ባለዘንጉ ጠቢብ

ደበበ ሰይፉ ስሙ ለማንም እንግዳ አይደለም፡፡ ከልጅ እስከ አዋቂ አብሮት የኖረ ያህል ስሙን ያስታውሰዋል። የስሙ ዝና መበርከቱ ከነበረው ሁለገብነት ይነሳል፡፡ ባለቅኔ ነውና ቅኔን የወደደም ያደመጠም ሁሉ ያውቀዋል። በተውኔት ዓለም ውስጥ የኖረም የጎበኘም ሁሉ አይረሳውም፡፡ በስነ ጽሁፍ ደጃፍ እልፍ ያለም ዘልቆ ገብቶ ሰላም ለዚህ ቤት! ካለው እኩል ያውቀዋል፡፡

በጥበብ መንበር ላይ ተቀምጠው፣ በዕውቀት ዘንግ ከጫፍ ጫፍ ከነኩ የጥበብ ሰዎች መካከል አንደኛው ደበበ ሰይፉ ነው፡፡ በኪነ ጥበቡ ብቻም ሳይሆን በምርምሩም ርቆ የሄደ የፈለገ ጥበብ ተጓዥ ነው፡፡ ከስሙ ፊት ረዳት ፕሮፌሰር የምትል ማዕረግም ጣል አድርጓል፡፡ እንደ ሙሴ ትውልዱን አስከትሎ ይመራል፡፡ ሲኖርም እንደ ጠቢቡ ሰለሞን ሁሉን ከጥበብ በጥበብ ይኖራል፡፡ ከምናቡ ባሕር እየጨለፈ በሌላው ምንጭን ያፈልቃል፡፡ ከሌላኛው ውቅያኖስ ላይ ቆሞ ደግሞ ይተረጉማል፡፡ ምርጡ ተርጓሚ ነበር፡፡ ልክ እንደ መርከበኛው ሁሉ ቦታውን ይዞ ሳይስት ይጓዛል፡፡ ደራሲ ብቻ ሳይሆን ትልቅ ሀያሲም ነው፡፡ በርሱ መሪነት፣ በርሱ መንገዱን በድል ሕይወቱን በስኬት ያጠናቀቀ ብዙ ነው፡፡ ጸሀፊ ተውኔትም ነውና የመድረክ ላይ መጋረጃዎች ምስሉን ተቀረጸው እንደ ፎቶ አቃፊ ይታያሉ፡፡

ደበብ አንዲት ልዩ የወርቅ ዘንግ አለችው፡፡ በስነ ጽሁፍና በቲያትር ትከሻዎች ላይ እየዘረጋት ድልድይ ሠርቶ ያሻግርባታል፡፡ በግጥም ስንኞቹ አግድም እየሰደደ አልፎ ልብን ይነካል፡፡ ብዙዎችም ከሁሉ ነገሩ አብልጠው ጣፋጭ የስንኝ ቋጠሮዎቹን ይወዱለታል፡፡ የደበበ ሰይፉ ግጥሞች ማለት ልክ በረሀብ ሰዓት እንደሚያገኙት ማዕድ ናቸው፡፡ በልተው የሚጠግቧቸው፣ ጠጥተው የሚረኳቸው አይመስሉም፡፡

በሲዳሞ ክፍለ ሀገር ታፍረውና ተከብረው፣ በይርጋለም ከተማ ውስጥ የሚኖሩት በጅሮንድ ሰይፉ አንተንይስጠኝ እና ወይዘሮ የማርያም ወርቅ አስፋው የበኩር የሆነውን ወንድ ልጅ በሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም ወልደው ስሙንም ደበበ ብለውታል፡፡ ምን ….ልጅ በጥበብ ይደብብ! ያለ ጎረቤትና ዘመድ ወዳጅ ብዙ ሳይሆን አይቀርምና ብዕር ሰክቶ የስነ ጽሁፍን ምሰሶ የሚያቆም፣ አንደበቱን ከፍቶ የዕውቀትና ጥበብን እሳት የሚተፋ ባለ ብሩህ አዕምሮ ልጅ ሆኖ አድጓል። እንደ አብዛኛዎቹ የስነ ጽሁፍ ኮማሪያን ሁሉ በልጅነቱ ከአስኳላው በፊት አዕምሮውን ያሟሸው በቤተ ክርስቲያን ሰንበትና ዳዊት ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ነበር ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘልቆ ክፍል ማስቆጠር የጀመረው፡፡ በዚያው በይርጋለም የመጀመሪያ ደረጃውን እስኪያጠናቅቅ ከራስ ደስታ ትምህርት ቤት ወደየትም ውልፍት አላለም። አንደኛውን ካጠናቀቀ ኋላ ግን ትምህርት ቤቱን ብቻም ሳይሆን አድራሻውንም የሚለውጥ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ አባት በጅሮንድ ሰይፉ በሥራ ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ ደበበም ቤተሰቡን ተከትሎ ገባ፡፡ ሲመጣ የሚገባበት ትምህርት ቤት ጀነራል ዊንጌት እንደነበር ነበር የሚያውቀው፡፡

ነገር ግን የትምህርት ቤት የምዝገባ ጊዜው አልፎ ስለነበር ቀጣዩን አማራጭ በኮከበ ጽባህ አድርጎ እዚያው ገባ። እስከ 12ኛ ክፍል ደርሶም በዚያው አጠናቀቀ፡፡ ነጥብ ይዞም ወደ ዩኒቨርሲቲ ተሸጋገረ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በዩኒቨርሲቲውም የጥበባት ትምህርት ክፍል ዓይኖቹን አማትሮ ልቡ ያረፈበት ቦታ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ የነበረውን የስነ ጽሁፍ ፍቅሩን ሳናወሳው ብናልፍም ከዩቨርሲቲ ሲገባ መርጦ ሊማር የሚችለው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ግን ለአብዛኛዎቻችን ግልጽ ነው፡፡ የስነ ጽሁፍ ተማሪነቱን ሊመርጥ እንደሚችል ከጠረጠርን አልተሳሳትንም፡፡

ከዓመታት የዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከስነ ጽሁፍ ውሎ አዳሩ መልስ በ1965 ዓ.ም ተመርቆ የመጀመሪያው የሆነውን ቆብ ደፋ፡፡ በ1966 ዓ.ም ለመጀመሪያው ጊዜ የሥራውን ዓለም ተቀላቀለ፡፡ በነበረው ድንቅ ብቃት የተማረበት ትምህርት ክፍል ለመምህርነት አጭቶ ከዚያው አስቀረው፡፡ ደበበ ግን በማስተማሩ ብቻ አልቀጠለም፡፡ በቀኝ ማስተማሩን፣ በግራ እንደገና የእንግሊዝኛን ስነ ጽሁፍ ጨብጦ አስተማሪም ተማሪም ሆነ፡፡ በ1970 ዓ.ም ተመርቆ ሌላኛውን ዲግሪ ታቀፈ፡፡ በስነ ጽሁፍ ድልድይ እየተሻገረ ደግሞ በቲያትር ጥበባት ማስተማሩንም አከለበት፡፡

ግጥም ማለት ለደበበ ከእስትንፋሱ ያልተናነሰ የመኖር ምስጢር ነው፡፡ ለመጻፍ ብሎ ሳይሆን ለመኖር ሲል ይጽፋል። ሲጽፍም በይሆን ይሆናል ሳይሆን እየሆነና ከሆነው፣ ከሚኖረውና ከኖረው እየጨለፈ ነው፡፡ ሕይወቱን በስንኝ ቋጥሮ በግጥም መተረክ ይወዳል። ግጥሞቹን ባነበብን ቁጥር አንድ የምናውቀውና የምንወደውን ታሪክ እያጣፈጠ የሚነግረን ይመስለናል። “የብርሃን ፍቅር” የመጀመሪያው መድብሉ ናት፡፡ ይህን መድብል ያነበበ፤ ችሎታውን ብቻ ሳይሆን ጥልቅ የሆነውን ስሜቱንም አብሮ ይጋራዋል፡፡

የሕይወትን እፍታዎች ሰብስቦ በግጥም ሚዛን ቁና መስፈርን እንደርሱ የተካነበት ያለ አይመስልም፡፡ በግጥም ውስጥ ቃላት ያነባሉ፡፡ ከስንኝ አጥር ውስጥ ሆነው ቃላት ይስቃሉ። ይጣራሉ። ይጮሃሉ። ከአንባቢው ጋር እያወጉ የልብን ምስጢር ይካፈላሉ፡፡ እንባን እያበሱ ያጽናናሉ። እየኮረኮሩ ያስቃሉ፡፡ ለጀግናው ክብርን፣ ለፈሪም ድፍረትን ያቀብላሉ። ቤት በመታ ቁጥር ሁሉ የልብን ምት ከፍ እያደረጉ ስሜትን ከስሜታችን ጋር ያዋህዳሉ። በደበበ ሰይፉ ግጥሞች ውስጥ የምንካፈለውም እኚህኑ ነው፡፡ ግጥሞቹ በልባችን ውስጥ የወዳጅነትን መንፈስ ያሰርጻሉ፡፡

ጠብቄሽ ነበረ

መንፈሴን አንጽቼ

ገላዬን አጥርቼ

አበባ አሳብቤ

አዱኛ ሰብስቤ

ጠብቄሽ ነበረ!

ብትቀሪ ጊዜ!

መንፈሴን አሳደፍኩ

ገላዬን አጎደፍኩ

አበባው ደረቀ

አዱኛው አለቀ!

ብትቀሪ ጊዜ

የጣልኩብሽ ተስፋ

እኔን ይዞኝ ጠፋ፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለደበብ የዕውቀትና ጥበብ ቤተ ጠለሉ ናት፡፡ ዕውቀትና ጥበብን እያፈለቀ ጠጥቶ አጠጥቶባታል፡፡ ምንጩ እየጨመረ ከኩሬ አልፎ ባሕር መስሎ ተንሰራፍቷል፡፡ በስነ ጽሁፍና ቲያትር መሃከል በሠራው ድልድይ ትውልዱን አሻግሮበታል፡፡ በስነ ጽሁፍና በቲያትሩ ወዲህም ወዲያም እያለ 20 ዓመታትን አገልግሏል። የዕውቀቱ ጥልቀትና ግዝፈት ከፍ እያለ ሄዶም በዘርፎቹ ውስጥ በጥናትና ምርምሮቹ እየቆፈረ አዳዲስ ጠብታዎችን ፈጥሯል፡፡ ከዚህ ወጣ ብሎ የረገጣቸው ደጆች በርካታ ናቸው፡፡ በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ የአባልነት ድርሻ ነበረው፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ጎራ ብሎ በኪነ ጥበብ ዘርፍ አማካሪ ሆኖ ከማያቋርጠው የዕውቀት ዥረቱ አዳዲስ ሀሳቦችን ሲያወርድ ኖሯል፡፡ በሁለት ተቋማት ውስጥ ሊቀመንበር ሆኖ እየገራ ከፊት መርቷል፡፡ የመጀመሪያው በቋንቋዎች ተቋም ውስጥ ሲሆን በሚያሳትመው ጆርናል የኮሚቴው ሊቀመንበርም ነበር፡፡ ሁለተኛውና ግዙፍ ስሙን የሰቀለበት ስፍራ ደግሞ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ነው። ማኅበሩን በሊቀመንበርነት ሲመራ ቆይቷል፡፡

ሊቅ መሪ ከወንበሩ ግርማ ሞገስ ብቻም ሳይሆን ደርበብ ካለ የሥራ ውጤት ጋር ከጠረጴዛው ላይ አሻራው ይኖራል፡፡ ማኅበሩን በመምራት የጊዜውን ባሕር ከፍሎ ዘመናትን እንዲሻገር ከማድረጉም ይዞ የሚሻገረውንም አስጨብጦታል፡፡ “ቅድሚያ የመቀመጫዬን” እንዳለች ዝንጀሮ፤ የመቀመጫ ነገር ፋታ የማይሰጡት የመጀመሪያው ነገር ነው፡፡ በሰው ልጆች ኑሮ ውስጥም መሠረታዊ ከሚባሉት አንዱ መጠለያ ነውና ማኅበሩም መጠለያ እንዲኖረው አድርጓል፡፡ የራሱ የሆነ ቋሚ ቢሮ ያለው ተቋም እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በሥራና ጥረቱም በማኅበሩ ሲታተም ለነበረው “ብሌን” መጽሔት የዓይን ብሌን እስከመሆን ድረስ ነበር፡፡

ደበበ ለብርሃን ያለው ፍቅርና ቦታ ከምንም በላይ ይመስላል፡፡ ሁለት የግጥም መድብሎች አሉት፤ ሁለቱም ከብርሃን ጨረር ነጸብራቅ ያልራቁ ናቸው፡፡ የቀደመውን መድብል ያሳተመው ራሱ ሲሆን ከሁለተኛውን መምጣት ግን የርሱ መሄድ ቀድሞ ነበር፡፡ “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ“(የብርሃን ፍቅር ቅጽ 2) የግጥም መድብል በተለያዩ ጊዜያት የተጻፉትን ማሕበርተኛ ግጥሞቹን በማሰባሰብ በ1992 ዓ.ም ለሕትመት የበቃ መድብል ነው፡፡

በመጀመሪያው መድብል ላይ የነበሩትን ግጥሞች ስንመለከት አብዛኛዎቹ የገሀድ ዓለም የፊት መስታየቶች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ የሚጠራቸው ስሞችና ቃላት ገሀዳዊ ውክልናና ቁልጭ ብሎ የሚታይ ምስል አላቸው፡፡ ይታያሉ፡፡ ይዳሰሳሉ፡፡ ይጨበጣሉ። ከምናባዊ ረቂቅነት ይልቅ ፊት ለፊት የሚታይ የእውነት ተራራ ናቸው። ታሪክ ነጋሪና ዕውቀትን አዝማሪ የስሜት ስበት ክሮች ይጎፍርባቸዋል፡፡ በሁለተኛው “የብርሃን ፍቅር” ግን ደበበ የእይታ አድራሻ ለውጥም ጭምር ያደረገ መስሎ ይታያል፡፡

ከገሀድ ምስል ይልቅ ምናባዊ ረቂቅ ምስሎች ታጭቀውበታል። በጥቅምት አደይ አበባ ላይ ሰፍረው እዝዝ! እንደሚሉ ንቦች በግጥሙ ላይ የሰፈሩት ቃላትና ስንኞች ካየን ከሰማነው ሌላ ውብ ቋንቋ አላቸው፡፡ ብሶትና ፍርሃት፣ ትናንትናና ዛሬ ቀጥሎም ነገን የታዘሉ የሀሳብ መጫኛዎች ስሜትን ወደ ውስጥ ይደፍቃሉ፡፡ ወደ ውጭ ቦርጨቅ! እያለ በውጫዊው አካል ከሚቸለስ የስሜት ውሀ ይልቅ ውስጥን ዘልቆ በሚገባ እርጥበት ይነካሉ፡፡ ምናልባትም ደበበ ሰይፉ፤ ከውጪው ኳኳታና ሆታ ይልቅ ከራሱ ጋር ማውጋትና ራሱን ማድመጥ ማብዛት ጀምሮ ይሆናል፡፡

ቲያትር መንደር ዘልቀው ስለ ደበበ ሰይፉ የጠየቁ እንደሆን የሚነገረውና የሚናገረው ብዙ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በቲያትር መሠረታዊያን ላይ ያሳረፈው አሻራ ይነገርለታል፡፡ ቃላትን ፈቶና ገጣጥሞ ሌላ የቃላት ታንኮችን በማቆም የተካነ ነው። የባዕድ ቋንቋ አረም እንደ ሀረግ ከተጠመጠመበት የቲያትር ቋንቋ አላባውያን መካከል ለብዙዎቹ ሀገር በቀል አቻዎችን አግኝቶላቸዋል። “ሴራ”፣ “ገፀ ባህሪ”፣ “መቼት”፣ “ቃለ-ተውኔት” እና ሌሎችም በእርሱ አዋቂነት ከእንግሊዝኛው ወደ አማርኛ የተተረጎሙ ተውኔታዊ ቃላት ናቸው። ከግጥሞቹ ባሻገር ሦስት አጫጭር ልቦለዶችን ጽፏል፡፡

ከዚህም ባሻገር ደግሞ በ1973 ዓ.ም “ማርክሲዝምና የቋንቋ ችግሮች” እንዲሁም ደግሞ “የቲያትር ጥበብ ከጸሐፊ ተውኔቱ አንጻር” የሚሉትን የዕውቀት ብርሃን መጽሐፍትን አሳትሟል። በተውኔት ሥራው በርከት ያሉትን ጽፏል። ያልተናነሱትን ተርጉሞ አሰናድቷል፡፡ ከሠራቸው መካከልም “እነሱና እሷ”፣ “ከባሕር የወጣ አሳ”፣ “የሕጻን ሽማግሌ”፣ “ማክቤዝ” እና “ጋሊሊዮ ጋሊሊ” ይገኙበታል፡፡ የትምህርቱ ማኅበረሰብም ቢሆን ከደበበ ስጦታ አልተጓደለም፡፡ “ልጅቱ የዘመነችቱ” የሚለውን የማስተማሪያ ግጥሙን ያስተማረም ተምሮ ያለፈም ያስታውሰዋል፡፡

አብረውት የተማሩም ሆነ አብረውት በአጋጣሚ አፍታ ጊዜን ያገኙ ሁሉ የሚሉለት አለ፡፡ የደበበ የዕውቀት አድማስ በየአቅጣጫው ቅርንጫፉን እንዳንዠረገገ ዋርካ ነው፡፡ በዚህም አሉት በዚያ የማያውቃቸውና እንግዳ የሚሆንባቸው ነገሮች የሉም፡፡ ከእርሱ ጋር ስለ አንድ ርእሰ ጉዳይ አንስተው ሲሞግቱም፣ ሲያወጉም መጨረሻው እልፍ ርእሰ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ገባር ጅረቶቹን እየተጣራና እያስከተለ ኃይሉን ጨምሮ እንደሚገሰግሰው የዓባይ ወንዝ፤ በሀሳብ ላይ ሀሳብ፣ በዕውቀት ላይ ዕውቀትን እየጨመረ ይወነጨፋል፡፡ የኋላ በአራቱም አቅጣጫ ከበባውን ወጥሮ ሞጋቹንም የመርታት ልዩ ብቃት አለው፡፡

እርሱን በዚህ ለመግጠም አስቀድሞ ልዩ ዝግጅት ማድረግን ያስፈልግ እንደነበረ ያወሳሉ፡፡ ስለ ደበበ ሰይፉ ግጥሞችና ገጣሚነት በልበ ሙሉነት ለመናገር ከሚችሉ ሰዎች አንዱ መስፍን ሀብተ ማርያም ነው፡፡ “…ተደራሲያንን የሚመስጥ ገጣሚ ነው፡፡ ስለ ተፈጥሮ ሲገጥም ፀሐይና ጨረቃ፣ ቀስተ ደመናና የገደል ማሚቱ ያጅቡታል። …ክህደት ላይ እንደ አንድ አንድ ገጣሚያን አያላዝንም። ይልቁንስ ውበትና ሕይወትን አገናዝቦ ያውላችሁ ስሙት፣ እዩት ማለትን ይመርጣል” በማለት በአንድ ወቅት ከሚያውቀው ብዙ አካፍሎም ነበር፡፡

ደበበ ብዙ ነገሮችን ማድረግ ይፈልግ ነበር፡፡ ብዙ ነገሮች ግን ከእርሱ ወዲያ ማዶ መሆኑ ጀመሩ፡፡ ሳቅና ደስታ፣ አብሮነትና ጨዋታ ይናፍቁት ነበር፡፡ ግን ሳይታወቀው ከውጭው ዓለም እየራቀ የራሱ ብቻ ወደሆነው ውስጣዊ ዓለሙ እየነጎደ ነበር፡፡ ከላይ የብቸኝነት ግርዶሽ እየተጋረደ፣ ጥላው ወደራሱ ማጠር መደብዘዙን ጀመረ፡፡ በብዙ ሰዎች ተከቦ በሕይወቱ ውስጥ ከራሱ ምስል ውጭ የሚታየውም ሆነ የሚያየው አልነበረም።

ጆሮን የሚያደነቁር ጫጫታና ወከባ ውስጥ ተቀምጦ የሚሰማው ግን ጭው! ካለ በረሃ ውስጥ እንዳለ ነበር፡፡ የቅርቡና በቅርቡ ከነበሩት መካከል አንደኛው ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ይገኛል፡፡ ከሞቱ ሁለት ዓመታትን ቀደም ብሎ ከአንድ ሚዲያ ጋር ባደረገው ቆይታ “…በኑሮው ውስጥ የደረሰበት ግላዊና ማኅበራዊና ቀውስ ይኖራል፡፡ እንደ ፍቅር እጦት ብቸኝነትን የሚፈጥር የለም…” ከሚል ሀሳብ ጋር ስለ ደበበ ሕይወት ተናግሮ ነበር፡፡

ብቸኝነት ባጠላበት የድባቴ ሕይወት ውስጥ ፊቱ የተደነቀረውን ተራራ ለመውጣት ሲል የኋላም መጠጥን ወዳጁ አደረገ፡፡ በታመመበት ወቅት ከቤቱ ርቆ መሄድም ሆነ ሌላ የሚሄድበት ቦታ አልነበረውም፡፡ ትናንት ከደጁ ላይ ወጥቶ የሞቃትን ጸሐይ ዛሬም ይሞቃታል፡፡ የትናንቱን ሰማይ መልሶ ዛሬም ይመለከተዋል፡፡ ከበራፉ ላይ ቁጭ ማለትን አብዝቶ ማዘውተር ጀመረ፡፡ ብዙውን ጊዜ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ አተኩሮ መመልከትን ይወዳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እየመጡ አብረውት ለመሆኑ ቢፈልጉም እርሱ ግን ብቻውን መሆንን ይመርጥ ነበር፡፡ አንዳች ደስ የማይል የትዝታ ስንቃር ውስጥ የገባም ይመስላል፡፡ ምናልባትም ደግሞ ሕይወት ያደረሰችበትን በደሎች እየቆጠረም ይሆናል።

በተለይ በሥራ ኃላፊነት በነበረባቸው ጊዜያቶች ክፋትን በመቃወሙ የኋላ የመንግሥትን ለውጥ ተገን አድርገው የበደል ዱላቸውን ያወረዱበት እንደነበሩ በቅርብ እማኝነት የሚናገሩ አሉ፡፡ በዚያም ይሁን በዚህ የሚታየውና ጭለማ ይወረሰው ምስል ፊቱ ድቅን ይል እንደነበረ እርግጥ ነው፡፡ ሕመሙ እየጠና ሲሄድ በዝምታ ወደ አርምሞ ሜዳ መግባት ጀመረ፡፡ እንዲያ ሆንኩ እንዲህ ተሰማኝ ብሎ የሚናገረው ምንም የለም፡፡

ጎርነን ፈንጠቅ ብሎ ልብን የሚያረሰርሰው ድምጹ እምብዛም አለመናገርን መረጠ፡፡ ለማንም ከማንም፤ ለአንድ እናቱ ብቻ ለእርሷም ቢሆን የሚሰጣት ፍቅር የተሞላበትን ፈገግታውን ነበር፡፡ እንደሌላው ሁሉ ትዳር መስርቶ፣ ከቀለሰው ጎጆ በታች ሦስት ጉልቻ አቁሞና በደስታ ኖሮ በደስታ ማለፍን ይፈልግ ነበር፡፡ ግን ሲፈልግ…እንደፈለገም ሳያገኝና ሳይገናኝ እንደሆነ ሆኖ ለሰባት ዓመታት እንደታመመ ከረመ፡፡ በብቸኝነት ጫፍ ደርሶ፣ እስከጫፍ ብቸኝነቱ ከሮ፣ በብቸኛው ሞት ተበጠሰ፡፡ ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም በሞት ተነጠቀ፡፡

ተይው እንተው

የዘመን ቃፊሩን

ማለፍ አልቻልንና

ይህ ዓለም ጥበቱ

አልመጠነንና

ተይው እንተው፡፡

እንዳለውም ሁሉንም ሆድ ይፍጀው ሲል ትቶ ሄደ፡፡ ሕይወትና ኑሮ ካስጣሉት ይልቅ ለኛ የተወው እጅግ ብዙ ነው፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You