ቂመኛው

ትዳር ሀ ተብሎ የተጀመረ ሰሞን ሙቀቱ የኤርታሌን ወላፈን ያስንቃል። የሕይወቴ ሕይወት አንቺ በመሆንሽ፣ ብለው የጀመሩት ትዳር ቀናት በሄዱ ቁጥር ሲቀዘቅዝ ማየት በአብዛኛው የተለመደ ነው፡፡ እንደ ቅዝቃዜው ልቆ ሙቀቱ የጠፋ ጊዜ ‘ዓይንሽን ላፈር’፣ ‘ዓይንህን ላፈር’ ተባብሎ መለያየት የተለመደ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። ትዳር ዓለም አቀፋዊ እውነት እንደሆነ ሁሉ፣ ፍችም እንዲሁ አይቀሬ እጣ ይመስላል።

የሶስት ጉልቻው መሠረት የተናጋበት ትዳር፣ ቋንቋቸው የተደበላለቀባቸው ጥንዶች፣ ጉንጫቸውን ልሳምሽ ሳይሆን ለንክሻ የሚፈላለጉ ባልና ሚስቶች እዚህም እዚያም መኖራቸው ደግሞ ምነው ይሄን ያህል ሳያሰኝ አይቀርም።

ኢትዮጵያ ለትዳር ትልቅ ስፍራ ከሚሰጡ ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በእልልታ የተጀመሩ ትዳሮች በፍቺ የመደመደም ሁኔታቸው የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል።

የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ በ2014 በጀት ዓመት ከ14 ሺህ በላይ ጋብቻ፣አንድ ሺህ 623 የፍቺ ምዝገባዎችን ማከናወኑን አሳውቆ ነበር። ይህንን ቁጥር በ2010 ዓ.ም ብናየው ደግሞ በ2010 አንድ ሺ 923 የሚሆኑ ጥንዶች ፍቺ መፈጸማቸውን የአዲስ አበባ ወሰኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ መረጃ ያሳያል።

ታዲያ የዚህ በአሳሳቢ ደረጃ ቁጥሩ እየሻቀበ ነው የተባለለት ፍቺ መንሰኤ የሌሎች ጣልቃ ገብነት መሆኑን ይህ መረጃ ያመለክታል። ስለ ፊቺ አሳሳቢነት ያነሳነው በዛሬው ተነጋሪው ዶሴ ዓምዳችን በትዳሬ ጣልቃ ገብታ ከባለቤቴ ጋር አለያይታኛለች በሚል ቂም በቀል የተፈፀመ ወንጀል ታሪክን ልናካፍላችሁ ስለሆነ ነው። መልካም ቆይታ።

ጥንዶቹ

“ሳየው ልቤ ደነገጠ” “ሳያት ልቤ ትርክክ አለብኝ ” ተባብለው ነበር የተጋቡት። ፍቅራቸው ንፋስ የሚገባው አይመሰልም ነበር። “ፍቅርና ገንፎ ትኩስ ትኩሱን ነው” ያሉት ጥንዶች የፍቅራቸው ግለት ሳይበርድ ወደ ቁም ነገር አሸጋግረው ሶሰት ጉልቻ መሰረቱ። የቁልምጫ አጠራራቸው እንኳን እርስ በእርሳቸው የሰሚያቸውንም ልብ ያቀልጣሉ።

እንዲህ እንዲህ እያሉ የጫጉላ ጊዜያቸው አልቆ ሁሉም ወደ እንጀራ ፍለጋው ሲሯሯጥ ነገር ቀስ እያለ ብቅ ማለት ጀመረ። በፍቅር ተሸሽገው የቆዩ አመሎች ከየጎሪያቸው ብቅ አሉ። በውሀ ቀጠነ ፀብ ነገሰ። ከፀብ በኋላ እርቅ፤ እንደገና ከእርቅ በኋላ ፀብ እየደጋገመ እየደጋገመ የቤታቸውን ደጃፍ አንኳኳ።

በዚህ መካከል ብርቱካን አበራ የተባለች የሙሽሪት ጓደኛ ቤታቸው እየመጣች ለማስማመት ሙከራ ታደርግ ነበር። እንዲታረቁ እየመከረች ካስማማች በኋላ ጓደኛዋን ለብቻዋ እስቀምጣ ትመክራት ነበር። ባል ሚስቱን ለብቻዋ ምን እንደምትነግራት ባለመረዳቱ ሁልጊዜ ይናደዳል።

አልፎ ተርፎ እቤታቸው እንዳትመጣ እስከ መከልከል ደረስ። ቀናት ቀናትን እየተኩ በመጡ ቁጥር የፍቅራቸው ሁኔታ መሻሻልን ከማሳየት ይልቅ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ መጣ። ቋንቋቸው ተደበላልቆ ቢነጋገሩም የማይግባቡበት ደረጃ ደረሱ። ተነጋግረው ችግሮቻቸውን ለመፍታት ቢሞክሩም በእልኸኝነትና በቁጣ ሰላማዊ ንግግር ሳያደርጉ ትትውት ይነሱ ነበር።

አቶ ባል

አገኘሁ ገድይሁን አጋሉ ይባላል። እንደዛ እሷን ካጣሁ ሞቴ ዛሬ ይሁን ብሎ ካገባት ሴት ጋር ለምን መግባባት እንዳቃተው እንቆቅልሽ ሆኖበታል። ውስጡን ሲያዳምጥ አሁንም ይወዳታል። ደግሞ በአንድ በኩል ነገረ ሥራዋ ሁሉ አልጥም እያለው ይቸገራል። የሚወዳት ሚስቱን በፍቅር አቀፎ አብሯት ሊያመሽ አስቦ ቤቱ ገብቶ በኩርፊያ ጀርባ የመሰጣታቸው ነገር አልዋጥልህ ብሎታል።

ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሰማይ ሰማያትን አልፎ በገነት በር ላይ ወክ ያደረገ እስኪመስለው ድረስ በደስታ የተንሳፈፈበትን ፍቅር የማሳለፋቸውን ነገር ትዝ እያለው ምን ነከቶን ነው እያለ ብቻውን ይብሰከሰካል። ለደግ ያለው ሁሉ ለክፉ እየሆነበት፤ እሷን ያስደስታል ብሎ የሞከረው ነገር በሙሉ እሷን አስከፍቶ ፀብ የሚፈጠር ጉዳይ የሆነበትን ውትብትብ ለመፈታተ ቢሞክር ውሉ አልጨበጥ እያለው አስቸግሮታል።

ከብዙ ከራስ ጋር ምክክር በኋላ የጓደኛዋ ብርቱካን ሴራ መሆኑን ድምዳሜ ላይ ይደርሳል። በፍቅራቸው መካከል እየገባች የምትበጠብጣቸው ብርቱካን እንደሆነች በማመን ከባለቤቷ እንደትርቅ ያደርጋታል። ብርቱካንም ካልተፈለኩማ በማለት እግሯን ትሰብስባለች። ይህ ጉዳይ ግን ሙሽሪትን ያስደሰታት ጉዳይ አልነበረም።

ብርቱካን አበራ

የሙሽሪት ጓደኛ የሆነችው ብርቱካን ጓደኛዋ የምትወደውን ሰው አግኝታ ትዳር መያዟ እጅግ በጣም ካስደሰታቸው የሙሽሪት ጓደኞች መካከል አንዷ ናት። ጓደኛዋ ቁም ነገር አስባ ሶስት ጉልቻ ስትመሰረት ከደገፉት መካከል ግንባር ቀደሟም እሷው ነበረች። በሞቀው የሙሽርነት ጊዜ እንደ ጓደኛ አንደኛ ሚዜ ሆና ቤቷን ሲቀና የሙሽሪት ደጋፊ ረዳት ሆናላት ነበር።

በግጭታቸውም ቋሚ ተጠሪ በመሆን ለማስማማት የበኩሉን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። ተቆጥታ ካስማማቻቸው በኋላ ጓደኛዋ በትእግስት ነገሮችን ማለፍ ለትዳር ዋና ቁልፍ ነገር መሆኑን ለብቻዋ ተመክራታለች። ነጋ ጠባ ፀብና ጭቅጭቅ ፍቅር የሚያቀዘቀዝና ቤት የሚያፈርስ ጉዳይ መሆኑን እየነገረች ወዳና ፈቅዳ የገባችበትን ትዳር እንድትጠብቅ ጓደኛዋን ዘወትር ትመክራት ጀመር።

ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ሆነና ነገሩ ብርቱካን ለበጎ ብላ ያስበችው ነገር በሙሉ አባወራውን እያስቀየመው፤ ከጓደኛዋ ቤት ያለ ፍላጎት እንድትቀር አደረጋት።

ሙሽሪትም ወትሮም ፀብና ጭቅጭቅ አሰላችቷት ትዳሯን ልትተው ጫፍ ደርሳ በነበረበት ወቅት የጓደኛዋ ቤት አለመምጣት ያናድዳታል። እሷ እዚህ ቤት የማትመጣ ከሆነ እኔ እወጣለሁ ብላ ጓዟን ሸክፋ ትዳሯን ትታ ከቤት ትወጣለች።

ይህ ጉዳይ የከነከነው ባል ቤቴን ትዳሬን እንዳጣ ምክንያት የሆነችው ጓደኛዋ ብርቱካን ናት በማለት ቂም ይዞ ለማጥቃተ ይፈልጋት ጀመር።

አሰቃቂው ማታ

በ8/10/2015 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡30 ነበር። በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ጎሮ አፍሪካ ክሊኒክ በመባል በሚጠራው አካባቢ አድብቶ እየተጠባበቃት ነበር። ከባለቤቴ ጋር አለያይታኛለች በሚል ቂም ቋጥሮ ብርቱካን ከርቀት ወደ ቤትዋ አቅጣጫ ስትሄድ ተመለከታት። በአካባቢው መብራት አለመኖሩንና ጭር ማለቱን ወዶታል። ብርቱካን ሀገር ሰላም ብላ ቤትዋ ስትሄድ ዛፍ ስር ተደብቆ ጫፉ ስለት ያለው ፌሮ ብረት ይዞ ይጠባበቃት ጀመር።

ልክ አጠገቡ ስትደርስ ጫፉ ስለት ባለው ፌሮ ብረት የተለያየ የሰውነት አካልዋ ላይ በመውጋት ይጥላታል። መውደቋን አየቶ እንደመሸሽ ፈንታ ደጋግሞ በወደቀችበት ሕይወትዋ እስኪያልፍ ድረስ ደጋግሞ ይወጋታል። በዚህ ድርጊቱም ብርቱካን ዳግም ላትነሳ በወደቀችበት ትቀራለች።

ልክ መሞቷን ሲያረጋግጥ በወደቀችበት ጥሏት ለማምለጥ ሙከራ ለማድረግ ሲሞክር በአጋጣሚ በአካባቢው ሲያልፉ የነበሩ ሰዎች ሰውዬው በጭካኔ እያደረገ የነበረውን ተግባር በመመልከት ሰፈሩን በጩኸት ያደባልቁታል፡፡ የሰራውን ሰርቶ እግሬ አውጪኝ ሲል የነበረው ጥፋተኛ የጩኸት ድምፅ ሰምተው ሲሮጡ ከነበሩ ፖሊሶች ጋር ፊት ለፊት ይገጣጠማል።

ፖሊሶቹም የሮጠበትን ምክንያት ባያወቁም እንዳያመልጥ በማሰብ ይዘው ጩኸት ወደሰሙበት አካባቢ ይደርሳሉ። በአካባቢውም መሬት ላይ የወደቀ የሴት አስከሬን በድንጋጤ የሚጮሁ ሁለት ሰዎችን በመመልከታቸው ተጨማሪ ኃይል ይጠራሉ።

አምቡላንስ ጠርተው አስከሬኑን ካሰነሱ በኋላ የዓይን ምስክሮችንም ሆነ ወንጀለኛውን በመያዝ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ቃላቸውን ተቀበሉ።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ የዓይን እማኞችን ቃል ከተቀበለ በኋላ በሰላም ወደቤታቸው ያደርሳቸዋል፡፡ የአስክሬን ምርመራ ውጤትም እጁ እንደገባለት የተከሳሽን የእምነት ክህደት ቃል ይቀበላል። መጀመሪያ ላይ ወንጀሉን እንዳልፈፀመ ለመካድ ቢሞክርም እየቆየ ግን ምርመራው መጠናከሩን ሲረዳ “ከባለቤቴ ጋር እንድንለያይ ትመክራት ነበር” በማለት ወንጀል መፈፀሙን ያምናል።

ይህ ሰው ሆን ብሎ በቂም በቀል ተነሳስቶ የሰው ሕይወት እንዲያልፍ በማድረጉ ምክንያት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በመላክ ክስ እንዲመሰረትበት ያደርጋል።

የዓቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር

ወንጀሉ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዓቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ህ/አ 539/1/ሀ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ ቀረበበት።

የዓቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር እንደሚያመለክተው አገኘሁ ገድይሁን አጋሉ የተባለ ተከሳሽ በ8/10/2015 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡30 ሲሆን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ጎሮ አፍሪካ ክሊኒክ በመባል በሚጠራው አካባቢ ከባለቤቴ ጋር አለያይታኛለች በሚል ሟች ብርቱካን አበራ ወደ ቤትዋ ስትሄድ ዛፍ ስር ተደብቆ ጫፉ ስለት ባለው ፌሮ ብረት የተለያየ የሰውነት አካልዋ ላይ በመውጋት ሕይወትዋ እንዲያልፍ በማድረጉ ምክንያት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዓቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ህ/አ 539/1/ሀ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

                                                                                                   -ውሳኔ

በክርክሩ ሂደትም የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ሶስት የመከላከያ ምስክሮች በማቅረብ ያሰማ ቢሆንም የቀረበበትን ክስ ሊከላከል ባለመቻሉ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ባስቻለው ችሎት በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት ተከሳሽ በ19 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You