በቁጭት የተገባበት የጤፍ ዱቄት ፋብሪካው ስኬት

የጤፍ እንጀራ ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ማዕድ ላይ የማይጠፋ የምግባቸው ሁሉ ቁንጮ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከጤፍ ለሌሎች የተለያዩ የምግብ አይነቶችን መሥራት ተጀምሯል፡፡ ጤፍ በሌሎች ሀገሮችም ተፈላጊ እየሆነ መጥቷል፡፡

ጤፍ እንጀራ ለመሆን ከማምረቱ ሥራ ጀምሮ ብዙ አድካሚ ሂደቶችን ያልፋል፡፡ ምርቱ ተበጥሮ፣ ተነፍቶና ተንገዋሎ ይፈጫል፡፡ የመፍጨቱ ሥራም በባህላዊም በዘመናዊ መንገድ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ እንደ ስንዴና ሌሎች ምርቶች ሁሉ በፋብሪካ ደረጃ በጥራት ተዘጋጅቶ ለገበያ መቅረብ ጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት ምግብ የሆነው የጤፍ እንጀራ ዱቄት እንደ ስንዴ ሁሉ በፋብሪካ ደረጃ ለምን አይዘጋጅም፤ ያለችው ብርቱ ኢትዮጵያዊት ጤፍን በፋብሪካ ደረጃ በጥራት ማዘጋጀት ከጀመረች ዓመታትን ተቆጥረዋል።

ጤፍን በፋብሪካ ደረጃ ማዘጋጀት እምብዛም ባልተለመደበት ወቅት ፣ የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ለጤፍ ካላት ስስት የተነሳ ግን ሞክራዋለች፤ መሞከር ብቻም አይደለም ሙከራዋን ወደ ተግባር ለውጣ ውጤታማ ሆናበታለች፡፡

ለዚህም ጤፍን ብቻ መፍጨት የሚችል ማሽን ራሷ ዲዛይን በማድረግ በቻይና አስመርታ ጤፍ የሚፈጭ ፋብሪካ ገንብታለች፡፡ የጤፍ ዱቄቱ ሶርስ ወይም ቱሬ ጤፍን በፋብሪካ ደረጃ በጥራት አዘጋጅታ ለገበያ ማቅረብ በመቻሏ ዕውቅናን አትርፋለች፡፡

በንግድ ሥራ ስመ ጥር ከሆነ ቤተሰብ የተገኘችውና ይህን የጤፍ ዱቄት በፋብሪካ በማምረት ላይ የምትገኘው የዕለቱ እንግዳችን ሙና መሀመድ ትባላለች። የፋብሪካ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ሙና መሀመድ ፤ ምንም እንኳን በነጋዴ ቤተሰብ ውስጥ ለንግድ ሥራ ቅርብ ሆና ብታድግም ንግድ ውስጥ ዘው ብላ አልገባችም፡፡ ከዛ ይልቅ የቀለም ትምህርቷን ተምራ፤ የንግድ ሥራንም እንዲሁ ተምራ የገበያ ባለሙያ በመሆን ጭምር ከስር ከመሰረቱ ተለማምዳ፤ ልምድና ዕውቀትን ቀስማ ነው ወደ ግል ሥራዋ የገባችው፡፡

የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን በተለይም የፋብሪካ ማሽኖችን በመሸጥ ብዙ ሠርታለች፡፡ ከብዙ ጥረትና ትጋት በኋላም ሶርስ ወይም ቱሬ ጤፍ ፋብሪካን በመገንባት በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ጥራትና ጥንቃቄ በፋብሪካ ደረጃ የጤፍ ዱቄትን አዘጋጅታ ለገበያ እያቀረበች ትገኛለች፡፡

አዲስ አበባ ከተማ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ሙና፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በሀገር ውስጥ ተከታትላለች፤ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በውጭ ሀገር ነው የተከታተለችው፡፡

