የመውሊድ እሴቶች

ለታላቁ ነብዩ መሐመድ/ሰ.ዐ.ወ/1499ኛው የመውሊድ በዓል አከባበር እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!!

የእስልምና እምነትና የእምነቱ ተከታዮች በዓለማችን ስልጣኔና ዝማኔ ላይ ጥልቅና ደማቅ አሻራ በማሳረፍ ከ6ኛው መቶ ክፍለ_ዘመን ጀምሮ ሙስሊሞች ለ700 ዓመታት ስፔንን በበላይነት አስተዳድረዋል። ሙስሊሞቹ ስፔንን ባስተዳደሩበት ወቅት አንዱሉስ በዓለም የእውቀት ማዕከል ባሳዩት ትጋት በተለይ በ711 ታላላቅ የስልጣኔ ጮራዎችን በመፍጠር በዘመናዊ የትምህርት አሰጣጥ በተገኘው ውጤት መሠረት በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በንግድ፣ በኪነ_ ጥበብ፣ በማህበረ_ሰብዓዊ ሳይንስ፣ በሂሳብና አስትሮኖሚ፣ በታሪክና በቋንቋ፣ በባሕል ግንባታ፣ በፍልስፍና፣ በሕክምና፣ በሥነ_ሕንፃ፣ በትርጉም ሥራ፣ በዕውቀት ሽግግር አስደናቂ ትዕንግርት ታይቷል፡፡

በዚህ ወቅት አውሮፓውያንን ከጭለማው ዘመን/Dark age/ሊያወጣቸው ያንደረደራቸው የብርሃን ምንጭም ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሙስሊሞች በዚያ ጊዜ እንኳን”ነፃ ትምህርት ለሁሉም” የተሰኘ ፖሊሲ ስለነበራቸው በዘመናዊ ዕውቀት የሰለጠነ ማሕበረሰብ ራሱ ከሚከተለው እምነት ተከታዮች ባሻገር ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር መቻቻልና፣ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ አመለካከት ማዳበር ተችሏል።

ታዲያ ታላቁ ነብዩ ሙሐመድ/ሰ.ዐ.ወ/ተወልደው፣ አድገው፣ በእውነት፣ በዕውቀት፣ በእምነት ተሞልተው፣ ታላቅ የዓለማት የነብይነት ማዕረግ አግኝተው የላቀ፣ የተመረጠ፣ ያማረ የመልካም ተግባራትን ማበልፀጊያ የፍትሃዊ የመሪነት ነገራቶቻቸውን የጀመሩት ማርን፣ ምርምርን፣ ጥበብን፣ ስልጣኔን፣ ዕውቀትን በሚያስታጥቅ የንባብ ምዕራፍ ነበር፡፡ ነብዩ ሙሐመድ/ሰ.ዐ.ወ/ሂራ ዋሻ ላይ ለመጀመሪያ ቅዱስ_ቁርዓን በወረደላቸው ጊዜ”ኢቅራዕ”የሚል መልዕክት/ትዕዛዝ/ነበር ከመላዒካው ጅብሪል የተላለፈላቸው።

“ኢቅራዕ”የሚለው የአረቢኛ ቃል”አንብብ!”ማለት ሲሆን “ኢቅራዕ”የሚልና በታሪካዊነቱና በመልዕክቱ ታላቅ ስፍራ የሚሰጠው የቁርዓን ምዕራፍም ይገኛል! ይኼ እውነታ ትልቅ የዕውቀት መፈለጊያ በር ማሳያ መሆኑ በግልፅ ያሳያልና የነቢዩ ሙሐመድ/ሠ.ዐ.ወ/መወለድ ድንቁርናን የገፈፈ፣ እንስሳዊ ባህሪን የሰየፈ፣ የእምነት ብርሃንን ያገዘፈ፣ ለመላው ዓለም የተሰጡ ልዩ መለኮታዊ የእውነትና የፍቅር ስጦታ ናቸው። እሳቸውን መከተል ደግሞ መታደልም መመረጥም ነው።

