ሁሉም በሽተኛ ሁሉም ራሴን ባይ
በቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ
ይላል ዘለሰኛው፤ ከግጭት ወሬ ራሳችንን ራቅ ብናደርግም ጎትቶ የሚያስገባን አይጠፋም፡፡ በየመንገዱም ሆነ በየእምነት ቦታው ብቻ የትም ቢኬድ ዜጎች ወቅታዊ ሁኔታው አሳስቧቸዋል፡፡ ዜጎች ‹‹ኧረ ለልጆቻችን ማስተዋልን ስጣቸው፤ ታውረው እንዳይፋጁ … ልቦናቸውን መልስላቸው›› እያሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ወጣቶች ከስሜት ተላቀው በምክንያታዊነት መጓዝ እንዳለባቸው ለማሳሰብ ነው፡፡
ቀደምት አባቶቻችን ነገሮችን በእርጋታ ነው ይመለከቱ የነበሩት፡፡ የዘመኑ ሰው ምን ነው እንዲህ አይነት እርጋታ አጣ? ስሜት አዕምሮውን ተቆጣጥሮት ተማርኩ ቢልም ትምህርቱ ከስሜታዊነት ተላቆ ለማመዛዘን እንኳ ሲያቅተው እጅግ ይገርማል። ዕውቀት በተስፋፋበት በዚህ ዘመን የዘመኑ ትውልዶች ማን ምን ለምን እንደተናገረ በትክክል ሳያረጋግጡ የተናገረውን በማንሻፈፍ መሸርደድ፣ ሰውን ማዋረድ እና መዘርጠጥ እንደ አዋቂነት እየተመለከቱት ነው፡፡ ይህ ተገቢና ምክንያታዊም አይደለም። ስለዚህ መታረም አለበት፡፡
ፍቅርን ጥላቻ አጠልሽቶት እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በሚል አጓጉል መሽቀዳደም እየደረሰ ያለው ጉዳት፤ በተለይ በምስኪን ድሃ ኢትዮጵያውያን ላይ እያስከተለ ያለው የህይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ እና የስነልቦና ጫና እንዲሁም የኢኮኖሚ ኪሳራው ሲታሰብ ያሳዝናል፡፡ ግጭት ወለድ መፈናቀሎች ማቆሚያ አጥተዋል፡፡ ይህ ችግር መቆም አለበት፡፡ ስሜታዊነት ሲጎዳን እንጂ ሲጠቅመን አላየንምና ዜጎች ሰከን ማለትና ከስሜት ወጥተው በምክንያታዊነት መንቀሳቀስ አለባቸው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡
ከሶማሌና ኦሮሚያ ክልል ስለተፈናቀሉት ተወርቶ ሳያልቅ እንደገና በጌዴዮ የደረሰው እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ በቅርቡም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የተከሰተው ግጭት መከሰት ያልነበረበት ነው፡፡ በዚህም የተጎዱ ንጹሃን ዜጎች ናቸው፡፡ ከግጭትና ረብሻ ምንም አይገኝምና ሰከን እንበል ማለታችን ለዚሁ ነው፡፡
የሰሞኑን ሳይጨምር በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአስቸኳይ ድጋፍ ፈላጊ ተፈናቃይ መኖራቸው ተገልፆ እርዳታ ሲሰባሰብ ከመሰንበቱ በተጨማሪ ‹‹አሁን ተረጋጋን››
ሲባል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ግጭት መከሰቱ አነጋጋሪ ነው፡፡ የግጭቱና መፈናቀሉ ምክንያት የፖለቲካ ትርፍም ለማግኘት ይሁን ኢኮኖሚውን ለማሽመድመድ ለሃገርና ለዜጎች የሚያትርፈው ነገር ቢኖር ጉዳት ነው፡፡ በድሃ ሀገርም ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠር ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህ ችግሮች በቀጣይነት እንዳይደገሙ መስራትና ከስሜታዊነት በመውጣት ምክንያታዊነትን ማጎልበት ተገቢ ነው፡፡
መቼም በሁሉም አዕምሮ ውስጥ ህግ አለ፡፡ የትኛውም ጤነኛ ሰው ሰዎች እንዲሰቃዩ እና እንዲሞቱ ፍላጎት አይኖረውም፡፡ ይህ እንዲሆን በገዛ እጁ ካደረገ መቼም ሊሆን የሚችለው በገንዘብ ፍቅር ወይም በስልጣን ፍላጎት ስሜታዊነት አውሮት የሚፈጥረው ችግር ነው፡፡
አንድ ሰው በስልጣን ላይ ለመቆየት፣ ስልጣኔን ለምን አጣሁ ብሎ ወይም ወደ ፊት ስልጣን ለማግኘት አሲሮ ሰዎች እንዲፈናቀሉ፤ እንዲጎሳቆሉ አልፎ ተርፎ እንዲሞቱ በዚህም መንግስት ላይ ዜጎች እንዲማረሩ እና እንዲነሱ ማድረግም ራሱ በስሜት ራስን አሳውሮ የሚፈፀም ካልሆነ በስተቀር ማመዛዘን የሚችል ሰው ይህን አያደርግም፡፡
በስሜት የማይመራ እና በምክንያት ላይ የሚመሰረት ግለሰብ ጤነኛ በመሆኑ ሰዎችን ለመጉዳት የሚያነሳሱ ቅስቀሳዎችን አያከናውንም፡፡ ሰዎች እንዳይጎዱ ይከላከላል፡፡ አሁን ግን ሁሉም ባይባል እንኳን ቁራቸው ሰፋ ያለ ሰዎች የብዙዎችን ሰላም እየነሱ ነው፡፡
ሰዎች በሰዎች ላይ እንዲነሱ ይመክራሉ፣ ዘርን ማዕከል አድርጎም ሆነ በሌላ መንገድ አንዱ ሌላውን እንዲያጠፋ የሚመክረው እና የሚያነሳሳው ሰው ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ አስደናቂው ጉዳይ ደግሞ ይህን የሚያደርጉ ሰዎችን የሚደግፍ እና እያራገበ የሚያቀጣጥሉ ሰዎች ቁጥርም ትንሽ አለመሆኑ በእጅጉ ያሳስባል፡፡
የዘመኑ ትውልድ መከባበር፣መደማመጥ፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ወገኖቹ መሆናቸውን አምኖ ወንድሞቼን እህቶቼን አልጎዳም ብሎ ጠንካራ አቋም ይዞ ለየትኛውም ዓላማ ማንም ኢትዮጵያዊ መጎዳት የለበትም ብሎ መንቀሳቀስ አለበት ፡፡
‹‹ከእኔ ውጪ የማንም ሃሳብ መስማት የለብኝም፣ ማለት ትክክል አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ የፈለገውን ዓላማ ይዞ በስሜት መነዳት ለማንም አይበጅም፡፡ መታመማችንን እንረዳ፤ ከቅዠት እንውጣ፤ ሠላማችንን ለማረጋገጥ ጠንከር ብለን ተረጋግተን በምክንያታዊነት ብቻ ማንም ላይ ጉዳት እንደማይደርስ አረጋግጠን እንንቀሳቀስ መልእክታችን ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011