በአሜሪካ የሒሳብ ትምህርትን በኮሌጅ ደረጃ አጠናቅቃ ወደ ሀገር ቤት ስትመለስም እንዲሁ በቤተሰብ ቢዝነስ ውስጥ ዘው ብላ አልገባችም፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው ተቀጥራ ሠርታለች፡፡ በዚህም ቤተሰቦቿ እንደ አለቃም እንደ አባትና ወንድም ሆነው ብዙ አስተምረዋታል፡፡ የንግድ ሥራን ከታች የጀመረችው ሙና፤ በወቅቱ ወጣትነት ሳያታልላት ለሥራ ትልቅ ፍቅርና አክብሮት እንዲሁም ጥረትና ትጋት ነበራት። ይህን የተረዱት ቤተሰቦቿም እምነት ያሳድሩባታል። ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንዲሉ ከፍ ያሉ የንግድ ሥራዎችን በኃላፊነት መሥራት እንድትችል ፈቅደውላታል፡፡

ቤተሰቡ በስፋት በተሠማራባቸው የአስመጪና ላኪ ንግድ ሥራዎች ውስጥ ትልቅ ተሳትፎ የነበራት ሙና፤ በተለይም ማሽኖችን በማስመጣት ለፋብሪካዎች በማቅረብ እና ወደ ሥራ በማስገባት በኩል ሰፊ ድርሻ ነበራት፤ በወቅቱ የዱቄት፣ የዘይት፣ የፕላስቲክና ሌሎች ፋብሪካዎች ማሽኖችን ከውጭ በማስመጣት ትሸጥ ነበር፡፡ ከሀገሪቱ ፋብሪካዎች የአብዛኞቹን ማሽኖች በመሸጥ እንዲሁም በሥራ ላይ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከቴክኒሻኖች ጋር ክትትል በማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሠርታለች፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ጭምር ማሽኖቹ በትክክል መሥራት እንዲችሉ ድጋፍ አደርግ ነበር የምትለው ሙና፤ በዚህ አጋጣሚ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ክፍል የማየት ዕድል አግኝቻለሁ ትላለች፡፡ ፋብሪካ ማቋቋም ፈልጎ ማሽን የገዛ ማንኛውም ደንበኛ የትም ይሁን የት ባለበት ሆኖ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል የተቻላትን ሁሉ ታደርግም ነበር፡፡ ከደንበኞቿ ጋር ያላት ግንኙነት ለአንድና ለሁለት ዓመት ሳይሆን እስከመጨረሻው እንደሆነም አስረድታለች፡፡

በዚህ መልክ የንግድ ሥራን በተለይም በማሽን ሽያጭ፣ ተከላና ጥገና ሥራ ላይ ዓመታትን የሠራችው ሙና፤ ከብዙ ትጋትና ጥረት በኋላ የራሷን ፋብሪካ ማቋቋም እንደቻለች ትናገራለች፡፡

አስመጪዎች በርካታ ማሽኖችን ሲያስመጡ የተከታተለችው ሙና፣ አንድም ጊዜ የጤፍ ማሽን የሚያስመጣ ሰው ሳታስተውል ትቀራለች፡፡ ‹‹ጤፍን እና ኢትዮጵያውያንን መነጣጠል አይቻልም፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው›› በማለት የኢትዮጵያውያን እራትና ኩራት በሆነችው ትንሿ ጤፍ ላይ ሙሉ ትኩረቷን በማድረግ የጤፍ ዱቄት ማምረት ሥራን ዛሬ ላይ ከትልቅ ቦታ ማድረስ ችላለች፡፡

ትንሿ ጤፍ እንጀራ ሆና ለምግብነት መቅረብ የምትችለው ብዙ ሂደቶችን አልፋ ሲሆን፤ ሂደቶቹም ቀላልና ዘመናዊ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የጤፍ ዱቄትን በዘመናዊ መንገድ አዘጋጅቶ ማቅረብ አዋጭና ተመራጭ መሆኑን ሙና ትገነዛበለች፡፡ ይህ እውን ሲሆን ሴቶችን በብዙ መልኩ ያግዛል ያለችው ሙና፤ የጤፍ ዱቄት በፋብሪካ አዘጋጅታ ለማቅረብ ብዙ ጥረት አድርጋለች፡፡

ጤፍን እንጀራ ለማድረግና ከእርሻ ሥራው ባለፈ ማዕድ ላይ ለማቅረብ ከመግዛት ጀምሮ ማበጠሩ፣ መንፋቱ፣ ማስፈጨቱ፣ ማቡካቱና መጋገሩ የሴቷ ኃላፊነት ሆኖ መቆየቱን ጠቅሳ፣ የእሷ ውጥን የሴቷን ድካም ያቀላል የሚል ጽኑ ዕምነት ያድርባትናም ፋብሪካውን እውን አደረገችው። ጤፍን በቀላሉ ከመጠቀም ባለፈ የኢትዮጵያ ብቻ እንደመሆኑ በዓለም በአቀፍ ገበያ ጭምር እንዲታወቅና በተለያየ መንገድ ለመጠቀምም ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡

‹‹ጤፍ ለኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት ምግብ እንደመሆኑ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ በቀላሉ መዘጋጀት አለበት›› የምትለው ሙና፤ ለዚህም በፋብሪካ ደረጃ መዘጋጀቱ ወሳኝ ነው ትላለች፡፡

እሷ እንዳለችው ሶርስ ወይም ቱሬ ጤፍ በፋብሪካ ደረጃ ሲዘጋጅ አንድ ጊዜ ፋብሪካ ውስጥ ከገባ በኋላ ማንም አይነት የሰው ንክኪ አይደርስበትም፡፡ ፋብሪካው ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ ሂደቱን ጠብቆ ጤፉንና ሌሎች ባእድ ነገሮችን ይለያል፡፡ ፋብሪካ ውስጥ የሚገኙ መስመሮች ከማበጠር ጀምሮ በቅደም ተከተል እብቅና አፈር ድንጋዩን ለይቶ ጤፉን በጥራት ፈጭቶ ያሽጋል፡፡

እንደ ስንዴ ሁሉ ጤፍስ ለምን ማሽን ውስጥ አትገባም፤ ለምን በፋብሪካ ደረጃ አትዘጋጅም በማለት ወደ ሥራው የገባችው ሙና፤ የጤፍ መፍጫ ማሽኑን ዲዛይን በማድረግ ወደ ሥራ ለመግባት ብዙ ጊዜ እንደወሰደባትም ትገልጻለች። ፋብሪካው በጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የማምረት አቅሙም በቀን 600 ኩንታል ያህል ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚመረተውን ጤፍ ከአርሶ አደር ሰብሳቢዎች ጋር ትስስር በመፍጠር እንደምታገኝ ያነሳችው ሙና፤ ጤፍ በሰፊ ማሳ ላይ የሚመረት ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ምርቱን በሚፈለገው መጠን ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነም ገልጻለች፡፡

አርሶ አደሩ በትናንሽ ማሳዎች ላይ ጤፉን እንደሚያመርትና የግብርና ሥራውም በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ እሷ እንዳለችው፤ እስካሁንም እንደ ስንዴና ሌሎች ምርቶች ሰፋፊ በሆነ የእርሻ መሬት ላይ ጤፍን ማልማት የቻለ የለም፡፡ ምክንያቱም የጤፍ ሥራ በጣም አድካሚና ሳርን ተከታትሎና ተንከባክቦ ለፍሬ እንደማብቃት ይቆጠራል ትላለች፡፡

‹‹የጤፍ ሥራ እጅግ ከባድና አስቸጋሪ ነው›› የምትለው ሙና፤ ከአመራረቱ ባለፈም እንደ ቡና ሁሉ ደረጃ ያልወጣለት በመሆኑ ሥራውን ከባድ እንዳደረገው ጠቁማለች፡፡ ለአብነትም አንደኛ ደረጃ ነጭ ጤፍ ተብሎ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚሰበሰበው ጤፍ፣ ጥራቱ የተለያየ ሆኖ እንደሚገኝ ገልጻ፣ ጤፍም እንደ ቡና አንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ሶስተኛ ተብሎ ደረጃ ሊወጣለት ይገባል ባይ ናት፡፡ ይሁንና እስከዚያው ከተለያዩ ጤፍ አምራቾች ጤፉን እየገዛች በፋብሪካ ደረጃ በጥራት አዘጋጅታ እያቀረበች ትገኛለች፡፡

‹‹ጤፍን ከእንጀራ ውጭ እሴት በመጨመር በተለያየ መንገድ በማዘጋጀት መጠቀም ስንችል ፋይዳውን በብዙ ከፍ ማድረግ ይቻላል›› የምትለው ሙና፤ በአሁኑ ወቅት ጤፍ በዓለም ደረጃ ዋና ምግብ (ሱፐር ፉድ) ተብሎ ተፈላጊነቱ እየጨመረ ስለመምጣቱም ትናገራለች፡፡

እሷ እንዳለችው፤ ጤፍ በውስጡ የያዘው ንጥረ ነገር በርካታ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በአሁኑ ወቅት መላው ዓለም የሚፈልገውና እያመረተው ያለም እንደሆነም ተናግራለች፡፡ ‹‹ስለዚህ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በስፋት አምርቶ ከእንጀራ ውጭ በተለያየ መንገድ ለመጠቀም ብዙ ሥራ ይቀራል›› በማለት ጤፍን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ጭምር ከቡና ያልተናነሰ ገቢ ማምጣት እንደሚቻል ገልጻለች፡፡

እሷ እንዳለችው በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብቻ ሆኖ የኖረው ጤፍ የመላው ዓለም እየሆነ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ብዙ ሊሠራበት ይገባል፡፡ አሁን ላይ ጤፍ በተለያዩ ሀገራት መመረት ጀምሯል፤ ምርትና ምርታማነቱን በማስፋት ዘመናዊ በሆነ መንገድ ማዘጋጀትና ከእንጀራ ውጭ በተለያየ አግባብ ዘመናዊ በሆነ መንገድ መጠቀም የግድ ይሆናል፡፡

ለዚህም ሶርስ ወይም ቱሬ ጤፍ የራሱን ሚና ለመወጣት በሚያደርገው ጥረት ደረጃውን የጠበቀ ንጹህ የጤፍ ዱቄት በጥራትና በጥንቃቄ አዘጋጅቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሀገር ውስጥ ገበያ ከሚያቀርበው ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ማቀዱንም ጠቁማለች፡፡

ሶርስ ወይም ቱሬ ጤፍ በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ገበያ በስፋት መግባቱን ገልጻ፣ በቀጣይም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን አቅዳ እየሠራች መሆኑን ሙና አስታውቃለች፡፡ ሶርስ ወይም ቱሬ ጤፍን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የኢትዮጵያ በሆነው ጤፍ የኢትዮጵያን ስም ማስጠራት የግድ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥታ ተናግራለች። ለዚህም ፋብሪካው አስፈላጊዎቹን የጥራት ደረጃዎች በሙሉ ማለፍ መቻሉን ጠቅሳ፣ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካላቸው አይኤስኦ 9001 እና ኤፍኤስሲ 22000 ድርጅቶ ዕውቅና አግኝቷል ብላለች፡፡

የገበያ ተደራሽነትን በሚመለከት ሶርስ ወይም ቱሬ ጤፍ ከግለሰብ ጀምሮ ለሱፐርማርኬቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆቴሎችና ሌሎችም ተደራሽ እየሆነ ይገኛል፡፡ በተለይም ሥራ የሚውሉ እናቶችን ማሳረፍ የቻለ ስለመሆኑ ያነሳችው ሙና፤ ፋብሪካው መቶ በመቶ ጤፍ ብቻ የሚያመርት መሆኑን ገልጻለች፡፡ ይህንንም ስታብራራ ብዙዎች ዱቄቱን ምርጫቸው ያደረጉት ‹‹ፋብሪካው ውስጥ ጤፍ ብቻ ገብቶ ጤፍ ብቻ ስለሚወጣ ነው›› ብላለች፡፡

ሙና እንዳለችው፤ በ2009 ዓ.ም ወደ ሥራ የገባው ሶርስ ወይም ቱሬ ጤፍ በአሁኑ ወቅት 78 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፤ በቀጣይም ማስፋፊያ በማድረግ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ይዟል፡፡ በቀጣይ ዕቅዱም ከጤፍ ዱቄት በተጨማሪ እሴት በመጨመር እንጀራ ወደ ማምረት ሥራ ይገባል። ለዚህም አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመሥራት ወደ ተግባር ሊሸጋገር ከጫፍ ደርሷል። ድርጅቱ ሌሎች በርካታ የሥራ እቅዶች ያሉት በመሆኑ በሥራ ዕድል ፈጠራ ረጅም ርቀት ይጓዛል፡፡

ሶርስ ወይም ቱሬ ጤፍ አሁን በተለያየ አይነትና መጠን ምርቱን ለገበያ እየቀረበ ነው፤ በአይነት ነጭና ቀይ ጤፍ በመጠን ደግሞ በ10 እና በ25 ኪሎ ግራም ያቀርባል።እነዚህም ቀይ ጤፍ ባለ 10 እና ባለ 25 ኪሎ ግራም እንዲሁም ነጭ ጤፍ ባለ 10 እና ባለ 25 ኪሎ ግራም መጠን ያላቸው ናቸው፡፡

ምርቱ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉት ሰባት ቅርንጫፎች አማካኝነት ከተማ ውስጥ ለሚገኙ የማህበረሰብ አካላት ተደራሽ መሆን ችሏል፡፡ ይሁንና በቀጣይ ከከተማ ውጭ ለሚገኙ የማህበረሰብ አካላት እና ለውጭ ገበያ የማድረስ ዕቅዱን ተግባራዊ ያደርጋል።

ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የተለያዩ ድጋፎችን እንደምታደርግ የገለጸችው ሙና፤ በተለይም ለሴቶች እንደምታደላ ነው የገለጸችው፡፡ ይህም ሲባል የሥራ ዕድል ቅድሚያ ለሴቶች ከመስጠት ጀምሮ ሴቶችን ማብቃትና ከታችኛው የሥራ ክፍል ከፍ ወዳለው የሥራ ክፍል ታሳድጋለች፡፡

ለሠራተኞቿ ጋር ያላት መልካም አቀራረብም ጠንካራ የሆነ ቤተሰባዊ ግንኙነት የፈጠረላት መሆኑን ጠቅሳ፣ ድርጅቱ ሲቋቋም ጀምሮ የተቀጠሩ ሠራተኞች ዛሬም ድረስ አብረዋት እንዳሉ ተናግራለች፡፡ ይህም በመልካም ግንኙነት የተገኘ ስኬት በመሆኑ አብረውኝ አድገዋል ትላለች፡፡ ሠራተኞች ምግብ በነጻ እንደምታቀርብም ገልጻለች፡፡

ሀገራዊ ለሆኑ ማንኛውም ጥሪዎች በአቅሟ ምላሽ የምትሰጠው ሙና፤ ኢትዮጵያዊ የሆነውን ጤፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ትልቅ ህልም እንዳላትም ተናግራለች፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You