አዲስ አበባ፡- በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የወጡ ሕጎች ተግባራዊ ባለመሆናቸው ሰዎች በጥፋታቸው እንዲቀጥሉ እያደረገ መሆኑ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሠሩ ሀገር በቀል ድርጅቶች ገለጹ፡፡
የኢኮ ጀስቲስ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እስከዳር አውግቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የውጡ ሕጎች ተግባራዊ ባለመሆናቸው ሰዎች በጥፋታቸው እንዲቀጥሉ እያደረገ ነው፡፡
ሕጎቹ ተግባራዊ ሲሆኑ ኢኮኖሚውን ይጫነዋል የሚል እሳቤ መኖሩ ለሕጉ መላላት ምክንያት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህ ደግሞ አካባቢ የሚበክሉ ግለሰቦችና ተቋማት በሁኔታው እንዲገፉ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
አቶ እስከዳር በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሻለ ቦታ የተሰጠው መሆኑን አመልክተው፤ በዚህም በማኅበረሰብ ደረጃ በፊት ከነበረው የተሻለ ግንዛቤ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
በመንግሥት ደረጃ ተቋማዊ አደረጃጀት ኖሮ ሥራዎች መሠራት መጀመራቸው ለዚህ ማሳያ ነው ያሉት አቶ እስከዳር፤ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ብዙ የወጡ ሕጎች ቢኖሩም ተግባራዊነታቸው ላይ ብዙ ውስንነቶች አሉ ብለዋል፡፡
አቶ እስከዳር በሕገመንግሥቱ በአንቀጽ 44 ሁሉም ሰው ጤናማና ደኅንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ላይ የመኖር መብት እንዳለው ተረድቶ መብቱን ማስከበር እንደሚኖርበት መክረዋል፡፡
በኢትዮጵያ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ወጣት እንደመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ ሥራ ላይ የወጣቱ ሚና የጎላ መሆኑ ገልጸዋል፡፡
ተቋማቸው የአካባቢ ጥበቃ መብትን ማሳወቅ፣ ተግባራዊ እንዲሆን ማገዝ፣ ጠያቂ ማኅበረሰብን መፍጠር እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የመደገፍ ሥራ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
ሌላኛው ሀሳባቸውን ለኢፕድ የገለጹት የኢንፍሎሰርስ ሀገር በቀል ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ጆዳሄ በዛብህ እንደሚሉት አካባቢን ጥበቃን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ውይይቶች የሚደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያም በእነዚህ መድረኮች ላይ በተደጋሚ ተሳታፊ ሆናለች፡፡አካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ቀጣይነት እንዲኖረው ወጣቶችን ያማከለ አሠራር ሊገነባ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም