«በዓሉን የምናከብረው ስለሰላም በማስተማርና የተቸገሩትን በመርዳት ሊሆን ይገባል»  – ሼህ አብዱልሃሚድ አሕመድ(በኢትዮጵያ አስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት የመውሊድ በዓል ዋና አስተባባሪ)

የነቢዩ መሐመድ የልደት ቀን በበርካታ ሀገራት በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበር ሀይማኖታዊ በአል ነው። በዓሉ በሀገራችን ኢትዮጵያም በአስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው። የዘንድሮውን የኢድ አለ አድሃ በዓልም በሀገራችን እንደተለመደው ሁሉ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር የተለያዩ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ይገኛል። እኛም ይህንን አስመልክቶ በኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት የነብዩ መሐመድ የልደት ቀን መታሰቢያ የመውሊድ በዓል ዋና አስተባባሪ ሼህ አብዱልሃሚድ አሕመድ ጋር የነበረንን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፤ የመውሊድ በዓል በእስልምና ኃይማኖት ከሚከበሩ በአላት መካከል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። በአሉ የሚከበርበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው ?

ሼህ አብዱል ሃሚድ፤ «መውሊድ» የሚከበረው ታላቁ ነብይ፤ ነብዩ መሐመድ መወለዳቸውን ለማሰብ ነው። አላህ በቁርአን ውስጥ «አላህ በሰጠን ሰፊ ችሮታ እና በአላህ እዝነት» እንድንደሰት ተነግሮናል። በዚህም መሰረት አንደኛ የእሳቸው ወደዚች ዓለም መምጣት ለዓለም እዝነት ተልከው በመሆኑ፤ ሁለተኛም ቀኑ በእሳቸው ምክንያት ከጨለማ ወደብርሃን የወጣንበት፤ የተሸጋገርንበት በመሆኑ ነው። በዚህ ምክንያት መላው ሕዝበ ሙስሊም እነዚህን መልካምና ምድራዊም ሰማያዊም ስጦታዎች በማሰብ በደስታና በመረዳዳት የሚያከብረው በዓል ነው።

አዲስ ዘመን፤ የበዓሉ አከባበር ምን ይመስላል?

ሼህ አብዱል ሃሚድ፤ የመውሊድ በዓል የሚከበረው በመስኪድና በየመኖሪያ ቤትም ነው። በእለቱ በመስኪድ ክብረ በዓሉ የሚከናወነው የነቢዩ መሐመድን መልካም አስተምህሮ ለመላው የእስልምና እምነት በማስተማር። እንዲሁም የእስልምና እምነት ተከታይ በሙሉ የእሳቸውን መልካም ስነ ምግባር እንዲይዝና እንዲከውን ለማድረግም ነው። ይህ አስተምህሮ ለሕዝቡ የሚደርሰውም በሁለት አይነት መንገድ ነው። አንደኛው በስድ ንባብ መልክ ለሙስሊሙ ማሕበረሰብ የሚቀርብ ሲሆን መነሻው የሚያደርገውም እሳቸው ከተወለዱ ጀምሮ እስከሞቱ ድረስ ያለውን ከሚገልጹ ኪታብ / መጻህፍቶችን ነው። ሁለተኛው ደግሞ እንደ ግጥም መድብል ተዘጋጅቶ በዜማ የሚቀርበው መንዙማ የሚባለው ነው።

በመንዙማ መልክ የሚቀርበው ሕዝበ ሙስሊሙ በቀላሉ መልእክቱን ተረድቶ፤ ገብቶት እሳቸውን እንዲወድ ለማድረግ ሁነኛ መንገድ በመሆኑ ነው። እነዚህ መልእክቶች የሚተላለፉትም በአረብኛ ቋንቋ እና ከሀገር ውስጥም በአማርኛ በኦሮምኛና በሌሎችም የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ይሆናል። ይህ ነገር ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን የቀደሙት አያት ቅድም አያቶቻችን ያዘጋጁልን ነው። አብዛኛው ሕዘበ ሙስሊም ይህንን ዜማ ደጋግሞ በመስማት በቃሉ የያዘው በመሆኑ በመቀባበል በዜማ የሚያደርሰው ይሆናል። በዚህ ሂደት ግጥሙን የሚያወጣውን ሰው የማዳመጥና የመደጋገም አካሄድም አለ።

በእለቱ የመንግስት ኃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ የክብር እንግዶች የሚገኙ ይሆናል። እነዚህ የክብር እንግዶችና በእለቱ የሚገኙ የሀይማኖቱ ምሁራንና አባቶች ከሀይማኖቱ አስተምህሮ ባለፈ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያም የሚያስተላልፏቸው መልእክቶች ይኖራሉ። በተለይም ዋናው ጉዳይ የሚሆነው የሰላም ጥሪ ነው። በዚህም የውስጥ ግጭቶችን ማቆም እንዳለብን እነዚህ ግጭቶች እንደ ሕዳሴው ግድብ የባሕር በር የማግኘት እንቅስቃሴ ለሚቃወሙ ሀገራት ሕብረታችንንም ለማሳየት የሚጠቅም መሆኑን እንገልጽበታለን። በተጨማሪም በእለቱ በተለያዩ ቦታዎች የችግኝ ተከላን ጨምሮ የሚከናወኑ ሌሎች መረሃ ግብሮችም ይኖራሉ።

አዲስ ዘመን፤ የነብዩ መሐመድ መልካም ስነምግባርና የሰላም መልእክቶች እንዳሉ ይታወቃል፤ ከእነዚህ ውስጥ ቀዳሚ የሚባሉትን ቢያብራሩልን ?

ሼህ አብዱል ሃሚድ፤ ነብዩ መሐመድም ሆኑ ከእሳቸው በፊት የነበሩት ነቢያቶች፣ መልእክተኞች ወደሰው ልጆች የተላኩት መልካም ስነ ምግባርን ለማሟላት ነው። ሁሉም ነብዮች የሰውን ልጅ ከአውሬነት ወደ ሰብአዊነት እንዲመለስ። ጥሩና የተስተካከለ ስነ ምግባር እንዲኖረው ለማድረግ እያስተማሩ የመጡ ናቸው። ነብዩ መሐመድ ደግሞ «የእኔ መምጣት ከዚህ በፊት የነበሩትንና የሰውን ልጅ ወደ መልካም ስነ ምግባር ሲመሩ የነበሩትን ነብያቶች ለማሟላት ነው» ብለዋል ።

ሁለተኛ ደግሞ አላህ በቁርአን ለይ « አንቱ የታላቅ ስነ ምግባር ባለቤት ነዎት » ብሎ ያወድሳቸዋል። በተጨማሪ ነብዩ መሐመድ በሕይወት እያሉ ቂም አይዙም፤ በቀልም አይበቀሉም ነበር። ይህንን ነገር ደግሞ በሕይወታቸው ሙሉ ያደረጉት ነገር ነው። ይህ ከእሳቸው ስነምግባር ከምንወስዳቸውና ለሰው ልጆች መማሪያነት ከሚያስፈልጉት መካከል አንዱ ነው።

በተጨማሪ ነብዩ መሐመድ ፊታቸው በፈገግታ የተሞላ የበላዮቻቸውን ሲያከብሩ የነበሩ ፤ ከበታቾቻቸው ለነበሩት ሁሉ ከፍተኛ እዝነት የነበራቸው፣ በአጠቃለይ ከማሕበረሰቡ ጋር መልካም ግንኙነት የነበራቸው ናቸው ። ከዚህም በላይ ደግሞ በዘመኑ በመዲና ውስጥ እንደ አይሁድ እና ክርስትና እምነት ተከታይ ከነበሩ ሰዎች ጋርም ጥሩ ግንኙነት የነበራቸውና በመልካም ስነ ምግባር አብረው ሲኖሩ የነበሩ ናቸው።

በቂያማ ቀን ማለትም ሞተን ከተነሳን በኋላ ፍርድ እንዳለ አስተምረውናል። በዛ ውስጥ ወደ ገነት ለመግባት የሚችለው ሰው መልካም ስነ ምግባሩ በልጦ የተገኘለት ሚዛን የደፋለት እንደሆነም ነግረውናል። ከዚህም ባለፈ የቂያማ ቀን ከጎኔ የሚቀመጠው መልካም ስነ ምግባር ያለው ሰው ነውም ብለዋል። የሰማይ ቤቱን የሚያስተካክል ለወላጅ፤ ለትዳር አጋር፤ ለልጆች ጥሩ ስነ ምግባር ያለው ሰው ነው ብለው ይመክራሉ ።

