ይሄን ሰሞን ጆሮ፤ ከአንድ ነገር ይዋደዳል። እንዲያውም ከመዋደድም አልፎ፤ በፍቅር ጠብ እርግፍ ሲል ይታያል። በጆሮ የገባ ለልብም አይቀርምና፤ ልባችንም ወደ አንድ ውስጣዊ ስውር ዓለም ሲሰወር ይሰማናል። በታክሲው ውስጥ ሆነን፤ እኛና ስሜታችን አብረን ስንሳፈር ይታወቀናል። ጆሮና ልባችን ተመሳጥረው፤ እያሴሩብን ይሁን ምን፤ ግራ ሊያጋቡንም ይችሉ ይሆናል። ታዲያ፤ ወርደን ከጎዳናው ላይ ስንሄድ፤ እግራችን ብቻውን አልነሳ ያለ እንደሆን፤ በውስጣዊ ኃይል ሲነዱ ከአንዱ ቦታ መድረስም አለ። እልፍ ስንል ደግሞ፤ ከቅዱሳተ ንዋያት መደብር፤ አሊያም ከሕንፃዎቹ በታችና በላይ ካሉት የዕቃ መሸጫ ሱቆች ደርሰን፤ ድንገት ከድምጹ ጋር ያለ ቀጠሮ እንገናኛለን። በደጀ ሰላሙ አልፈን፤ ከሆቴልና ካፍቴሪያው ብንገባ፤ ከዚሁ ዋል.. ከዚሁ እደር ያሰኘናል። ለሥጋችን ስንቅ ፍለጋ ከገባንበት ምግብ ቤት፤ ቁጭ ስንል ይሄው ድምጽ በድጋሚ እያቃጨለ፤ ከሆዳችን ቀድሞ ልባችን ይጮኻል። ምነው? ብንለው፤ “ምንም እንዲሁ ደስ ብሎኝ ነው” ለምን? “እንዴ አትሰማም ይሄን ድምጽ!”… ይገርማል፤ እኔ ምልህ ግን የኔ ልብ፤ ብለን ልንጠራው ስንፈልግ፤ እርሱ ግን የለም። ጭልጥ ብሎ ከአንድ ቦታ ነጉዷል። … በገና እንዲህ አያደርገውም አትበሉ፤ ያደርገዋል። ጆሮ፤ ይህን የበገናን ማራኪና ጎርናና ድምጽ ሰምቶ፤ ሃይማኖቴ… እኔነቴ አይልም። የንዝረቱ ኃይል፤ ልብን በምስጠት ከማንሳፈፍ አይመለስም። ሙዚቃ የስሜቶች ሁሉ ገመድ እንጂ፤ የአንድ ዓለም ነጸብራቅ ብቻ አይደለምና ባንወድም ልባችን ልጥፍ ማለቱ አይቀርም። በገና ከነንዝረቱ፤ ታሪክና ውልደቱ… እንዲህ እየደረደርን በቃላት እንቀኘው።
“በገና”፤ በጥሬ ትርጓሜው መዝሙር እንደማለት ነው። በግእዙ ደግሞ “እንዚራ” የሚል ስያሜ አለው። በሀገራችን ከጥንት እስከ አሁኗ ሰዓት፤ ያለምንም የቅኝት መንሻፈፍ ደርሶ፤ ዛሬም በመዝሙራዊ ደምግባት፤ በሙዚቃዊ መዓዛ ከጆሮና ልባችን ላይ ይንቆረቆራል። ሥጋችንን አጥቦ መንፈሳችንን ይከሽነዋል። መነሻው መንፈሳዊው ዓለም እንደመሆኑ፤ ወደዚያ ገባ ብሎ መጠየቁም የግድ ነው። እንደሚነግረንም፤ በገናን ለመጀመሪያ ጊዜ የደረደሩት፤ የዓይነ ስውሩ የ”ላሜህ” ልጅ ልጆች ወይንም የ”ኢዮቤል” ልጆች ናቸው። ቢሆንም ግን፤ “በገና” ስንል በጠራን ቁጥር፤ አዕምሯችን የጠቢቡን አባት፤ ንጉሥ ዳዊትን ያስታውሰናል። በገናን እየደረደረ፤ ከታች በእጁ ይዞ ከላይ፤ ከመንፈሳዊው ዓለም በለስን ወደ ምድር ያረገፈ፤ ምናልባትም እንደእርሱ ያለ የለም። የበገናው ጌታ ነው። በገና በዋናነት የሚታወቀው፤ በቤተክርስቲያን ውስጥና በመንፈሳዊ ዓለም ቢሆንም፤ ለዛሬው የዘመናዊ ሙዚቃ ውልደት መሠረት ነው። ቅዱስ ያሬድ ያደገውም ሆነ የተማረው በቤተክርስቲያን ውስጥ ነው። በእጁ፤ ከበገና በላይ የያዘው የሙዚቃ መሳሪያ አለ ለማለት አይቻልም። ምናልባትም ወንድሞቹ መሰንቆና ከበሮ ካልሆኑ በቀር። ቢሆኑም ግን፤ ከወሰን አልባ ውቅያኖስ ውስጥ ጠልቆ እልፍ ዜማዎችን ለማስገር፤ እንደበገና ያለው የቅኝት ማስገሪያ አይገኝም። ከእያንዳንዱ አሥር አውታሮች ውስጥ የሚወጣው ንዝረት፤ በምንፈልገው የዜማ ምት ውስጥ ለማረፍ አመቺ ነው።
ከድምጾቹ በላይ፤ አሠራሩን ተከትሎ ስለሚታየው መልኩ ምን ይሉ ይሆን? “በገና በገነ” ይሉናል። በገናውን ደረደረ፤ አነዘረ እንደማለት ነው። “በገነ” የምትለዋ ቃል ከውስጧ ለዓይን የማይታይ አደገኛ እሳት አለባት። “በገነ” በሌላኛው ጫፍ ነደደ፤ ተቃጠለ…የመሳሰሉትን፤ የሰውኛን ውስጣዊ ባህሪያት የተላበሱ ትርጓሜዎችን ይሰጠናል። “በገና በገነ” ሲባልም፤ በዘፈቀደ ሳይሆን በገና የሚሠራበት እያንዳንዱ ግብዓት የደረቀ አሊያም የተቃጠለ በመሆኑ ስያሜውን ከዚሁ ወሰደው። በበገናው፤ በእያንዳንዱ ማዕዘናት ያሉት እንጨቶች የደረቁ መሆን አለባቸው። ቆዳውም በደንብ ከደረቀ ቁርበት መሆን አለበት። አሥርቱ ጅማቶች ወይንም አውታሮች የሚሠሩት፤ ደህና አድርጎ ከደረቀ ጅማት ነው። የበገና፤ አጀማመሩም ከውስጣዊ ስሜት ጋር የተቆራኘ ምክንያት አለው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፤ የቅዱሱን መጽሐፍ ታሪክ በመንተራስ፤ በገና የተጀመረው የአዳም አምስተኛ ትውልድ በሆኑት በኢዮቤል/በዮባል ልጆች ነው፤ ይላሉ። የአዳም ልጅ ቃኤል፤ ወንድሙን አቤልን ይገድላል። ፈጣሪም “ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደው” ብሏልና ከነአገዳደሉ ሳያስቀርለት፤ ቃኤልም በገዛ ልጁ በላሜህ ተገደለ። በእርሱ ሞት ሀዘናቸው የከፋው ልጆችም፤ በገናን በማበጀት የውስጥ ሀዘናቸውን በበገና እንጉርጉሮ መግለጽ ጀመሩ። ከዚያን ጊዜ ወዲህም፤ በገናን ለእንጉርጉሮ ብቻም ሳይሆን፤ በንስሐ ከአምላካቸው ፊት ለመውደቅ፤ ለልመናና ለምሥጋናም ጭምር ይጠቀሙበት ነበር። ይህ በገና የሚያወጣው ድምጽም የራሱ የሆነ ስያሜ አለው። ቤተ ክርስቲያኗም “ድምፀ ማኅዘኒ ወይንም ቃለ ማኅዘኒ” ትለዋለች። ታሪኩ እንሚነግረንም፤ አጀማመሩ ከዮባል ልጆች ሀዘን የተነሳ ነበር። የሚሰጠውም፤ የሀዘንና የእንጉርጉሮ ድምጽ ነውና ስያሜውን ይመስላል። ድምጹን ባደመጥነው ቁጥር አንጀታችንን እያላወሰ በስሜት ደፍቆ፤ በትካዜ የማጥመቅ ኃይል አለው። እልፍ ስንል እንኳን ድንገት ከጆሯችን ውስጥ ጥልቅ ያለ እንደሆነ፤ ከንዝረቱ የተነሳ፤ በዓይናችን ወደ ውጭ ሳይሆን በልባችን ወደ ውስጥ እንድንመለከት ከማድረግም ወደኋላ አይልም። ከጆሮ ደምስር እየገባ መላ ሰውነታችንን ከስሜታችን ጋር የሚያጠላልፍ አንዳች ስውር ማሰሪያ አለው።
በገና ከሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎች ለየት የሚያደርገው፤ የእርሱ ብቻ የሆኑ ባህሪያት አሉት። በሚሠራበት ጊዜ፤ አገኘሁ ተብሎ ለየት ባለ መልኩ ልሥራው አይባልም። የሚወጣው ድምጽ፤ ሁሌም በየትኛውም ጊዜና ቦታ በምክንያትና በዓላማ የታጀበ ነው። በጽሞና ውስጣዊ መንፈስን ለማደስ እንጂ በዳንስ በዳንኪራ፤ በፉከራም ሆነ በሽለላ ሥጋን በቼ በለው! ለማታለል አይውልም። ሁሌም፤ ወይ ከራሳችን ጋር ወይ ደግሞ ከፈጣሪያችን ጋር ለመገናኘት ነው። የበገና ቁሳዊ አካል፤ ከአቀማመጡ ጀምሮ የያዘው ተምሳሌታዊ ትርጓሜ አለው። በዋናነት አራት ክፍሎችን እንመለከትበታለን። ከታችኛው፤ በቆዳ ከተሠራው አራት ማዕዘን፤ በሁለቱም አቅጣጫ በቅስት መልክ የቆሙትን ወደ ጎን አንድ አጣምሮ የያዘው፤ የላይኛው ክፍል፤ ፈቃደ እግዚአብሔርን የሚያመለክት ሆኖ እናገኘዋለን። ከላይኛው ጫፍ በመስቀል ቅርጽ፤ በግራና በቀኝ የቆሙት ደግሞ፤ የሚካኤልና የገብርኤል ተምሳሌት ናቸው። አሠርቱ አውታሮች፤ አሥርቱን የሙሴ ትዕዛዛትን ወይንም ቃለ እግዚአብሔርን የሚወክሉ ናቸው። አውታሮቹ ሲደረደሩ፤ ድምጹ የሚወጣው ከታችኛው በቆዳ ከተሠራው አራት ማዕዘን ውስጥ ሲሆን፤ ተምሳሌትነቱ እጅና አውታር ተዋህደው ድምጹን እንደፈጠሩ ሁሉ፤ ሥጋና መለኮት ተዋህደው ከድንግል ማኅጸን ስለማደራቸው ነጋሪ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፤ በሌላ ተጨማሪ ተምሳሌተ ትርጓሜም ያስቀምጡታል። እላይና ታቹ፤ በሥጋና መንፈስ እንዲሁም ግራና ቀኙን በብሉይና ሐዲስ ኪዳን ይመስሉታል።
