ጀርመን 250 ሺህ ኬንያውያን ሠራተኞችን ልትቀጥር ነው

ጀርመን ለ250 ሺህ ኬንያውያን ሠራተኞች በሯን ልትከፍት መሆኑ ተሰማ። የኬንያ እና የጀርመን መንግሥት ባደረጉት የሥራ ስምምነት መሠረት በከፊል እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የሠለጠኑ 250 ሺህ ኬንያውያን ሠራተኞች ወደ ጀርመን ይሄዳሉ ተብሏል። ኬንያውያን ሠራተኞችን በአውሮፓ ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤት በሆነችው ጀርመን ለመቅጠር በሚል ሀገሪቱ ያላትን የስደተኞች ሕግ ለማላላት ተስማማታለች።

ኬንያ በሀገሯ ውስጥ ለወጣት ባለሙያዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም በቂ ገቢ እንዲኖራቸው ማድረግ ሳትችል የቀረች ሲሆን በተቃራኒው ጀርመን ደግሞ ከፍተኛ የሠራተኛ ኃይል እጥረት አለባት። አምስት የአውቶብስ ሹፌሮች በሰሜን ጀርመኗ ፍሌንስበርግ ፕሮጀክቱን ለመሞከር እንዲሄዱ መደረጋቸውም ተገልጿል።

የጀርመን መንግሥት ወደ ሀገሪቱ በሕገ ወጥ መልኩ የሚሰደዱ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ከያዛቸው ዋና ዋና መንገዶች አንዱ ከሀገራት ጋር የሚያደርገው የስደተኞች ስምምነት ነው። ይህ ስምምነት በጀርመን ያለ ሕጋዊ ፈቃድ እየኖሩ የሚገኙ ኬንያውያንም ተጠርዘው የሚመለሱበትን መንገድ ያቀላል ተብሏል።

የሠራተኞች ስምምነቱ የተፈረመው በኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ እና በጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ መካከል ነው። የበርሊን ባለሥልጣናት ኬንያውያን ሠራተኞች የተፈቀደላቸውን ሥራ ሲጀምሩ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያመቻቻሉ ተብሏል። እንደ ሁለቱ ሀገራት ስምምነት ከሆነ ኬንያውያን በጀርመን ለትምህርት ወይንም የሙያ ሥልጠና ለማግኘት የረዥም ጊዜ ቪዛ ማግኘት ይችላሉ።

“የረዥም ጊዜ ቪዛቸው በሚያበቃበት ወቅት ትምህርታቸውን ለመቀጠል የሚያስችል እስከ ሁለት ዓመት የሚቆይ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ” እንደሚያገኙ ስምምነቱ ላይ ሰፍሯል። በተጨማሪም የጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃዱ ኬንያውያን ወደ ሀገር ውስጥ የገቡበትን ዓላማ ካላሳኩ እና “በተወሰነ ጊዜ” የሚሳካ ከሆነ ሊራዘም የሚችልበት ዕድል አለ ይላል ስምምነቱ።

እንደ ሁለቱ ሀገራት ስምምነት ከሆነ ኬንያውያን የአይቲ ባለሙያዎች ምንም እንኳን መደበኛ የሆነ የብቃት ማረጋጋጫ ባይኖራቸውም ጀርመን ገብተው መሥራት ይችላሉ። ሁለቱም መንግሥታት የተማሩ ሠራተኞች፣ የሙያ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወይንም ደግሞ የዩኒቨርስቲ ዲግሪያቸው በሌላኛው አካል ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ ጀርመን ገብተው እንዲሠሩ ድጋፍ ያደርጋሉ። ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት ዜጎቻቸውን መልሶ መቀበል ወይንም የመመለስ ስምምነትም ይዟል።

የሠራተኛ ፍልሰት፣ የጉልበት ብዝበዛ እና የሕገወጥ ሰዎች ዝውውርን ለመከላከልም የራሱን መመሪያ አካትቷል። ሐሙስ ዕለት አምስት ኬንያውያን ሹፌሮች ፍሌንስበርግ መድረሳቸውን ተከትሎ የጀርመን ትራንስፖርት ሚኒስትር ክላውስ ሩሄ ማድሰን፣ “ጀርመን ጠንክረው የሚሠሩ እጆች እና ብሩህ አዕምሮ ትፈልጋለች” ብለዋል። ሹፌሮቹ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር አክቲቭ በተሰኘ ኩባንያ የሠለጠኑ ናቸው። ከዚህ በመቀጠል ዶክተሮች፣ ነርሶችና መምህራን በዚህ ፕሮግራም ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የዓለምአቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ይህ ስምምነት ኬንያውያን ሠራተኞች በጀርመን ጥሩ የሚባል ሥራ እንዲያገኙ ዕድሎችን እንደሚጨምር በጀርመንም ያለውን የሠራተኞች እጥረትም እንደሚቀርፍ ያለውን ተስፋ ገልጿል።

የዓለም አቀፉ ድርጅት በመግለጫው “የኬንያውያን ስደተኛ ሠራተኞችን መብት እና ደኅንነት ይከላከላል፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ሥርዓት ያለው እና ውጤታማ የሆነ የስደተኛ ሥርዓት ይፈጥራል” ብሏል።

እንደ ዶክተር እና ነርሶች ያሉ የተማሩ ሰዎችን ወደ ሌላ ሀገር ማፍለስ ሀገሪቱ በተማረ ሰው ኃይል ድርቅ እንድትመታ ያደርጋል፣ የሀገሪቱ የሕክምና ተቋማትም በባለሙያዎች እጥረት እየተቸገሩ ነው ሲሉ ቅሬታ ያቀረቡም አሉ። ጠበቃ እና ፖለቲከኛ የሆነው ኢኩሩ ኡኮት ለቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም “ በሀገራችን ወጪ ሌላ ሀገርን ልናገለግል መሆኑ በጣም ያሳዝናል” ብሏል።

ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ባለሙያ የሆነችው ሮስሊን ንጆጉ ግን ኬንያ ለዓለም አቀፉ የሠራተኞች ገበያ ፍላጎት ምላሽ እየሰጠች ነው ስትል ትገልጻለች። “እዚህ ኬንያ ውስጥ በርካታ ወጣት ዜጋ አለን። በየዓመቱ ደግሞ ሚሊዮኖች የሀገር ውስጥ የሠራተኞች ገበያን ይቀላቀላሉ። በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጊዜ እና ሀብት ይጠይቃል” ስትልም ታክላለች።

ጀርመን እኤአ በ2015-2016 በሶሪያ ያለውን ጦርነት ተከትሎ በተከሰተው ከፍተኛ የፍልሰተኞች ቁጥር የተነሳ አንድ ሚሊዮን ሰዎችን የተቀበለች ሲሆን፣ የዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ ደግሞ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዩክሬናውያንን አስተናግዳለች ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You