ነብዩ መሐመድ የታላቅ ስብዕና ባለቤት ናቸው፡፡ ታማኝነት፤ እውነተኛነትና ፍጡራን ሁሉ በእኩል ማየት ከነብዩ መሐመድ ስብዕናዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ነብዩ መሐመድ በምድር ላይ በቆዩባቸው 65 ዓመታት በሰዎች መካከል ፍቅር፤ ሠላም እና አንድነት እንዲሰፍን አበክረው ሰብከዋል፡፡ በተግባርም አሳይተዋል፡፡
ዛሬ 1499ኛው የመውሊድ በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡ በዓሉ ሲከበር እነዚህን የነብዩ መሐመድን በጎ ስብዕናዎች በማሰብ ሊሆን ይገባል፡፡ አሁን ላለንበት ነባራዊ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ የነብዩ መሐመድ ነብያዊ ስብዕናዎች በእጅጉ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡
የመውሊድ በዓል የአንድነት፤ የመረዳዳትና የመተሳሰብ በዓል ነው፡፡ መውሊድ ሲታሰብ አብሮ መብላት፤ መተዛዘን፤ ፍቅርና አንድነት ደምቀው ይወጣሉ፡፡ ልዩነት፤ ጥላቻ፤ ግጭትና መፈናቀል ቦታ የላቸውም፡፡ ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያውያን የሚያስፈልጋቸውም ከልዩነት ይልቅ አንድነት፤ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፤ ከግጭት ይልቅ ሠላም ነው፡፡ መውሊድንም ስናከብር እነዚህን የመውሊድ እሴቶች መሠረት ባደረገ መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡
የነብዩ መሐመድ ታሪክ ሲነሳ ኢትዮጵያም አብራ ትነሳለች፡፡ ነብዩ መሐመድ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን የተለየ ክብር ነበራቸው፡፡ ነብዩ መሐመድ ፍትሐዊና እውነተኛ ወደ ሆነችው ሀገር ሂዱ ብለው ባልደረቦቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል፡፡
ነብዩ መሐመድ እንዳሉትም ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱት አማኞች ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት መልካም መስተንግዶ አግኝተው ከመኖራቸውም ባሻገር የእስልምና ኃይማኖት በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆም ኢትዮጵያ ባለውለታ ሆናለች፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የኢትዮጵያ ውለታ አለበት የሚባለውም ከዚህ አንጻር ነው፡፡ ሆኖም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ውለታ በአግባቡ ተወጥቶታል ማለት አይቻልም።
ዛሬም አንዳንድ ሀገራት እየፈጸሙት ያለውም ከዚህ ነብያዊ ትዕዛዝ ያፈነገጠ ነው፡፡ ከዓባይ ወንዝ አጠቃቀም እና ከባሕር በር ጥያቄ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን እየፈተኑ ያሉና የኢትዮጵያን ውለታ የረሱ ታሪካዊ ጠላቶች ዛሬም ድረስ አልታጡም፡፡
ነብዩ መሐመድ የኢትዮጵያን ውለታ በማስታወስ ኢትዮጵያን አትንኩ ቢሉም ዛሬ አንዳንድ ሀገራት ይህንን ቃል ከመጠበቅ ይልቅ ረጃጅም እጆቻቸውን በመስደድ ኢትዮጵያ ሠላም እንድታጣ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። በተለይም በዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ተስፋ የቆረጡት እነዚሁ ታሪካዊ ጠላቶች ዛሬ ደግሞ በሠላማዊ መንገድ እየተፈታ ያለውን የባሕር በር ጥያቄ ወደ ግጭትና ጦርነት ለመውሰድ የተለመደው ሴራቸውን እየገመዱና ዙሪያችንን እየተሽከረከሩ ነው፡፡
ሆኖም እስልምናን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሃይማኖቶች ያለ ልዩነት ተቀብላ ያስተናገደችና የእንግዳ ተቀባይነት ተምሳሌት የሆነች ሀገር ብዙዎች ውለታዋን ረስተው ሊያፈርሷት ቢሞክሩም የተገነባችበት መሠረት ጠንካራ ነውና ከመፍረስ ይልቅ አንድነቷ እየጠበቀ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የዓባይን ግድብ ገንብታ ወደ ማጠናቀቁ ደርሳለች፡፡ የባሕር በሩም ጥያቄ ሠላማዊ በሆነ መልኩ ምላሽ እያገኘ ነው፡፡
ነብዩ መሐመድ እንዳሉት ኢትዮጵያ የእውነተኞች እና የፍትሕ ሰዎች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለአንድም ቀን ቢሆን ሌሎች ሀገራትን ወርራ ወይንም ተንኩሳ አታውቅም፡፡ ለጎረቤት ሀገራት ከፍተኛ ክብር አላት፡፡ የጎረቤት ሀገራት በተቸገሩ ቁጥር ቀድማ በመገኘትና ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ጥላ እና ከለላ ስትሆን ቆታለች፡፡ ዛሬም የብዙዎች መከታ ነች፡፡
በጎረቤት ሀገራት የሚነሱ አለመግባባቶች በፍጥነት እንዲፈቱና ሀገራቱ ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለችው ሚና መተኪያ የሌለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሰሜን ሱዳን፤ በሱዳንና በሶማሊያ ወደ ግጭት የገቡ ኃይሎችን በመሸምገል ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች፡፡
ሆኖም አንዳንድ ሀገራት ሠላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጠብ አጫሪ ንግግሮችን በማድረግና ጦርነት በማወጅ ጭምር ሠላሟን ለማወክ ሲውተረተሩ ይታያሉ፡፡
ሆኖም እነዚህ የኢትዮጵያ ውለታ ያልተረዱ እና አለፍ ሲልም ውለታዋን የዘነጉ ሀገራት ኢትዮጵያን አትንኩ የሚለውን የነብዩ መሐመድን ትዕዛዝ ሊያከብሩ ይገባል፡፡ ሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉትም ኢትዮጵያን ከመንካታቸው በፊት አስር ጊዜ ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል!
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም