ልክ ነው! ዛሬ እንደአገር የምንገኝበት ሁኔታ በብዙ ውጣውረዶች የተሞላና የሚያሳስብም ነው። በብዙ ቦታዎች ግጭቶች ነበሩ አሁንም አሉ። እርስ በእርስ እንድንባላና እንድንጫረስ ሌት ተቀን ያለእረፍት የሚሰሩ ኃይሎች እንዳሉም ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመመልከት በቀላሉ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።
አንዱ ጋር በረደ ስንል ሌላው ቦታ እያገረሸ ልንሰማና ልናያቸው የማንፈልጋቸው የሞትና የአካል እንዲሁም የንብረት መውደም ዜናዎች አሁንም ድረስ አብረውን አሉ።
በውይይትና በመነጋገር ሊፈቱ የሚችሉ ቀላል ጉዳዮች በአይዞህ ባዮች አቀጣጣይነት እየተጋጋሉ ለሁከት ምንጭ ሲሆኑ፣ ህይወትን ሲያስተጓጉሉና ኢኮኖሚ ሲያቀዛቅዙም ይስተዋላል። በሽግግር ላይ መገኘታችን ተረስቶ ጊዜ ተወስደው ሊፈቱና የንትርክ መንስዔ ሊሆኑ የማይገባቸው ጉዳዮችን እየመዘዙ ህዝብን ከህዝብ ለማቃቃር የሚደረጉ ሙከራዎችም ብዙ ናቸው። አንዱ ጉዳይ ሲቋጭ ሌላ እየመዘዙ አገርና ህዝብ ትኩረታቸውን ከልማት ላይ እንዲያነሱ የሚደረገው ሙከራም ቀላል አይደለም።
የህዝብ ያልሆነ አጀንዳን ለእኩይ ዓላማ በመጠቀም ግጭት ከፈጠሩ በኋላ ግጭቱን የህዝብ ለህዝብ መልክ ለማስያዝ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም።ያልተፈጠረን ነገር እንደተፈጠረ በማስመሰልም መንግስትና ህዝብን ለማቃረን ይህንንም ተከትሎ ውጥረት ለማንገስ ወገባቸውን አስረው የሚሰሩ ኃይሎች እንዳሉም ሳይታለም የተፈታ ነው።
ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በሌላ አገር ላይ የተፈጸመን ድርጊት አገራችን ውስጥ እንደተፈጸመ አድርጎ በማቅረብ ግጭትን ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ዕለት ከዕለት የምናስተውለው ነው። እኒህን መሰል ሁኔታዎች ወቅታዊውን የአገራችንን ሁኔታ የዳመነ እንዲሆንና ህዝብ በስጋት እንዲሸበብ አድርገውታል።
ይሁንና ይህን ያህል ለጥፋት እየተሰራም እንኳ ታሪካችንን ጨለማ ማልበስ ግን አልተቻለም። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ጨዋ፣ አስተዋይና ልዩነትን አክብሮና ተወዳጅቶ ሺዎች ዓመታትን በፍቅር የኖረ ህዝብ መኖሩ ነው። እገሌ ተነስቶብሃል፣ አጥቅቶሃል እንዲህ አድርጎሃል በሚል እኩይ ቅስቀሳ መካከል እንኳ አንዱ ህዝብ ለሌላው ጋሻና ከለላ እየሆነ ድንቅ ታሪክ መጻፉን ቀጥሏል።
ይህ ጉዳይ ተስፋችን እንዲበረታና መተማመናችን እንዲጸና ትልቅ አቅም ሆኖናል። እንዲህ ዓይነት ህዝብ ባይኖረንና እንደተዘራው የጥላቻ ቅስቀሳ ቢሆን ኖሮ ዛሬ እንደ አገርና እንደ ህዝብ መቆም አቅቶን ለዓለም መተረቻ ከመሆን ባልተረፍን ነበር። ለዚህም ነው የጨለመ ቢመስልም እንኳ ከፊታችን ትልቅ የተስፋ ብርሃን አለ ማለታችን።
በኢኮኖሚውም መስክ እንዲሁ ነው። የህዝባችን ህይወት አሁንም ድረስ ትርጉም ባለው ደረጃ አልተቀየረም። የኑሮ ውድነቱ መቆሚያ የሌለው በሚመስል መልኩ የሀዝብን ስቃይ እያበረታው ነው።
የመኖሪያ ቤት እጥረቱ አሁንም አብሮን ያለ አሳሳቢ ችግር ነው። ከከፍተኛ ትምህርት የሚመረቁና እድሜያቸው ለሥራ የሚደርስ ወጣቶችን የሚመጥን የሥራ እድል ፈጥረን ወጣቶቻችንን ከስጋት አላላቀቅንም። ኢኮኖሚያችን በዚህ በመቶ ያህል እያደገ ነው ተብሎ ቢለፈፍም በህገወጥ ስደት ህይወታቸውን እያጡ የሚገኙ ወጣቶቻችንን ሲታደግ አልታየም። የውጭ ምንዛሪ እጥረቱም አገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶ ይገኛል።
የጨለማ ኢኮኖሚው ክንዱን እንዳፈረጠመና እንዳገነገነ ይገኛል። ታክስ መሰወር፣ ገንዘብ ማሸሽና ሙስናው የአገሪቱን ኢኮኖሚ ላይ ጥላውን እንዳሳረፈ ይገኛል። ይህን ያህል ሚሊዮን ብር በዚህ ኬላና አየር ማረፊያ ሊወጣ ሲል ተያዘ ሲባል በየዕለቱ የምንሰማው ዜና በዚህ ዘርፍ
የሚስተዋለው ችግር ምን ያህል ያገነገነ እንደሆነ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። እኒህና መሰል ሁኔታዎችም ህዝብ በነገው ላይ ያለው ተስፋ እንዲጨልም እያደረገ ይገኛል።
ሆኖም በዚህም መስክ ያለው ሁኔታ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም። እንደ አገርና ህዝብ አስቦና ኃላፊነትን ተገንዝቦ መስራት ከተቻለ ካደመነው ስጋት የበለጠ ትልቅ የተስፋ ብርሃን አለ። ለማንም ግልጽ እንደሆነው ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች አገር ናት። ሌላውን ትተን ያለንን የውሃ ሀብት እንኳን ለዘመናዊ ግብርናና ለኃይል ማመንጫ በሚገባ ብንጠቀምበት ከራሳችን አልፎ ለአፍሪካ የሚተርፍ ነው።
በሌብነትና በበልሹ አሰራሮች ተጓተው የነበሩ የአገር ተስፋ የሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ችግር በመፍታት ወደሥራ ለማስገባት እየተሰራ ያለውም ስራ እንደ አገር ያለንን ተስፋ የሚያፈካና ከፊታችን ያለው ጊዜ ብሩህ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የስኳር፣ የመስኖና ማዳበሪያ ፋብሪካዎች ከተተበተቡበት ቸግር ወጥተው ፍጻሜያቸውን በሚያቃርብ መልኩ እየተሰሩ መገኘታቸው ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ ወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ ዳመና ያጠላበትና በተግዳሮት የተከበበ ቢሆንም ከህዝባችን አርቆ አስተዋይነትና ሰላም ወዳድነት እንዲሁም መንግስት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመፍታት እየወሰዳቸው ያሉ ተጨባጭ እርምጃዎች የአገራችን መጻዒ ተስፋ ብሩህ መሆኑን የሚመሰክሩ ናቸውና እኩዩን በማክሰም ለበጎው ተግባር ሁሉም ይረባረብ እንላለን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2011