ሀገራችን በለውጥ ሂደት ውስጥ የገባችበት አንድ አመት በተለያዩ መርሀ ግብሮች ተዘክሯል።በዚህም በለውጡ የተገኙ ስኬቶች፣ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና መፍትሄዎች ተዳሰዋል።ይህም ለውጡን ለማስቀጠል ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።ከእዚህ የአመት ጉዞ ዳሰሳ ማግስት ደግሞ ገዥው ፓርቲ አህአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ማካሄድ ጀምሯል።
ምክር ቤቱ ሀገሪቱ በወሳኝ ምእራፍ ላይ ባለችበት በአሁኑ ወቅት እንደመካሄዱ በተለይ ከህግ የበላይነት አኳያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሚገባ መመልከት እና ዘላቂ መፍትሄም ማስቀመጥ ይኖርበታል።
እንደሚታወቀው ለውጡ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ቢሆንም ፣ከሰላም እና ደህንነት አኳያ ግን ችግሮች ሲስተዋሉ ቆይተዋል፤በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም የሰላም እጦት ይታያል። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለውጡን የማይፈልጉ ሀይሎች በሚያቀጣጥሉት እሳት የዜጎች ህይወት አልፏል፤ተፈናቅለዋል፣ የህዝብና የመንግስት ንብረት ወድሟል ።አሁን አልፎ አልፎ ችግሮች እያጋጠመ ነው ።
የሀገሪቱ መገለጫ እስከሚመስል ድረስ መፈናቀል በዝቷል፤መፈናቀል የጉንፋን ያህል እየታየ ነውን ያሰኛል።በርካታ ተፈናቃዮች ችግር ውስጥ እያሉም ሌሎች ደግሞ እንዲፈናቀሉ ሲደረግ ይስተዋላል።በዚህ የተነሳ ዜጎች ለአመታት ያፈሩትን ጥሪት እንደዋዛ ትተው ቀዬአቸውን እየለቀቁ በየመጠለያው ለመኖር ተገደዋል።
ይህ ችግር በሀገር ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል፤እያሳረፈም ነው።ለአብነት እንኳ ብንመለከት በኦሮሚያ ክልል በምእራብ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሼ ዞን በተፈጠረ የሰላም ችግር የየዞኖቹ ህዝብ መውጫ መግቢያ አጥቶ ነበር፤የእርዳታ እህል ለማሳለፍ እንኳ ችግር ነበር።
እርግጥ ነው መንግስት ለውጡን ወደኋላ ለመመለስ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች የሚያቀጣጥሉትን እሳት ለማጥፋት የተለያዩ ሰላምን የማስከበር ስራዎች እየሰራ ነው።በሀገር ሽማግሌዎች ፣በሀይማኖት አባቶች፣በእናቶች ወዘተ፣ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።፡
በየክልሎቹ ጥያቄ መሰረት የፌዴራል መንግስት የመከላከያ ሰራዊትን ግጭት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች እያስገባ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ችግሮቹን እየፈታ ይገኛል።በእዚህ አይነት መንገድ በርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላማቸው ተረጋግጧል።ሰራዊቱ መድረኮችን እያዘጋጀ ግጭት የፈጠሩ ወገኖችን እያቀራረበም ነው ። በእርግጥ በሰራዊቱ ታላቅ ስራ እየተከናወነ ነው፤ሰራዊቱ ባይገባ ሀገር ምን ልትሆን እንደምትችል መገመት አይከብድም።
ይሁንና ከዚህ የህግ የበላይነትን የማስጠበቅ ተግባር አሁንም ያልተማሩ ሀይሎች ይስተዋላሉ።እነዚህ ሀይሎች አሁንም ድረስ በሚቀሰቅሱት ግጭት እና በሚፈጽሙት አጥፊ ተግባር ሀገሪቱን ማቁሰላቸውን ቀጥለዋል።የአሮጌ ጨርቅ ያህል እዚህ ሲሰፋ እዚያ የሚቀደድ ዓይነት ሁኔታ ይስተዋላል።ይህን ያስተዋሉ የተለያዩ ወገኖችም መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር በኩል መለሳለስ እያሳየ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።
የሁሉም ነገር መሰረቱ ሰላም ነውና መንግስትን የሚመራው ገዥ ፓርቲ የሆነው ኢህአዴግ በምክር ቤቱ ስብሰባ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ከማረጋገጥ አኳያ እየተከናወነ ያለውን የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ውጤታማነት በሚገባ ፈትሾ ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሄ የሚሆን አቅጣጫ ማስቀመጥ ይኖርበታል።
ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ማህበራዊውም ኢኮኖሚውም እንቅስቃሴ በእጅጉ ይታመማል።ሰዎች ተረጋግተው ስለቀጣዩ ስራቸው እና ሕይወታቸው ማሰብ አይችሉም።ይህን ደግሞ ባለፈው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ማስተዋል ተችሏል።በመሆኑም ምክር ቤቱ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ የመከላከያ ሀይሉን እያስገባ ሰላምና መረጋጋት እያመጣ እያለ በሌሎች አካባቢዎች ለምን የሰላም መደፍረስ ተስተዋለ የሚለውን መመልከት ይኖርበታል።
ሰላምና መረጋጋትን ከማስጠበቅ አኳያ የሌሎች የደህንነት ሀይሎች ሚናም መታየት ይኖርበታል።አንዳንድ ግጭቶች ለያዥ ለገራዥ ያስቸገሩት ሴራዎቹን ተከታትሎ ቀድሞ ማምከን ካለመቻል ጋር በተያያዘ ነው የሚሉ መረጃዎችም ስላሉ የእነዚህ ድርሻም በሚገባ መታየት ይኖርበታል።በዚህ በኩል የክልል እና የፌዴራል ፖሊስና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎቱ በሚገባ መፈተሽም ይኖርበታል።ክፍተቶቹ ተለይተው መፍትሄ ማስቀመጥ ይገባል።
ህዝቡ የቀኝ እጁ እንደሆነ ፖሊስ ሁሌም ይገልጻል።መከላከያውም ህዝባዊ ነው ።አሁን እንደሚባለው ግን ህዝቡ የሚሰጣቸው መረጃዎች ላይ ተመሰርቶ ጥናት በማድረግ በጸረ ሰላም ሀይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ሴራቸውን የማምከን ስራ ጠንካራ ነው አይባልም።ለምን የሚለው ጥያቄ መታየት ይኖርበታል።መከላከያ ሰራዊቱም በፖሊስ ስራ ውስጥ ተጠምዶ መቆየት የለበትም።ሌሎች ሃላፊነቶች ያሉበት እንደመሆኑ ሌሎች የደኅንነትን የፀጥታ ሀይሎች ሃላፊነታቸውን የሚወጡበት ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል።
የሰላም መጠበቅ ጉዳይ በቀጣይ ለሚመዘገቡ ስኬቶች ብቻም ሳይሆን የተመዘገቡትን ስኬቶች ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።የኢህአዴግ ምክር ቤት በሚያደርገው ግምገማ የህግ የበላይነት ማስጠበቅ ላይ በትኩረት ሊዳስሰውና ዘላቂ መፍትሄ የሚሆን አቅጣጫ ሊያስቀምጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2011