ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባትና ለዓለም ማህበረሰብ ጭምር የሚተርፉ የተለያዩ ጠንካራ ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች ያላት አገር ናት፡፡ ከአንድ መቶ ሚሊዮን የሚልቁት ህዝቦቿም የቀደምት ስልጣኔና ለሌሎች ጥቁር ህዝቦችም የሞራል ስንቅ የሚሆኑ ድሎች ባለቤቶች ናቸው፡፡
በተለይ አገራዊ ጉዳይ ሲነሳ ያለምንም ማወላወል ህብረታቸው አንድ ክንድ ተደምሮ ይቆማል፡፡ ለዚህም የመላው ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆነው የአድዋ ድል አንድ ምስክር ነው፡፡ከዚህም ባሻገር እነዚህ ብሄር ብሄረሰቦች እርስ በርስ ያላቸው መስተጋብር ጠንካራ የአብሮ መኖርና የፍቅር ተምሳሌት ነው፡፡ በማህበራዊ ኑሮ ውስጥ የገነቧቸው የአኗኗር ዘይቤዎች በችግርም ሆነ በደስታ ጊዜ አብሮነታቸው እንዳይለያይ አድርጎታል፡፡
እነዚህ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የፈጠሯቸው ትስስሮች አንድም በመዋለድ ሲሆን፣ በሌላም በኩል በተለያዩ ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ በሚንፀባረቁ የአኗኗር ስልቶች ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ እድር፣ እቁብ፣ ጉዲፈቻ፣ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ግጭቶችን ለመፍታትም ሆነ ትስስሮቹን ለማጠናከር በአገራዊ የሽምግልና ባህሎች የማይፈቱ የግጭት ቋጠሮዎችና የማይጠብቁ የአንድነት ገመዶች እንደሌሉ የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ፡፡
ከነዚህ ብሄር ብሄረሰቦች ውስጥ ደግሞ ከአጠቃላይ አገሪቱ ህዝብ ከ61 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የሚይዙት የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ማህበረሰቦች ከቁጥርም ባሻገር አገሪቱ ውስጥ በጉርብትናና አብሮ በመኖር፣ በመዋለድና በመተሳሰር ሰፊ ትስስር ፈጥረዋል፡፡ አንዳንድ የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት እነዚህ ሁለት ህዝቦች ልክ እንደ ሰርገኛ ጤፍ አንዱን ከሌላው መለየት በማይቻልበት ደረጃ የተዋሃዱ ናቸው፡፡
ሁለቱ ህዝቦች በአገሪቱ ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥም ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በአገሪቱ በተካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ለውጡን በመምራትም ሆነ ለፍሬ በማብቃት የሁለቱ ህዝቦች ተሳትፎ ቀዳሚ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ለውጡን ለማደናቀፍ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እነዚህን ሁለት ህዝቦች በማጋጨት ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ሰፊ ዘመቻዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ዘመቻዎችም ውስጥ የተሳሳቱ ትርክቶችን በመፍጠርና ሁለቱ ህዝቦች የሚለያዩበትን የፈጠራ ታሪክ በመጨመር ለውጡ ወደፊት እንዳይቀጥል የሚደረጉ የግጭት ጥንስሶች አሉ፡፡
በዚህም መሰረት ቀደም ሲል በነበሩ ሂደቶች አንዱ ብሄር ጨቋኝ፤ ሌላው ተጨቋኝ፤ አንዱ ገዢ ሌላው ተገዢ በማድረግ የሚቀርቡ ከእውነት የራቁ ትርክቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ህዝቦች ግን እንደሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ሁሉ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ በጎም ሆኑ መጥፎ አጋጣሚዎችን ከመጋራት በዘለለ እንደ ህዝብ አንዳቸው በአንዳቸው የፈጠሩት አንዳችም ችግር አለመኖሩ በተለያዩ መንገዶች ከተፃፉ የታሪክ ድርሳናት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ሁለቱን ህዝቦች በማጋጨት አገር ለማፍረስና ለውጡን ለመቀልበስ የተፈበረኩ ትርክቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው ሁለቱ ህዝቦች አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህም ትልቁ ማሳያ ከለውጡ ወዲህ ሁለቱን ህዝቦች ለማጋጨት የተፈጠሩ ሴራዎች ህዝቦቹን ወደ ግጭት ከመውሰድ ይልቅ አንዱ ለሌላው እንዲያስብና ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር የሞራል ስንቅ መሆናቸው ነው፡፡
በአማራ ክልል የሚገኘው የጣና ሃይቅ በእንቦጭ አረም መጠቃቱን ተከትሎ ያለማንም ቀስቃሽነት ጣና ኬኛ (ጣና የኛ) የሚል መርህ በማንገብ በጣና ሃይቅ ላይ የበቀለውን የእምቦጭ አረም ብቻ ሳይሆን የተሳሳቱ አመለካከቶችና የጥላቻን አረም ነቅለው የጣሉ የኦሮሞ ወጣቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡
የመጀመሪያው የአማራና የኦሮሞ ህዝብ የህዝብ ለህዝብ ኮንፈረንስ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ በተካሄደበት ወቅት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ገዱ አንዳርጋቸው «የሁለቱን ህዝቦች አንድነትና ግንኙነት ለማሻከር፣ ለማዳከምና ብሎም ለማጥፋት ለዓመታት የተሰራበት ሴራ ሳይሳካ ቀርቶ ሁለቱ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ ቀጥሏል» ሲሉም በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ለማ መገርሳም በዚሁ መድረክ «የአማራና የኦሮሞ ህዝብ አንድነት በመኖር ብቻ ሳይሆን በመሞትም ጭምር ነው፡፡ በአድዋ፣ በሶማሌ፣ በባድመ ለውድ አገራችን ስንል ውድ ህይወታችንን እኩል ገብረናል» ሲሉ የሁለቱን ህዝቦች ታሪካዊ ትስስር ገልፀውታል፡፡
ትናንት በአምቦ ከተማ የተካሄደው የአማራና የኦሮሞ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ይህንኑ የቀደመውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ታልሞ የተዘጋጀ መድረክ ነው፡፡ የዚህ መድረክም አላማ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለው የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር ዘር ፍሬያማ ሆኖ እንዲያድግና ለቀጣዩ ትውልድም የመተሳሰብና የአብሮነት ምርትን ለማውረስ ታልሞ የተዘጋጀ ነው፡፡ በህዝቦች ውድ የህይወት መስዋዕትነት የተመዘገበውን ለውጥም ለፍሬ ለማብቃት ነው።
እንዲህ ዓይነት መድረኮች አንዱ ማህበረሰብ የሌላውን ባህል፣ አኗኗርና ሌሎች ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን በጥልቀት እንዲገነዘብና በተሳሳተ መንገድ ከሚተላለፉ የታሪክ ዝንፈቶች ታቅቦ የቀደመውን ግንኙነት ይበልጥ እንዲያጠናክር ወሳኝ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
በተለይ እንደ አማራና ኦሮሞ ያሉ ሰፊ ትስስር ያላቸው ህዝቦች አንዱ የሌላው ስጋት ሳይሆን ኩራት የሚሆንበት ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲህ ዓይነት የህዝብ ለህዝብ ኮንፈረንሶች ጠቃሚ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2011