ባለፉት ዓመታት ለውጥ እንዲመጣ በመላ አገሪቱ ሕዝባዊ ንቅናቄ መፈጠሩን ተከትሎ በጎም መጥፎም ተግባራት መከሰታቸው በታሪክነት ተመዝግቦ የሚታወስ ነው።ለውጥ የሕዝብ የማያቋርጥ ፍላጎት ነውና ለበጎ ተግባር መከናወን ሲባል አንዳንድ ያልተጠበቁ አሳዛኝ ሁኔታዎች ቢከሰቱም እንኳ ልንቀበላቸው ተገድደናል።
ከለውጥ በኋላ ያሳለፍናቸው 12 ወራት በርካታ ስኬት የተመዘገበባቸው ሆነው ማለፋቸው ደግሞ ከጠፋው ይልቅ የለሙት ልቀው እናገኛቸዋለን።የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሙሉ በሙሉ ስኬታማ ነበርን ባይባልም ወደ ባሰ አዘቅት እንዳንገባ ታጋሽነትን ጨምሮ የተወሰደው ርምጃ ሊመሰገን የሚገባው ነው ፡፡
በብዙዎች መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላም ለማደፍረስና ለሕዝቦቿ መበጣበጥን የሚመኙት ያሰቡት እንዳይሳካላቸው ለማድረግ መንግሥት ያሳየው ታጋሽነት ወደር የሚገኝለት አይደለም።ለበርካታ ዓመታት ከአገራቸውና ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በስደት ይኖሩ የነበሩ ወገኖቻችን መንግሥት ባቀረበላቸው ጥሪ ወደ አገር ቤት መግባታቸው ፣ መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል አስበው በበረሀ የነበሩ ተቃዋሚዎች በተደረገው የሰላም ጥሪ ከወገኖቻቸው መቀላቀላቸው፣ በእስር ይማቅቁ የነበሩ ነፃ መውጣታቸው፣በጦርነት ይፈላለጉ የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም አስፍነው የሁለቱ አገራት ሕዝቦች በፍቅር ሲላቀሱ ማየታችን፣ የዲፕሎማሲው ሥራ ሰፍቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት ወዳጅነት አጠናክረው በልዩ ልዩ ምክንያት በየአገራቱ በእሥር ላይ የነበሩ ዜጎቻችንን አስፈትተው ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ማድረጋቸው፣ እንዲሁም አገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የውጭ ዕዳ ለማቃለል የተደረገው ግዙፍ ድጋፍ ፣የአገር መከላከያን ጨምሮ የፀጥታ ሃይሉን ለማጠናከር የተካሄደው አደረጃጀት አንኳር ከሚባሉት የሚጠቀሱ ናቸው።
ይሁን እንጂ ለመልካም ሥራ የሚተጉ እንዳሉ ሁሉ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩ አገርን የማበጣበጥ ተግባራት የሚፈፅሙ በመኖራቸው መስዋዕትነት
ቢያስከፍሉም ፤ በነቃ የሕዝብ ተሳትፎ መጥፎ ተግባራቸውን ባለመቀበል የሕዝቡን በጋራ የመኖር አንድነትና የጋራ እሴት መጠበቅ ተችሏል፡፡
መጪው ጊዜ የአገራችን ስም በበለጠ መልካምነትና በዕድገት የሚጠራበት እንዲሆን ዛሬ የምናከናውነው በጎ ተግባር መሰረት ስለሚሆን ለነገ የላቀ ዕድገታችን እያንዳንዷን የዛሬ ተግባራችንን በበጎ ሁለገብ ጥረታችን ማለምለም ይኖርብናል፡፡
ከነገ በስቲያ ለምናከብረው የፋሲካ በዓል ለመድረስ ያሳለፍናቸው በርካታ ወራቶች አልጋ በአልጋ የተጓዝንባቸው እንዳልሆኑ በመረዳት፤ችግሮች ሲያጋጥሙም በውይይት በመፍታት እስካሁን የተገኘውን ድል ወደተሻለ ደረጃ በማሳደግ የላቀ ከፍታ ላይ መድረስ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር የሚሆነው ሁላችንም ለሰላም ቅድሚያ ስንሰጥ ነው።
በተለይም ከኦሮሚያና ከደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች በመጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ 528 ሺ761 ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው መመለሳቸውን ተከትሎ እየተካሄደ ያለው የዕርቅ ጉባዔ በክፉ አሳቢዎች አነሳሽነት ግጭት ቢከሰትም በኢትዮጵያዊ ባህላችን ይቅርታ መደራረግ ተገቢ በመሆኑ ያለፈውን በማስታወስ ከመቆዘም ይልቅ መጪውን ብሩህ ጊዜ በማሰብ ተስፋችንን ማለምለም ያስፈልጋል ፡፡
በዓሉን ስናከብር ስለ ሰላም፣ ስለ አብሮ መኖር ፣ ስለ መተሳሰብ፣ ስለአንድነትና በጋራ ስለማደግ እያለምን በአገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ሰርተው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ ፣ ወጣቱ ትውልድ የትምህርት ዕድል በሰፊው አግኝቶ የዕውቀት ባለቤት እንዲሆንና አገሩን ለመረከብ ተስፋ እንዲሰንቅ፣ አርሶ አደሩ በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የምርት ባለቤት እንዲሆን፣ ባለሀብቱ በልማት ተሳትፎ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኝና የሥራ ዕድል እንዲፈጥር፣ በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡ ጤና እንዲጠበቅ ፣ የኢንዱስትሪ ልማት እንዲስፋፋ ወዘተ… ለሰላም በፅኑ መቆም ከኢትዮጵያውያን ይጠበቃል፡፡መልካም የፋሲካ በዓል እንዲሆንላችሁ እንመኛለን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም