ፈጣን ህክምና አደጋን ለመከላከል

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አደጋዎች ምክንያት በየዓመቱ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚሞቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ አሃዝ ወባ፣ ሳምባና ኤች አይ ቪ ኤድስ ተዳምረው በየዓመቱ ከሚያስከትሉት ሞት የበለጠ ነው፡፡ ይህም አደጋዎች ከሌሎች በሽታዎች የበለጠ የሰው ልጆችን ሕይወት በመቅጠፍ ረገድ ወደር እንዳልተገኘላቸው ያመላክታል፡፡

በኢትዮጵያም አደጋ የሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍና ከፍተኛ የአካል ጉዳት በማድረስ የመሪነቱን ቦታ ይወስዳል፡፡ እያደረሰ ያለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ተላላፊና ተላላፊ ካልሆኑ በሸታዎች ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጫና እያስከተለ የሚገኝም ነው፡፡

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ከሆነ አደጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ 10 ከመቶ የሚሆነውን ሞት ያስከትላል፡፡ ቲቢ፣ ወባና ኤች አይ ቪ ኤድስ በጋራ ሆነው ከሚያስከትሉት 32 ከመቶ ሞት በላይ በአደጋ ምክንያት ይከሰታል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ65 እስከ 85 በመቶ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች በሪፈራል ሥርዓት መዘግየት፣ በትራንስፖርት እጦት፣ በፋይናንስ እጥረትና በመሳሰሉት ችግሮች ምክንያት ዘግይተው ሆስፒታል እንደሚደርሱ ይነገራል፡፡

ከዚህ አንፃር አደጋ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያየ መልኩ ከፍተኛ ጫና እያደረሰ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን በመሰሉና ደህንነትና ጥንቃቄ ትኩረት በማይሰጥባቸው ብሎም አደጋ ከተከሰተም በኋላ ለተጎጂዎች በቂ ምላሽ የሚሰጥ የድንገተኛ አደጋ ህክምና ማዕከል እንደልብ በሌለባቸው ሀገራት እያደረሰ ያለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና እክል ጫና ከፍተኛ ነው፡፡

አደጋ አምራቹንና ወጣቱን የህብረተሰብ ቁጥር በመቀነስ፣ ብዙዎችን ለሞት በመዳረግ፣ ለአካል ጉዳት በማጋለጥ፣ በህመምተኞች፣ በቤተሰቦቻቸውና በማህበረሰቡ ላይ ከባድ ተፅእኖ በማሳደር፣ ለከፍተኛ የህክምና ወጪና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመዳረግ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡

ዶክተር ስንታየሁ ቡሳ በሞያቸው የአጥንት ቀዶ ሐኪምና የአጥንትና መገጣጠሚያዎች ንዑስ ስፔሽያሊስት ናቸው፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የአጥንት ህክምና ትምህርት ክፍል ዲን ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ አሁን ደግሞ ቦሳድ /Bone Setting Associated Disabil­ity/ በተሰኘው ሀገር አቀፍ የጥናትና የምርምር ቡድን አማካኝነት በኢትዮጵያ በአጥንትና መገጣጣጠሚያ ጉዳቶች ዙሪያ በተሰራው የሦስት ዓመት ጥናት ውስጥ አባልና መስራች ናቸው፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፣ አደጋ በኢትዮጵያ የሞትና የአካል ጉዳት በማድረስ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በማድረስ ረገድም ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑና በሽታዎች ተወጥራ ትገኛለች፡፡ ከነዚህ በሽታዎች ቀጥሎ ደግሞ ሀገሪቱ በከፍተኛ አደጋ ጫና ውስጥ ነው ያላቸው፡፡ በየእለቱ አደጋዎችን መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ 10 ከመቶ ያህሉ ሞት የሚከሰተው በአደጋ ምክንያት ነው፡፡ ይህም ቲቢ፣ ወባና ኤች አይ ቪ ኤድስ ተደምረው ከሚያደርሱት ሞት በ32 ከመቶ ከፍ ይላል፡፡ በኢትዮጵያ አስፈላጊውን ህክምና በማድረግ አብዛኛዎቹ ጉዳቶችን መከላከል ይቻላል፡፡ ይሁንና እስከ 85 ከመቶ ያህል የሚሆኑ አደጋ የደረሰባቸው ታማሚዎች ሆስፒታል ዘግይተው በመድረሳቸውና አፋጣኝ ህክምና ባለማግኘታቸው ለከፋ አካል ጉዳትና ለሞት ይዳረጋሉ፡፡

አብዛኛዎቹ ሪፈር ተፅፎላቸው ወደ ሆስፒታል የሚላኩት ዘግይተው ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ትራንስፖርት በማጣት፣ በገንዘብ እጥረትና ባሕላዊ ህክምናን እንደ መጀመሪያ አማራጭ በመውሰድ ዘግይተው ወደ ሆስፒታል ይመጣሉ፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ለከፋ አካል ጉዳትና ለሞት ይዳረጋሉ፡፡

ዶክተር ስንታየሁ እንደሚያብራሩት፣ በአሁኑ ጊዜ አደጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ለአደጋ የሚያጋልጡ ተገቢ ላልሆኑ ባህሪያትም አሉ፡፡ አብዛኛው ሞተር ብስክሌት አሽከርካሪ የጭንቅላት መከላከያ ቆብ አያደርግም፡፡ መኪና አሽከርካሪዎችም ከትራፊክ ለመሸሽ እንጂ ራሳቸውን ለመጠበቅ አይደለም ቀበቶ የሚያደርጉት። በአንድ የትራንስፖርት መጓጓዣ ላይ ለምሳሌ ሞተር ሳይክል የሚጠቀሙ የሰው ቁጥርም ከመጠን በላይ ነው፡፡

በፍጥነት ማሽከርከር፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ጫት ቅሞ ማሽከርከር፣ በግንባታ ቦታዎች ላይ በቂ የደህንነት መሳሪያዎችና መመሪያዎች አለመኖርና ቢኖሩም ተግባራዊ አለመሆን ፣ የመንገድ ላይ ደህንነት በሚፈለገው ልክ አለመኖር፣ ጦርነትና ግጭቶችም ለአደጋዎች መከሰት ቁልፍ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ አደጋዎች የሚከሰቱት በሁለት ዓይነት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው ሳይታሰብ ሁለተኛው ደግሞ ታስቦበት ነው፡፡ ሳይታሰቡ የሚያጋጥሙ ጉዳቶች ሰዎች በሥራ ላይ እያሉ የሚገጥማቸው፣ የትራፊክና መሰል አደጋዎች ናቸው፡፡ ታስበው የሚጋጥሙ አደጋዎች ደግሞ ሰዎች ራሳቸውን ለመጉዳትና ለማጥፋት የሚያደርጓቸው ሙከራዎች፣ በግለሰቦች መካከል ያለ ፀብና ሌሎችም ናቸው፡፡

በአደጋ ምክንያት አብዛኛው ሞት የሚከሰተው ሰዎች በጭንቅላታቸው ላይ ጉዳት ሲደርስባቸው ነው፡፡ ለዛም ነው ሰዎች በግንባታ ቦታዎች ላይና ሞተር ብስክሌት ሲያሽከረክሩ የጭንቅላት ቆብ ማድረግ አለባቸው የሚባለው፡፡ በተመሳሳይ ወድቀው አደጋ የሚደርስባቸው ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሰው አደጋ ከደረሰበት በኋላ መቼና የት ነው የሚሞተው የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

አደጋ ከሚደርስባቸው ውስጥ 50 ከመቶዎቹ የሚሞቱት እዛው አደጋው የደረሰባቸው ቦታ ላይ ነው። 30 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ አደጋ ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ከመጡ በኋላ በሰዓታት ውስጥ የሚሞቱ ናቸው፡፡ 20 ከመቶዎቹ ሆስፒታል ከመጡ በኋላ ከሶስትና አራት ሳምንት ቆይታ በኋላ የሚሞቱ ናቸው፡፡ 50 ከመቶ ያህሉን የአደጋ ሞት ማንኛውም ሐኪም ሊከላከለው አይችልም፡፡ ይህን ሞት መከላከል የሚቻለው አደጋው እንዳይደርስ የመከላከል ሥራ አስቀድሞ ከተሰራ ብቻ ነው፡፡

30 ከመቶ በአደጋ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ሞት በህክምና መከላከል ይቻላል፡፡ እነዚህ 30 ከመቶ የሚሆኑ ሞቶች ሊከሰቱ የሚችሉት በቂ የአምቡላንስ አገልግሎት አለመኖር፣ አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ የሚሰጠው ህክምና በቂ አለመሆን፣ ወደ ህክምና ቦታ ከመጡ በኋላ በቂ ህክምና ባለማግኘት ነው፡፡

ስለዚህ አደጋው በደረሰበት ሊሰጥ የሚችለውን ህክምና በደንብ በማስተካከል፣ አምቡላንሶችን በመመደብ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ሆስፒታል የሚመጡበትን ሁኔታ በመፍጠርና በሆስፒታል የሚሰጠውን ህክምና በማስተካከል ሊከሰት የሚችለውን ሞት መቀነስ ይቻላል። ከዚህ ባለፈ አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች በሆስፒታሎች ተገቢ ህክምናዎች በማድረግ 20 ከመቶ በአደጋ ሊከሰት የሚችለውን ሞት መቀነስ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በነዚህ መንገዶች 50 ከመቶ ያህሉን በአደጋ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት መከላከል ይቻላል፡፡

ለምሳሌ በሀዋሳ ከተማ በተጠና ጥናት ወደ 1 ሺ 920 የሚሆኑ አደጋዎች ደርሰዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 80 ከመቶ የሚሆኑት ወንዶች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ደግሞ በአማካይ በ28 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ይህም በአደጋ ምክንያት እየተጠቃ ያለው አምራቹና ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ያሳያል፡፡ አደጋ በወጣቱ ላይ የአካል ጉዳት ሲያስከትል በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም ተዘዋዋሪ ተፅእኖ የሚያሳድር ነው፡፡

እንደ ዶክተር ስንታየሁ ገለፃ በኢትዮጵያ በአብዛኛው ለአደጋ ዋነኛ መንስኤ የሚሆነውና 53 ከመቶ ድርሻ የሚወስደው የትራፊክ አደጋ ነው፡፡ 18 ከመቶ ያህሉ ደግሞ በሥራ ላይ በአብዛኛው በመውደቅ መንስኤ የሚከሰት ነው፡፡ ከመጡት አደጋዎች 86 ከመቶ ያህሉ የጭንቅላት፣ የእጅና የእግር አደጋ ያጋጠማቸው ናቸው፡፡ በሆስፒታል ውስጥም እስከ 78 ቀን ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ በሆስፒታል ቆይታቸው የምግብ፣ ህክምና፣ የአልጋ ወጪዎች አሉባቸው፡፡ ከቤተሰብ ተነጥለው መምጣታቸውና ከሥራ መስተጓጎላቸውም ትልቅ የኢኮኖሚ ጫና አለው፡፡

በአንድ ዓመት ውስጥ ከአደጋ ጋር በተያያዘ 26 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ቁጥሩ ትንሽ ቢመስልም ሁልጊዜም ቢሆን ሰነድ ያለው በሆስፒታሎች ብቻ ከመሆኑ አኳያ አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ የሚሞተው ሰው ቁጥር ሲጨመር ከዚህ በላይ ይሆናል፡፡ ይህ አሃዝ ወደ ሀገር አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ሲቀየር አደጋ በብዛት የሚያጠቃው ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ይህም ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብና ለሀገር ከፍተኛ ተፅእኖ አለው፡፡

አንድ ሰው አደጋ የሚደርስበት አስቦ አይደለምና ድንገት አደጋ ሲደርስበት ለህክምና ከሚያወጣው ወጪ ጀምሮ በሕይወት እስከሚለይበት ድረስ የሚያመጣው ትልቅ የኢኮኖሚ ቀውስ አለ፡፡ ስለዚህ አደጋ ይህን ያህል ተፅእኖ የሚያስከትል ከሆነ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰተም በኋላ በአፋጣኝ አክሞ ለማዳን ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ አደጋ ከተከሰተ በኋላ አደጋውን ለማከም የሚያስችል የተሟላ አቅም የላትም፡፡ በተለይ ከፍተኛ የጭንቅላት አደጋ ሲያጋጥም ህክምና የሚደረገው ከውጪ ተገዝተው በሚገቡ እቃዎች ነው፡፡ እቃዎቹም በአብዛኛው ውድ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከሁሉ በፊት መሰራት ያለበት ሥራ አደጋን አስቀድሞ መከላከል ነው፡፡ ሰዎች ከተጎዱ በኋላ በተጎዱበት ቦታ ላይ ከሚሰጠው ህክምና ባሻገር ዋናው ህክምና የሚሰጥበት ቦታ ላይ የሚደረጉትን ህክምናዎች ማጣመር ያስፈልጋል፡፡ የሪሃብሊቴሽን ህክምናም እንደዚሁ ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ረገድ የሚዲያ ተቋማትም የራሳቸው ሚና ይኖራቸዋል፡፡ በተለይ በሥራ ቦታ ላይ የሥራ ላይ ደህንነት እንዲኖርና በዚህ ላይ የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። አንድ ሰው አደጋ ሲደርስበት ሆስፒታል ከመድረሱ በፊት ሊሰጠው በሚችለው ህክምና ዙሪያ የሚሰጡ ስልጠናዎችን ማስተዋወቅ ከተቻለም ግንዛቤ መፍጠር ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻል ከሆነ በአደጋ ምክንያት የሚከሰቱ አብዛኛዎቹን ሞቶች መቀነስ ይቻላል፡፡

ከዚህ ባሻገር በጤና ተቋም ውስጥ በአብዛኛው የሚታየው ችግር ተጎጂዎች ዘግይተው ወደ ህክምና ተቋም መምጣት ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጣቢያዎች ላይ የሚሰጠው ህክምና በቂ አለመሆንም ተጨማሪ ችግር ነው፡፡ ይህንን ክፍተት በማየትም ነው አብዛኛዎቹ ታካሚዎች የባሕላዊ ህክምናን መርጠው ወደ ወጌሻ የሚሄዱት፡፡

ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጣቢያዎች ላይ የሚሰጠውን ህክምና ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ታማሚዎች ለህክምና የሚሆናቸው በቂ ገንዘብ አለመኖርም በአደጋ ምክንያት የሚከሰት ሞትን ከሚጨምሩ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ ስለዚህ አደጋ የማህበረሰብ ትልቅ የጤና ችግር መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በተለይ አስቀድሞ መከላከል ላይ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You