የደርግ አመሠራረት

የደርግ ሥርዓተ መንግሥት አመሠራረት በተለይም ባለፈው ዓመት 50ኛ ዓመቱ ነበርና(አብዮቱ) በሰፊው ተወርቶበታል። ብሔራዊውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጨምሮ ብዙ መገናኛ ብዙኃን የታሪክ ምሁራንን እና ፖለቲከኞችን እየጋበዙ ብዙ ትንታኔ አሠርተውበታል። በተለይም በእዚያ ዘመን በተሳታፊነትም ሆነ በነዋሪነት (በታዛቢነት) የነበሩ ትዝታቸውን እንዲያካፍሉ ተጋብዘዋል። ይህ ሁሉ የሆነበት ምክንያት ባለፈው ዓመት 50ኛ ዓመቱ ስለሆነ ነው። እነሆ ዘንድሮ ደግሞ ሥልጣን የያዘበት ዓመት (1967 ዓ.ም) 50ኛ ዓመት ነው።

ለሺህ ዘመናት የኖረው የኢትዮጵያ ንጉሳዊ ሥርዓት ከተገረሰሰ እነሆ ዘንድሮ 51ኛ ዓመት ሆነው። በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ51 ዓመታት በፊት የነበረውን አብዮት እና የደርግን አመሠራረት እናስታውሳለን። ከእዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የእዚህ ሳምንት ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውስ።

ከ30 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ሰኔ 19 ቀን 1987 ዓ.ም በአዲስ አበባ የወቅቱ የግብጹ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ የግድያ ሙከራ ተደረገ። ሙባረክ ወደ አዲስ አበባ የመጡት በወቅቱ ስያሜው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 31ኛውን መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ለመታደም ነበር። በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 2፡00 አካባቢ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሱት የግብጹ መሪ ከወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አቶ መለስ ዜናዊ ጋር ፕሮቶኮላዊ አቀባበል ተደርጎላቸው ጥይት በማይበሳው ተሽከርካሪያቸው ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉዞ ተጀመረ።

ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ገና 110 ሜትር ወጣ እንዳሉ ለረጅም ጊዜ ሁኔታውን ሲያጠና እና በዕለቱም ሲጠባበቅ የነበረው አሸባሪ ኃይል የግብጹ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ ተኩስ ለመክፈት በተሽከርካሪ መንገዱን ዘጋ። ይኼኔ በኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች እንዲቆም ተጠየቀ። ለሽብር የተዘጋጀ ነበርና አንድ የኢትዮጵያን የጸጥታ ኃይል ተኩሶ ጣለ። ቀጥሎም እየተጠጋው ያለው የፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ተሽከርካሪ ላይ አከታትሎ ተኮሰ። በእዚያው ቅጽበት ግን አንደኛው አሸባሪ ያነጣጠረውን ሳይተኩስ ከኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል በተተኮሰ ጥይት ጭንቅላቱ ሲበተን ታየ። ቀጥሎም ሌላኛው አሸባሪ አሁንም በኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል በተተኮሰ ጥይት የእግረኛው መንገድ ላይ ሲወድቅ ታየ። የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ሙባረክ ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስ የአሸባሪዎቹን ዒላማ አከሸፉት። ሙባረክም ወዲያውኑ በሰላም ወደ ሀገራቸው ሄደው፣ የኢትዮጵያን መንግሥትና የጸጥታ ኃይል አመስግነው በሰላም መድረሳቸውን አሳወቁ። ብዙ የሴራ ትንታኔዎች የተደረጉበት ሲሆን፤ እነሆ ያ ክስተት በተለያዩ አጋጣሚዎች ይታወሳል።

ከ80 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ሰኔ 19 ቀን 1937 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው የተመራ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ላይ፣ በሳንፍራንሲስኮ የጦር መታሰቢያና ኪነ ጥበብ ማዕከል ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የቃል ኪዳን ሰነድ (የመመስረቻ ስምምነት /ቻርተር) ፈረመ። ቻርተሩ ከሚያዝያ 17 ቀን 1937 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ወራት ያህል ውይይት ሲደረግበት ከቆየ በኋላ ለመጨረሻ የፊርማ ስምምነት ክፍት ሆኖ ፊርማው የተጀመረው በእዚሁ ቀን (ሰኔ 19 ቀን 1937 ዓ.ም) ነበር።

