ግን በዘንድሮው ላይ ነበር። ከዚህም አንዱ ሽልማቱ ሀገር አቀፍ በማድረግ የክልል ባለተሰጥኦዎችንም ያበረታታ ነበር።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፊቱን ወደ ኪነ ጥበብና ለኪነ ጥበብ ማዞሩን ያሳየበት ሌላኛው አዲስ ጉዳይ ከሰኔ 13 እስከ ሰኔ 15 ለተከታታይ ሦስት ቀናት ያካሄደው ሀገር አቀፉ የኪነ ጥበብና ስነ ጥበብ ውድድር ነበር። ከዚህ ቀደም በነበሩ ልዩ ልዩ ውድድሮች ውስጥ ተወዳዳሪዎች ከየክልሉ በግል ፍላጎት እየመጡ ሲወዳደሩ ነበር። ይሁንና ክልሎች የባህል እሴቶቻቸውን የማሳየት ዕድል ያመቻቹ ውድድሮች ሲካሄዱ አይታይም ነበር። ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይ እያንዳንዱ የውድድር ይዘት ባህል ተኮር መሆኑና ሁሉንም አሳታፊ በማድረጉ ባህል ላበቀለው የሀገራችን ኪነ ጥበብ የከፍታ ድልድይ ነው። የዛሬ ጅምር የስኬት ፍሬው ነገ ላይ ነውና ጅምሩ አድጎና ተመንድጎ ነገ ላይ እንመለከተው ይሆናል።

2016 ዓ.ም ካሉ ኪነ ጥበብ፣ ኪነ ጥበብ ካሉም አንዱ ሙዚቃ ነው። ሙዚቃ…ሙዚቃ ምን አለ በሙዚቃ? ምን ጠፍቶ ምን የለም ይባልና…ስንት አጃኢብ! ያስባሉን ስንቱ አልበም አለ አይደል… መርጦ መስማቱን፣ ሰምቶ መሸለሙን ለናንተው ልተውና በዚህ ዓመት ከወጡ አልበሞች አንድ ወደፊት አንድ ወደኋላ እያልን አንድ ሁለት እንበል።

ለብዙ ጊዜያት በነጠላ ዜማዎቹ ልባችንን ሲደርስ የነበረው ወጣቱ ድምጻዊ መሳይ ተፈራ ካሳ “የልቤን” የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሙን እንካችሁ ያለን በወርሀ ሰኔ ላይ ነበር። እጅግ ጥንቅቅ ባለ ተወዳጅ የአልበም ሥራ እዚያ የጥር ወር ላይ ደርሶ አድምጠነዋል። እሱም የማርያም ቸርነት “የደጋ ሰው” የተሰኘው አልበም ነው። “አስቻለ” አስቻለው ፈጠን (አርዲ) ለየት ባለ የባህል አዚያዚያም ስልቱ ሙሉውን አልበም ጀምሮ ጨርሶታል። ከዚያው የጥር ወር ሳንወጣ፤ በጥር 24/ 2016 ዓ.ም “ሕይወት” የተሰኘው የዳዊት ቸርነት አልበምም አለ። ካሳሁን እሸቱ ደግሞ በጥር 17/2016 ዓ.ም “ይሁን” ያለን ሌላኛው ባለ አልበም ነው።

ከታህሳስ ግርግር ቀደም ብሎ ሕዳር ሲታጠን ፍቅር የሺዋስ “ፍቅር” ነበር፤ ቅሉ ግማሽ አልበም ቢሆንም። “ልዑል” የሕዳር 28 የራሱ የልዑል ሲሳይ አልበም ነበር። ወርሃ የካቲት ላይ ሁለት አዳዲስ አልበሞች ተደምጠዋል። ሲደመጡም የዋዛ አልነበረም። በየካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም የማስተዋል እያዩ “እንዚራ” እና በየካቲት 3 ደግሞ የሮፍናን ኑሪ “ሐራምቤና ኖር” ተከታትለው ገብተዋል።

በመጋቢት ወር ላይ በንጉሡ ፈረስ እሳት ለብሶ “እሳቱ ሰ” አልበም ከች ብሏል። የጀምበሩ ደመቀ የሆነው ይሄው አልበምም በመጋቢት 13 አድማጩን ተገናኝቷል። የአልበሙ ዥረት ማቆሚያም መቆሚያም አልነበረውም። በግንቦት 6 የእብነ ሐኪም “ብራና” እንዲሁም በግንቦት 9 ደግሞ የለምለም ኃ/ሚካኤል “ማያዬ”ን አይተናል። የእውነትም ፓፓፓ! የሚያስብል ነበር። ያለው ግን አብዱ ኪያር ነበር። ግሩም የሆነውን አልበም ሠርቶ ሐምሌ 21 ቀን “ፓፓፓ” ከሚል መጠሪያ ጋር አውጥቶታል።

አንጋፋዎቹ በ2016 ከፊትም ከኋላም፣ ከጅምር እስከ አጨራረሱ አልደከሙም። የራፕ ስልት አቀንቃኙ ልጅ ሚካኤል ዘንድሮም አለን! አለን! ብሏል። ካሳለፍናት የነሐሴ ወርም ምርጥ ምርጡን አሰምተውናል። በክረምቱ በነሐሴ ብርድና ቆፈን “አንድ ቃል” ደርሶ ሳይታደገን አይቀርም። ተወዳጁ ሚካኤል በላይነህ በነሐሴ 17 ጀባችሁ እንዳለን ነው። ሞትን ይረሳኝ! ያውም የትናንቷን እሷን እንደምን ይረሳ…”መጠሪያዬ” ነው ብላለችና ቬሮኒካ አዳነንም አንረሳም። ብዙዎች ያደነቁለትን የጉቱ አበራን ”ጋፊ ጎ”ን እንመርቅና ቀሪውን ቤቱ ይቁጠረው።

2016 ከደራሲያን ዓለምም አልቦዘነችም። አንባቢው ሲመናመን ቢሄድም ደራሲያኑ ግን በጀ! ሳይሉ ለአመልም ቢሆን ከመጻፍ አንቆጠብም ብለው በታላላቅ ሥራዎቻቸው ስነ ጽሁፉን አሙቀውታል። ከእነዚህም የመጀመሪያው ታላቁ ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ ነው። ከሀመሮቹ መንደር ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ እየከተበ ሲያስነብበን ከነበረው ጣፋጭ ጦማር ድንገት ብድግ ብሎ ሰው ሀገር እንደገባ ለብዙ ጊዜያት ጠፍቶብን ከርሞ ነበር። ታዲያ እጅ ነስቶ ሲመለስ እጅ ስሞ ስጦታ አበረከተልን። እርሱም “የሚሳም ተራራ”ን ነበር። ከተራራው ላይ ከወጣበት አስወጥቶ፣ ከወረደበት እያስወረደን ድንቁን ግለታሪክ እንድንኮመኩም አድርጎናል። ነገርን ነገር ያነሳዋልና የፍቅረማርቆስና የሀመሮቹን ጉዳይ ሳስታውስ “ዶሳይስ” ትዝ አለኝ። መጽሐፉ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ሲሆን ጸሀፊዋ ደግሞ ኩሪ አየለ ናት።

ከአንድ ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ የሚፈልቁ የባህል እሴቶችን የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ምናልባትም ትውስታው ለዚህ ይሆናል። በ2016 ዓ.ም ቆንጆ ሥራ ይዘው ብቅ ያሉ አዳዲስ ደራሲያንም ነበሩ። “አባት ዐልባ ሕልሞች” ዳጎስ ካሉ ገጾቹ ጋር ፈርጠም ብሎ የመጣ የደራሲ ማስረሻ ማሞ የበኩር መጽሐፉና ለስነ ጽሁፍ የሰጠው በኩራቱ ነበር። በወርሃ የካቲት እውነትና ትረካ፣ ትረካና ታሪክ በመጽሐፍ ተገናኝተዋል። ከዓመታት በፊት ብዙ ኢትዮጵያውያንን ያስነባው የቦይንግ አውሮፕላን መከስከስን ተክትሎ የወጣቱ አብራሪ ታምራት ሙሉ ሁኔታ ይባስ አንጀት ሲበላም ነበር። እናም እርሱን በዋና ገጸ ባህሪ ወንበር አስቀምጣ ታሪኩን ወደመጽሐፍነት የቀየረችው ደግሞ እህቱ ፋሲካ ሙሉ ነበረች። “ያልገሩትን ፈረስ” በሚል ርዕስ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተውን የልቦለድ ይዘት ያለውን መጽሐፏን በየካቲት 30 ቀን 2016ዓ.ም ለንባብ አብቅታም ነበር። “ጥላዬን ቀደምኩት” በጥላዬ ታደሰ፣ “አይሆንም ሰረዝኩት” (የግጥም መድብል) በገጣሚ አብርሃም አስቻለው እና ሌሎችም የመጽሐፍት ዓለም በረከቶች በ2016 ዓ.ም ተበርክተዋል።

ፊልምና የፊልም ጥበብ በዓመቱ ሞቅ ደመቅ ብሎ አልፏል ለማለት ይቻላል። ከዚህ ቀደም ስንክሳር የነበሩ ብዙ ጉዳዮች ለመመንገል የተደረጉ ጥረትና ጥበባዊ ተጋድሎዎች አይዘነጉም። ሰማይ በብሩህ ደመና፣ ምድር በአደይ አበባ በተንቆጠቆጡበት ወርሃ ጥቅምት ሁለት የሀገራችን ፊልሞች በአበባው እንዳሸበረቁ ወደ ባህር ማዶ ተሻግረዋል። የኢትዮጵያን ፊልሞች በአውሮፓና አሜሪካ ከተሞች ውስጥ በማሳየት የአምስት ዓመታት ያህል ልምድ ያለው ሀበሻ ቪው፤ በዘንድሮው ዓመትም ከ30 ዓመታት በፊት የተሠራውን “ጸጸት” የተሰኘውን ፊልም ጨምሮ ከቅርብ ደግሞ “ዝምታዬ”ን በማከል ቀጠሮውን በለንደን ከተማ ውስጥ አድርጎ ነበር። ፊልምና ቴክኖሎጂን ያዋደደውና የነገ ተስፋና ማሳያ የሆነው “አስተውሎት” የተሰኘውን ፊልም የተመለከትነውም በ2016 ዓ.ም ነበር። ፊልሙ ቀርቦ የነበረው በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ሲሆን ቴክኖሎጂ ሰራሽ ሮኅቦቶችን በመጠቀም የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ በማዘመኑ ትልቁን ተስፋም ተጥሎበታል።

እጅግ ተወዳጅና ዓለም አቀፍ እይታን ያገኙ ፊልሞችን ከመመልከት አንጻር እንደ “ዶቃ” ያሉ ድንቅ ፊልሞችን የተመለከትንበት ዓመትም ጭምር ነው። እንዲያው ካለማውራት ማውራት ይሻላል በማለት እንዲሁ ለጨረፍታ እንጂ በፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ የተከናወነው እንኳን ብዙ ነበር።

ብዙ መልካም ነገሮች ሆኗዋል። እኛም ሰምተናል። ተመልክተናል። ግን ደግሞ ጥሩ ነገሮች ባሉበት መጥፎ ክስተቶችና አጋጣሚዎች እንዳፈጠጡ ነው። በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ደስታ ሁሌም ጣፋጭ ነገር ቢሆንም መርጦ መኖር ግን አይቻልም። በምንፈልገውና በምንመርጠው ልክ የማንመርጣቸውና የማንፈልጋቸው ነገሮች ይመጣሉ። ከእነዚህ አንዱ ሞት ነው። ሞትም ሆነ መወለድ ከሰው ልጆች ፍላጎትና ምርጫ ውጭ የሆኑ ነገሮች ናቸው። በዘንድሮው ዓመት ብዙ መልካም የኪነ ጥበብ ጣፋጮችን እንደበላን ሁሉ ድንገት መራራ የሆኑ ዜናዎች ከጆሯችን እየገቡም እንዲሁ አዝነን ልባችን ተሰብሯል።

ጥበብን ለኛ የሰጡ እነርሱ ግን ለሞት ተሰጥተዋል። ከእነዚህም መካከል አንጋፋውን ድምጻዊ ሙሉቀን መለሰን አንደኛው ነው። ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ ደግሞ ሌላኛው ነው። በ70 እና በ80 የዕድሜ እርከን ወደ ሞት ተጉዘዋል። ክረምት መጣሁ መጣሁ እያለ ሰማይ የጉም ጭጋግ ለብሶ ሲያስገመግም ከወረዱ መብረቆች አንዱ የጥበብን ቤት ያደባየ ይመስላል። በተለይ ከሦስት ወራት ወዲህ የሞት ክንድ አለት የሚሰብር መዶሻ ያህል ጠንከር ብሎ ነበር። በዚሁ ሰለባ ከሆኑትም ሰዓሊና ገጣሚ ነብይ መኮንን ይገኝበታል። በሰኔ ዶፍ አውሎንፋስ ቀላቅሎ በሞት ወሰደው። ደግሞ እንደገና ሁለት አንድ ዓይነት ድንገቴዎች ተከታትለው መጡ። ነሐሴ 18 እና ነሐሴ 19 እጅግ አስፈሪ ነበሩ። በቀን 18 ወጣቱ የ60 ፊልሞች ባለጸጋ ጌታቸው እጅጉ (ባቡጂ) አረፈ። ቀጥሎ ደግሞ በቀን 19 የቲያትር ፈርጥ የነበረው ከያኒ ኩራባቸው ደነቀ ላይመለስ ተከትሎ ሄደ።

እንግዲህ ያለፈው እንዲህ ባለመልኩ አልፎ ከ2016 ጋር ለመተላለፍ የቀረን የለም። ታዲያ እሱም ገጭቶን፣ እኛም ተሳድበን እንዳንተላለፍ ያሳለፍነው ጥሩም ቢሆን መጥፎ ኋላን በፍቅር ተምሮ ማለፍ ታላቅነት ነው። ለነገ ነገ ብቻውን በቂ አይደለምና ከዛሬ ቆርሰው የያዙት ስንቅ ለራስ ነው። እንደምን ሰነበተች እያልን ጥበብን በ2016 ዓ.ም ስንቃኛት ከባህር ላይ የጭልፋ ታህል ብትሆንም ለቀጣዩ ጥቂት ማሰላሰያ ትሆናለች። የዛሬው ዳሰሳ ለነገው አዲስ አሰሳ መንገድ ነውና መንገዱን አንሳት።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You