ታላቁ ዓለም አቀፋዊ ዳኢ/የሐይማኖት መምህር/ሸይኽ አህመድ ዲዳት መውሊድን በማክበር ዙርያ እንዲህ ብለው ነበር። “እኛ አላህን በብቸኝነት እንገዛለን! የነብዩ ሙሐመድን ልደት ማክበራችን ሰው ሆነው መወለዳቸውን ማመንን ያሳያል! ነቢዩ የተላኩት ለመላው የሰው ልጆች እዝነት ነው። የነብዩ መወለድ፣ ወደዚህ ዓለም መምጣት ይህች ዓለም በመጀመሪያ ደረጃ እንድትፈጠር ምክንያት የሆነው እና አላህ ለውዱ ነብይ ትውልድ ጀነትን ቃል የገባበት ምክንያት ነው።”

በእርግጥ ዛሬ ዘመነኛው ትውልድ”መውሊድ ማክበር መጥፎ ነው”የሚል ሃሳብ አንግቦ የተቃውሞና የተቃርኖ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያደርግ ይታወቃል፤ ሆኖም እልፍ አዕላፍ ሙስሊሞች ከበርካታ ምእተ_ዓመታት ጀምረው በየዓመቱ አላህ በነብዩ ውልደት ስለዋለላቸው ውለታና ስላደላቸው ታላቅ ፀጋ ምስጋና ለማድረስ የመልእክተኛውን መውሊድ ያከብራሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ከሚያጣቅሷቸው ማስረጃዎች መካከል ኢማሙ ነሳኢይ እንደዘገቡት (መልእክተኛው በሱረቱ ሷድ የቁርአን ሱጁድ ላይ ሱጁድ ከወረዱ በኋላ”ዳውድ ለተውበት ሲል ሰገዳት፤ እነሆ አኛ ደግሞ ለምስጋና እንሰግዳታለን”) የሚለው ሀዲስ አንዱ ሲሆን በመሰረቱ ይህ ሀዲስ ለምስጋና ሲባል አምልኮን ማስገኘት እንደሚቻል ይጠቁማል። ኢማሙ ሱዩጥይም ስለ ድግግሞሹ (በየአመቱ ስለመከበሩ) ከተነሳ ደግሞ አቡ ዳውድ ከአኢሻ ይዘው እንደዘገቡት አላህ ዘንድ የተወደደ ስራ እንደ ሆነ እሙን ነው።

የመውሊድ ክዋኔ ከሸሪዓው ጋር የሚስማማ ነው እንጂ የሚጣረስ አይደለም። መልእክተኛው አለማክበራቸው መከልከልን አያሳይም። ክዋኔውም አዲስ ሸሪዓዊ ሕግ መደንገግ ሳይሆን በሸሪዓው የተሞካሹ ተግባራት ድምር ውጤት ነው። አላህን ማውሳት፣ የመልእክተኛውን አጠቃላይ ስብዕና ማብራራት፣ ለማህበረሰቡ እውቀትን ማድረስ እና የኢስላምን መገለጫዎች ይፋ በማድረግ የተራበን ማብላት እና መደሰትን ሸሪዓው ያሞግሳቸዋልና።

ኢማም ሙስሊም እንደዘገቡት በጥቅሉ መውሊድ “በእስልምና ውስጥ መልካም ግኝት ያስገኘ ምንዳ አለው፡፡ ተከትለው ግኝቱን የሚተገብሩትም ከፈር ቀዳጁ ምንዳ ሳይቀነስ ይመነዳሉ።”ከሚለው ሀዲስ ማዕቀፍ ውስጥ ይገባል፤ ይህ የሆነውም የንግግሩ ጠቅላይነት እንጂ የንግግሩ መንስዔ የሚታይ ባለመሆኑ ነው።

ለአንዳንድ የቅርብ አስተሳሰብ ይዘው በልዩነት ዳር ዳር ለሚበረቱ ወገኖች መውሊድን ማክበር በኢስላም ላይ ጉድለት ማምጣት ነው ለሚለው ንግግራቸው ማስተካከያው”ዛሬ ዲኑን ሞላሁላችሁ”የምትለው አንቀፅ ከወረደችበት ቅፅበት በኋላ የተደነገጉ ሕግጋት የማይቆጠሩና ፋይዳ የሌላቸው ናቸው የሚለውን ያስይዛል፤ ይህቺ አንቀፅ ደግሞ በነብዩ /ሠ.ዐ.ወ/ላይ የተወረደች የመጨረሻ አንቀፅ ያለመሆኑ ትኩረት ሊሰጠውና ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። ሁሉም አዲስ ግኝት ጥሜት ነው የሚለው ሀዲስም ቃሉ ጥቅል ትርጉሙ ደግሞ አንፃራዊ መሆኑና አብዛኛነትን ጠቋሚ በመሆኑ መውሊድን ለመከልከል ማስረጃ ሊሆን አለመቻሉ ሊሰመርበት ይገባል።

ተጠቃሽ አብነት ካስፈለገ…፡፡ በኢስላም ውስጥ ከፍ ያለ ዝና እና ስም በዲኑ ላይ ትልቅ ሚና ያላቸው ሊቃውንቶች ማለትም ሻፍእይን፣ ኢዝ ቢን አብዱ ሰላምን፣ ሱብክይን፣ ነወውይን፣ ኢብኑ ሀጀር አል ዓስቀላንይን፣ ሱዩጥይን፣ አዙርቃኒይ አልማሊኪይን፣ ኢብኑ ዓቢዲን አልሀነፍይን፣ ኢብኑ ረጀብ አል ሀንበልይን የመሳሰሉ በርካታ ሊሂቃን “ቢድኣን” መልካምና መጥፎ በማለት መክፈላቸው ሊታወቅ ይገባል። በዚህም መሰረት ከሸሪዓ ጋር የገጠመው መልካም ከሸሪዓው ጋር የሚጋጨው ደግሞ መጥፎ ይሆናል ማለት ነው።

ለምሳሌ ኢብኑ ሀጀር አል ዐስቀላንይ”ፈትሁል ባሪ”ላይ ቃል በቃል የጠቀሱትን ማስፈር አስፈላጊ ነው” ማንኛውም በነብዩ ዘመን ያልነበረ ነገር ቢድዓ ነው፤ ግን ከነሱ ውስጥ መልካምና መጥፎ ሊኖር ይችላል”የታላቁን ነብይ ሙሐመድ/ሰ.ዐ.ወ/የልደት ቀንን/መውሊድን/ማክበር ፍፁም ከመልካም ነገራቶች ውስጥ ስለመሆኑ እናምናለን።

  • ወደ ዕለቱ ዋና ሃሳባችን ስንመለስ የመውሊድ አከባበር በኢትዮጵያችን ምን እንደሚመስል ለማስታወስ እንሞክራለን።

ነቢዩ ሙሐመድ/ሠ.ዐ.ወ/ስለተወለዱበት ወር መውሊድ በሚያከብሩ ሕዝቦች ዘንድ የተለየ ክብር አላቸው። ይህ ወር ‹‹ረቢእ›› ተብሎ ይጠራል። ወሩ የዓለሙ መሪ ነቢዩ የተወለዱበት፣ ከፈጣሪ ወህይ/መመሪያ/መቀበል የጀመሩበት፣ ተልእኳቸውን አድርሰው፣ ለሕዝባቸው አደራ ሰጥተው ያለፉበት ወር ነው።

የመውሊድ አከባበር በኢትዮጵያ

በአገራችን የመውሊድ ከበራ ከአገሪቱ የሱፊዝም መስፋፋት ጋር እንደሚያያዝ ይታመናል። ሱፊዎች መውሊድን የአምልኮ ተግባሮቻቸውና የመንፈሳዊ ንቃታቸው ማበልጸጊያ፣ የአንድነታቸው ማጠናከሪያ መሳሪያ፣ የሰላም የፍቅር፣ የመተዋወቅና የተግባቦት፣ የሰናይ ተግባራት ማስታወሻ፣ የፅድቅ ስንቅ መሰነቂያ አድርገው ይገለገሉበታል። በዚህ አጠቃላይ መንፈስና በተለየ ሁኔታ በአገራችን የመውሊድ ከበራ እልፍ ዕድሜ እንዳስቆጠረ ይነገራል። አንዳንድ መዛግብቶችና የእምነቱ ልሂቃን እንደሚያወሱት መውሊድ ይበልጥ እየደመቀ መከበር የጀመረው ከ1734–1799 እንደኖሩ የሚነገርላቸው የወሎው ሸይኽ ሙሐመድ ሻፊ መሆናቸው ይወሳል።

ሸይኽ ሙሐመድ ሻፊ የከበደ የአዋቂነት ስም የወጣላቸው የታላቅ ዕውቀት ባለቤት/አሊም/ና ሱፊይ ነበሩ። መቀመጫቸውን ጀማ ንጉስ ካደረጉ በኋላ ዓመቱን በሶስት ወቅቶች አሰናድተው ይጠቀሙ ነበር፡፡

