የ90ዎቹ የጥበብ እልፍኝ

ጊዜው ይነጉዳል፤ ልጓም አልባ ፈረስ ሆኗል። በሚሊኒየሙ ዋዜማ እንደዋዛ ትተን ያለፍናቸው 1990ዎች አሁን ላይ እንደቀልድ ልዩነታችንን በሁለት ክፍለ ዘመናት መካከል አድርገውታል። በዚያ 90ዎቹ በምንለው የዘመን እርስት ላይ የተሠራችው ውብ የሆነችው እልፍኝ አንዳችም ሳትዘምና ሳታረጅ እንዳማረባት ቆማ ዛሬም ድረስ ከነግርማ ሞገሷ አለች።

ከሰው ሰው ከወዳጅም ወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለካስ ከዘመንም መርጠው የሚያስታውሱት ዘመን አለ…? ትልቁ ነገር ግን እንድናስታውሰው የሚያስገድደን ምን የተለየ ነገር ቢኖር ነው? የሚለው ነው። ታሪክና ሰው፤ ሰውና ጥበብ፤ ጥበብና የጥበብ እልፍኝ የተዋቀሩበት ያ ዘመን ትውስታና ትዝታ አለበት። 90ዎቹ ሲባል ልባችን ትርክክ የሚልብን ብዙዎች ነን። ምክንያቱም እዚያ እልፍኝ ውስጥ ልዩ ትዝታና ትውስታ አለን። 90ዎቹ ለኢትዮጵያ ልጆች የዘመን ቁጥር ብቻ አይደለም። የእልፍኟ ምሰሶ የቆመው በያኔዎቹና በአሁኖቹ የጥበብ አፍቃሪያን ልብ ውስጥ ነውና በምንም ዓይነት ነቅሎ ለመጣል የሚሆን አይደለም። እዚያ እልፍኝ ውስጥ ያሉት ነገሮች ከዓመት ዓመት፤ ከወር ወር፤ ከዕለት ዕለት ሁሌም አዲስና እየቆዩ እንደ ወይን የሚጣፍጡ ናቸውና አንዴ የቀመሱትን ሳይናፍቁ ውሎ ማደር የለም።

ትውልዱ ብቻ ሳይሆን ጥበብም ብትሆን የዚህ እልፍኝ ነገር አይሆንላትም። ኪነ ጥበብ በየትኛውም ዘመን የነበረና የሚኖር ቢሆንም ከዘመን ጥበብ ሁሉ ለ90ዎቹ የተለየ ቦታና ናፍቆት አላት። እሷም ሆነች እኛ ይህን ያህል በፍቅር የወደቅንለት ሚስጥሩ ምን ይሆን? የኪነ ጥበቡ ድጓዎቻቸውን አልፎ ሰዎቹም ጭምር እጅግ ይወደዱና ይናፈቃሉ። ርግጥ ነው፤ ሚሊኒየሙን ስንቀበል ከዘመኑ ጋር እዚህ ማዶና እዚያ ማዶ ሆነናል።

በደቂቃና ሴኮንዶች ልዩነት ሁለት ክፍለ ዘመናትን አስተናግደናል። አንዱን ተቀብለን ሌላውንም ሸኝተናል። ታዲያ እንደ ዘመናቱ ሁሉ እዚያው በዚያው የተራራቅንባቸው ኪነ ጥበባዊ ድንበሮችም ብዙ ናቸው። መልካቸውን የቀየሩና እኚህ ዓይነቶቹ ኮተትና ጓዞች አያስፈልጉንም በማለት፤ ከመጨረሻዎቹ 90ዎች እና ከመጀመሪያዎቹ 2ሺዎች ባህር ውስጥ የጣልናቸው የጥበብ ስንቆቻችን ጥቂት አይደሉም። 90ዎቹ የቅርባችን ቢሆንም እንደ ኪነ ጥበብ ታሪክ ግን ከዓይን እንደተሰወረ ተራራ ያህል ርቀን የሄድን ያህል ይሰማናል።

እውነት ነው፤ የዛሬው አብዛኛው ትውልድ በዚያን ጊዜ የልጅነት ትዝታዎች አሉት። ታዲያ ዛሬ ላይ ሆኖ ለሚያስታውሰው ሁሉ ልዩ የሆነች የ90ዎቹ የኪነ ጥበብ ጨረቃ ከምናቡ ላይ ብልጭ የምትለው፤ ምናልባትም በልጅነቱ ምክንያት ይሆን? ወይንስ የእውነታም፤ ዛሬም ድረስ ያልወጣች የጥበብ ጨረቃ በዚያን ጊዜ ነበረች? ምናልባትም ከሁለቱም ጥያቄዎች አንጻር ልክ ለመሆን ይቻላል። ልጅነትም ሆነ ወጣትነት በ90ዎቹ ውስጥ የተለየ ቦታ ነበረው። የኪነ ጥበብ ምንጭ ፈልቆም፤ ሐይቅ የሠራበት ጊዜ ነበር። ከሁለቱም አንጻር፤ ብዙ ነገሮች ለአንዴና ለመጨረሻ የታዩበትም ጭምር ነው።

የ90ዎቹ ልጅና ሕፃናት፤ የአሁኖቹ ወጣትና ጎልማሳ ወደሆኑት የጥበብ ሰዎች ዘንድ ጠጋ ብላችሁ፤ እንዴትስ ወደ ኪነ ጥበቡ ዓለም ገባህ?፤ ገባሽ? ብትሏቸው…“በልጅነት ዓለም ውስጥ፤ ከትምህርትና ከሠፈር…” በማለት፤ የልጅነት ትዝታና ትውስታ የተሞላበትን ዓይነት ምላሽ ከብዙዎቹ ታገኛላችሁ። ልብ ያላልን ይሆናል እንጂ፤ የያኔዎቹ የልጅነት ጨዋታና ቡረቃዎች ሁሉ፤ በደንብ ያልተገነዘቡት ኪነ ጥበባዊ መዓዛ ያላቸው ናቸው። ለአብነታዊ ትውስታ እንዲሆኑን ጥቂቱን እናንሳቸው። የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ላይ፤ ባልና ሚስት ሆነን ብቻም ሳይሆን ሌላ ገጸ ባህሪያትንም ተላብሰን ተጫውተን ይሆናል። እዚህ ጨዋታ ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ፤ ልዩ ልዩ ፈጠራዎች የሚታከልባቸውና ትውፊታዊ የልጅነት ትወና ናቸው።

ቀላልና ተጫውተን ብቻ ያለፍነው ቢመስለንም፤ ልጅነታችን ግን ነጭ ወረቀት ነውና ሳናስተውልም ለእድሜ ዘመናችን ሁሉ እንዲሆን አድርጎ፤ ልብና አዕምሯችን ላይ ማስፈሩ አይቀርም። “አሌ ቡሌ….” “መሀረቤን ያያችሁ…” “ጨረቃ ድንቡል ቦቃ…” እና መሰል ሙዚቃዊ ጨዋታዎች፤ ከትምህርት ቤቱ የሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ጋር አብረው፤ የሙዚቀኝነትን የጥበብ ዓይን የሚያበሩ ናቸው። ያቺ ጎጆና ቆርቆሮ ቤት፤ የብዙ ሰዓሊያን የመጀመሪያዋ የስዕል ጠብታ ናት። ጦሯንም ቢሆን፤ በቀለማት አሳምሮ፤ ልቡ ላይ ያልሰካት የ90ዎቹ ቱርፋት የሆነ ሰዓሊ አለ ለማለት ያዳግታል።

ፍቅርም እንደዛሬው፤ በፌስቡክና ቴሌግራም አልነበረምና ከልቦለድ ያልተናነሱ ደብዳቤዎች ይጻፋሉ። እኚህ ደብዳቤዎችም፤ የጥበብን ጓዳ የሚሞሉ ብዙ ደራሲያንን ያበረከቱልን ባለውለታዎች ናቸው። “እንኪያ ሰላምታ!” “በምን ልምታ?” እየተባለ፤ ከወዲያና ወዲህ የሚጠቀጠቁት ነገሮች እንኳን የጥበብ ማጣፈጫ ጨው የሚነሰነስባቸው ነበሩ። ሁለቱም አንድ ለአንድ፤ አሊያም ደግሞ በቡድን በቡድን ሆነው፤ ተራ በተራ በሚያደርጉት የእንኪያ ሰላምታ ጨዋታ ውስጥ፤ ድንገተኛ የሆኑ የግጥም ፈጠራዎች ያሉበት ነው። አስቀድሞ ከጠራት አንዲት ቃል ጋር፤ በግጥም ቤት መምታትና አለፍ ሲልም ቅኔያዊ ማድረጉ፤ ጨዋታውን በስኬትና በድል አጠናቆ አንጀቱን ለማራስ ያስችለዋል።

የ90ዎቹ የጥበብ እንፋሎት ዛሬ ላይ፤ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በሙዚቃው ውስጥ እንደ እጣን ጭስ ወደላይ ሲግተለተል ይታያል። ዛሬን፤ ያለዚያን ጊዜ ሙዚቃ ማሰብ በራሱ የማይታሰብ ነው። ለአብዛኛዎቹ የሙዚቃ አፍቃሪያን፤ እንዲህ ማሰብ፤ ጎረምሳውን በሙታንታ መለመሉን አደባባይ ይዞ እንደመውጣት ነው። በከተማ በገጠሩ፤ በታክሲ በሆቴል፤ በመዝናኛና ሙዚቃ ቤቱ ውስጥ ሁሉ፤ ማጫወቻ ቴፑ ያለ እነርሱ አልሰራም ያለ ይመስል፤ እኚያን ሙዚቃዎች ሳያደምጡ ማለፍ አይታሰብም። ዛሬ ላይ ሆነን 90ዎቹን እየኖርን የሚመስልም ነገር አለው። ደግሞ የሙዚቃዎቹ የስሜት ቋጠሮስ ቢሆን፤ በየመንገዱ ሁሉ ጠልፎ የሚጥል ነው። “ፍቅር ፍቅር ሲያሰኘኝ፤ ትዝ ሲለኝ ስሜቱ…” እያለ፤ ባደመጡት ቁጥር የፍቅርን ውቃቢ እየቀሰቀሰ፤ ልብንም ጭምር መንገደኛ ያደርጋል። ከዚያማ “መንገደኛው ልቤ…” እያሉ መሄድ ብቻ ነው። ማዜም ብቻ ነው።

በጓደኛ፤ በፍቅር ወዳጅ፤ በእናትና በሀገር ልባችን ሲዋልል፤ ወደ እነርሱ መኮብለልን እንመርጣለን። የውስጣችን ስሜት በትክክልም የሚጋመድባቸውና፤ እኛ እንደምናደምጣቸው ሁሉ፤ እነርሱም ውስጠታችንን የሚያደምጡ ስለመሆናቸው አንጠራጠርም። ለመዝናናቱም ሆነ ለመተከዙ፤ ያለ እነዚያ ሙዚቃዎች አይሆንልንም። “ማርም ሲበዛ ይመራል” ቢሆንም ተረቱ፤ በ90ዎቹ ሙዚቃ ግን ይህ የሚሠራ አልሆነም። ይህን ሁሉ ዓመት ሲሰሙት፤ ሲያደምጡትና አብረው ውለው አብረው ሲያድሩ፤ ለአንዴም ቢሆን ስልችት አለማለቱ የሚገርም ነው። እለት እለት፤ መሽቶ ሲነጋ ለጆሮ አዲስ እየሆኑ፤ እንደ አዲስ ይደመጣሉ።

