«የእብድ ውሻ በሽታ መቶ በመቶ ገዳይ ነው» – ተመራማሪና የምርምር አማካሪ አሰፋ ደሬሳ (ዶ/ር)

የእብድ ውሻ በሽታ በቫይረስ አማካኝነት በበሽታው ከተለከፈ እንስሳ ወደ ሌላ ጤነኛ እንስሳ ወይም ወደ ሰው በንክሻ የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን ውሻን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ደመ ሞቃት እና አጥቢ የሆኑ እንስሳት እንዲሁም ሰዎችን የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ ነገር ግን በሽታው በአብዛኛው በውሾች ላይ ስለሚታይና ሰዎችም የሚያስተውሉት ይሄንኑ ስለሆነ የእብድ ውሻ በሽታ የሚል ስያሜ አሰጥቶታል፡፡

እ.አ.አ ከ2018 እስከ 2022 የተሰራ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በዓመት ከ37 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው የሚጠቁ ሲሆን ሁለት መቶ 97 ሰዎች በበሽታው ምክንያት እንደሚሞቱ ያሳያል።

በሀገራችን በሽታውን ሊያስተላልፉ ከሚችሉ እንስሳት ውሻ በዋናነት በሽታውን የሚያስተላልፍ እንስሳ መሆኑ በተለያዩ ጊዚያት በተሰሩ ጥናቶች ተመላክቷል፡፡

በአብዛኛው በሀገሪቱ ከተሞች ከቤታችን ወጣ ስንል ባለቤት አልባ የሆኑ በርካታ ውሾች በየመንገዱ ማየት የተለመደ ነው፡፡ እነዚህ ውሾች ኃላፊነት ወስዶ ቫይረሱን ለመከላከል የሚሰጠውን ክትባት እንዲከተቡ የሚያደርግ እና ንጽህናቸውን የሚጠብቅ ባለቤት ስለሌላቸው ለቫይረሱ የተጋለጡ ናቸው፡፡

እንደ ሀገር በሽታውን በተመለከት ለማኅበረሰቡ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ የውሻ ንክሻ ሲያጋጥም ወደ ህክምና ተቋም ሄዶ ከመታየት ይልቅ ንቆ የመተው ወይም ባሕላዊ መድኃኒቶች የመጠቀም ሁኔታ ይታያል፡፡

በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል ካለው የመረጃ እጥረት አንጻር የግንዛቤ እጥረቱ የሚሰፋ ይመስላል፡፡ በገጠር አካባቢ አብዛኛው ማህበረሰብ በግብርና ሥራ የሚተዳደር እንደመሆኑ ከውሻ ውጭ ከተለያዩ በሽታውን ሊያስተላልፉ ከሚችሉ እንስሳት ጋር የሚኖርበት ሁኔታ ስላለ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡

በእብድ ውሻ ንክሻ በሽታ ዙሪያ በሽታው ከምን እንደሚመጣ፣ በሽታውን ለመከላከል በሚያስችሉ መፍትሔ ሃሳቦች በተመለከተ እና ሌሎች ከበሽታው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ተመራማሪና የምርምር አማካሪ ከሆኑት አሰፋ ደሬሳ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የእብድ ውሻ በሽታ የሚመጣው ከምንድነው ?

ዶክተር አሰፋ፡- ውሻን የሚያሳብደው በሽታ በእንግሊዝኛ(ጥራውሬሪስ) ተብሎ ይጠራል፡፡ በአማርኛ የእብድ ውሻ በሽታ ነው የምንለው፡፡ በሽታው የሚመጣው ከቫይረስ ሲሆን (አር.ኤን.ኤ ቫይረስ) ይባላል፡፡ ቫይረሱ ውሻን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ደመ ሞቃት የሆኑ ወይም የጀርባ አጥንት ያላቸውን እንስሳት ሁሉ የሚያጠቃ ነው፡፡

በእኛ ሀገር ግን የተለመደው የውሻ እብደት በሽታ ተብሎ ነው፡፡ ምክንያቱም በሽታው ከመቶ 90 እጅ በአብዛኛው ውሾች ላይ የሚከሰት ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ማኅበረሰቡ ሁሌ ውሻ አብዶ ሲቅበዘበዝ ስለሚያይ ይሄ የውሻ እብደት ነው በሚል በተለምዶ ስያሜ አውጥቶለታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሽታው ምን ዓይነት ጉዳት ያስከትላል?

ዶክተር አሰፋ፡– የእብድ ውሻ በሽታ መቶ በመቶ ገዳይ ነው፡፡ በዚህ በሽታ የተያዘ ሰው ድኗል የሚል ሪፖርት እስካሁን ዓለም ላይ የለም። ምናልባት አንዳንድ ጥናቶች ላይ እንደሚታየው፤ በጣም ጥንቃቄ የሚደረግበት አያያዝ እና እንክብካቤ ተደርጎ እድሜውን ማራዘም የሚቻል ይሆናል እንጂ፤ በዚህ በሽታ ተይዞ የዳነ ሰው የለም፡፡

በሽታው በጣም አደገኛ፣ ገዳይ እና አስፈሪ ነው፡፡ ለእንስሳትም ሆነ ለሰው ምንም ዓይነት ልዩነት ሳያደርግ እኩል ገዳይ የሆነ በሽታ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ጥሩ ነገር ይህን በሽታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል መሳሪያ ክትባት አለ፡፡

ችግሩ ክትባቱን እንደሚፈለገው መጠን የአለማግኘት ችግር አለ፡፡ ለበሽታው ሁለት ዓይነት ክትባት ነው ያለው፡፡ በሀገር ውስጥ የሚመረት እና ከውጭ ሀገራት የሚገባ፡፡ ከውጭ ሀገራት የሚገባው ትንሽ ምቾት ስላለው ብዙ ሰው በስፋት እሱን ነው የሚፈልገው፡፡ ነገር ግን እሱ ደግሞ ዋጋው የሚወደድበት ሁኔታ ስላለ በሚፈለገው ደረጃ ለማግኘት ያስቸግራል፡፡

ይህ በሽታ የእብድ ውሻ በሽታ የተባለበት ምክንያት በሽታውን በአብዛኛው የሚያሰራጩት ውሾች ስለሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በውሾች ላይ ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡

እንደ ሀገር ጤናን የሚያስተባብር ኮሚቴ አለ፡፡ ይህ ኮሚቴ ጤና ሚኒስቴርን፣ ግብርና ሚኒስቴርን እና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣንን በማስተባበር፤ በሽታውን በዋናነት በሚያሰራጩት ላይ የቁጥጥር ሥራ ሊሰራ ይገባል፡፡

በሽታው ዱር እንስሳት እና ውሾች ላይ በስፋት የሚገኝ ከሆነ ቁጥጥሩ በሽታውን በዋናነት በሚያስተላለፉት ላይ ነው መሆን ያለበት፡፡ በኢትዮጵያ በውሻ ላይ ቁጥጥር ቢደረግ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣም ይቀንሳል፡፡

አሁን ላይ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓለም አምስት ሺህ ሰዎች በእብድ ውሻ በሽታ ይሞታሉ። ከዛ ውስጥ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ከሰሃራ በታች ባሉት ሀገራት ላይ ነው፡፡

በእኛ ሀገር በተሰራ ጥናት ደግሞ ከ100 ሺህ ሰው ከአንድ እስከ ሁለት ሰው በየዓመቱ በበሽታው አማካኝነት ይሞታል፡፡ ስለዚህ ይህ በ120 ሚሊዮን ሕዝብ ቢወሰድ ብዙ ሰው ይሞታል ማለት ነው፡፡

ይህን ያህል ሰው ይሞታል የሚል መረጃ ባለበት እና 90 በመቶ በሽታውን የሚያስተላልፉት ውሾች እንደመሆናቸው በውሻ ላይ ቁጥጥር ቢደረግ፤ የሚሞተው ሰው ቁጥር ይቀንሳል፤ የክትባት ፍላጎት መጠንም እየቀነሰ ይመጣል፡፡

ውሻ የመኖር መብት አለው፡፡ ነገር ግን የውሻ ባለቤት ውሻን የሚያረባ ሰው በሕግ ማዕቀፍ መመራት አለበት፡፡ ውሻ ያለው ግለሰብ ንጽህናውን በመጠበቅ፤ የሚበላውን ምግብ በሥርዓት በማቅረብ እና መጠለያ እንዲኖረው በማድረግ በእራሱ ግቢ ውስጥ እንዲዝናና ማድረግ ይቻላል፡፡

ምክንያቱም ውሻ በጣም ለሰው ልጅ ቀረቤታ ያለው እና እንደ ቤተሰብ የሚታይ እንስሳ ስለሆነ በዚህ ልክ ከውሻ ጋር አብሮ መኖር ይቻላል። ነገር ግን አሁን በእኛ ሀገር የሚስተዋለው ነገር ውሻ በየቦታው ሜዳ ላይ ነው የሚታየው፡፡ ይሄ በሕግ ማዕቀፍ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፤ ውሾች በየዓመቱ መከተብ አለባቸው፡፡

አንድ ውሻ ከተወለደ በሶስት ወር የእድሜ ክልል ክትባት መውሰድ ይኖርበታል፡፡ በየዓመቱ ደግሞ የማጠናከሪያ ክትባት ይወስዳል፡፡ በዚህ ልክ እየታየ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡ ይህን ተከታትሎ የማያደርግ የውሻ ባለቤት በሕግ አግባብ መጠየቅ አለበት፡፡ አሁን እዚህ ላይ ነው ክፍተቱ የሚታየው፡፡ ይሄ ወደ ሥራ ከገባ እና በየከተማው እንደዚህ ዓይነት ቁጥጥር ካለ እ.አ.አ በ2030 የተቀመጠውን ሰዎችን ከእብድ ውሻ በሽታ የመታደግ ጥረት ግብን ማሳካት ይቻላል፡፡

ግቡን ለማሳካት ትልቅ ማነቆ የሆነ ውሻን አለመቆጣጠር ነው፡፡ ይህን ለመቆጣጠር የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተቸገርነው ከሆቴሎች እና ከተለያዩ ተቋማት በሚደፉ ተረፈ ምግቦች ነው። በስፋት ባለቤት አልባ ውሾች የሚራቡት በእነዚህ አካባቢዎች ነው፡፡ ምግብ ከሌለ ሊራቡ አይችሉም፡፡ እንደ ሀገር ተረፈ ምግብ ለውሻ ተብሎ ነው የሚጣለው፡፡

እንደዚህ ዓይነት ልማዳዊ አሰራር ሊቀየር ይገባል፡፡ ውሻም እንደማንኛውም በጀት ኖሮት የሚመግበው ቤተሰብ ነው የሚፈልገው፡፡ እዚህ ሀገር የሕግ አሰራር ስላልተዘረጋ፤ ሰው በልማድ ነው ውሻን የሚይዘው፡፡ በልማዳዊ አሰራር ይህን በሽታ ለመቆጣጠር በጣም ያዳግታል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ የሁሉም ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ተቀናጅተው የሚሰሩት ሥራ ነው፡፡ የሚሞተው ሰው እንደመሆኑ ጤና ሚኒስቴር ይመለከተዋል፤ የውሻውን ጤንነት የሚከታተለው ግብርና ሚኒስቴር ነው፤ የአ.አ ከተማ አስተዳደር፤ የእንስሳት ጤና ዘርፍ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ ዘርፎች ይመለከታቸዋል፡፡

ስለዚህ የእነዚህ ሴክተሮች አመራር አንድ ላይ ተረባርቦ የውሻ ቁጥጥር ካደረገ፤ በ2030 አንድም ሰው በእብድ ውሻ ተነክሶ መሞት የለበትም የሚለውን መርህ ማሳካት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- 90 በመቶ በሽታውን የሚያስተላልፈው ውሻ መሆኑን ገልጸውልናል፤ ከሌሎች እንስሳት በተለየ መልኩ ውሻ ለዚህ ቫይረስ ተጋላጭ የሆነው ለምንድነው?

ዶክተር አሰፋ፡- ውሻ አመጣጡ ከዱር እንስሳት ቢሆንም ተላምዶ ከሰዎች ጋር የሚኖር እንስሳ ነው፡፡ ከሌሎች እንስሳት እና ከሰዎች ጋር ያለውም ቀረቤታ ትልቅ ነው፡፡

ሥጋ በሊታ እንደመሆኑ በተለያየ ቦታ ከተለያዩ እንስሳት ጋር ያለው ግንኙነቱ የበዛ ነው። የበሽታው መራቢያ መንገድም የውሻም ሆነ የሌሎች እንስሳት አንድ ነው፡፡ የበሽታው ቫይረስ የሚራባው አንጎል ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው እግሩ ላይ ቢነከስ በሽታው ቀስ እያለ ነው ወደ ነርቭ ውስጥ የሚገባውና አንጎሉን የሚያጠቃው፡፡

ግን የውሻ የመራባት መጠን ሲታይ አንድ እናት ውሻ እስከ ዘጠኝ ነው የምትወልደው። በኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ ማህበረሰቡ ውሻን የሚያሳድገው ወንድ ወንዱን ነው፡፡ ዘጠኝ ከተወለዱት ሁለቱ ብቻ ቢወሰድ ሰባቱ ይጣላሉ። እነዚህ የተጣሉ ውሾች ከሌሎች ውሾች ጋር ሲገናኙ አንድ በበሽታው የተያዘ ካለ በመነካከስ እና በሌሎች መንገዶች ሊተላለፍ ይችላል፡፡ በእነዚህ ምክንያት የውሾች በሽታውን የማሰራጨት መጠን ጎልቶ ሊታይ ችሏል፡፡

በስፋት ሰዎችም በበሽታው ሊጎዳ የቻለው፤ ከሌሎች እንስሳቶች ይልቅ ለውሻ ያለው ቀረቤታ ከፍ ያለ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ እስካሁን ባደረግነው ጥናት ስርጭቱ ውሻ ላይ ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡

በተጠቀሱት ምክንያት ነው እንጂ ቫይረሱ የተለየ ውሻን የወደደበት ምክንያት የለም። ቫይረሱየሚባዛበትም መንገድ አንድ ዓይነት ነው፡፡ ሆኖም ግን ሊሰመርበት የሚገባው የውሻ አያያዛችን ነው ተጋላጭነታችንን ያሰፋው፡፡ ሌላ ሀገር የሌሊት ወፍ ነው በሽታውን በማሰራጨት የሚታወቀው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ላይ ለምሳሌ (አንቲሎፒ) የሚባል የድኩላ ዘር ነው በሽታውን የሚያስተላልፈው፡፡

በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ግን ውሻ የሚኖረው በዘልማድ ነው፣ የሚሰጠውም ምግብ ተረፈ ምርት ነው፡፡ አያያዛችን ውሻ ላይ በሽታ እንዲበዛ አድርጓል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከውሻ ውጭ በሽታውን የሚያስተላልፍ እንስሳ አለ?

ዶክተር አሰፋ፡- ከተሰራው ጥናት አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛ የበሽታው አስተላላፊ ውሻ ነው፡፡ ሁለተኛ ድመት ናት፡፡ እነዚህ እንስሳት የቤት እንስሳት ስለሆኑ እና ከሰው ጋር ቅርበት ስላላቸው ያስተላልፋሉ እንጂ፤ ቀበሮ፣ አንበሳ፣ ነብር እና ሌሎችም ደመ ሞቃት የሚባሉ እንስሳት የእብድ ውሻ በሽታ አስተላላፊዎች ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አንድ ሰው በበሽታው ከተያዘ መዳን እንደማይችል ገልጸዋል፤ አንዳንዴ ውሻ ነክሷቸው ሐኪም ቤት እየሄዱ ህክምና የሚወስዱ አሉ፡፡ ይሄስ ህክምና የምንድነው?