ሀ) አራቱን ወር ለማስተማር

ለ) አራቱን ወር ለዚክር ወይም ለተመስጦ መንፈሳዊ ጉዞ

ሐ) ቀሪውን አራት ወር ለትግል–የሙስሊሙን ማሕበረሰብና የሀገሪቱን ጠላቶች የመከላከል ዘመቻ ለማካሄድ ብለው በዕቅድ ከፍለው፣ እስልምናንና ዕውቀትን በማስተማርና ጠላቶቻቸውን በመከላከል ይታወቃሉ። የሸኽ ሙሐመድ ሻፊ ታሪክ ሰፊ በመሆኑ እዚህ ቦታ ከመውሊድ ጋር ባለው የታሪካቸው ክፍል በአንድ በኩል በሱፊዝም ብቻ የማስተማር ስልት እስልምናን የማነጽና የማደስ፣ ዕውቀትን የማስረፅ፣ የሙስሊሞችን አንድነት የማጠናከር አቅሙ ውስን፣ ውጤቱ ትንሽ ሆኖ ስለታያቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሳቸውም ሆነ በሀገሪቱ በውስጥና በውጭ የተነሳባቸው የጠላት ጫና እያየለ ስለመጣባቸው ትግልን እንደ አማራጭ ለመውሰድ ወስነው ፈቃድና ምክር ለመቀበልና የሎጂስቲክ እርዳታ ለመጠየቅ ወደ ሂጃዝ ወይም መካ መንፈሳዊ ጉዞ አደረጉ። ሸይኹ በሂጃዝ ቆይታቸው ከመካው ሙፍቲ ጋር ተገናኝተው ሀሳባቸውን አቀረቡ።

ሙፍቲውም ጊዜው ከትግል ይልቅ ሕዝቡን ለማንቃትና ለማብቃት የማሰባሰቢያ መንገድ ፈልገው ማስተማሩ እንደሚሻል ይገልጹላቸዋል። ሸኹ ከሙፍቲው በተሰጣቸው መልስ አንዳች መልካም ነገር ቢገነዘቡም ባለ መርካታቸው የነቢዩ ሙሐመድን/ሰ.ዐ.ወ/መቃብርና መስጊድ ለመዘየር ወደ መዲና ይሄዳሉ፤ በዚሁ መካከል ነቢዩ ሙሐመድ/ሰ.ዐ.ወ/ተገልጠውላቸው አላማቸውን ለማሳካት ከለውጥ ትግል ያልተናነሰ ሌላ መንገድ እንዳለ ያመላክቷቸዋል።

ሸኹም ቀድሞ የነበረ ውስን ዝግጅታቸውን ወደ አገራቸው ተመልሰው መውሊድን ሕዝባዊ በሆነ መንገድ አቋቋሙ።‹‹እናም መውሊድ ዐሊሞችን/ሊሂቃንን/ከተራው ሕዝብ የሚያገናኝ፣ የዲን ፍቅርን በሺዎች ልቦና ውስጥ የሚያቀጣጥል፣ ዘመን ተሻጋሪ የዕውቀት ቱርፋቶችን የሚለዋወጡበት፣ ያለ እምነትና ኢልም በድንቁርና ሲደናበሩ የነበሩ ወገኖችን ወደ ዕውቀት የሚጠሩበት፣ የተቸጋገሩ ምስኪኖች የሚረዱበት የመተዛዘኛ መድረክ ሆኖ በሀበሻ ምድር በይፋ ታወጀ። ከዚያ በኋላ ላደረጓቸው የጂሃድ ፍልሚያዎች መውሊድን እንደ ግብአት ሳይጠቀሙበት አልቀሩም›› ጂሃድ”ሲባል ሰይፍ ይዞ ለጦርነት መሰለፍ እንዳልሆነ ልብ ይሏል።

ማሕበረሰብን ከማይምነት፣ ከድህነት፣ ከድንቁርና፣ ከወቅታዊ የበሽታ ወረርሽኝ ለመታደግ፣ ሀገርን በልማት ለማሳደግ፣ በኢኮኖሚ ለመለወጥ፣ ክፉና አዋኪ ነገራቶችን ለማስቀረት፣ ጎጂ ድርጊቶችን ለመከላከል፣ ሀቅንና እውነትን በሕዝብ ልቦና ለማስረፅ እና ሌሎችንም መልካም ነገሮችን ለማበልፀግ የሚደረግ ትግል በሙሉ”ጂሃድ”ተብሎ እንደሚገለፅ ለማሳሰብ እንወዳለን።