90ዎቹ በጥበብ አፍቃሪው ዘንድ ሁሉ ለምን ጣፋጭና ተወዳጅ ሆኑ? ይህን መጠየቅም ሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። ለዚህ የመጀመሪያው ምላሽ ሊሆን የሚችለው፤ በትውልድ ቅብብሎሽ መቆም በመቻላቸው ነው። እንደሚታወቀው ከእነርሱ ቀደም ያሉት የስድሳና 70ዎቹ አንጋፋዎች፤ ለኪነ ጥበቡ አዳዲስ በረከቶችን ይዘው ብቅ ያሉ የዘመን ትውስታዎች ናቸው። የ90ዎቹ እርሾም ከእነዚሁ የመጣ ነው። የቀደሙት በፀሐፊነታቸው የተዋጣላቸው ብዕረኛም ጭምር የነበሩ ሲሆን፤ የኋላኛዎቹ ደግሞ በማንበብና አዳዲስ ነገሮችን ፍለጋ በማሰሱ ምንም የሚወጣላቸው አልነበሩም። 90ዎቹ በ70ዎቹ ሥራዎች ምርኮኛና አድናቂም ጭምር ነበሩ። ቢሆንም ግን፤ የተቀበሉትን ብቻ ይዘው ለመቀጠልም ሆነ ባዕዱን ከሌላ ለመቀላቀል አልፈለጉም። ሀገራዊ የሆነውን ቱባ ማንነት በመያዝ፤ የራሳቸው የሆነውን አዲስ መንገድ ከፈቱ። በዚያኛውና በዚህኛው ትውልድ መሀከል አድረገው የሠሩት ድልድይ፤ ዛሬም ለኛም ጭምር ተርፏል።

ቀጥሎ በመጣውና ባለንበት ዝብርቅርቅ ውስጥ፤ የዘነጋነው ነገር ምናልባትም ይህን መሻገሪያ ድልድይ በሁለት ጫፍ መሥራቱን ይሆናል። እነርሱ፤ የብቻቸው የሆነና የማይፋቅ መገለጫ ባለቤት ናቸው። ከዚህ በፊት ሰምተንም አይተንም የማናውቃቸው ቢሆኑ እንኳን የ90ዎቹን ሥራዎች እንዲሆኑ በቃናቸው እንለያቸዋለን። አዲስና የማይጠገብ መዓዛ አላቸው። ሌላኛውና ሁለተኛው ምክንያት፤ በ90ዎቹ ቤት የብቻና ለብቻ ብሎ ነገር አይታወቅም ነበር። በአንዱ ተውኔት፤ በአንዱ ፊልምና አልበም ውስጥ ሥራ ብቻ የማያገናኛቸው ምርጥ ስብስቦች አሉበት።

እንደ ሙዚቃው፤ ኮሌክሽን የሚባለው ጥምረት ያከተመለት ምናልባትም ከእነርሱ በኋላ ነው። በዚያን ጊዜ ሙዚቀኛው ብቻም ሳይሆን፤ ኮሜዲያኑም በጋራ ጥምረት የሚያወጧቸው ሲዲዎች በርካታ ነበሩ። ከ90ዎቹ ፈርጦች፤ የአንደኛውን ስም ስናነሳ፤ ከእያንዳንዱ በስተጀርባ አብረን የምናወሳው ቢያንስ፤ ሌላ አንድ ሰው አይጠፋም። ይህ የሆነው፤ ብዙ ሆነው እንደ አንድ ከመሥራታቸውም፤ ጥምረቱ የእውነትና ከልብ የመነጨ በመሆኑ አንዱን ከሌላው ለመነጠል ያስቸግረናል፤ ልክ ደረጀና ሀብቴ እንደምንለው ዓይነት ነው። በ90ዎቹ መንደር ውስጥ ከነበረው እንዲህ ዓይነቱ ባህል የተነሳ፤ አንድ ዘመን የማይረሳውን ምርጥ ስብስብ ለመሥራት ችለዋል።

90ዎቹ ሲባል፤ ዘመንን ብቻ የሚገልጽ አይደለም፤ የ90ዎቹ ማለትም የተለየ ክብርና መወደድ ያለው ነው። የሕዝቡና የጥበብ አፍቃሪውን የልብ ትርታ የሚያደምጡና የሚረዱም ስለነበሩ፤ የስሜት ቋጠሮው ላይ ለመድረስ የሚቸገሩ አልነበሩም። የጥበበኛው ኮከብ፤ ከሰውና ዘመኑ ጋር ሲገጥም፤ እንዲህ የዘመኑ መታወሻ ለመሆን ይበቃል።

“…ጭራሽ በሀገሩ፤ …እነማን ነበሩ፤” የሚለውን ዜማ ማዜም አሁን ነው። በዚያ የ90ዎቹ ግዙፍ እልፍኝ ውስጥ እነማንስ ነበሩ? ማለት ያስፈልጋልና። እያንዳንዱን ለማንሳት ባይቻልም፤ በዚያ የነበሩት አብዛኛዎቹ፤ የዘመንን ድልድይ ለማለፍ ተስኗቸው ይሁን እረስተናቸው፤ ከምንወደው ሥራዎቻቸው እኩል ዛሬ ላይ ልንመለከታቸው አልቻልንም። የነበረው ጥምረትና ምርጥ ስብስብ፤ ከዚያው የ90ዎቹ የመጨረሻ የምሽት እራት ለማለፍ አልቻለም። ሰኔና ሰኞ ተገጣጥሞ፤ በአሳዛኝ የሕይወት ሸለቆ ውስጥ ገብተው የተረሱ ጥቂት አይደሉም። ገሚሱ ከሀገር ውጭ፤ ገሚሱም ከዓለም ውጭ ወደ ሞት ነጉደዋል። ዛሬም ድረስ ዘልቀው፤ ሥራዎቻቸውን እያበረከቱልን ያሉም አሉ። ለዛሬና ለነገ የሚሆነንን የጥበብ ንዋይ የሰጡን አብዛኛዎቹ ግን፤ ከሕይወት በረሃ፤ ከኑሮ ገዳም ውስጥ ገብተዋል። ከዘመናቸው በላይ ደምቀው፤ እንደ አብረቅራቂ ክዋክብት የታዩት ከትላንቱ ዛሬ ቢሆንም፤ ዛሬ ላይ ግን ከሕይወት መሰላል ላይ ተገፍትረው ወድቀዋል። በዚያው ለዘለዓለሙ ያሸለቡና የት እንደገቡ የማይታወቁ ቢኖሩም፤ አንዳንዶቹ ግን ያየ ያዘነ ደርሶ፤ መልካም የሕይወት ምዕራፍን ዳግም እንዲገልጡ አድርጓቸዋል። በማይነጋ ሌሊት ውስጥ ተመልካች አጥተው ለብቻ የሚሰቃዩ፤ አሁንም አሉ።

ከ90ዎቹ ቅመሞችና ከምርጡ የሙዚቃ ስብስብ ውስጥ ጠቀስ ለማድረግ ያህል… የሙዚቃው ጋሻ ጃግሬው ኤሊያስ መልካ፤ የስብስቡን ትልቁን ጃንጥላ ይዞ የቆመ፤ የብዙዎቹ የጥበብ አባት ነው። እስከዛሬም በፍቅር ከምንሰማቸው የ90ዎቹ በረከቶች ውስጥ ምናልባትም ከግማሽ በላዩ የእርሱ ዐሻራ አለባቸው። ቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ)…አብነት አጎናፍር ዛሬም ድረስ አሉን ከምንላቸው ክዋክብት መሀል ናቸው። እዮብ መኮንን፣ ታምራት ደስታ፣ ማዲንጎ አፈወርቅ…እና ሌሎች ከአፈር በታች፤ ከደሳሳው የሞት ጎጆ ገብተዋል። ብዙዎች አልበም እንኳን ደርድረው ያልሆነላቸውን፤ ከ90ዎቹ ምትሀተኞች አንዱ የሆነው ኤርሚያስ አስፋው(ልረሳሽ አልቻልኩም) በአንዲት ነጠላ ዜማ ብቻ ከሙዚቃ አፍቃሪው ልብ የግዛት ባንዲራውን ሰቅሏል። ኧረ ለመሆኑ! እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) የት ናት? የዳንሱ ፈርጥ በረከት እንዲሁም በአዲስ ነገር ብቅ ብለው የጠፉት የጋሞ ቦይስ ሙዚቃና ዳንስ…ኮሜዲያን ክበበው ገዳና ሌሎቹስ ወዴት ገቡ? ለረዥም ጊዜያት ደብዛቸው ጠፍቶ ከቆዩት የእልፍኙ ስብስብ መካከል፤ በጥቂቶች የጥያቄ አሰሳ ጥቂቶቹን በቅርቡ ልንመለከታቸው ችለናል። ከእነዚህ ጌቱ ኦማሂሬና ቤተልሄም መኮንን(አነጋግረኝ) ይገኙበታል። ሙዚቃቸውንስ እንደሆን በየዳንስ ክለቡና በሆቴል ግሮሰሪው ሁሉ “ይደገም! ይደገም!” የሚል ብዙ ነው። ነገር ግን፤ ሥራዎቻቸውን ካልሆነ በቀር እነርሱን ግን የት ገቡ? ለምንስ ጠፉ? ብለን እራሳችንን እንኳን ለአፍታ ጠይቀን እናውቅ ይሆን? አሁን አሁን በአንዳንድ ሚዲያዎች ብርታት፤ በወራትና ሳምንታት ውስጥ የ90ዎቹን፤ አዳዲስ የመምጣት ዜና እንሰማለን።

የቀድሞውን ጤንነትና ማንነት አጥተውና ተጎሳቅለው በተመለከትን ጊዜ፤ ለእነርሱ ማዘን ብቻም ሳይሆን በራሳችን ላይ አዝነን፤ ራሳችንን ካልወቀስን ጤንነት አይደለም። ምክንያቱም፤ ማር በልተን ማር እየወደድን፤ ስለንቦቹ ግድ የማይለን ከሆነ፤ እራስ ወዳድ… ውለታቢሶች ነን።

እንደዚያን ጊዜ አቅም፤ ምርጥ የምንላቸውን ፊልሞችን ሠርተው፤ ግሩም ትዝታን ስላስቀመጡልን የፊልም ባለሙያና ተዋንያን፤ ዛሬ ግድ ብሎ ስለምንስ ጠፉ እንል ይሆን? ሰዓሊያን፣ ገጣሚያን፣ ድንቅ ፀሐፊያን… የመድረክ ላይ ኮሜዲያን፤ በዓላት በመጡ ቁጥር በጉጉት ናፍቀን ስንጠብቃቸው የነበሩት አባላት በሙሉስ? ካሴቶቻቸውን ከየፊልም ቤቱ እየወሰድን፤ ሆዳችንን ይዘን በሳቅ ፍርስ እስክንል ድረስ ስናደምጥ ስንመለከታቸው ነበር። እና ዛሬስ? ከነካሴትና ከሳቅ ጨዋታቸው ጋር እንደወጡ ቀርተዋል። ወዴት ገቡ፤ ለምንስ ጠፉ ብለን ግን አልጠየቅንም። በአሁኑ ሰዓት እየኖሩ ያሉት፤ በድሎትም ይሁን በችግር፤ ያጣነው እነርሱን ብቻ ሳይሆን ሊሰጡን ይችሉ የነበረውን ውድ የጥበብ ስጦታቸውንም ጭምር ነው። ወደኋላኛው ዘመን ሄደን የምንናፍቀውን ነገር፤ ዛሬም በ2ሺዎቹ የኛ የምንለውን በሰጡን ነበር። እነርሱን እንዲህ 90ዎቹ እያልን በናፍቆት እንደምናስታውሳቸው ሁሉ፤ እኛንም ከዘመን ጥበብ ጋር የሚያስታውስ የኋላኛው ትውልድ ይመጣልና። የትናንትናዎቹ 90ዎች ጥበብን ከቀደምት ተምረውና በአደራ ተቀብለው፤ ያማረውን እልፍኝ ሠርተውልናል። እልፍኙን ብቻ ሳይሆን በእልፍኙ ውስጥ የነበሩትን ዓይነት ስብስብ ዛሬም እንናፍቃለን።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You