ከዚህም ባለፈ ከጎረቤቶቻቸንም ጋር በሚኖረን ግንኙነት በመልካም ስነ ምግባር ልንኖር እንደሚገባ አዘውናል። አጠቃላይ የእስልምና እምነት የሚያዘው እሳቸውም የሚያስተምሩት የሰው ልጅ በምድር በቆየበት ግዜ በመልካም ስነ ምግባርና በጥሩ ባህሪ መኖር እንደሚገባ ነው።

ዛሬ ለይ እንደ ሀገር በእስልምና እምነት ብቻ ሳይሆን በክርስትናውም ቢሆን ስነ ምግባር በማስያዝ ረገድ የሀይማኖት አባቶች ብዙ አልሰራንም። በዚህም የተነሳ በዚህ ዘመን በርካታ የስነ ምግባር ጉድለቶችን በማሕበረሰቡ በተለይም በወጣቱ ትውልድ ላይ እያየን እንገኛለን። በዚህም የተነሳ ብዙዎቻችን በአንድ ወገን ሀይማኖታችንን በስርዓት ስንከተል ስናከብርና ስንገዛ አንታይም።

ሁለተኛም በመልካም ስነ ምግባር መጠበቅ ረገድ እንደ ማሕበረሰብ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን በርካታ ባሕልና ትውፊቶቻችንን እየለቀቅን እየሄድን እንደሆነም በግልጽ የሚታይ ነው። እንደ ግለሰብ ታላቅ ታናሹን ልጅ ወላጁን ማክበር እየተወ መጥቷል፤ ሙስና እና ጥቅመኝነትም ውሎ ባደረ እየተስፋፋ መጥተዋል፤ የዜጎች መንግስትን የማያዳምጥና የመታዘዝ ሁኔታም እየቀነሰ ነው ።

እንደ ማሕበረሰብም ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር ሰላም ማጣት አለመካባበርና መናናቅ ይታያል። ትንንሽ አጀንዳዎችን በመያዝ እያጋጋሉ በመንቀሳቀስ ሀገር ወደማፍረስ የሚደርስ አካሄድም ይስተዋላል። በእርግጥ ይህ እውነታ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በርካታ ሀገራትም የሚስተዋል ወቅታዊ ችግር ነው። ችግሩን ለመቅረፍ መሰራት ያለበት ደግሞ መልካም ስነ ምግባርን ወደ ሰው ልጆች ላይ በማምጣት መሆን አለበት።

ለምሳሌ ከዚህ ቀደም በነበረው ሂደት የነበሩ ማለትም ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ ቁጥጥር የሚደረግበት ብቻ ሳይሆን ለስነምግባር ሲሰጡ የነበሩ ትኩረቶች ዛሬ አይታዩም። እስከ ቅርብ ግዜ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ ከሌሎች ጓደኞቻቸውና ከመምህራኖቻቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጸባይ ተብሎ ኤ.. ቢ… ሲ…ዲ… እየተባለ በካርድ ላይ ውጤት የሚቀመጥበት አሰራር ነበር። ይህ ነገር ዛሬ ላይ በመቀዛቀዙ በብዙ መልኩ እየጎዳን እይገኛል።

ይህ የስነ ምግባር መጓደል የነገ ሀገር ተረካቢ በሆነው በወጣቱ ትውልድ ላይ ሲሆን የሚፈጥረው ተጽእኖ ትልቅ ነው። ወጣቱ ትውልድ የተማረ አምራችና ትኩስ ኃይል ያለው መሆኑ ይታወቃል። ይህንን እምቅ ኃይል ሊጠቀምበት የሚገባው ለሀገርና ለሕዝብ በሚጠቅም መልኩ በስነ ምግባር የታነጸ በመሆን ለበጎ ነገር ብቻ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ሀገርን ለመረከብና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ከቀደሙት አባቶች ያነሰ ሳይሆን የተሻለ ሆኖ ሊገኝ ይገባዋል።

ሀገርን ማሳደግ ሕዝብን መደገፍ በዘመናዊ ትምህርት እውቀት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። በቴክኖሎጂ እና በሌሎች እውቀቶች ምንም ያህል የተራቀቀ ቢሆንም የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ማመዛዘን የሚችልና ለይቶ የመቀበል ብቃቱ ትልቅ ካልሆነ ዋጋ አይኖረውም። በመሆኑም ይህንን ለመሻገር እያንዳንዱ የሀይማኖት አባት ልጆችን በስነ ምግባር በማነጽ ረገድ ጠንካራ ስራ መስራት የሚጠበቅበት ይሆናል።

አዲስ ዘመን ፤ የመውሊድ በአል ከኢድ አልፈጥርና ከኢድ አል አድሃ የሚለየው በምን መልኩ ነው ?

ሼህ አብዱል ሃሚድ ፤ በእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበሩ ሶሰት ሃይማኖታዊ በዓላት መውሊድ፤ ኢድ አልፈጥር እና ኢድ አል አድሃ ናቸው ። ኢድ አልፈጥር አንድ ወር ቀኑን ሙሉ እየተጾመ ሌሊቱንም በመቆም የምስጋና ሰላት በመስገድ የሚከናወን ነው። ሁለተኛው የኢድ አል አድሃ በአል ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እስማኤልን እንዲያርዱ ታዘው ነበር ። ይህን ታሳቢ ያደረገ ታሪክ ያለው ነው። ይህም ለወላጅ የሚታዘዝ መልካም ልጅ እንዲኖር እኛን ለማስተማር የተቀመጠ ትልቅ የምስጋና ቀን ነው።

ኢድ አልፈጥር እና ኢድ አል አድሃ በዓላት ከነብዩ መሐመድ በኋላ የመጡና እሳቸው ያስተማሯቸው ናቸው። እኛ ከኢድ አልፈጥር እና ከኢድ አል አድሃ በላይ አስበልጠን የምናከብረው የመውሊድ በአልን ነው። ምክንያቱም ከኢድ አልፈጥር እና ከኢድ አል አድሃ የሚከበሩት ነብዩ መሐመድ በመፈጠራቸው ነው። አከባበሩንም ስናይ በኢድ አልፈጥር እና በኢድ አል አድሃ በአል ሕዝበ ሙስሊሙ በመስኪድ ወይንም ሀይማኖቱ በሚከበርበት ቦታ ተሰባስቦ ከሰገደ በኋላ ወደ የቤቱ የሚመለስ ይሆናል። የመውሊድ በዓል ሲሆን ግን ከጠዋት ጀምሮ የነብዩ መሐመድን ስም በማንሳት ቁርአን በመቅራት የሚከበር ይሆናል። በተጨማሪ በየቤታችን ጣፋጭ የሆኑ ምግቦችን በማዘጋጀትና በመንዙማ ምስጋና የሚከበር በመሆኑ ለየት ይላል።

አዲስ ዘመን፤ በኢትዮጵያ የሚከበረው የመውሊድ በዓል ያለው ገጽታ ምን ይመስላል ?

ሼህ አብዱል ሃሚድ፤ በእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ሪፎርም ከመጣ ሶስት ዓመት እየደረሰ ነው። በእነዚህ ግዜያትም በየዓመቱ ለመውሊድ በአል ከፍተኛ በጀት በማውጣት ሰፊና አስተማሪ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ይገኛል። በፌደራል ደረጃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚከበረው አዲስ አበባ በሚገኘው በታላቁ አንዋር መስኪድ ነው። ለዘንድሮም « የሰላሙ ነቢይ » የሚል መሪ ቃል የተቀመጠ ሲሆን ይህም የተደረገው የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በማየት ትኩረቱ ሰላም ላይ እንዲሆንና ሕዝቡን ስለ ሰላም ለማስተማር ነው። ከዚህም ባለፈ ሰላም ዋነኛ መልእክት የሆነው በእስልምና አስተምህሮ ነብዩ መሐመድ ስለ ሰላም ያስተማሩትን በተገቢው መንገድ ለሕዝበ ሙስሊሙ ተደራሽ ለማድረግም ነው።

በአሁኑ ወቅት በተደጋጋሚ በሀገራችን እንዳየነው በተፈጥሮ የሚከሰቱና ሰው ሰራሽ ችግሮች ዜጎችን ለተለያዩ ጉዳትና መከራ እየተዳረጉ ይገኛሉ። በተፈጥሮ ጎርፍ፤ የመሬት መንሸራተት፤ የአንበጣ ወረርሽኝ መከሰት፤ የእሳት አደጋ የመሳሰሉት ሲከሰቱ እርስ በእርስ በመረባረብ በመደጋገፍ የደረሰውን ጉዳት መታደግ የምንችልበት ሆኖ ተገኝቷል። ሁለተኛው እና አስቸጋሪ የሆነው የችግሩ ምንጭም የጉዳቱ ሰለባም እኛው የሆንባቸው ሰው ሰራሽ ችግሮች ናቸው። ከእነዚህም መከካል በብሄር፤ በጎሳ፤ በድንበር… ሌሎች ማንነቶች በተፈጠሩ አለመግባባቶች የሚከሰቱ ጦርነትና ግጭቶች ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ነገሮች ተምሯል የተሻለ ያስባል የሚባለውንም ማሕበረሰብ የሚመለከቱ ናቸው። በውጤቱም ግለሰቦች ጥረው ግረው ያፈሯቸው ንብረቶች እንዲወድሙ መንግስትም ከድህነት ለመውጣት በከፍተኛ ወጪ ያስገነባቸው ሕዝብ የሚገለገልባቸው መሰረተ ልማቶችና ሌሎች ሀብቶች እንዲወድሙ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ክቡር የሆነው የሰው ለጅ ለሞት እንዲዳረግ ከመኖሪያው እንዲፈናቀልና ለተለያዩ አሰቃቂ ችግሮች እንዲጋለጥ የሚያደርጉ ናቸው።

የሰው ልጅ በምድር እስካለ ድረስ አለመስማማት አለመግባባት መፈጠሩ አይቀሬ ነው። ነገር ግን ምንም ቢፈጠር ሰላሙን ሊያመጣው የሚችለው ራሱ የሰው ልጅ ነው። የእስልምና እምነት መሰረተ ሃሳቡ ሰላም ነው። ሶላት ተሰግዶ ሲጨረስ በሰላምታ ነው። ነቢዩ መሐመድ ከመካ ወደ መዲና ተሰደው ሲሄዱ የመጀመሪያ መልእክት ሰላምን አብዙ በመካከላችሁ ሰላምን አስፍኑ ነው።

በሀይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት የምንወርሳቸው ስምንት ጀነቶች አሉ ከእነዚህ አንዱ «ዳረ ሰላም» የሰላም ሀገር ነው። በዓመት ከሶስት መቶ ስልሳ አምስቱ ቀን አንዱን ሌሊት የሰላም ሌሊት በማለት እናሳልፋለን። ሶስት መቶ ስልሳ አምስቱን ቀን ሰላም ማድረግ ይቻላል ነገር ግን አንዷን ቀን ለዚህ እንድናስብ ለሰላም ትኩረት እንድንሰጥ ተደርጓል። ይህ የሚያሳየን ከሰላም የሚቀድም ከሰላም የሚበልጥ ነገር አለመኖሩን ነው።

አዲስ ዘመን፤ የመውሊድ በዓል ከአንድነትና ከመቀራረብ አንጻር ያለው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል ?

ሼህ አብዱል ሃሚድ፤ ከላይ እንዳነሳሁት ነብዩ መሐመድ እንኳን በእስልምና ሀይማኖት ስር ይቅርና ቀኖናችን መንገዳችን መጻህፋችን የተለያየ ቢሆንም ከሁሉም ጋር በሰላም በመኖር እንዳለብን በቂ ትምህርትና ምክር ሰጥተውናል። ነብዩ መሐመድ በሀዲስም በደንብ አድርገው አስቀምጠውልናል። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሌሎች ጋር አብሮ በመኖር ረገድ ትልቅ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን።

ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ሀገርም ናት ይህንን ማስቀጠል ከእኛም የሚጠበቅ ይሆናል። ኢትዮጵያ በእስልምናውም በክርስትናውም አብሮ በመኖርም በመቻቻልም ከሌላው ዓለም የተለየች ናት። እሳቸው በሰላም ረገድ ምሳሌ መሆናቸውን ማወቅና መተግበር ዛሬ ለይ ካለው ሕዝበ ሙስሊም ይጠበቃል። በዚህም መሰረት ሕዝበ ሙስሊሙ የነብዩ መሐመድ ልደትን ሲያከብር አዲስ የተፈጠረ ሳይሆን ለዘመናት የቆየውን አብሮነትና መቻቻል ባሕል ማጎልበት ማሳደግ አለበት። በተጨማሪም ሀገሪቷ የጀመረችውን ልማትና የሰላም ጉዞ ማስቀጠል የአያንዳንዳችን ኃላፊነት መሆኑን ልንገነዘብም ይገባል።

አዲስ ዘመን፤ በሀይማኖቱ አስተምሮ በዓሉ በምን መልኩ ሊከበር ይገባል ?

ሼህ አብዱል ሃሚድ ፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች መውሊድን ምክንያት በማድረግ ያላቸው ሰዎች የተቸገሩትን መርዳት የታመሙትን መጠየቅ ጎረቤትን መጎብኘት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ግዴታም ነው። በታላቁ አንዋር መስኪድ መውሊድን ምክንያት በማድረግ ወቅቱ አዲስ ዓመትና የትምህርት መጀመሪያ በመሆኑ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት መሳሪያዎች ድጋፍ ይደረጋል። ልጆች እየተራቡ ረሀባቸውን እያሰቡ በስነ ስርዓት ሊማሩ አይችሉም በመሆኑም በትምህርት ቤቶች ለሚከናወኑ የምገባ መርሐ ግብሮችም የሚደረጉ ድጋፎች ይኖራሉ።

አዲስ ዘመን፤ የነብዩ መሐመድ ታሪክ ሲነሳ አብሮ የኢትዮጵያም ጉዳይ ይነሳል። ነብዩ መሐመድ ለኢትዮ ጵያ ያላቸው አመለካከት ምን ይመስል ነበር ?

ሼህ አብዱል ሃሚድ፤ ነብዩ መሐመድ ሲወለዱ ኡሙ አይመን የሚባሉ ኢትዮጵያዊ ሴት አጠገባቸው ነበሩ። በኋላ ያሳደጓቸውም እሳቸው ነበሩ። ነብዩ መሐመድም ኡሙ አይመንን ከእናቴ በኋላ እናቴ ናት ይሉ ነበር። ሁለተኛ ነብዩ መሐመድ ኢማም አሰጋጅ ናቸው ለዚህም ወደ ሰላት ሰው ለመጥራት ሙአዚን የሚባል አለ ለአዛኑ ጥሪ የሚያደርገውም ቢላል የሚባል ኢትዮጵያዊ ነበር።

ለዚህም ቢላል አል ሀበሺ ታማኝ የሆነ ሰው ነበር ። ሶስተኛ እሳቸው ተወልደው ባደጉበት ንብረት ባፈሩበት በመካ ሀገር ባይተዋር እንግዳ ተደርገው የተለያዩ ችግሮች ሲደርሱባቸው፤ ተከታዮቻቸውንና የቅርብ የስጋ ዘመዶቻቸውን በመጨመር ወደ ሀበሻ ኢትዮጵያ ሂዱ፤ እዛ ፍትሃዊ የሆነ መሪ አለ የሰው ልጅ እሱ ዘንድ አይበደልም በማለት እኛ ኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ እንደሆንን እና በደል እንደሌለ የመሰከሩልን ናቸው።

መካ ላይ ቁርአን እንዳይቀራ ሲታገድ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ውቅሮ ለይ በቤተ መንግስት ሱረቱ መሪየም የሚባል ከመሪየም ጋር የተያያዘ አንቀጽ ተነቦ እንዳለቀሱና እንዳነቡ የሚገልጽ በቂ መረጃ አለ። በተጨማሪ በታሪክ ዓለምን ይመሩ የነበሩት ሶስት ሀገራት ማለትም ፐርሺያ፣ ሮማውያን አና ኢትዮጵያ ነበሩ። በዚያ ዘመንም ኢትዮጵያ አረብ ሀገራትን ጨምራ ትመራ ነበር በወቅቱም የራሳችን ፊደል የነበረን ቢሆንም ቋንቋውም የሚወራረስ ሆኖ ዛሬም ድረስ ዘልቋል። በእነዚህ ነገሮች ሁሉ እኛ ኢትዮጵያውያን ለነብዩ መሐመድ ልዩ ፍቅር እንዲኖረን አድርጓል።

አዲስ ዘመን ፤ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ለእስልምና እምነት ያበረከ ተችውን አስተዋጽኦ እና ውለታ እንዴት ያዩታል ?

ሼህ አብዱል ሃሚድ፤ በነብዩ መሐመድ ትእዛዝ መሰረት ወደዚህ የመጡት ቤተሰቦቻቸው የተደረገላቸው አቀባበልና መስተንግዶ ዋናው ነው። እዚህ የመጡትን ተከትለው የመጡ ከሳሾች ነበሩባቸው እግርና እጃቸውን በሰንሰለት አስረው ለመቅጣትም ብዙ ወርቅና ብር ስጦታ የያዙ ንጉሱን አታለው ሀሳባቸውን ለማሳከት ሞክረው ነበር። ነገር ግን በወቅቱ ንጉሱ ነብዩ መሐመድ እንደ መሰከሩለት ፍትሃዊ ስለነበር የአንዱን ወገን ቃል ብቻ ሳይሰማ ቤተ መንግስት አስጠርቶ የሁለቱንም በማዳመጥ ፍትሃዊ ዳኝነት ሰጥቷል።

ከዚህም ባለፈ ሀገራችሁ ሰላም ሰፍኖ እስክትመለሱ ድረስ እንደ ፈለጋችሁ እንደ ዜጋ እንድትኖሩ የሚል መልእክት ነጃሺ አስተላልፈው ነበር። በወቅቱ ነብዩ መሐመድ ሊያገቧት የፈለጓት ሴት ስለነበርችም ከስጦታ ጋር ኒካህ «የጋብቻ ቀለበቱን» ያሰሩት ንጉሱ ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያ ምንም በደል ሳይደርስባቸው ጥሩ ዳኝነት አግኝተው በደስታ የኖሩባት ሀገር ናት።

እኛ አሁን ያለነው ኢትዮጵያውያን ከዚህ ብዙ ልንማር ይገባል። በአድ ለሆኑት አረቦች እንዲህ የሆንን ይህንን የመሰለ ፍቅርና ፍትህ የሰጠን… በዚህ ደረጃ በሰላም ማስተናገድ የቻልን ነን። ታዲያ እኛ አንድ ላይ ሆነን አንድ ደም ሆነን፤ አንድ ባንዲራ አንድ መሪ እያለን እርስ በእርስ ልንጠፋፋ ልንጎዳዳ አይገባም። አላስፈላጊ ነገር ውስጥ ሀገራችንንም ሕዝባችንንም ልናስገባ አይገባም።

ሀገራችን በቂ ሀብት አላት ተስማምተን ተፋቅረን በዛ ልንጠቀም ይገባል። ለዚህም በአሁኑ ወቅት አንድ እድል አለን እሱም ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ነው። ይህንንም እውን ለማድረግ የምክክር ኮሚሽኑ ለይ ሁሉም መሳተፍ ይጠበቅበታል፤ ከምሁራንም ሀገሪቱ አንድነቷ እንዲጠበቅ መስራት.. የፖለቲካ ሰዎችና አክቲቪስቶችም አላህን በመፍራት ማሕበራዊ ሚድያዎችን ለበጎ ዓላማ ብቻ ሊጠቀሙ ይገባል። መንግስትም የሕብረተሰቡን ችግር እታች ድረስ ዘልቆ በማየት ችግሩን ለመፍታተ መስራት አለበት። በተለይም በኑሮ ውድነት የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍ ሕዝቡን ከድህነት ለማውጣት መስራት ይጠበቅበታል። አዲስ ዘመን ፤ ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፤

ሼህ አብዱል ሃሚድ ፤ እኔም አመሰግናለሁ ፤

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You