አንዴ ለመቁረጥ አስር ጊዜ ለካ የሚል ብሂል አለ። በዚህ ብሂል ሊተላለፍ የሞከረው ትልቅ መልዕክት ከተግባር በፊት ማሰብ ይቅደም የሚል ነው። እውነት ነው በትክክለኛ ሃሳብ ያልተመራ ተግባር መጨረሻው ውድቀት እንደሆነ የሚያሳዩ እልፍ መረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። በቤተሰብ፣ በአገርም ሆነ ለማንኛውም ዓላማ በሚፈጠሩ ቡድኖች መካከል የአስተሳሰብ አንድነት ካልተፈጠረ ተፈላጊው ውጤት እንደማይመጣ ሳይታለም የተፈታ ነው።
አንድን ተልዕኮ በስኬት ለመፈጸም ቀደም ብሎ በሃሳቡ ላይ መከራከር መወያየትና የጋራ አስተሳሰብ መያዝን ይጠይቃል። ከዚህ በኋላ ምን ለመስራት እንደተፈለገና ማን ምን መስራት እንዳለበት ስለሚታወቅ ተግባርን በስኬት ለመፈጸም አመቺ ይሆናል። በመስመሩ ላይ እየተጓዘ ያለውንና ያፈነገጠውን በመለየትም የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
በዚህ ሃሳብ የተንደረደርነው አገር በመምራት ላይ የሚገኘውን መንግስትና አስፈጻሚ አካላቱን የአስተሳሰብ አንድነታችሁ ምን ድረስ ነው? በተደጋጋሚ እንደምትሉትስ የአስተሳሰብ አንድነት ፈጥራችኋል ወይ ስንል ተጨባጭ መረጃዎችን በማንሳት ለመሞገት ነው። ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው በአሁኑ ወቅት በምርጫ ስልጣኑን ተቆጣጥሮ አገር እያስተዳደረ ያለው ኢህአዴግ ነው።
ስለዚህ ኢህአዴግ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን መንግስትም ነው ማለት ነው። ኢህአዴግ የአራት ብሄራዊ ፓርቲዎች ጥምረት እንደመሆኑም ለሚወስናቸው ውሳኔዎችና ለሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች ስኬት በድርጅቶቹ መካከል የሚፈጥረው የአስተሳሰብ አንድነት ወሳኝ ድርሻ አለው።
ኢህአዴግ እንደ ደርጅት ሁሌም ሰብሰባዎችና ካካሄደ በኋላ በሚያወጣው መግለጫ የአስተሳሰብ አንድነት ፈጥሮ መውጣቱንና ይህንንም በመንግስታዊ ተግባሩ እንደሚተግበር ሳይታክት ያስታውቃል።
ይሁንና መግለጫው ከተገለጸ በኋላ ግን የአስተሳሰብ አንድነቱ በተግባር የማይገለጽበት ሁኔታ ደጋግሞ ይስተዋላል። ይህንንም በብሄራዊ ድርጅቱ ስር ያሉ ፓርቲዎች በሚያወጡት ተቃራኒ መግለጫና አቋም በያዘባቸው ጉዳዮች በሚታዩ የአፈጻጸም መዛነፎች ይገለጻል።
ሌላውን ለጊዜው ትተን የአስተሳሰብ አንድነት እንዳልተፈጠረ ከሚያሳዩ ጉዳዮች መካከል የህግ የበላይነት ማረጋገጥን የተመለከተውን እናንሳ። መንግስት እንደ መንግስትም ሆነ ኢህአዴግ አገር እንደሚመራ ፓርቲ ሁሌም ጠንካራ አቋም ይዘው ከሚገልጿቸው ጉዳዮች ቀዳሚው የህግ የበላይነትን ማስከበሩ ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ መሆኑንና ይህንኑ ለማስተግበር ቁርጠኛ አቋም እንደተያዘ ነው። ይሁንና እንደመንግስትም ሆነ አገር እንደሚመራ ፓርቲ ደግሞ በድክመት ሁሌም የሚነሳ ጉዳይ ቢኖር የህግ የበላይነት ማስከበር ላይ ያለው ክፍተት ነው።
ይህም እውነታ በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ የአስተሳሰብ አንድነት ተፈጥሯል ወይ የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል። የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሃሳብ አንድነት ፈጥረናል ከተባለ በኋላ ህገወጥ ድርጊቶችን የፈጸሙ አካላትን ለህግ አሳልፎ ለመስጠት የተለያዩ ምክንያቶች የሚደረደሩ ከሆነ፣ የዜጎች መፈናቀልን ለማስቆም ከልብ ካልተሰራና ህግ የተላለፉት አካላትን በህግ ፊት አቅርቦ ተፈላጊውን የእርምት እርምጃ ማስወሰድ ከተሳነ በጉዳዩ ላይ የአስተሳሰብ አንድነት እንዳልተፈጠረ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ የአስተሳሰብ አንድነቱን ለማምጣት ግልጽ ውይይትና ሰፋፊ የክርክር መድረኮች አስፈላጊዎች መሆናቸው ነው። ይሁንና እነዚህ ሂደቶች ታልፈው የጋራ የተደረገ አስተሳብብና አቅጣጫን መተግበር ግን የሁሉም አካላት ግዴታ ነው።
የጋራ አስተሳሰብ ተፈጠረ የሚባለው ደግሞ በአቋም መግለጫ ስለተንጸባረቀ ወይም እንዲህ ልናደርግ ነው በሚል መግለጫ ሳይሆን በተጨባጭ ተግባራት ነው። መንግስት የህግ የበላይነት የሚጣረሱ ተግባራትን እንደማይታገስና አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚውስድ ምሎ ተገዝቶ ቢናገርም የህግ የበላይነትን የመሸርሸሩ ስራ ተደጋግሞ እየስተዋለ ነው። በዚህ ደግሞ በርካታ ወገኖች ከገዛ አገራቸው እየተፈናቀሉ፣ ውድ ህይወታቸውን እያጡና ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩት ሀብት እየወደመባቸው ነው።
ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው የመንግስት መኖር ዋነኛ ፋይዳ ዜጎች በመንግስታቸው ተማምነው ደህንነት እንዲሰማቸው ማድረጉ ላይ ነው። ብሎም ማንም በፈለገ ጊዜ ተነስቶ እንዳያፈናቅላቸውና ጉዳት እንዳያደርስባቸው መከላከሉ ነው። መንግስት ይህን ሃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ የመንግስትነት ጣዕሙን ከማጣቱም በላይ ከተጠያቂነትም አያመልጥም። ከዴሞክራሲ መርሆዎች መካከልም የህግ የበላይነት መከበር ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ሰላም፣ ልማትም ሆነ ዴሞክራሲ ያለ የህግ የበላይነት ፈጽሞ የማይታሰቡ ናቸውና።
ስለሆነም በተግባር ያልተገለጸ የአስተሳብ አንድነት አይኖርምና መንግስት የህግ ማስከበር ሥራው ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጋራ አስተሳሰብ መፍጠሩን ማሳየት ያለበት የህግ የበላይነትን በማስከበር ተግባሩ ሊሆን ይገባል። ይህንንም በማድረግ ለህዝብ የገባው ቃል የእውነት መሆኑን ማሳየት ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