በእርግጥ በአገራችን የመውሊድ በዓል ከአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ ሕዝባዊ ክብረ_ በዓል ሆኖ ቢቀጥልም እስከ ደርግ ዘመን ድረስ የአገሪቱ ኦፊሴላዊ ክብረ_በአል አልነበረም። ከ1967 ወዲህ ግን፣ በሕዝበ ሙስሊሙ የቀደመና ተከታታይ ጥያቄ መሰረት የአገሪቱ ኦፊሴላዊ በአል ሆኖ፣ በረቢየል አወል አስራ ሁለተኛው ቀን በድምቀት መከበር ጀምሯል።

  • የመውሊድ ከበራ ቦታ፣ ጊዜና የከበራው ተሳታፊዎች

በአገራችን የመውሊድ ከበራን በሶስት ቦታዎችና ጊዜዎች የማክበር ልማድ አላቸው። የማክበሪያ ቦታን በሚመለከት መውሊድ በመኖሪያ ቤት፣ በመስጊድና በሱፊይ የአስተምህሮት ማዕከሎች ይከበራል። የመውሊዱ ጊዜ ደግሞ ባብዛኛው ነቢዩ ሙሐመድ/ሠ.ዐ.ወ/በተወለዱበት በረቢየል አወል ወር አስራ ሁለተኛው ቀን (በተለይ ዕለተ_ሰኞ) ወይም በተወለዱበት ወር ውስጥ በሚገኝ በማንኛውም ወርና ቀን ይከበራል።

የመውሊድ ሥርዓት ተሳታፊዎች እንደ መውሊድ የማክበሪያ ቦታና አቅም የሚወሰን ሆኖ አይነታቸውና መጠናቸው ብዙ ነው። በመኖሪያ ቤት ውስጥ በሚደረግ መውሊድ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ በአካባቢው የሚገኙ ሸኾችና ደረሶች፣ ሽማግሌዎች፣ ድሆች፣ ወዘተ. የመውሊድ ተካፋዮች ይሆናሉ። ብዙውን ጊዜ የመውሊዱ ታዳሚ በጥሪ የሚካፈል ቢሆንም ላልተጠራውም ወገን ክልከላ የለውም። በመስጊድ የሚደረግ መውሊድ ደግሞ በቅርብ ርቀት ለሚገኙ መስጊዶችና ለአካባቢ ነዋሪዎች፣ አጋጣሚ ለሚመጡ ዕንግዶችም ክፍት ይሆናል። በቤት ውስጥ ከሚደረግ መውሊድ የሚበልጥ የሰው ቁጥር የመውሊዱ ተካፋይ ይሆናል። መውሊዱ መቼ እንደሚደረግ በሁሉም የመስጊድ ኢማሞች በኩል እንዲታወቅ ይደረጋል።

በሱፊይ የኢልም ወይም የሐይማኖታዊ ትምህርት ማእከሎች ማለትም በሀና፣ በዳና፣ በሾንኬ፣ በአልከሶ፣ በአብሬት፣ በቃጥባሬ፣ በዘቢሞላ፣ በዳንግላና በሌሎችም ታላላቅ ሀድራዎች ውስጥ በሚካሄድ መውሊድ ከሁለቱ የመውሊድ ማክበሪያ ቦታዎች የሚበልጥ ከፍተኛ ሕዝብ ይካፈላል። ከገጠርና ከከተማ፣ ከቅርብና ከሩቅ/ከውጭ ሀገራት ጭምር/ለሚመጡ ሰዎች ሁሉ ክፍት ይሆናል፤ በእነዚህ ማዕከሎች የሚካሄድ መውሊድ ጊዜው ቀድሞ ስለሚታወቅ ብዙም ቀስቃሽና አስታዋሽ አያስፈልገውም። ሁሉም ተጠራርቶ በእለቱና በቦታው ይገኛል።

በሱፊይ ማዕከሎቹ/ ሀድራዎች\ የመውሊድ ታዳሚው ቁጥር እጅግ በጣም ብዙ ስለሚሆን ታዳሚዎች/ተሳታፊዎች/በማእከሎቹ ቅጥር ግቢና በአካባቢው ዙሪያ በአጥር ጥግና በዛፎች ጥላ ስር ወይም ድንኳን ዘርግተው ይጠለላሉ፤ በአጠቃላይ መውሊድ ለሁሉም የህብረተሰብ አይነት ክፍት ነው። አዛውንት፣ ወጣት፣ አዋቂ፣ ህጻን፣ ወንድ፣ ሴት፣ ከተሜ፣ ባላገር፣ የተማረ፣ ያልተማረ፣ ጤነኛ፣ የታመመ፣ ሀብታም፣ ድሃ፣ ባለ ማዕረግ፣ ምንዝር፣ የቤት እመቤት፣ የኪዮስክ ሰራተኛ፣ ሙስሊም፣ ክርስቲያን ወዘተ..ሳይለይ ሁሉም የሕብረሰብ ክፍል መሳተፍ ይችላል።

የመውሊድ አከባበር ሂደት

የመውሊድ አከባበር በበርካታ ድርጊቶች ይደምቃል። ከእነዚህም መካከል የሰደቃ ወይም የምጽዋት፣ የቡና ጀባታ፣ የተመረጡ የቁርአን ክፍሎችና የመውሊድ ምንባብ፣ የመንዙማ ፕሮግራሞች ይገኛሉ። በሰደቃው ወይም በምጽዋቱ ሃብታሞች በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ ዶሮ አርደው፣ ሌሎች ከቤት ያዘጋጁትን ምግብና መጠጥ (ለምሳሌ፣ ወተት፣ የማር ብጥብጥ/ብርዝ/፣ ወዘተ.) ለድሆች ያበላሉ፤ ያጠጣሉ።

በጀባታ ክፍለ ጊዜ ሰዎች በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ቡና እየጠጡ፣ ጀባታ ወይም ስጦታ እየተሰጠ የታመመው እንዲሽር፣ የደኸየው እንዲከብር፣ መካኑ ልጅ እንዲያገኝ፣ የተራራቀው እንዲቀራረብ፣ የተጣላው እንዲታረቅ፣ የተበደለው እንዲካስ፣ ጥላቻ እንዲጠፋ፣ ፍቅር እንዲፋፋ፣ አገር ሰላም እንዲሆን፣ መንግስት እንዲረጋጋና ለሕዝብ የሚጠቅም ስራ እንዲሰራ፣ ወዘተ. ዱዓ/ጸሎት/ያደርጋሉ።

በቁርአንና በመውሊድ ንባብ ክፍለ_ጊዜ ከነቢዩ ሙሐመድ/ሠ.ዐ.ወ/ጋር የተያያዙ ነቢዩ የዓለሙ እዝነትና መሪ፣ ለሰናዮች መልካሙን አብሳሪ፣ ለእኩይ ሰሪዎች አስፈራሪ፣ ለሕዝባቸው ሀላልና ሀራሙን አስተማሪ ወዘተ.. ሆነው የተላኩ የመጨረሻው ነብይ መሆናቸውን በተለይ የሚመሰክሩ የቅዱስ ቁርአን ክፍሎች ይቀራሉ። ስለ ነቢዩ ሙሐመድ/ሰ.ዐ.ወ/ውልደት፣ በሕይወት በነበሩ ጊዜ ስለ ፈጸሟቸው ድንቅ ገድሎችና ተአምራት፣ ስለ ባህሪያቸው፣ ወዘተ.,.በቀደምት አሊሞች/የዕውቀት ባልተቤቶች/የተዘጋጁ የመውሊድ ኪታቦች/መጽሓፍቶች/መሳጭ በሆነ የአነባብ ስልት ይነበባሉ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የመውሊድ አከባበር ደማቅና የራሱ ሆነ አሻራ ያለቀው ነው፡፡ ከሃይማኖቱ ተከታዮች ባሻገር የሌሎች እምነት ተከታዮችም በበዓሉ የሚሳተፉ ሙስሊሞችን በመመልከት እና ታሳታፊም በመሆኑ አብሮነታቸውን ያጠናክራሉ፡፡ ይህም የመውሊድ በአልን አይረሴ ከሚደርጉት ውስጥ አንዱ ሲሆን በየዓመቱም በድምቀት እንዲከበር አይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም አቅመ ደካማ ሰዎች በአሉን ምክንት በማድረግ ድጋፍ የሚያገኙበትና ጠግበው የሚውሉበት ዕለት ነው፡፡ መልካም የመውሊድ በአል ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች።

ኃይረዲን ከድር ነኝ/የአሰላው/

 አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You