«ሀብታም ለመሆን የተሻለው ጊዜ ወጣትነት ነው፤ ድሃ ለመሆንም ጊዜው ወጣትነት ነውና ወጣቶቻችን እባካችሁ የተሻለውን ምረጡ፤ የዚህ ዘመን ጀግኖች ወጣቶች ናቸው፤ ወጣቶች ተስፋ ሲኖራችሁ እኛም ተስፋ ይኖረናል» ይህ መልካምና በወጣቶች ላይ ተስፋን ያሳደረ ንግግር ሚያዝያ 7 ቀን 2010ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የተነገረ መሆኑን ልብ እንላለን፡፡
በርግጥም የአሁኑም ሆነ የወደፊቱ ታላቅ ተስፋ በወጣቱ ትውልድ ላይ የተጣለ ስለመሆኑ እንደምን መጠራጠር ይቻላል? ለዚህም ነው አበው « ወጣት የነብር ጣት» ሲሉ የሚያሞካሹት፡፡ የወጣቱ በሁሉም ዘርፍ ወንዝ ያሻግራል የሚል መተማመን መኖሩ በቀደመው ጊዜ እንደታየው ሁሉ ዛሬም ያንን የተመሰገነ ተግባሩን በተግባር ሊያሳይ የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት መንግሥት የወጣቶችን ህይወት ለመለወጥ እንዲቻል የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል። በዚህም የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን በማስፋፋት ሥራ አጥ ዜጎች ሥራ እንዲፈጠርላቸው በመደረጉ የበርካቶች ህይወት በመጠኑም ቢሆን መለወጥ ችሏል።
ይህንኑ ጅምር ተግባር ለማስፋትም መንግሥት 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶች በየአካባቢያቸው በጥቃቅንና አነስተኛ በመደራጀት መነሻ ካፒታል አግኝተው የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር እንዲችሉ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ የገንዘብ አቅርቦት ብቻውን ሥራ ፈጣሪ ሊያደርግ እንደማይችል፤ ይልቁንም በመንግሥትም ሆነ በሚመለከታቸው ተቋማት በበለጠ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የአንድን የሥራ መስክ ውጤታማነት የሚወስኑ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የሥራ ተነሳሽነትና የሥራ ፈጠራ ክህሎት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፤ እነዚህ ጉዳዮች በቦታና በጊዜ እንደየሰው ሁኔታ የሚለያዩ ናቸው፡፡
ባለፉት ዓመታት ብዙ የመንግሥትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመከፈታቸው የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ብቻ ከ36 በላይ ሲደርስ፤ የግል ዩኒቨርሲቲዎችም የዚያኑ ያህል ቢያድጉም ዲግሪና ዲፕሎማ የያዙ ዜጎችን ማፍራት እንጂ የሥራ መስክ የሚሰፋበትንና ወጣት አምራች ኃይሉን መሸከም የሚችል መደላድል መፍጠር ላይ አልተተኮረም ፡፡ ከዚህ ባሻገርም ምንም እንኳ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቢያድግም አብሮት የመጣው የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በውጤታማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል፡፡
ለዚህ ችግር መፍትሄ ለመስጠት በቅርቡ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት የሚደረግ መሆኑን በመግለፅ « በከተማችን
ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሥራ አጥ ወጣት በመኖሩ ወቅቱ የምናንቀላፋበት ሳይሆን ያለምንም ፋታ የምንሰራበትም ነው» ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ይህንን ተከትሎም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለወጣቶች በመደበው የ2 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ዙሪያ ምክክር ተደርጓል፡፡ ፈንዱን ወደ ሥራ ለማስገባትና ወጣቶችን ለመመልመል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅቶችም መጠናቀቃቸው ተገልጿል፡፡
ተግባራዊ ይሆናሉ ተብለው የታሰቡት የሥራ ዘርፎች በ100 ወረዳዎች የነዳጅ ማደያዎችን፣ በ116 ወረዳዎች የከተማዋን ደረጃ እና ውበት በጠበቀ መልኩ በአዲስ ዲዛይን የተሰሩ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆችን ፣ ከ2000 በላይ ዘመናዊ የንግድ ሱቆችን መገንባት፣ ያገለገሉ 300 የከተማ አውቶብሶችን በመጠቀም ተንቀሳቃሽ የምግብ እና መጠጥ መሸጫ ማዘጋጀት፣ በከተማዋና በዙሪያዋ ባሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ወጣቶችን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ማሠማራት፣ የዳቦ መጋገሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት በርካታ ወጣቶችን በዘርፉ ማሰማራት ጥቂቶቹ ሲሆኑ፤ ወጣቶች የራሳቸውን ተጨማሪ የሥራ ሃሳብ በማምጣት መሳተፍ የሚችሉ መሆኑ ተነግሯል፡፡
እያገባደድን ባለው ሳምንት የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ አካሂዶ ያሳለፈው ውሳኔም የዚሁ ዕቅድ አንድ አካል እንደሆነና ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ማየት ይቻላል፡ ፡ የወጣቶችን የተሳታፊነትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች በተለይም የሥራ አጥነት ችግርን ለመፍታት እስካሁን ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር አሁንም ከለውጡ በሚገባው ደረጃ ያልተጠቀሙበት ሁኔታ መኖሩን ምክር ቤቱ በአጽንኦት መገምገሙን፤ በተጨማሪም ወጣቶቹ ያሏቸው የፖለቲካ ተሳትፎ ጥያቄዎች ገና በተሟላ ሁኔታ አለመመለሳቸውን በማየቱ፤የተጠቃሚነት ጉዳይ በቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራት ልዩ አገራዊ አጀንዳ እና የርብርብ ማዕከል እንደሚሆን ምክር ቤቱ መወሰኑን አፅንኦት እንደተሰጠው ያሳያል።
ይኸው አቋም በፅኑ ወደ ተግባር ተለውጦ ማየት የሚቻለው ወጣቶች ለሥራ ያላቸውን ፍላጎት በተግባር ሲያሳዩና ተሳታፊ ሲሆኑበት ነው። የብጥብጥና የሰላም እጦት አውድ የሚቀየረውም የወጣቶቹ ተሳትፎ ሲታከልበት በመሆኑ መንግሥት የገባውን ቃል በተግባር እንዲያረጋግጥ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ከወጣቶች የሚጠበቅ ሊሆን ይገባል፡፡
መንግሥት ይህንን ያህል ርምጃ ለመጓዝ ፍላጎት ማሳየቱ አንድ ውጤት ቢሆንም፤ ወጣቱ «አገር ተረካቢ እኔ ነኝ፡፡ ሥራ ሰርቶ መለወጥ ክቡር ሀሳብ ነው፡፡ በአቋራጭ ለመበልፀግ መፈለግም አስነዋሪ ነው » ብሎ በሙሉ የሥራ ፍላጎት መነሳቱ ለነገ የማይባል ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ11/2011