ከአድማስ ባሻገር

ሀሳቤን አገልድሜ ከአድማስ ማዶ ሽቅብ ብወጣ አንድ ነገር ታየኝ። ጸጉሩ ጥቁር የሀር ጥጥ የመሰለ፣ አፍንጫው እንደ ጎበዝ ወታደር ቀጥ ብሎ የቆመ ሰልካካ… በረዶ ከሚያስንቁ ጥርሶቹ የሚወጣው የፈገግታ ጸዳል ለልብ ሀሴትን ይቸራል። የአዕምሮ ምጥቀቱን ግን በቃላት ላጌጠው ያልቻልኩት ጥልቅ ውቅያኖስ የመሰለ ሶታ ጎረምሳ ጎምላልዬ ወጣት ከወደኋላኛው ዘመን ታየኝ።

ውበትን ከደም ግባቱ ችሮት ሳያንሰው መግነጢሳዊ የአዕምሮ ምጥቀትና ልህቀትን ከጥበብ ጋር ሲሰጠው እግዜሩም ለእርሱ ብቻ ያዳላ መስሎ ተሰማኝ። ነገሩ ቅናት አንጨርጭሮኝ ምቀኝነት አብግኖኝ አልነበረም። የህይወት ግርማ ሞገሱ ልቤን ቢያቀልጠው እንጂ። እግዜር ይህን ሁሉ ሰጥቶት ሲያበቃ እድሜውን ግን ለምን እንደዘነጋው አልገባኝም፡፡ አንድ ታላቅ ጀብዱ ፈጽሞ እንዲመለስ እንጂ በምድር ላይ ሸብቶ በከዘራ እንዲንዛዛ አልፈቀደለትም፡፡ እናም ይበልህ ሲለው አመጸኛና ሞገደኛ ጸሀፊ አደረገው።

የብዕሩ አንደኛው ጫፍም ከላይ የሚመዘዝ ይመስለኛል። የሚጽፈው ብቻም ሳይሆን እርሱ እራሱ ትንግርት ነው። የብዕሩም ጫፍ ለገባው የላም ጡት፤ ለጠላቶቹ ደግሞ ሳማና እሬት ነው፡፡ እንደለመደው በአዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች፤ እንዲሁም በመነን መጽሔት ታንኩን ከመድፉ ሲያገላብጥ አንድ ቀን ግን አንጠልጥለው ለፍርድ አቀረቡት፡፡ አንድ ብቻውን ሆኖ በብዕሩ ሀገር ምድሩን የሚያናውጠው አመጸኛውን ከሥራ አግደው ጋዜጣና መጽሔቱን ለዓይኑ እንዲናፍቅ አደረጉት፡፡ ከደሞዙም ላይ ጎማመዱበት፡፡ ሥራ የፈታ ቀውላላ ሆነ። የዚህን ጊዜ አወጣ አወረደ። እኔ የመጣሁበት ትልቁ ዓላማ በጋዜጣና መጽሔት ብቻ የሚቆም አይደለም ብሎ አሰበ፡፡ በደማቋ ውብ ጨረቃ ከመስኮቱ ላይ ቆሞ አሻግሮ ከአድማስ ማዶ ቢመለከት…”ከአድማስ ባሻገር” የተሰኘች አንዲት ዓለም ታየችው፡፡

በ1962 ዓ.ም ወጣቱ በዓሉ ግርማ የበኩር ሥራው የሆነችውን “ከአድማስ ባሻገር”ን ጽፎ አስነበበ፡፡ ዛሬ የምንመለከታትም ይህችኑ የመጽሐፍ ዓለም ነው፡፡ በክረምቱ ዝናብ የወንዙ ሙላት ሳይሞላ፤ የጨረቃዋም ጀንበር ሳትጠልቅ ተሻግረን ልንቃኛት ወደድን፡፡

አብዛኛዎቻችን በዓሉን የምናስታውሰው የሞትን ጽዋ ከተጎነጨባት ከ”ኦሮማይ” ጋር ነው፡፡ ነገር ግን፤ የታላቅነቱ ቁልፍ የተንጠለጠለባት መጽሐፍ “ከአድማስ ባሻገር” ናት ብለው ሚሞግቱም ጥቂት አይደሉም። ልክ ሀዲስ አለማየሁ ብለን “ፍቅር እስከ መቃብር” እንደምንለው ማለት ነው። ይሁንና ደራሲው የበሰለው በልምድ ብቻ ሳይሆን ገና ከመጀመሪያውም የብዕር ሱናሚ ያስነሳው ሞገደኛ ስለመሆኑ “ከአድማስ ባሻገር” ይነግረናል፡፡ መጽሐፉ የሁሉም የበኩር መክፈቻው ሲሆን፤ ከእርሱ መጽሐፍት መካከል በውጭ ቋንቋ ተተርጉሞ የተጻፈ ብቸኛው መጽሐፍም ነው።

ብዕሩ እንደ ግዙፉ የመድፍ ቀለሀ ነው። በጻፈ ቁጥር ይተኩሳል። በተኮሰ ቁጥርም ጠላቶቹን እያሸበረ አንባቢውንም የሚያወዛግብ ጭምር ነው። “ከአድማስ ባሻገር” አርቆ የተመለከተበት አርቆም ያሰበበት ድንቅ ሥራው ነው፡፡ በብዙ ገጾች ባይገጠገጥም በብዙ ሀሳቦች የተደጎሰ ረዥም ልቦለድ ነው፡፡

የገጸ ባህሪያቱ ሞገደኛነት ከራሱ ይወለዳል፡፡ አስተሳሰብንም ሆነ ሀገርና ሕዝብ ወዳድነቱን የሚማሩት ከራሱ ከደራሲው ነው። በእውን የሚወልዳቸው እንጂ በምናብ የሚፈጥራቸው አይደሉም። ለአብነትም “የቀይ ኮከብ ጥሪ” በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ ዋና ገጸ ባህሪው “ሲራክ” ከየትም የመጣ ሳይሆን ስብሐት ገ/ እግዚአብሔር ነበር። እርሱን አስፈቅዶ ስብሐትን ከነቃጭሉ ዱብ አደረገበት። ወደዚህኛው መጽሐፋችን ስንመጣ ደግሞ “አበራ ወርቁ” የተሰኘው ዋናው ገጸ ባህሪ እራሱ በዓሉ ግርማ ነው። የሁለቱን መመሳሰል በጥቂቱ ብንመለከተው እንኳን፤ የአበራ መላው አስተሳሰብና ፍላጎት ከበዓሉ ጋር ልክክ ብሎ የሚገጥም ነው።

እንደ ትዝታ ሁለቱም በዊንጌት ትምህርት ቤት ውስጥ ተምረዋል። ዲግሪያቸውንም የጫኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመበጠስ ነው። ከዚያ ወዲያም ወደ አሜሪካን ይጓዙና በጋዜጠኝነት ላይ የፖለቲካ ሳይንስ አክለው ይመረቃሉ። እኚህ ሁለቱ ትንግርቶች ሥራ የሚይዙትም በማስታወቂያ ሚኒስቴር ነው። መንቲያ ላለመምሰል ግን በአንዲት ነገር የተስማሙ ይመስላል፡፡ በዓሉ ግርማ ሞገደኛ ጸሀፊ፤ አበራ ደግሞ የስነ ስዕል ከራማው የሚያይልበት ዓይነት ነው።

ከአድማስ ባሻገር ላይ ያለው የአበራ የኑሮ ትዕይንት ገና በገጽ አንድ ሲጀምር፤ “ቤቱን የዝምታ አዘቅት ውጦታል። ከዚያ ዝምታ… ከዝምታ የሚመነጨው የሙዚቃ ቃና መጨረሻ የለውም፡፡ ነብስን ከሀሴት ሊያወራጭ፤ አዕምሮን ኮርኩሮ ሀሳብን በስልት ሊያስደንስ ይችላል፡፡ አበራ ወርቁ በዚያ መጨረሻ በሌለው ዝምታ ተውጦ ሙሉውን የሌሊት ልብሱን ለብሶ እንደልማዱ የጣት ጥፍሩን በጥርሱ እየከረከመ ወዲህና ወዲያ በመንጎራደድ ለገላው ያሞቀው ውሀ ወደ ገንዳው እስኪወርድለት ድረስ የወትሮ ባልሆነ ትዕግስት ይጠባበቃል፡፡

…ትኩስ የሕይወት ጠብታ፤ ትኩስ ወፍራም የሕይወት ጠብታ የሚል ሀሳብ ለአንድ አፍታ በአበራ አዕምሮ ውስጥ ብልጭ ብሎ መልሶ ድርግም አለ፡፡ የአበራ አዕምሮ ከአንድ ሀሳብ ወደሌላ ሀሳብ እንዳሻው ስለሚጋልብ አንድ ነገር ላይ በተለይ ጊዜ ወስዶ እስከመጨረሻው ድረስ ሊያስብ አይችልም፡፡ ለዚህ ነበር ባለቅኔ ወይንም ደራሲ ወይንም ሰዓሊ የመሆን ተስፋውን ውስጡ ቀብሮ ያስቀረው፡፡ ነብሱ ግን እራሷን በአንድ ነገር ለመግለጥ ዘለዓለም እንደዋተተች፤ እንደቃተተች ትኖራለች፡፡” በማለት ይጀምራል፡፡

የአበራ የስዕል ተሰጥኦ አንገቱን በመዳፏ ጨብጣ ሲጥ ልታደርገው ምንም አልቀራትም፡፡ እርሱም በእርሷ መሸነፉን አውቆ የምትፈልገውን ሁሉ ሊሰጣት ፈልጓል። ግን ደግሞ የመንግሥት ሥራውን አቋርጦ ሊካድማት ቢያስብም፤ በመወሰንና ባለመወሰን ገመድ ታንቋል፡፡ በሌላ በኩል የትምህርት ቀለም ያልነከረው ታላቅ ወንድሙ አባተ ሚስት የማግባት ሩጫ ላይ ተጠምዷል፡፡ ልፋቱ እያለከለከም ጭምር ነው፡፡ ቀናኢ ፍቅር ያለው በጎ ሰው ቢሆንም ልጅ የማግኘቱ ነገር ግን ከላይ የታዘዘለት አይመስልም፡፡ ብዙ ሚስት ቢያገባም ከአንዱም ጠብ የሚል ልጅ ጠፋ፡፡

መቼም ከእግዜሩ ጋር ግብ ግብ ባይፈጥርም በስተመጨረሻ ግን ለተስፋ መቁረጥ እጅ ወደመስጠት አድልቷል፡፡ አሁን ያለው አንድ ተስፋ አበራ ብቻ ነው፡፡ ዓይኑን በዓይኑ ለማየት ባይችልም የወንድሙን ልጅ የማየት ጽኑ ምኞት አድሮበታል፡፡ በበዛው ቤተሰባዊ ፍቅራችን ውስጥ እንኳንስ የወንድምና የአጎትና የአክስት ልጅም ከራስ የማይቆረጥ ስጋ ነበር፡፡ ያኔ “…ዘመድ እስከ አክስት” ሳይሆን በፊት፤ መወለድ ቋንቋ በነበረበት ጊዜ፡፡ እናም አባተ፤ አበራ ሚስት አግብቶ ልጅ እንዲወልድ እሳቱን ይቆሰቁሰዋል፡፡ ቢሆንም ኃይለማርያም የተባለው የአበራ የልብ ጓደኛ እሳቱ ላይ ንፋስ እያስገባ ጥረቱን የሚያከስም እየመሰለው አይነ ውሀም ደስ አይለውም፡፡ በመሀል ግን ሉሊት ጎምላሌዋ እየተዘናከተች ከተፍ አለች፡፡ ሱዛናም ከትዝታው ጋር ብቻ ትኖራለች፡፡ ለትዳር ተቆልፎ ሲንቀዋለል የነበረው የአበራ ልብ በአንዴ ተከፈተ፡፡

የተማረ ሰው እቅድና ሂደት ይወዳል፤ ሁሉን ቦታ ቦታ አሳክቼ ቀስ ብዬ አገባለሁ ብሎ የሚያስብ የነበረ ቢሆንም ሉሊትን ወዷታልና እንድታመልጠው አልፈለገም፡፡ ከዚያም በፍቅር እሳት ነደው የትዳር ጎጆ ቀለሱ፡፡ አባተ በልቡ ስንቱን ታቦት ተስሎ የተገኘ ነገር ነውና የተሰማው ጥልቅ የደስታ ስሜት ወደሌላው ሰውም የሚዛመት ነበር፡፡

ከላይ እንደጠቀስነው አበራ በዚህች ምድር የመኖሩ ትርጉምና የሕይወት ደወል ጥሪው ከስዕል ጥበብ ላይ እንዳረፈ እርግጠኛ ነው፡፡ ወደፊት ለመራመድ አንድ ባለ ቁጥር ከፊቱ እንደጅብራ የሚቆመው ፈተና ግን ከመንገዱ ውልፍት አላደርግ ብሎታል፡፡ ችንካሩን ለመንቀል በተነሳ ቁጥር አንገቱን አስግጎ እያፈጠጠ የሚመጣበት ይብሳል፡፡ በጊዜው ለነበረው ስርዓት የእርሱ ተሰጥኦ ደንታም የሚሰጠው እንዳልሆነ ያስባል፡፡ ከእርሱ ሕይወት የምናገኘው የታሪክ ጭብጥ በብዛትም ፖለቲካው በዘረጋው ወጥመድ ውስጥ እየወደቁ ያሉትን ባለተሰጥኦ ወጣቶችን ሕይወት የሚያሳይ ነው፡፡

በትዕይንት የተሞላውን የገጸ ባህሪያቱን ታሪክ ደራሲው አሰባጥሮ ያስቀመጠበት መንገድ ልዩ የሆነ ስዕላዊ ምስልን የሚከስቱ ናቸው፡፡ የእያንዳንዱ ገጸ ባህሪያት የታሪክ ፍሰት ከምስላዊ ትዕይንቱ ጋር ሲታይ በዝምታ እንደሚወርድ ወራጅ ወንዝ የሚማርኩ ናቸው፡፡ መጽሐፍ እያነበብን ሳይሆን ከመሳጭ የቲያትር መድረክ ጋር የተፋጠጥን ይመስለናል፡፡ በዓሉ ያለውን እምቅ የጥበብ ጉልበት እንድናይለት ያደረገበት ሌላኛው ነገር በትንሽ ቃላት ውስጥ ብዙ ስሜቶችን መሰነግ መቻሉ ነው፡፡

አንድን ስሜት ለመረዳት አሊያም ለማስረዳት ቃላት ሲዘንቡ ነበር የምናውቀው፤ “ከአድማስ ባሻገር” ግን በእንዲህ ለመቆም አልፈለገም፡፡ ከምናነባቸው ከእያንዳንዱ አራት ነጥቦች በመለስ፤ ከነገረን ውጪ ውስጣችንን የሚሰረስሩን ሌላ ተጨማሪ ስሜቶችን ይልክብናል፡፡ የትዕይንቱ ግለት የገጸ ባህሪያቱ ላይ ታች ማለት በጉጉት ቆንጥጦ በተመስጦ እየመዠለገን ያቁነጠንጠናል፡፡ ገጸ ባህሪያቱ ከዓይነ ህሊናችን፤ ትዕይንታዊ ስሜቱ ደግሞ ከልባችን ሰፍረው ለማሰላሰል እንኳን ፋታ አይሰጡንም፡፡ በቃላት ከሚፈሰው ታሪክ ይልቅ በድርጊት የተሞላው እንቅስቃሴ ስሜታችንን እንዲጠልፈው አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ምሁራኑም “ሜሎድራማቲክ” ይሉታል፡፡ ልብ አንጠልጥል፤ ልብ ሰቅዝ በመሆኑ ነው፡፡ ታዲያ እኚያ ሁሉ እያነበብን የተጋራናቸውና የተዛመቱብን ስሜቶች ሁሉ ይህችን ከምታህል በጥቂት ገጾች ከተደጎሰች መጽሐፍ ውስጥ ስለመሆኑ ያጠራጥረናል፡፡ እንግዲህ የማይጋፉትን ጥበቡን ሰጥቶታልና እኛም ስንቀምስ ዝም ብለን አምነን ማጣጣም ካልሆነ በቀር እንዴትስ በዓሉን ላለማድነቅ ይቻለናል…

ከአድማስ ባሻገር ካለችው የመጽሐፍ ጎጆ ውስጥ አለፍ ብለን ወደ ገጽ 72 ስንሻገር የሚለን ይህንን ነው፤

“…እነሱ እነሱ የምትሉት እነማን ናቸው? እኛስ እነማን ነን? እነሱ እነሱ ከማለት ራሳችንን ዞር ብለን እንመልከት፡፡ ወደኛ ዞር ብንል የምናየው ምንድነው? ወኔ ቢስ አታሞዎች ሆነን እንገኛለን፡፡ ከካስቲል ወይም ከኢትዮጵያ ሆቴል ስንወጣ፤ ለማኞች ላይ እያገሳን የምናልፈው እኛው ነን፡፡

ለሀገር ልማት ይህን ያህል ከደሞዛችሁ ስጡ ብንባል መጀመሪያ የምናለቅሰው እኛው ነን፡፡ መንግሥት ጀርባ ላይ እንደ ቱሀን ተጣብቀን የምንኖረው እኛው ነን፡፡ ከሞግዚት ጉያ ወጥተን፤ በሁለት እግራችን መቆም ያስፈራናል፡፡ በራሳችን ላይ እምነት የለንም፡፡ ማንነታችንን አናውቅም፡፡

….እንደኛ ያሉት ሰዎች በየትኛውም መንግሥት ስር ያው ናቸው፤ ከማማረር አያልፉም፡፡ …ግን እስከመቼ?”

ከዚህች ከአንዲት ገጽ ውስጥ ከተቀነጨበ ጽሁፍ ላይ እንኳን የበዓሉን የፖለቲካ ጓዳ ወለል አድርጎ ያሳየናል። ፍትህና እውነትን ፍለጋ የሚሞግተው መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ሕዝቡንም ጭምር ነው፡፡ ሽንጡን ገትሮ ሲቆም በምክንያት እንጂ በጭፍን የስሜት ጨለማ ውስጥ ተውጦ አይደለም። ለመንግሥትም ሆነ ለተለያዩ አካላት ጥላቻ የለውም፤ እውነትን ሲጋርዷት ግን ብዕሩ የሚያነድ የእሳት እረመጥ ነው። የልቡን እንጂ ልወደድ ባይ ቅቤ አንጓችነት አይታይበትም። የ“ኦሮማይ” የሞት በቅሎ አስደንብራ ነብሱን ከገደል ብትጨምረውም፤ ገና “ከአድማስ ባሻገር” ሳይወለድ ጀምሮ ጠላቶቹ ብዙ ነበሩ፡፡ “ከአድማስ ባሻገር”ም ታማኝ ጠላቶችን አላፈራለትም ለማለት አይቻልም፡፡ ነገሩን በውል አስተውሎት ለማሰብ ቢቃጣኝ ጊዜ አንዲት ሀሳብ ሽው! አለችብኝ፡፡ በዓሉ መጽሐፍ የመጻፍ ችሎታ እንዳለው ገና በፊትም ያውቅ ነበር፡፡ ለዚህ የሚሆን ሀሳብም ጠፍቶበት አነበረም፡፡ የመረጠው ግን አሳቻ ጊዜ እየጠበቁ በጋዜጣና መጽሔቱ ላይ መጻፍን ነበር፡፡ አንድ የሚጠብቀው ጊዜ እንደነበረም ተሰማኝ፡፡ ጠብቆም ጊዜው ሲደርስ “ከአድማስ ባሻገር”ን ጻፈ፡፡ ከዚህ በኋላ የነበሩትን ቀሪ አምስት መጽሐፍት ለመጻፍ የፈጀበት ጊዜ ግን ከአሥር ዓመት ያልበለጠ ነበር። እናም የገጠመልኝ ሀሳብ ቢኖር፤ በዓሉ የሕይወት ጥሪውን ብቻም ሳይሆን ጠላቶቹ አኮብኩበው የሚጠብቋትን የእስትንፋሱን የመቋጫ ቀንም አስቀድሞ ያውቃት የነበረ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ለራሱ ከንቱውን ሕይወት ኖሮ አንዳችም ሳያጎድል እያከታተለ ሁሉንም ሰጥቶን መሄዱ፡፡

የበዓሉ ግርማን መጽሐፍቶች ባነበብን ቁጥር በእያንዳንዱ ውስጥ አንዲት ጀብዱ መራሽ የሆነች ሴት አናጣም። እኚህ ሞገደኛ ሴት ገጸ ባህሪያት ወንዱንም ጀግና ሁሉ የሚያርበደብዱና ያሻቸውን ነገር ከማድረግ የማይዛነፉ ብርቱዎች ናቸው፡፡ እኚህን የሴት አብዮተኞች በዚህን ያህል ደረጃ ለማስቀመጥ የፈለገበትን ምክንያት ኖሮ ብንጠይቀውና ቢመልስልን እንዴት ደስ ባለን…በ”ኦሮማይ” መጽሐፉ ውስጥ ያለችውን ፊያሜታ ጊላይን እናስታውሳለን፡፡ እዚህ “ከአድማስ ባሻገር” ደግሞ ሉሊት አለች፡፡ ከጎሊያድ ጎራዴ ይልቅ እንደ ዳዊት ጠጠር ስትወነጨፍ እንመለከታታለን፡፡ ይህን ያህሉን በራስ መተማመን ከወዴት እንደምታመጣው ያስገርመናል። ሱዛናም ሌላኛዋ ናት፡፡ ሴትነት ከምንም ነገር ሊያጎድል የማይችል፤ የአዕምሮ እንጂ የተፈጥሮ ዳገት አለመሆኑን ደራሲው ነግሮ ሳይሆን አሳይቶ ያሳምነናል፡፡

ከአድማስ ባሻገር የነበረው የመጨረሻ አድማስ በበርካታ ውጥንቅጦች የተሞላ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረው የትዕይንቱ ግለት ተጧጡፎ ሌላ ሆኗል፡፡ አበራ ለሉሊት ያለው ፍቅር ባይቀዘቅዝም ከልቡ ውስጥ ሹክ ያለውን ሰይጣን ጆሮ ዳባ ለማለት ግን አልቻለም፡፡ ቅናት የልቡን በር ሰብሮ አንጨረጨረው፡፡ ልበሙሉነቷ ከውስጧ የሚንጎማለልባትን ሉሊትን በሌላ ወንድ ጠረጠራት፡፡ የገባበትን ጥርጣሬ እያባባሰ የሚያቀጣጥለው ነፋስ እንጂ የሚያረግብለትን የስሜት ውርጭ አጣ፡፡ ትንሽዬ ሆና ከውስጡ የበቀለችውና እንደ ፓራሳይት የተጣበቀችው ቅናት፤ የፍቅር ደሙን እየመጠጠች ወፍራና ደልባ አረፈችው፡፡ ይህን ጊዜ ክፉ ክፉውን ሆነ ዓይነህሊናው የሚቃርመው፡፡ መጨረሻህ አይመር ሲለው ሾተላዩን አንስቶ የሞት አንካሴውን ጨብጦ የፍቅሬ ተኩላ ነው ብሎ ሲጠረጥረው የነበረውን ሰው ገደለው፡፡ የሰውየውን ነብስ ወደ ገነት ይሁን ወደ ሲኦል ሸኝቶ እሱም በዚያው ወደ ከርቸሌ ወረደ፡፡ ታላቅ ወንድሙ አባተም ስህተትን በስህተት ለማረም ገባ፡፡ በአበራ ለደረሰው ነገር ሁሉ ጥፋተኛው ያ ወትሮም ቀልቡ ያልወደደው ጓደኛው ኃይለማሪያም እንደሆነ እርግጠኛ ሆነ፡፡ በተራ ፍላጻውን አንስቶ ወደ ኃይለማሪያም ገሰገሰ፡፡ እስትንፋሱንም ጸጥ እረጭ አሰኛት፡፡ ገደለው፡፡ ቀጥሎም የሞት ጽዋውን ለራሱ ተጎነጨ። እራሱንም ደገመና አብረው አሸለቡ፡፡

ሁሉም ሰው የሞትን ባህር ተሻግሮ ከመሄድ አይቀርም፡፡ ሁሉም ሰው ግን እንዴት ይሆን የሚሻገረው? በዓሉ ስድስቱን መጽሐፍቶቹን ጨምሮ ሌላ አንድ መጽሐፍም አለው፡፡ 7ኛው ግን እራሱ ነው፡፡ እሱም ያለው ከእኛው ውስጥ ነው። ይህንንም ከቀሪ መጽሐፍቶቹ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You