ከ61ሺ በላይ ታዳጊዎች የሚሳተፉበት የክረምት መሠረታዊ የስፖርት ሥልጠና

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት የክረምት ሥልጠና መርሐ ግብርን በተለያዩ ስፖርቶች እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሥልጠናው በከተማዋ በሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞችና 5 የትምህርት ሥልጠና ማዕከላት የሚሰጥ ሲሆን ተማሪዎች በእረፍት ጊዜያቸው መሠረታዊ የስፖርት እውቀትን ይጨብጡበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከክፍለ ከተሞች፣ ከማኅበራት እና ከትምህርትና ሥልጠና ማዕከላት ጋር በመተባበር በክረምቱ መርሐግብር ከ60 ሺ በላይ ታዳጊዎችን ለማሠልጠን አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በበጋው የሥልጠና መርሐግብር በ19 የስፖርት ዓይነቶች ሥልጠና ሲሰጥም ቆይተል፡፡ አሁን ደግሞ ከ61 ሺ በላይ ታዳጊዎች የክረምት ሥልጠናቸውን በ23 የስፖርት ዓይነቶች በመከታተል ላይ እንዳሉ ተገልጿል፡፡ አብዛኞቹ የሥልጠና መርሐግብር ማዕከላት ሥልጠናቸውን በማጠናቀቅ ሠልጣኞችን እያስመረቁም ይገኛሉ፡፡

በሴቶች ቅርጫት ኳስ ሥልጠናውን እየሰጠ የሚገኘው አሠልጣኝ ሳሙኤል ሲሳይ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የሠልጣኞች ቁጥር መቀነሱን በማስታወስ፣ ታዳጊዎች በትምህርትና በሌሎች ነገሮች የደከመን አዕምሮ እንዲዝናና እንዲሁም መሠረታዊ የስፖርት እውቀት ለመያዝ የሚያስችል ሥልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ ይናገራል፡፡ በተጨማሪም ታዳጊዎቹ በክረምት ሥልጠና መርሐግብሩ ሙያን፣ ግብረገብነትን፣ የጊዜ ጥቅምን እና መልካምነትን ይቀስማሉ፡፡

የቦክስ አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ፀጋዬ አድማሱ በበኩላቸው፣ በሥልጠናው ጥሩ ውጤት ያላቸው ታዳጊዎችን ወደ በጋው የሥልጠና መርሐግብር እንዲገቡ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው በበጋው የሥልጠና መርሐግብር ለመታቀፍ ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በቦክስ ስፖርት ሥልጠናውን እየተከታተለ የሚገኘው ዮሴፍ ፍቅሩ፤ የሚሰጠው ሥልጠና ቴክኒክ፣ ታክቲክ እና ጥንካሬን ያካተተ መሆኑን ያነሳል፡፡ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በስፖርት እንዲያሳልፉና እውቀት እየቀሰሙ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋልም ሲል አስተያየት ሰጥቷል፡፡

ከ5ቱ የክረምት ታዳጊ ሥልጠና ልማት መርሐግብር ጣቢያዎች ውስጥ የአራት ኪሎ ትምህርት ሥልጠና ማዕከል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኤርሚያስ ወንድሙ፣ በስምንት የስፖርት ዓይነቶች ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ይናገራል፡፡ በማዕከሉ በሁሉም ስፖርቶች በ11 አሠልጣኞች ለ822 ታዳጊዎች ሥልጠና እየተሰጠም ነው፡፡ ተማሪዎች እየተዝናኑ የስፖርት እውቀት የሚቀስሙበት ቢሆንም፣ የማዘውተሪያ ስፍራ እና የግብዓት እጥረት እንዳለም ያስረዳል፡፡

የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ትምህርት ሥልጠና ዳይሬክተር አቶ ጎሣዬ ዓለማየሁ፣ ሥልጠናው ከመጀመሩ በፊት ከክፍለ ከተሞች፣ ማኅበራት እና ከስፖርት ትምህርት ሥልጠና ማዕከላት ጋር እቅዶችን የጋራ በማድረግ የተሰጥዖ ስፍራዎችን እና የሠልጣኞችን ፍላጎት ከግምት በማስገባት ተደራሽ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ክረምት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ የሚሆኑበት ወቅት መሠረታዊ የስፖርት ሥልጠና እንዲያውቁ ታሳቢ ተደርጎ የሚሰጥ ሥልጠና መሆኑንም አክለዋል፡፡ ነገር ግን የክረምት ሥልጠና ተጠናቆ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ሲመለሱ እንዳያቋርጡ የተሻለ ሥልጠና የወሰዱና ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ወደ በጋው ሥልጠና እንዲገቡ ይደረጋል፡፡

በበጋ የሥልጠና መርሐግብር በተደረገ ግምገማ ልዩ ትኩረት የሚሹ ስፖርቶች የተለዩ ሲሆን የተሳታፊ ቁጥር የቀነሰባቸው የሥልጠና ጣቢያዎች ላይ በትኩረት ለመሥራት ታቅዷል፡፡ በአንጻሩ የቅርጫት ኳስ፣ ዳርት፣ መረብ ኳስ እና ባድሚንተን ስፖርቶች ደግሞ እንቅስቃሴያቸው ጥሩ ስለሆነ በበጋ ሥልጠናም እንዲቀጥሉ ፍላጎት መኖሩን ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ፡፡ ክፍለ ከተሞች፣ የሥልጠና ጣቢያዎች አሠልጣኞችን ከመመደብና የሥልጠና ጣቢያዎችን ከማመቻቸትም በተጨማሪ የተማሪ ወላጆች የተሻለ ድጋፍ አሳይተዋል፡፡ በሁለት ወር አፈጻጸም በበጋ ሥልጠና የሚቀጥሉ ሠልጣኞች በብዛት የተለዩበት እና በየትኛው ትምህርት ቤት በምን ስፖርት ላይ የሚሉት መለየታቸውንም ያብራራሉ፡፡

በክረምት ሥልጠና መርሐግብር ታዳጊዎች ከስፖርቱ ጋር የሚተዋወቁበት እንደመሆኑ አሠልጣኞች እና ታዳጊዎች ስፖርቱን እንዲወዱ የሚያደርጉበት መንገድ አንዱ የውጤታማነቱ መለኪያ ነው፡፡ የበጋ ሥልጠና ጣቢያዎችን ወደ 21 ለማሳደግ የታቀደ ሲሆን፣ የአካል ጉዳተኞች እና ሴቶች ላይም በትኩረት ይሠራል፡፡

በሥልጠናው 988 አሠልጣኞች በበጎ ፍቃድ አሠልጣኝነት በክፍለ ከተማ ደረጃ እየተሳተፉ ሲሆን፣ የስፖርት ቁሳቁሶችን ለክረምት መርሐግብር የማሰራጨት እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ውስንነት ላይ እንደሚሠራም ተጠቅሷል፡፡ የስፖርት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢሆንም አሁንም የምሑራን አስተዋፅዖ ላይ ውስንነቶች ይታያሉ፡፡

የዘንድሮ የስፖርት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በገንዘብ ሲተመን ወደ 2 ሚሊየን ብር እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ የታዳጊዎች ስፖርት የክረምት ሥልጠና መርሐግብር በበጎ ፈቃድ መሰጠቱ ታዳጊዎች መሠረታዊ የስፖርት ሥልጠና እንዲወስዱ ከማድረጉም በተጨማሪ አሠልጣኞች እውቀታቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ተመላክቷል፡፡ የክረምት ታዳጊዎች ሥልጠና ልማት መርሐግብር መዝጊያና የበጋ ሥልጠና መርሐግብር መክፈቻ መስከረም 28/2017 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You