የአገርና የሕዝብን ፍቅር በተላበሱ ዜጎቿ የማትደገፍ አገር መልካም አጋጣሚዎችና ዕድሎች እንደሚያመልጧት ከቀደመው ውድቀታችን ከመገንዘብ ሌላ አማራጭ የለም። መፃኢ ዕድሎቻችንን በጥንቃቄ መጠቀም ወይም ፍሬ አልባ የማድረግ ምርጫው የራሳችን ጉዳይ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በአንዳንድ ሥፍራዎች እየተስተዋለ ያለው የሰላም መደፍረስ በርካታ ጥቅሞቻችንን ሊያሳጣንና አገራችንን ሊበታትን ጫፍ ደርሶ ቢታይም፤ አገሪቱን እየመራ ያለው መንግስት የችግሩን አደገኛነት ተገንዝቦ ለወቅታዊው ጉዳይ እልባት ለመስጠትና መፍትሄ ያለውን ዕርምጃ ለመውሰድ የበለጠ ቁርጠኝነትን ሊላበስ እንደሚገባው ግልጽ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መሾማቸውን ሕዝቡ ሳያቅማማ በፍቅር መቀበሉ መንግሥት ሕዝብን ለማገልገል ከልቡ ሲነሳሳ ሕዝብ አብሮት እንደሚቆም ማሳያ ሆኗል፡፡
ይሁን እንጂ ዴሞክራሲና ነፃነት አጥቼ ነበር አሁን አገኘሁ ሲል የነበረ ዜጋ ያገኘውን ዴሞክራሲና ነፃነት በአግባቡ መያዝ አቅቶት መረን ለወጣ ተግባር ተጠቅሞበት ሕዝብን ሲያፈናቅል፣ ሲገድልና ሲዘርፍ ማስተዋል በርግጥ የዴሞክራሲና የነፃነት ጥማት ይህንን ያህል ሥርዓት አልበኛ ያደርጋልን? ከሆነስ ሕግ በጣሱና ሕዝብን በበደሉ ወንጀለኞች ላይ ምን አስተማሪ እርምጃ ተወሰደ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡
አገሪቱን የሚያስተዳድረው መንግስት ሰላምና መልካም አስተዳደርን ካላሰፈነ ስለዴሞክራሲ መነጋገር አይቻልም፡፡ የዜጎች ደኅንነት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት ተንሰራፍቶ አገር እየተበዘበዘች ከሆነ የሕግ የበላይነት ጠፍቶ ሕገወጥነት ተስፋፍቷል ማለት ነው፡፡ ሕገወጥነት ሲሰፍን ሰላምና መረጋጋት ስለማይኖር የልማት ሥራዎች ይዳከማሉ፤ አምባገነኖች ማን አለብኝነትን ይላበሳሉ፡፡
መንግሥት የሕግ የበላይነት ለማስፈን ቁርጠኝነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ዜጎች ከኖሩበት ቀዬ ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉና ንብረታቸው ሲወድም እንዲሁም የመንግሥት አስተዳደር በሕገወጦች ሲፈርስ በዝምታ ከተስተዋለ ድርጊቱ ማዕከላዊ መንግሥትንም ሆነ መላ አገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥል ስለሚሆን ቅድሚያ ለመረጋጋትና ለሰላም መስፈን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የህግ የበላይነት ለድርድር ሊቀርብ አይገባም፡፡
የሕግ የበላይነትን አምኖ የማይቀበል በሰላም ለመኖር ፈቃደኛ እንዳልሆነና ለአገርም ለሕዝብም እንደማይጠቅም ለመገንዘብ ቀላል በመሆኑ መንግሥት ራሱንም ሆነ ሕዝብን ለአደጋ ከማጋለጡ በፊት የማያዳግምና አስተማሪ የእርምት ርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ የሕዝቦች በሐሳብ መለያየት ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የእያንዳንዳቸው በሰላምና በነፃነት የመኖርን መብታቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ አይገባም፡፡ ይህንን የሕዝብ መብት ለመታደግም የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ፅኑ አቋም ሊያዝበት ያስፈልጋል፡፡
ባለፉት ሁለት ቀናት ውይይት ሲያካሂድ የነበረው የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ምክር ቤት በቀጣይ ሊያተኩርባቸው የሚገቡ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቅቋል፡፡ ጉባዔው ያለፉትን ወራት የእቅድ አፈፃፀም በተመለከተ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣በኢኮኖሚው መስክ የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎችን፣ የስራ አጥነት ችግርን ለመፍታት እስካሁን የተደረጉት ጥረቶችን፣ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚነሱ የህዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተጀመረውን የሪፎርም ስራ፣ የፀጥታና የፍትህ ስርዓቱን ለማስተካከል የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች፣ የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ያሉ ክፍተቶች፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይን፣ ከሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ወዳጅነት መመስረቱና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብር እየተካሄደ መሆኑን በጥልቀት በመፈተሽ የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን፤ ፍትህን፣ ሀገራዊ አንድነትንና ክብርን ማረጋገጥ ለነገ የማይባሉ የድርጅቱ ቀዳሚ ተልዕኮዎች መሆናቸውን በአፅንኦት አስቀምጧል።
ምክር ቤቱ ለውጡን እየተፈታተኑ ያሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተም ለውጡ ህዝባዊ መሰረት ይዞ እንዳይጓዝ፤ ከተቻለም እንዲቀለበስ የሚጥሩ ኃይሎች በመኖራቸው ጽንፈኛ ብሄርተኝነትን፣ ስርዓት አልበኝነትን የመከላከልና የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ፈተናዎች የአገራዊ አንድነት ችግሮች በመሆናቸው በተባበረ ክንድ በመፍታት፤ ለውጡን ማስቀጠልና ማስፋት ለምርጫ የሚቀርብ እንደማይሆን፤ ለዚህም በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል፡፡
አዎ! መንግስት መኖሩ የሚታወቀው አገርም ሕዝብም ከዋይታ ሲድኑ፣ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ ሲገባ፣ ለወንጀል ድርጊት የሚነሳሱ በሕግ የበላይነት አደብ እንዲገዙ ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ ያኔ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንደሚገባ ሳይጠራጠር በተሰለፈበት መስክ አገሩን ለማሳደግ ጥረት ያደርጋል፡፡ የኢህአዴግ ምክር ቤት የትኩረት አቅጣጫም ይህንኑ ማዕከል ማድረጉ መልካም ቢሆንም ከቃላት በዘለለ ግን በተግባር መታየት ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2011