ዶክተር አሰፋ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። መዳኛው ክትባትና ክትባት ብቻ ነው፡፡ ሰው የማይድነው ካልተከተበ ብቻ ነው፡፡ ምን ማለት ነው ይሄ? እኛም ሀገር ክትባቱ አለ እናመርታለን። መርፌ አሰጣጡ ከውጭ ሀገራት ከሚገባው ክትባት ዓይነት በርከት ይላል እንጂ ነፍስ፤ ያድናል ሲያድንም አይተናል፡፡

እንደ ሌሎች በሽታዎች ቫይረሱን ሊገል የሚችል የሚዋጥ መድኃኒት የለውም እንጂ፤ አንድ ሰው በተነከሰ በ24 ሰዓት ውስጥ ቫይረሱ እንዳይራባ የሚያደርግ ክትባት ከወሰደ ቫይረሱ አይራባም፡፡

የበሽታው የመደራጃ ጊዜ አንድ ሰው ከተነከሰ ከሶስት ሳምንት እስከ አንድ ዓመት እንደሆነ ነው ሳይንሱ የሚገልጸው፡፡ በሽታውን አስቸጋሪ ያደረገው የመደራጃ ጊዜው ረጅም መሆኑ ነው። ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር በርካታ ሥራዎች ተሰርተው እኮ በሽታውን ቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡

ሌላው ደግሞ ማህበረሰቡ ለበሽታው ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰው በውሻ ሲነከስ የውሻ ቁስል ነው ተብሎ ዝም ብሎ ይተወዋል፡፡ ስለዚህ በባሕላዊ መድኃኒት ወይም በሌሎች መንገዶች ለመዳን ይሞክራል፡፡

ዘግይቶ ወደ ህክምና ሲመጣ ተጎድቶ እናያለን። መሆን ያለበት በ24 ሰዓት ውስጥ በራሱም ሆነ በሌላ ውሻ የተነከሰ ሰው ሐኪም ቤት ሄዶ መናገር አለበት፡፡ ሐኪሙ አይቶ ክትባት የሚያስፈልገው ከሆነ ህክምና እንዲከታተል ያደርገዋል፡፡ ክትባት ስላለው መድኃኒት አለው ማለት ነው፡፡ ችግር የሆነው ነገር ግን የሰው ግንዛቤ ስላላደገ ሐኪም ቤት ሄዶ ክትባቱን በአግባቡ አለመውሰዱ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አንድ ሰው በውሻ ሲነከስ የባሕል መድኃኒቶችን የመጠቀም ሁኔታ አለ፡፡ የመድኃኒቱ አስተማማኝነት ምን ያህል ነው?

ዶክተር አሰፋ፡– በሀገራችን ሰፊ የሆነ የባሕል መድኃኒት ሀብት አለ፡፡ በእውነቱ ለሌሎች በሽታዎች ፍቱን የሆኑ የባሕል መድኃኒቶች አሉን። ከእብድ ውሻ በሽታ ጋር ተያይዞ ባደረግነው ጥናት ብዙ ሞክረን ሁለት ችግሮች ገጥመውናል፡፡ አንደኛ የባሕል መድኃኒት የሚቀምሙት ትክክለኛ መረጃ ሰጥተው ወደሚሰሩበት ቦታ ገብተን እንድንፈትሽ አይፈቅዱም፡፡

ለምን እንደማያስገቡ ምክንያታቸው ሲጠየቅ መድኃኒቱ በሶስተኛ ሰው ከታየ ይረክሳ የሚል ምክንያት ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ችግር ምክንያት ያለው የባሕል መድኃኒት ፈዋሽነት በጥናት አልተረጋገጠም፡፡ ነገር ግን ጥናቱ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡

ሌላኛው ከባሕል መድኃኒት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር፤ በውሻ የተነከሰ ሰው የባሕል መድኃኒቱን ከወሰደ በኋላ መድኃኒቱ ይረክሳል ተብሎ ስለሚታሰብ፤ መድኃኒቱን የወሰደው ግለሰብ ለ40 ቀን ያህል ወንዝ እንዳይሻገር ይደረጋል፡፡

