ስትሄድ ያደናቀፈህ እንቅፋት ስትመለስም ከደገምህ እንቅፋቱ ዕቃው ሳይሆን አንተ ነህ፤ ብልህ ከሰው ከሌላው ችግር ይማራል ሞኝ ደግሞ ከራሱ የሚል የቆየ አገራዊ ብሂል አለ። መልዕክቱ ግልጽ ነው። ስህተትን አትድገም ወይም ለመማር ራስህ ላይ እስኪደርስ አትጠብቅ ነው የሚለው። እኒህን ብሂሎች እኛ ኢትዮጵያውያን በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት አጥብቀን ልንረዳቸው ብሎም ልንተገብራቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።
እንደ አገርና ሕዝብ ከሌላው ስህተት ከምንማርባቸው ጉዳዮች አንዱ የቅርባችን የሩዋንዳ ጉዳይ ነው። የጥላቻ ቅስቀሳ፣ ሚዲያን በኃላፊነት አለመጠቀም ሩዋንዳንና ሕዝቦቿን ትልቅ ዋጋ እንዳስከፈላቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። በጭፍን ጥላቻ የተሞሉ ኃይሎች መገናኛ ብዙኃንን በተለይም ኤፍ.ኤም ሬዲዮዎችን በመጠቀም በከፈቱት የጥፋት ዘመቻ ከ800ሺ በላይ ርዋንዳውያን በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ልጆች ያለወላጅ አዛውንቶች ያለ ጧሪ ቀርተዋል። ቤተሰብ ተበትኗል፤ አገርም ፈርሷል። የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ከእዚህ እልቂት ምንም አላተረፈም። እልቂቱ ያተረፈው ነገር ቢኖር የዕድሜ ልክ ኀዘን፣ ሰቆቃ እና ጸጸት ብቻ ነበር።
ሰሞኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በተገኙበት የርዋንዳው ዘር ፍጅት
የታሰበውም በዚህ መንፈስ ነው። ምነው ባልተደረገና ከዚህ በኋላ የትም መቼም መደገም አይኖርበትም በሚል ጥልቅ ስሜት! በዛ ወንጀል በቀስቃሽነትም ሆነ በፈጻሚነት የተሳተፉ ሰዎች ለዓለም አቀፍ ሚዲያ በተደጋጋሚ እንደገለጹት፣ በጭፍን ጥላቻ መጓዝ መጨረሻው ጨለማ ነው። ሕዝብን አስፈጅቶና አጨራርሶ የሚገኝ ፖለቲካዊ ትርፍ የለም፤ አይኖርምም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የሚስተዋለው ሁኔታ እኛ ኢትዮጵያውያን ከርዋንዳውያን ተምረናልን ወይ? ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን ነው። ልዩነቶቻችንን አቻችለንና እንደ ውበት ተላበስን አሁን በፈነጠቀው ለውጥ ዴሞክራሲያችንን ማበልጸግ፣ ልማታችንን ማፋጠንና ለልጆቻችን የተሻለ አገር የማውረስ ተስፋ ቢኖረንም ይህን ተስፋችንን ለማጨለም ጥቂቶች በተቀናጀ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ እየታየ ነው።
ሰባራና ሰንካላ መንስዔዎችን በመደርደር ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳ መቀስቀስ፣ ትንሽ ግጭት ስትነሳ እሷኑ በማራገብና አንዱ ሕዝብ በአንዱ ላይ እንደተነሳ በማስመሰል ገጽታውን ሌላ መልክ ማላበስና የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት እንዲኖር መሯሯጥ በስፋት እየስተዋለ ነው። በሳል፣ ነገሮችን ቆም ብሎ የሚመረምርና ለሰላም የቆመ ታላቅ ሕዝብ ባይኖረን ኖሮ ታቅዶ እንደሚከናወነው የጥፋት ዘመቻ የአገራችን ገጽታ ሌላ በሆነም ነበር።
ከፊታችን ተደቅኖ ቁም ስቅላችን የሚያሳንን ድህነት እንዳንዋጋና የተጀመረው ተስፋ ሰጪ ለውጥ ፍሬ እንዳያፈራ መልካቸውን በመለዋወጥ የጥፋት ኃይሎች የእልቂትና የፍጅት አጀንዳዎችን መፈበርካቸውን እንዳላቆሙ ከሰሞኑ በሰሜን ሸዋና ከሚሴ አካባቢ ከተፈጠሩ ችግሮች መረዳት ይቻላል። የእነዚህ ኃይሎች ዋነኛ ዓላማ ጥቃቅን ችግሮችን አራግበው ችግር በመፍጠር ለዘመናት ተከባብረውና ተወዳጅተው የኖሩ ሕዝቦችን ማፋጀት ነው። ይህንንም ለመተግበር ማህበራዊ ሚዲያውን በሰፊው ሲጠቀሙ ይስተዋላል።
ሀሰተኛ ፎቶዎችን በመጠቀም ስሜትን አጋግሎ ግጭቱን ለማስፋፋት መሞከርና እገሌ የተባለው ብሔር እገሌ ላይ እንዲህ አድርጓል ወይም ለማድረግ አስቧልና ቅደመው የሚሉ መልዕክቶች የእነዚህን ኃይሎች ፍላጎትና ምኞት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። እውነታው ግን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ተዋደውና ተፋቅረው በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታትን በፍቅር የኖሩ መሆናቸው ነው።
በተለያዩ ምክንያቶች በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ ግጭቶች ቢስተዋሉም በታሪካችን የትኛውም ሕዝብ የትኛውንም ሕዝብ በድሎና አጥቅቶ አያወቅም። ይልቁኑ በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ለአካባቢው እንግዳ ለሆነ ሰው ሽፋንና ከለላ በመሆን ነው የሚታወቀው። ስለሆነም ችግሩ የአገራችን ዕድገትና መረጋጋት እንዲሁም የሕዝቦችን አብሮነት የማይፈልጉ የጥቂት ኃይሎች መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ርዋንዳውያንም የተጨፈጨፉትም በእንዲህ ዓይነቱ ሴራና ቅስቀሳ መሆኑም ሊሸፈንብን አይገባም።
ብልህ ከሌላው ይማራል እንደሚለው ብሂል ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ መጨረሻው ከርዋንዳውም የከፋ ስለሚሆን መንግሥት በጥፋት ላይ የተሰማሩ ኃይሎች ላይ የማያዳግምና አስተማሪ እርምጃ ሊወስድ ሕዝባችንም የጥፋት ኃይሎቹ ሴራ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨትና እልቂትን መጋበዝ መሆኑን ተረድቶ የሴራቸው ተባባሪ ባለመሆን ያጠላብንን የጥፋት ዳመና በአስተማማኝ ሁኔታ ገፈን ልንጥለው ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 5/2011