በአንድ ወቅት አንዲት በአሜሪካ ትኖር የነበረች እስራኤላዊት «አገሬ በጠላቶቿ እየተጠቃች ነው፤ ይህንን ጥቃት ለመከላከል ወደዚያው እሄዳለሁ »በማለት ተናግራ ነበር፡፡ ይህንን ስናደምጥ ምን ሊታሰበን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ይህቺ እስራኤላዊ አገርዋን ከጥቃት ለመታደግ መነሳቷ ያላትን ፅኑ የአገር ፍቅር ስሜት ያሳያል፡፡ የእርስዋ በሰላም አገር ውሎ ማደር የአገሯን ሰላም ውሎ ማደር አላረጋገጠላትም፡፡ ለዚህ ነው ለአገሯ ሰላም መከበር በምድርዋ ለመገኘት መወሰኗ፡፡
በርግጥም ሰላም ከምንተነፍሰው አየር ያልተናነሰ ዋጋ እንዳለው የምንረዳው፤ ሰላም ከሌለ ስለነገ ማሰብም ማቀድም እንደማይቻል በቅጡ መረዳት ስንችል ብቻ ነው፡፡ አንዳንዶች በጆሮአቸው የሚያደምጡትና በአፋቸው የሚናገሩት እጅግ የተለያየ ነው፡፡
በዓለም ላይ በሰላም ዕጦት ለስደት ስለተዳረጉት፣ በስደት ሕይወታቸውን ስለሚያጡት፣ በእርስ በርስ ጦርነት ስለሚተላለቁት፣ በጦርነት አገራቸው ፈርሶ መጠለያ ስላጡት፣ለልመና ጎዳና ላይ ስለወጡት፣ ከመኖሪያቸው ስለሚፈናቀሉት እያደመጡ ነገ በእኔ ሊደርስ ይችላል ብለው ትምህርት መውሰድ ሲገባቸው እነርሱ ግን ስደትን፣ መፈናቀልን፣ በጦርነት መጨራረስን ወደ እራሳቸው ለማምጣት ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡
አገራችን ዛሬ ላይ ልትደርስ የቻለችበት የቀደመው ታሪካችን የሚያስረዳን ከውስጥ እርስ በርስ ባለመስማማት፣ ከውጭ በወራሪ ሃይሎች የድንበራችን መደፈር ምክንያት ተረጋግቶ ለመኖር በርካታ አዳጋች ጊዜያትን ማሳለፍ መቻላችንን ነው፡፡
እነዚያን በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ዛሬ በምናየው ተነፃፃሪ ሰላም፣ ልማትና እድገት ውስጥ ለመገኘት አገርን የማስተዳደር ኃላፊነት የተረከበው የወቅቱ ትውልድ አገሪቷና ሕዝቦቿ ያሳለፉትን መከራና ችግር ተረድቶ የተሻለ መረጋጋትና የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት ሲገባው ዴሞክራሲን በማፈን፣ ሥልጣንን ለመጠበቅ ሲባል ሃይል በመጠቀምና እስር ቤት በማጎር፣ ጥቂት የማይባሉ የመንግሥት ሹማምንት ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅምን እንዲያስቀድሙ ዕድል መፍጠሩ ኢትዮጵያውያን መራራ ሕይወትን እንዲላመዱትና ዕጣ ፋንታቸው አድርገው እንዲያስቡት አስገድዷል፡፡
ኢትዮጵያውያን ከነድህነታቸውም ቢሆን እንኳ በፍቅርና በሰላም እንዳይኖሩ የአብሮ መኖር እሴቶቻቸውን የሚሸረሽር ሴራ እየተደገሰላቸው እርስ በርሳቸው ሲተላለቁ ለማየትና የፖለቲካ ሴራቸው እንዲሳካ የፍላጎታቸው አስፈፃሚ ለመሆን መነሳት በርግጥ በጥሞና ማሰብና ማመዛዘን ከሚችል አእምሮ የሚጠበቅ አይደለም።
ያለፉት ዓመታት ኢትዮጵያውያን ለሰላም መስፈን በከፈሉት ዋጋ ድህነትን በማስወገድ ላይ መረባረባቸው የሚያኩራራም ባይሆን በዕድገት ጎዳና ለመራመድ እንደምንችል ፍንጭ የታዩበት ጊዜያት ነበሩ፡፡
