በአፋር ክልል 550 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– በ2016/17 የመኸር ምርት ዘመን ሃያ አራት ሺህ 500 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 550 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የአፋር ክልል የግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

በአፋር ክልል ግብርና ቢሮ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ምክትል ኃላፊ ያሲን አሕመድ ያሲን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016/17 የምርት ዘመን በክልሉ ለማምረት የታቀደውን 550 ሺህ ኩንታል ምርት ለማሳካት እየተሠራ ነው፡፡

የምርት ዘመኑን ዕቅድ ለማሳካትም በቂ የግብርና ግብዓት ተደራሽ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ያሉት አቶ ያሲን፤ ሰብሎችን ከፀረ ተባይና አረም የመከላከል ሥራም እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በክልሉን የሚታረሰውን መሬት በማስፋት፤ አርብቶ አደሮችን ወደ እርሻ በማስገባት፤ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአምራቾች በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በክልሉ የግብርና ግብዓት እጥረትን በመፍታት፤ አርብቶ አደሮችን ወደ ጥምር ግብርና በማምጣት በክልሉ ተመርተው የማይታወቁ ምርቶችን ማለትም ጤፍና የተለያዩ ምርቶችን የማምረት ሥራ እየተከናወነ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአፋር ክልል የበቆሎ፤ የሽንኩርት፤ የጥጥ ምርቶች ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዙ የቆላ ስንዴና ማሽላ ምርቶችም በስፋት ይመረታሉ ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ ጤፍ እየተመረተ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በክልሉ የሚታረሰው መሬት እያደገ መሄዱ ምርታማነት እያደገ ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ በተለይ በአዋሽ ወንዝ ዳርቻዎች በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በአፋር ክልል ከሁለት ዓመታት በፊት የክልሉ መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት በጀት በጅቶ አያቀርብም ነበር፤ በድጋፍ ነበር የሚገኘው፡፡ በዚህ ምክንያት በክልሉ በቂ የግብርና ግብዓት አልነበረም፤ እጥረቱም ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ትልቅ ፈተና ሆኖ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡

ከ2015/16 የምርት ዘመን ጀምሮ የክልሉ መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ በጀት በጅቶ ማቅረብ በመጀመሩም 70 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን አውስተው፤ ይህም በክልሉ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ምክንያት ሆኗል›› ብለዋል፡፡

አቶ ያሲን በክልሉ ችግሩ በመፈታቱም በቂ የሆነ የአፈር ማዳበሪያ፣ የተሻሻሉ ዝርያዎች፤ አረም መከላከያና የፀረ ተባይ ኬሚካል ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You