በዚህ ሁኔታ በውሻ የተነከሰው ሰው ክትባት ለመውሰድ ወደ ህክምና ተቋማት አይመጣም። አንድ ሰው በሽታው ከተደራጀበት በኋላ በዛ ቢባል በሕይወት ሊቆይ የሚችለው ከ55 እስከ 60 ቀን ነው፡፡

አንድ ሰው 40 ቀን ቆይቶ ለህክምና ከመጣ ለሞት ከተቃረበ በኋላ ነው፡፡ የሚሰጠው ክትባት በሽታው ምልክት ካሳየ በኋላ ቢሰጥ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡

ክትባቱ የሚያገለግለው ምንም ዓይነት ምልክት ከመታየቱ አስቀድሞ ነው፡፡ በውሻ መነከስ የሚያጋጥም ነገር ነው፡፡ ከተነከሱ በኋላ ቫይረሱ ተደራጅቶ የማበድ ምልክት ከታየ በኋላ ክትባቱ ስለማይሰራ ቀደም ብሎ መምጣት መፍትሔ ያለው ነገር ነው፡፡

በህብረተሰቡ ዘንድ በግንዛቤነት መያዝ ያለበት፤ በሽታው ምልክት ካሳየ በኋላ ለምሳሌ ለሀጭ የማዝረብረብ፤ ብዙ ማውራት፣ ለመዋጥ መቸገር ፣ ውሃ መጥላት፣ የማቃጠል እና ሌሎች ምልክቶች የሚታዩበት ደረጃ ከደረሰ ክትባቱ አይሰራም፡፡ ክትባቱ የሚሰራው ወዲያው በውሻ እንደተነከሱ ከተወሰድ መሆኑ ግንዛቤው ብዙም ማህበረሰቡ ጋር የለም፡፡ ይህንን በመገናኛ ብዙሃን እና በተለያዩ መንገዶች ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሽታው የሚተላለ ፈው በንክሻ ብቻ ነው፡፡ ወይስ ሌሎች መተላለፊያ መንገዶች አሉ?

ዶክተር አሰፋ፡- ምንድነው መሰለሽ፤ በአብዛኛው በጥርስ መነከስ ሲያጋጥም፤ ዞሮ ዞሮ በሽታው የሚገባው በምራቅ አማካኝነት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ሲነከስ ውሻው ታማሚ ከሆነ ቫይረሱ በምራቅ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ጭንቅላት ውስጥ ተራብቶ ወደታች ሲመለስ እጢዎችን ነው የሚበክለው፡፡ የሚወጣው ፈሳሽ በሙሉ የቫይረሱ ምንጭ ነው፡፡

ጥናቶች እንደሚሉት የቫይረሱ ምልክት አንዳንዴ ያስተፋል ይላል፡፡ ለምሳሌ እኔ በሽታው ኖሮብኝ በየቦታው ብተፋ በምራቅ አማካኝነት ይተላለፋል፡፡ በንክሻ ብቻ አይደለም ማለት ነው። አንዳንድ ጥናቶች ደግሞ እንደሚሉ በጭረት አማካኝነት እንደሚተላለፍ ያስረዳሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በውሻ ሲቧጨሩ ‹‹አልነከሰኝም ዝም ብሎ ጫር ያደረገኝ ›› ብለው ችላ የሚሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ሆኖም በጭረት ብቻ በሽታው ሊተላለፍ ይችላል፡፡

ጭረቱ በሚፈጠርበት ወቅት ቆዳችን ስለሚቆጣ ቫይረሱ ሊገባ ይችላል፡፡ በርግጥ ቆዳ ሲቆረጥ ነው ቫይረሱ የሚገባው፡፡ እኛ ግን እንደ ባለሙያ እንደተቆረጠ ነው የምናየው፡፡ ስለዚህ ይሄ ችግር አለው ይሄ ችግር የለውም ብሎ ምላሽ የሚሰጠው ሐኪም ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሽታው በላብ አማካኝነት ይተላለፋል?

ዶክተር አሰፋ፡- እንግዲህ እስካሁን ባለን መረጃ፤ በላብ ይተላለፋል፣ በመጨባበጥ እና በመሳሳም ይተላለፋል የሚሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ነገር ግን አይተላለፍም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ይህን በሽታ ለመቆጣ ጠር ከማን ምን ይጠበቃል?

ዶክተር አሰፋ፡– አሁን እኔ እየሰራሁ ያለሁበት ተቋም ለረጅም ዘመን ክትባት ሲያመርት ኖሯል፡፡ ለውሻም ለሌሎች እንስሳትም፡፡ አሁን ላይ ቢሾፍቱ ብሔራዊ እንስሳት ተቋም በስፋት አምርቶ እያሰራጨ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ኢንስትቲዩት በውሻ ለተነከሱ ሰዎች የሚሆን ክትባት ሲያመርት ቆይቷል፡፡ አሁን የማምረት ሥራ ወደ አርምን ሃንሰን ምርምር ኢንስትቲዩት ተላልፏል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለቱ ተቋማት ክትባት በማምረት ኃላፊነት አለባቸው ማለት ነው፡፡

በሌላ ዘርፍ ደግሞ በግብርና እና በከተማ አስተዳደር የእንስሳት ጤና የሚከታተሉ ዘርፎች አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ የውሻ ባለቤቶች በአግባብ ውሾቻቸውን እንዲያስከትቡ ክትትል እና ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል፡፡

ተከታትሎ ውሻውን የማያስከትብ አካል በሕግ አግባብ እንዲጠየቅ ማድረግ ይኖርበታል። ከባለሙያውም ሆነ ይህንን ዘርፍ የሚመራው ተቋም በዚህ ልክ ክትትል ሊያደርግ ይገባል፡፡ ሆኖም በዚህ ረገድ ክፍተት አለ፡፡

በሀገር ደረጃ ደግሞ የውሻ በሽታን የሚከታተል አንድ የጤና ጽሕፈት ቤት አለን። ጽሕፈት ቤቱ ባደረገው ጥናት በሽታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ሊመጣ የቻለው በውሾ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ አሁን ስትራቴጂውን ለመከለስ ታስቧል፡፡ ውሾችን ለመቆጣጠር በሁሉም ሴክተር ምን መደረግ አለበት? የሚል የባለሙያ ምክክር በሁሉም ደረጃ ባሉ መዋቅሮች እየተደረገ ነው፡፡ በቀጣይ በሚሰራው ሥራ በበሽታው አንድም ሰው እንዳይሞት የተቀመጠውን ግብ ማሳካት ይቻላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

በሽታውን በማስቀረት ረገድ የመጀመሪያው ባለድርሻ አካል የውሻ ባለቤት ነው፡፡ የውሻ ባለቤቶች ቢተባበሩን እና ውሾቻቸውን በአግባቡ ቢይዙ በሽታውን ከ50 በመቶ በላይ እንዳይዛመት ማድረግ ይቻላል፡፡

ከዛ ውጭ የሚሆን ከሆነ ደግሞ የሕግ ማዕቀፍ መኖር አለበት፡፡ እስካሁን ትልቁ አድምተን ያልሰራነው፤ መሬት አልወርድ ያለው እሱ ነው። አንዳንዴ አንዳንድ በሽታዎች ክትባት ወይም መድኃኒት ስለሌላቸው ነው ሰው የሚሞተው። ይሄ እኮ በእጃችን ላይ ያለ ነገር ሆኖ በትክክል መሥራት ባለመቻላችን ችግሩ እየከፋ ሄዷል፡፡

ለሁሉም ባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች የተሰጣቸው ኃላፊነት አለ፡፡ እሱን አንድ ላይ አቀናጅቶ የሚሰራ መሥሪያ ቤት ነበር እስካሁን ክፍተት የነበረው፡፡ አሁን ግን የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በአዋጅ ጸድቆ ተቋሙ እንዲመሰረት ተፈቅዷል፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ለውጥ ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You