ፈጣንና ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ አገራችን ተስፋ የሚጣልባት፣ ሕዝቦቿም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ብሩህ ተስፋ ማየት እንዲቻል ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የለውጥ ዓርአያ የሆኑት ታጋዮች የጀመሩት መልካም መንገድ ወጣ ገባ እንዲሆን የአብሮነት ጠንቆች ያሰቡት ክፉ ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ ባይሳካላቸውም በሕዝቦች መካከል ሳንካ መፍጠራቸው አልቀረም፡፡
በአሁኑ ወቅትም ለዓመታት ተገንብቶ የቆየው የመተሳሰብና አብሮ የመኖር እሴቶቻችን፣ የኢትዮጵያዊነት ፍቅራችንም አንዱ አንዱን በመጥላት እንዲለወጥ አተኩረው የሚሰሩ ክፉዎች አልጠፉም፡፡
ይሁን እንጂ ይህንን ክፉ ተግባር እያራመዱ ካሉት ይልቅ ክፉውን ተግባር በፅኑ የሚኮንኑ በእጅጉ የሚልቁ ናቸውና ባለፈው አንድ ዓመት በሕዝቦች መካከል ያጠመዱት የእልቂት ወጥመድ የሚፈልጉትን አልያዘላቸውም፡፡ ይህንኑ እኩይ ተግባራቸውን ለማክሸፍም መንግስት በየደረጃው እያከናወነ ያለው ሰላምን የማስፈን ሥራ ለክፉ ተግባራቸው በጎ ምላሽ እየሆነ፣ ሃሳባቸውን እያመከነ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ አድርሶናል፡፡
ከትናንት በስቲያ በአምቦ ከተማ በአማራና በኦሮሞ ብሄረሰቦች መካከል የተካሄደው የሰላም ኮንፍረንስ ለነዚሁ ክፉ አሳቢዎች የተሰጠ በጎ ምላሽ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አምቦ ከተማ ለገባው የአማራ የሰላም የልዑካን ቡድን የተደረገለት ፍቅር የተሞላው ደማቅ አቀባበል ክፉዎችን ማሳፈሩን መጠራጠር አያሻም፡፡ ከዚህ ቀደምም በአማራና ትግራይ በኦሮሞና በቤኒሻንጉል እንዲሁም በአማራና አፋር ህዝቦች መካከል የተካሄዱ የህዝብ ለህዝብ መድረኮች ለሰላማችንና ለአገራዊ አንድነታችን መጠናከር ጉልህ ድርሻ ነበራቸው።
እነዚህን መሰል አስደሳችና አስተማሪ የሰላም የፍቅርና የአንድነት መድረኮች በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በማስፋፋት እስከዛሬ በፍቅርና በመተሳሰብ የኖረውን ኢትዮጵያዊ መልሶ አንድነቱን በማጠናከር በአሉባልታና በዘመቻ ወሬ እንዳይፈታ የማድረግ ሥራ በሰፊው መሥራት ይገባል፡ ፡ አሁን የተጀመሩት የሰላም ጉባዔዎችም በተጀመረው ግለት እንዲቀጥሉ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ድጋፋቸውን ሊሰጡም የግድ ያስፈልጋል፡፡
በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካዊ መስኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ውጤት የምናስመዝግበው፣ ዴሞክራሲም ማስፈን የሚቻለው፣ የዜጎች የኑሮ ደረጃም የሚሻሻለው ሁሉም ለሰላም መስፈን በሚያደርገው ጥረት ብቻ በመሆኑ የሰላሙ ጉዞ ለሁሉም ይዳረስ እንላለን፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2011