እጅ አለኝ አሊያም ተመቸኝ ተብሎ እጅ ወደ በገና አይሰደድም። አደራደሩ ትውፊታዊ ሥርዓት አለው። ምን ጊዜም በገና ለመደርደር ስናስብ፤ ወደ አውታሩ የምንልከው የግራ እጅ ጣቶቻችንን ነው። የግራ እጅ አሊያም ጣቶቻችን ካልጎደሉ በስተቀር ማለት ነው። በሳይንሱ ግራና ቀኝ እጆቻችን ከግራና ቀኝ የአዕምሯችን ክፍሎች ጋር የተዛመዱ ስለመሆናቸው ሳይንሱ ይነግረናል። የግራ እጃችን ወደ ቀኝ የአዕምሮ ክፍል ያደላል። ቀኙ የአእምሮ ክፍል ደግሞ ስሜታዊና ከስሜት ጋር የተሳሰረ ነው። ሙዚቃ፣ ስዕል፣ ዳንስ…በአጠቃላይ ኪነ ጥበባዊና መሰል ስሜታዊ ግብሮች የሚበስሉበት ነው። የማይታየውን ዓለም፤ በፈጠራና በምናብ ማሳየት የሚችልና ተመስጦን የሚሻም ጭምር ነው። ታዲያ ከሳይንሱ በፊት፤ የኛ አባቶች በገናን በግራ እጅና ጣት እንዲደረደር ማለታቸው፤ በመንፈስ ብቻም ሳይሆን፤ በእውቀትና በጥበብም፤ የደረሱበትን አያሳይም ትላላችሁ… በገናውን ስናበግን በሁለት ዓይነት መንገዶች ሊሆን ይችላል። የመጀመሪያው፤ የእጆቻችንን ጣቶች በመጠቀም እንቀኛለን። ሁለተኛው ደግሞ፤ በድሕንጻ ነው። “ድሕንጻ” የበገናውን አውታር ለመግረፍ የምንጠቀምበት አጫዋች ነው። አውታሮቹን፤ በቀጥታ በጣቶቻችን ከመነካካት ይልቅ በድሕንጻ መጠቀሙ፤ የበለጠ ድምጽና መሳጭ ዜማ እንድናገኝ ይረዳናል።
በገናን በቃላት ስለመደርደራችን፤ ሰሞነኛው የአብይ ጾም አልፎም ሳምንተ ህማማት መስታየታችን ነው። ከጾሙ ሳምንታት ሁሉም፤ በህማማት ወቅት በተለየ ሁኔታ የበገና ድምጽ ከወዲያና ወዲህ፤ ..እርር!…ድርር! ድርን!..ድር!.. ሲል እንሰማለን። እራስን ከማግኘት በላይ፤ ፈጣሪን ለማግኘትና ለመገናኘት፤ ፋይዳው በብዛት ይጎላል። “ድምፀ ማኅዘኒ” ወይንም የሀዘን ድምጽ የሚለውን ትርጓሜን፤ ከመቼውም በላይ በትክክል ይገልጽልናል። ምክንያቱም ደግሞ፤ በስቅለቱ ያለውን የሀዘን ድባብ ይፈጥራል። መድረሱንም ጭምር ይነግረናል። ከዚህ በተለየ መነጽር ለመመልከት ከሞከርን፤ አንድ ጥያቄ ልንጠይቅ እንችላለን። በገናና የአብይ ጾም፤ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የሚያገናኛቸው ነገር አለ ወይ? በማለት ሊቃውንቱን ብንጠይቅ፤ ምላሹ “ምንም የለም” የሚል ይሆን ነበር። ነገር ግን፤ በገናና የአብይ ጾም ለመቆራኘታቸው፤ አንድ ታሪካዊ ምክንያት አለ። ይኸውም፤ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነበር። በዚያን ጊዜ ታዲያ፤ በአብይ ጾም ወቅት፤ በሬዲዮ ከሕዝቡ ጆሮ የሚንቆረቆረው ሁሉ የበገና ድምጽ ነው። በገና፤ የሕዝቡን ልብ እንደፈለገ ውሎ ያመሻል። ውስጥን ዳሳሽ ንዝረቱ፤ ሞገዱን እየዳበሰና እያለሰለሰ፤ አልፎ ከስሜት ጋር ተቆራኘና፤ አብይ ጾም በመጣ ቁጥር ሁሉ በገና የሚናፈቅ ትዝታ ሆኖ ቀረ። ጆሮ ስሙ ስሙ፤ ልብም አምጡ አምጡ ማለት ጀመሩና በገናን ከሰሞኑ ለሰሞኑ ያስመሰሉት ቢሆንም፤ እንደ ቤተ ክርስቲያኗና የሊቃውንት አስተምህሮ፤ በገና በ365ቱም ቀናት በእኩል የሚደረደር ነው።
በገናና በታሪክ ቅኝት የኋልዮሽ መለስ ስንል፤ እድሜው ከ5 ሺህ ስምንት መቶ በላይ ሆኖ እናገኘዋለን። አዛውንትም፤ ሽማግሌም ብለን ለመግለጽ ብናስብ፤ ቁጥሩ ከቃላት በላይ ይሆንና “ቃል አጣሁልህ” ያስብለናል። ከሀገራችን ኢትዮጵያ ጋር ትውውቅ የፈጠረበት ጊዜ በውል ባይታወቅም፤ በዓለም የመጀመሪያዋ አሊያም ሁለተኛዋ ደርዳሪ ስለመሆኗ ግን ጥርጥር የለውም። የበገና እናት፤ ኢትዮጵያ ወይንስ እስራኤል? ምላሹ በራሱ፤ ጥያቄ አጫሪ ይሆንና፤ ገላጋይ ዳኛ የሌለበትን ዳገት ያሳየናል። በገና፤ በንጉሥ ዳዊት ቤት፤ ምግብና ውሃ እንደነበር ቅዱሱ መጽሐፍ ይነግረናልና “እውነቱን ተናግሮ በመሸበት ማደር” ሲሉ፤ ውልደቱ በእስራኤል ነው በማለት የሚሞግቱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ጥቂት አይደለም። ወደ ኢትዮጵያ የመጣውም፤ ሁለቱ ሀገራት በፍቅር በወደቁበት፤ በዘመነ ሰለሞን ጊዜ ስለመሆኑ ይናገራሉ። “ኧረ በጭራሽ!”፤ የሰው ዘር መገኛ፤ የሁሉም ነገር መጀመሪያ፤ የቅዱስ ያሬድ ሀገር ኢትዮጵያ እያለችማ ከእስራኤል ነው አንልም በሚል እሳቤ፤ ሽንጣቸውን ገትረው “ኢትዮጵያ!” የሚሉትም እንዲሁ ጎራ ይዘው አሉ።
ነገርዬው፤ ከወዴትም ይሁን ከማን፤ እራሱን በገናን በዜማ አባብሎ ለመጠየቅ የቻለ፤ ምላሹን ከራሱ ያገኘው ይሆናል። በጀመረ ቢሆን ኖሮማ፤ ስንቱን ጀምረን “እንኩ!” ያልን፤ እኛን ምስኪን መጽዋቾቹን ማን ይደርስብን ነበር…ይህን በመሳሰሉ ጥያቄዎች ድንጋይ አዝሎ ጣና ላይ ከመዋኘትና ኤርታሌ ውስጥ አሳ ከመፈለግ… በያዝነው ነገር ምን ሠራንበት ብሎ፤ ውስጥን ማሰሱ የተሻለ ነው። በራሳችን የታሪክ አሰሳ ውስጥ፤ የበገናው እናት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መሆኗ እሙን ነው። ከያሬዳዊ የሙዚቃ ፈለግ አንስቶ፤ ወደ ውጭ ከቤተክርስቲያኗ አልፎ መውጣቱ ግን አልቀረም። በቀደሙት የነገሥታቱ ዘመን፤ በገና ከሹማምንቱ ቤት ሁሉ የማይጠፋ ውስጠታዊ ኒሻን ነበር። ከሁሉም በተለየ፤ አፄ ቴዎድሮስ ያለ በገና ውሎ ማደር የሚጨንቃቸው ዓይነት ነበሩ። ፈጣሪያቸውን ለማመስገንም ሆነ፤ የጭንቀት ስሜታቸውን ለማርገብ ሲሹ፤ በገናውን ከተሰቀለበት ውርድ! በማድረግ፤ በቀኝ አንቀብቅበው በግራ የሚያጨዋውቱ ስለመሆናቸው ታሪክ ይነግረናል። እንዲያውም፤ በእሳቸው ዘመን የተደረደረ አንድ የበገና ዜማ፤ ዛሬም ድረስ ለማስተማሪያነት ሲያገለግል እንመለከታለን።
በገናና የኛ ትውልድ፤ ተጠፋፍተው ከረዥም ጊዜያት በኋላ የተገናኙ ዘመዳሞች መስለዋል። እግዜር፤ በገናን ትረፍ ሲለው፤ አንዱን የጥበብ ኖህ አስነስቶ ከመጥፋት አዳነው። እንጂማ፤ ከሀይቅ ጫፍ ላይ ቆሞ እንደሚንደረደር ዋናተኛ፤ በገናም ሲያኮበኩብ ነበር። የበገና አባት ለመባል የበቃው፤ ስብሐት አለሙ አጋ፤ ደርሶ በገናን ታደገው። የደበዘዘውን ማንነቱን እያፈካ፤ እልፍ ተማሪና የበገና ነብስ አድን ሠራተኞችን ለመሰብሰብ ቻለ። በውስጡ ያለውን ልዩ የበገና እውቀትና ችሎታ ለደረሰው ሁሉ እያካፈለ፤ በገናን አፍቃሪ ትውልድ ለመሥራት በቃ። ዛሬ ላይ በየሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ሁሉ፤ በገናን በፍቅር አቅፎ በስሜት የሚዳስሰው ወጣት ቁጥሩ በገፍ ነው። እያንቆለጳጰሰና እያባበለ፤ ሙዚቃን ከውብ ዜማ ጋር የሚያልብበትም እልፍ ነው። በአንዱ የአዲስ አበባ ጎዳና ላይ፤ በገናን ከነነብሱ ተሸክሞ፤ በኩራት ወዲያና ወዲህ የሚልን ሰው ለማግኘት፤ ብዙ መጠበቅ አያሻንም። እንደ ገበያና ገበያተኛ፤ ትርምስምስ ብሎ ውጥንቅጡ ከወጣው መንገደኛ መሃል፤ ትኩር ብሎ በዓይን ማንጠር ብቻ ነው። ጎምለል ሲል ከነ በገናው… እሷም ከነበገናዋ… ሲያዘግሙ እንመለከታለን። መውደድ ይስጥህ ካሉ አይቀርም፤ የበገናን ይስጥህ ማለት ነው። ከሞት ተርፎ፤ ሕይወት ማብቀልም ጀምሯል። በመጨረሻም፤ ይህችን እቋጥርለት ዘንድ፤ የገዛ ንዝረቱ አነሆለለኝ።
የበገናው ዜማ ከንዝረቱ፤
ከአጽዋማት ጀንበር በፍልሰቱ፤
ልቤን ባውታር፤ ቃኘው በቅኝቱ፤
በጸባኦት በእግዜር ሰማእቱ።
ስንኩል ሀሳብ፤ ከመንፈስ ተሰቃቅሎ፤
ከህማማት ማዕልት ተንከባሎ፤
እንዳይወድቅ ምሽት ተሰናክሎ፤
ሲደረደር ያቆም አደላድሎ።
የሀገሬ ቅኝት በበገናው፤
እንዴት ያምራል፤ ጎበዝ ከነዜማው፤
አስር አውታር ባንዱ ተሰባጥረው፤
ማዕዘናቱም ቁርጥ ሀገሬን ነው።
ከአጽናፍ አጽናፍ ድሮ ዝንተዓለም፤
ሙዚቃ ለነብስ፤ ተብላ ሳትቀመም፤
ይህ በገና ያኔም፤ ነበር ሲያዜም፤
ከምድር ሆኖ ድጓ ለአርያም።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም