አዲስ አበባ፡– ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ መተግበር በኋላ የሚታዩ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ተገለጸ፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ መዝገቡ አመሐ እንደገለጹት፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋናው ስኬት ሕዝቡ ማሻሻያውን መረዳት እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ ማሻሻያው ተግባራዊ ከሆነ በኋላም የሚታዩ ተጨባጭ የሆኑ ውጤቶች እየተመዘገቡበት ነው ፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይም የውጭ ምንዛሪ መዋዠቅን እያስቀረ ያለና የውጭ ምንዛሪው በገበያ ሁኔታ እንዲወሰን ማስቻሉ አንዱ መልካም ውጤት ነው ያሉት አቶ መዝገቡ፤ የውጭ ኢንቨስትመንትን ፍሰት እንዲያድግ ምቹ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል ፡፡
አቶ መዝገቡ፤ ማሻሻያው በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚደገፍ መሆኑ ሀገሪቱ ተጨማሪ ሃብት እንድታገኝ ማድረጉን ገልጸው፤ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚገኘው 10 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከገንዘብ ድጋፉ ባለፈ ማሻሻያው በዕዳ ሽግሽግ፣ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የውጭ ምንዛሪ አቅም እንዲጨምር የሚያደርግ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው መነሻ ያደረገው መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማስተካከል የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጉ ተከትሎ ነው የሚሉት አቶ መዝገቡ፤ በዓለም ተከስቶ የነበረው የኮሮና ወረርሽኝ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ላይ ጫና መፍጠሩንም አውስተዋል፡፡
እንደ አቶ መዝገቡ ገለጻ፤ ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላም የሠላም እጦት እንዲሁም የተለያዩ ምክንያቶች የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲዋዥቅ ሲያደርገው ቆይቷል፡፡ በዚህም የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት እና የውጭ ሀገር ብድር እንዲጨምር አድርጓል፡፡
መንግሥት ኢኮኖሚው ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያግዛል ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል ያሉት አቶ መዝገቡ፤ ማሻሻያው ተግባራዊ ከሆነ በኋላ እየታዩ ያሉ ውጤቶች አበረታችና ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህ ሲባል ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው ማለት እንዳልሆነና በአንድ ጊዜ ለውጥ የሚያመጣ እንዳልሆነም አመልክተው፤ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር የቁጥጥር (ሞኒተሪንግ)፣ የፊስካል እንዲሁም የገንዘብ ፖሊሲዎችንም ማሻሻልና ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለእነዚህ ማሻሻያዎች መሳካት ገቢን ማሳደግ ወሳኝነት አለው ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም