እሥራኤል ሊባኖስ የሚገኙ 100 የሄዝቦላህ የሮኬት ማስወንጨፊያዎች እና ሌሎች “የሽብር ቦታዎች” እንዲሁም የመሣሪያ ማከማቻዎችን መምታቷን አስታወቀች።
የእሥራኤል መከላከያ ኃይል እንዳለው ወደ እሥራኤል ለመላክ ዝግጅት ላይ የነበሩ ማስወንጨፊያዎች ናቸው የወደሙት። እስካሁን በጥቃቱ የሞተ ሰው ስለመኖሩ አልተዘገበም።
በመንግሥት የሚተዳደረው የሊባኖሱ ናሽናል ኒውስ ኤጀንሲ ሐሙስ አመሻሹን እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ 52 የአየር ጥቃቶች ማድረጓን አስታውቆ ሊባኖስ ደግሞ ሰሜን እሥራኤል የሚገኙ ወታደራዊ ቦታዎችን መትታለች ብሏል።
የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ በያዝነው ሳምንት በሀገሪቱ በተለያዩ ሥፍራዎች የደረሱ ፍንዳታዎችን ተከትሎ ጥቃቶቹ “ቀይ መስመር ጥሰዋል” በማለት እሥራኤል ጦርነት ማወጇን ተናግረዋል።
እሥራኤል ከሰሞኑ በጥቃቅን የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ሊባኖስ ውስጥ ለደረሱት ጥቃቶች ኃላፊነት አልወሰደችም።
ማክሰኞ እና ረቡዕ በደረሱት ጥቃቶች ‘ፔጀሮች’ እና ‘ዎኪ ቶኪዎች’ በተመሳሳይ ሰዓት ፈንድተው 37 ሰዎች ሲሞቱ 3 ሺህ ገደማ ደግሞ መቁሰላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
የእሥራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ዮዋቭ ጋላንት ሀገራቸው በተለይ በሰሜኑ ክፍል በማተኮር “አዲስ የጦርነት ሂደት” መጀመሯን ተናግረዋል።
የሐማስ ታጣቂዎች በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7፤ 2023 በእሥራኤል ላይ ጥቃት ባደረሱ በማግስቱ ነው ሄዝቦላህ እና እሥራኤል ድንበር አካባቢ የተኩስ ልውውጥ ያደረጉት።
ከዚህ በኋላ በተደረጉ የተለያዩ የተኩስ ልውውጦች በመቶዎች የሚቆጠሩ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ሲገደሉ ድንበር አካባቢ የሚገኙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያንና እሥራኤላውያን መኖሪያቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል።
ሄዝቦላህ ጥቃቱን የሚፈፅመው ለፍል ስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ያለውን አጋርነት ለማሳየት እንደሆነ ይገልፃል። በእሥራኤል፣ ዩኬ እና ሌሎች ሀገራት ሽብርተኛ ተብለው የተፈረጁት ሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች በኢራን ይደገፋሉ።
ሐሙስ አመሻሹን መግለጫ ያወጣው የእሥራኤል መከላከያ ኃይል የጦር አውሮፕላኖቹ “100 ገደማ ማስወንጨፊያዎችን እና ሌሎች የሽብር መሠረተ ልማቶችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን አውድሟል” ይላል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እና ኒው ዮርክ ታይምስ የሊባኖስ ፀጥታ ኃይሎችን ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት እስራኤል ሐሙስ ዕለት የፈፀመችው ጥቃት ከጋዛው ጦርነት በኋላ እጅግ ከባዱ ነው።
ሐሙስ ንጋት ደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች ሁለት ፀረ-ታንክ ሚሳዔ ሎችን እና ድሮኖችን ወደ ድንበር ተኩሰዋል።
የእስራል መከላከያ ኃይል ሁለት እሥራኤላውያን መገደላቸውን እንዲሁም አንድ ወታደር ክፉኛ መቁሰሉን አስታውቋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም