ዓለም አቀፉ የፕሬስ ነጻነት ቀን ዘንድሮ ለ26ኛ ጊዜ ከመጪው ሚያዚያ 23-25 (ሜይ 1-3/2019) በአዲስ አበባ ይከበራል። ለሦስት ቀናት የሚቆየው ይህ ሁነት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት፤ በአፍሪካ ህብረትና በኢትዮጵያ መንግሥት የሦስትዮሽ ትብብር የሚከበር ነው።
የዘንድሮው የፕሬስ ነጻነት ቀን ሲከበር መሪ ቃሉ “መገናኛ ብዙሀን ለዴሞክራሲ፤ ጋዜጠኝነትና ምርጫ በዘመነ የሀሰት/የፈጠራ መረጃ ስርጭት” የሚል ጭብጥ ያለው ነው። አዎን ሚዲያ በደሞክራሲ ስርዓት ግንባታና በምርጫ ወቅት ትልቅ ሀገራዊና ህዝባዊ ሚናና ኃላፊነት አለው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ሁነት ለማስተናገድ ፈቃደኝነቱን ሲገልጽ የመንግሥታቱ የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት የኢንፎርሜሽንና የኮሙዩኒኬሽን ም/ዳይሬክተር፤ “ውሳኔው ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ፤ በተለይም የመገናኛ ብዙሀንን ነጻነትና ሰብዓዊ መብት ማክበርን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል” ብለዋል።
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙሀን ነጻነት ረገድ በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እመርታዊ ለውጥ አሳይታለች። በምንም ሰበብና ውንጀላ ይሁን ለበርካታ ዓመታት የታሰሩ፤ የተፈረደባቸውና በቀጠሮ የሚገኙ ጋዜጠኞች ከእስር ተፈትተዋል። ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል። በነጻነትም እንዲሰሩ ተፈቅዷል። ይህ ደግሞ ሁሉንም የብሮድካስት፤ የህትመትና የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎችን የሚያጠቃልል ነው።
እናም ቀደም ባሉት ዓመታት በየትኛውም የመገናኛ ብዙሀን ተጠቅሞ ስለዴሞክራሲ ማውራት፤ ስለህዝቦች ነጻነት መስበክ በተነወረበት፤ መንግሥትን መንቀፍ በተከለከለበት አገር እንዲህ ያለው ርምጃ በመንግሥት ሲወሰድ ማየትም ሆነ መስማት የሚያስገርም ነው። አዲሱንም የለውጥ መንገድ እውነተኛ ነው ከሚያሰኙት ምክንያቶችም ቀዳሚ ይኸው መገናኛ ብዙሀንና ጋዜጠኞች የተቀዳጁት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ አዲስ መብት ነው።
እንዲህ ዓይነቱ የመገናኛ ብዙሀን ነጻነት ላለፉት አራት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የማይታሰብ ጉዳይ ነበር። ይህንን ተከትሎም የዴሞክራሲና የፖለቲካ ምህዳሩም እንዲሁ ጠባብና የማያላውስ ሆኖ ቆይቷል። የለውጡ ብርሀን ከፈነጠቀ ወዲህ ግን የህዝብም ሆኑ የግል ሚዲያዎች ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸው ተከበረ።
ዜጎች በመገናኛ ብዙሀን አማካይነት ሀሳባቸውን የመግለጽም ሆነ መረጃ የመቀበል ነጻነታቸው ተረጋገጠ። ተዘግተው የነበሩ ሚዲያዎች ተከፈቱ፤ ተሰድደው የነበሩ ድርጅቶችና ባለሙያዎችም ወደ ሀገራቸው ተመለሰው በነፈሰው የነጻነት አየር በመጠቀም ሃሳባቸውን ያለ ፍርሃት ማንሸራሸር ጀመሩ።
የፕሬስ ነጻነት ቀን በየዓመቱ የሚከበረው የመረጃ ነጻነትን መሰረታዊ መርሆዎችን በመዘከር፤ እነዚህንም መርሆዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበሩ ለማስቻልና ከጥቃትም ለመጠበቅ፤ እንዲሁም ለፕሬስ ነጻነት ሲሉ ውድ ህይወታቸውን ያጡና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ጋዜጠኞች ለመዘከር ነው።
በዚህ በአዲስ አበባ ከተማ አስተናጋጅነት በሚከበረው 26ኛው የፕሬስ ነጻነት ሁነት ላይ ከአንድ ሺህ በላይ የመንግሥታትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችና ተጋባዥ ተሳታፊዎች ይገኛሉ። በወቅቱም በዘርፉ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ግለሰቦች ንግግር እንደሚያደርጉ ሲጠበቅ፤ የመንግሥታቱ የትምህርትና የሳይንስ ድርጅትም ለፕሬስ ነጻነት መከበር ጥብቅና ለቆሙና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች የዩኔስኮ “ጉለርም ካኖ” የተሰኘውን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ሽልማት ይሰጣል፡፡
ይህን መሰል ታላቅ ሁነት በአገራችን መካሄዱ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አዎን ኢትዮጵያ ባለፉት 12 ወራት ዓለምን ያስደመሙ ለውጦች አሳይታለች፡፡ ለዚህም ትልቁን ድርሻ የሚይዘው መንግሥት ነው፡፡
መንግሥት ዴሞክራሲን በማስፋትና የመረጃ ነጻነትን በማስከበር ረገድ በወሰዳቸው አፋጣኝና ቆራጥ ርምጃዎች በአሁኑ ሰዓት በመናገሩ፤ በመጻፉ፤ በመሰብሰቡ ወይም በመደራጀቱ ምክንያት ማረሚያ ቤት የሚገኝ ጋዜጠኛ ወይም የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያ የለም፡፡ እንግዲህ ይህ ነው ቀደም ባሉት ሥርዓት ሊታሰብ አይደለም ሊታለም የማይችል ለውጥ እውን ማድረጓ ይሁንታን ያጎናጸፋት። ታዲያ ይኸ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡
አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የፕሬስ ነጻነት በከፍተኛ ተጋድሎና መስዋዕትነት የተገኘ ነው። በመሆኑም ሊከበርና በአግባቡ ሊያዝ ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ተዋናዮች የጋራ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
በዚህ ረገድ መንግሥት የጀመረውን የዴሞክራሲ ባህል የበለጠ የማዳበርና የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ጉዞ ያለ ሚዲያ፤ ያለመረጃ ነጻነት ከዳር ሊያደርሰው አይችልምና የሚታዩ ሕጸጾችን በማረም በታጋሽነት ወደ ፊት ሊቀጥል ይገባዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ወይም ጋዜጠኞችም ሥራቸው በበለጠ ሙያዊ ኃላፊነት ሕዝባዊ አደራቸውን ሊወጡ ይገባቸዋል፡፡ በየትም ሙያና አገር ግዴታ የሌለው ነጻነት የለም፡፡
እናም በየመስኩ የሙያው ሥነ ምግባር የሚጠይቃቸውን መርሆዎች፤ ባህል፤ እምነትና ማህበራዊ መስተጋብር የሚጠይቃቸው የግልና የወል ግዴታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በኃላፊነት ተከብረው ሊተገበሩ የግድ ነው፡፡ ይህ ባይሆንና የተገኘውን ነጻነት እንደሌጣ ፈረስ ያለልጓም እንጠቀም ከተባለ አገራችንንና ህዝቦቿን ለከፋ ችግር ሊዳርጋት እንደሚችል ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል።
አሁን በአገራችን እየታየ ያለው እውነታም ሕግን ወይም የጉልበት ድንጋጌን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ግላዊና ማህበራዊ ኃላፊነትን፤ ተፈጥሯዊና ሰብዓዊና ግዴታዎችን የሚሻ ነው። እናም ሚዲያዎች የተገኘውን ነጻነት በኃላፊነት ልንጠቀምበት ይገባል። በዚህም ህዝብንና አገርን ለአደጋ ከሚያጋልጥ የፈጠራ ወሬ ተጠብቀን፤ ከስሜታዊነት ወጥተን ለአገር ብልጽግናና ለህዝብ ልዕልና የሚጠቅሙ መረጃዎችን በኃላፊነት ልናስተላልፍ ይገባል፡፡ ኃላፊነታችንንም በአግባቡ ልንወጣና በብዙ መስዋዕትነት የተገኘውን ለውጥ ፍሬ እነዲያፈራ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው እንላለን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011