ከ101 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ሰኔ 20 ቀን 1916 ዓ.ም ሁለገቡ አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) ተወለዱ። በልጆች ፕሮግራም የታወቁት እና ለልጆች ፕሮግራም አርዓያ የሆኑት አባባ ተስፋዬ፤ ከ60 ዓመታት በፊት ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም የልጆች ጊዜ የተሰኝ ፕሮግራም እንዲኖር ሃሳቡን አቅርበው በማፀደቅ የራሳቸውን የአቀራረብ መንገድና የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተዋወቃቸውን ዝግጅታቸውን ለ42 ዓመታት በአባትነት መርተዋል። ፕሮግራማቸውን ሲጀምሩ ‹‹ጤና ይስጥልኝ ! … የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች እንደምናችሁ ልጆች!›› እያሉ አቅርበዋል። በበርካቶች ዘንድ የሚታወስና የልጆች ፕሮግራም አርዓያ ሆኖ ቀጥሏል።

ከ89 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ሰኔ 20 ቀን 1928 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ወጣት አርበኞች የመሠረቱት ‹‹የጥቁር አንበሳ ጦር›› ነቀምት፣ ወለጋ አካባቢ ሰፍሮ በነበረው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር አየር ኃይል ላይ ጥቃት ከፍቶ በእሳት አወደመው። የጥቁር አንበሳ ጦር በፋሽሽት ጣሊያን ወረራ ወቅ በአርበኝነት የተሳተፉ የሆለታ ገነት ጦር ምሩቃን እና በውጭ የተማሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን የመሠረቱት ፀረ ፋሽሽት እንቅስቃሴ ነው። በጣሊያን ላይ ዘመናዊ የጦር ውጊያ በማሳየት ብቻ ሳይሆን በጥንታዊ መንገድ ለሚዋጋው የኢትዮጵያ ገበሬ አርበኛ ዘመናዊ የውጊያ ስልትን በማስተማር የጥቁር አንበሳ ጦር ያደረገው አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም። የሆሎታ ገነት የጦር ትምህርት ቤት ፋሽስት ጣሊያን ከሀገራችን ተባርሮ ንጉሰ ነገስቱ ተመልሰው ከመጡ በኋላ በ1935 ዓ.ም እንደገና ተመሰረተ። የጦር ትምህርት ቤቱ በአፍሪካ አንጋፋው በዓለማችንም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊት ከተመሠረቱ ጥቂት የጦር ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ነው።

ከ5 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት 3፡00 አካባቢ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል ተሰማ። ከእናቱ ወይዘሮ ጉደቱ ሆራ እና ከአባቱ ከአቶ ሁንዴሳ ቦንሳ በ1978 ዓ.ም በአምቦ የተወለደው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ፤ በሙዚቃዎቹም የኦሮሞን ትግል የሚገልጹ መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ የኖረ ነው። ሃጫሉ ከዘፈን ባሻገር ለኦሮሞ ሕዝብ መብትና ነፃነት በመታገሉ ለኦሮሞ ሕዝብ ዘፋኝ ብቻ ሳይሆን እንደ ታጋይ ይታያል። አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን፤ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ለብዙዎች ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ተገሏል። እነሆ ሥራዎቹና ታሪኩ ግን ሲታወስ ይኖራል። የአርቲስት ሃጫሉን ድንገተኛ ግድያ ክስተቶች በተመለከተ ዝርዝሩ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም በታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ይገኛል።

አሁን ወደ ደርግ አመሠራረት እና የአብዮቱ 51ኛ ዓመት ጉዳዮች እንሂድ።

ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት፣ በተለይም ለግማሽ ክፍለ ዘመን የኖረውንና በኢትዮጵያ የመጨረሻ የሆነውን የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ንጉሣዊ ሥርዓት ያስወገደው ወታደራዊው ደርግ የተመሠረተው በእዚህ ሳምንት ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም ነው።

የታሪክ ባለሙያዎች ደርግ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን ያስወገደበትን መንገድ ‹‹አዝጋሚው መፈንቅለ መንግሥት›› ይሉታል። ምክንያቱም አንድ ጊዜ አይደለም ያስወገዳቸው። የደርግ ምሥረታ ራሱ አንድ ጊዜ አይደለም። ሰኔ 21 ቀን በይፋ የተመሠረተበት ይሁን እንጂ ወታደሮቹ ሃሳቡን ከጠነሰሱትና የውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴውን ከጀመሩት ቆይተዋል።

ከታሪክ ባለሙያው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847-1983››፣ ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን›› መጽሐፎች እና ከተለያዩ ድረ ገጾች ባገኘናቸው መረጃዎች ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም የተመሠረተውን የደርግ መንግሥት ታሪክ እንዲህ እናስታውሳለን።

ደርግ የሚለው ቃል ከግዕዝ የተወሰደ ሲሆን፤ ትርጓሜውም ቡድን ወይንም ኮሚቴ ማለት ነው። ይህን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ለሥርዓቱ መገለጫነት የተጠቀመው ግለሰብ ሻለቃ ናደው ዘካሪያስ ሲሆን ቀኑም፤ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም ነበር።

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የአራተኛ እግረኛ ክፍለ ጦር መምሪያ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ መለዮ ለባሾች በየካቲት ወር ስለፈነዳው አብዮት ከሰኔ 19 ጀምሮ ውይይት ማካሄድ ጀመሩ። ደርግ በዝቅተኛ መኮንኖች (ከኮሎኔል ማዕረግ በታች የሆኑት ማለት ነው) ከተመሠረተ በኋላ በእዚያው ቀን ሻለቃ መንግስቱ ኃይለማርያም የደርግ ሊቀመንበር በመሆን ተመረጡ።

በ1953 ዓ.ም የተሞከረበትን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ፤ የንጉሱ ሥርዓት የተለያዩ ጥገናዎችን ሲያደርግ ቢቆይም በ1966 ዓ.ም አብዮቱ ፈነዳ። አብዮቱን የጀመረው የወታደሩ መደብ ሲሆን፤ ነገሌ እና ሲዳሞ ላይ ሰፍሮ የነበረው የምድር ጦር ሠራዊት አዛዥ መኮንኖቻቸውን ሲያግቱ ይጀምራል። ጉዳዩ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚኖሩ የሠራዊቱ ክፍሎች ድጋፍን በማግኘቱ በወታደሩ መደብ ከመዛመቱም ባሻገር ወደ ተቀረው ዜጋም በመዝለል አብዮቱ ተቀጣጠለ። አሁንም የንጉሱ መንግሥት ብዙ ጥገናዎችን እያደረገ ነው።

የዘውዱ መንግሥት አብዮቱን ለማርገብ የተለያዩ ለውጦችን አድርጓል። ለምሳሌ አክሊሉ ሃብተወልድን አንስቶ እንዳልካቸው መኮንንን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጓል። ለወታደሩ ልዩ ደመወዝ ጭማሪ አድርጓል፤ ሊተገበር የነበር የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ ለውጥ በተነሳበት ተቃውሞ ምክንያት አስቁሟል። ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ሞክሯል። ይሄ ሁሉ ግን የወታደሩን አዝጋሚ መፈንቅለ መንግሥት ማስቀረት አልቻለም።

ሰኔ 21 ቀን በአራተኛ ክፍለ ጦር የተመሠረተው ደርግ የቀድሞውን ባለሥልጣናት ማሰር ጀመረ። ከሐምሌ 2 ቀን 1966 ዓ.ም ጀምሮ እስረኞቹ ጋዜጣና ሬዲዮ እንዳያስገቡ ተከለከሉ። ጠያቂዎች እስረኞችን የሚጎበኙት በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ ጠዋት ብቻ ነበር። ከሐምሌ 9 ቀን 1966 ዓ.ም በኋላ እሥረኞች ከነበሩበት የጎፋ ሠፈር ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ተዛወሩ።

እንዲህ እንዲህ እያለ የቆየው ደርግ፤ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሱን ገርስሶ መንግሥት መሆኑን በይፋ አወጀ። አሁን ደርግ የሀገሪቱ መንግሥት ሆኗል። ንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣን መውረዳቸውን፣ ሕገ መንግሥቱ መሻሩን፣ ፓርላማው መዘጋቱን አወጀ።

አላግባብ የበለጸጉ፣ ፍርድ ያጎደሉ፣ አስተዳደር የበደሉ የተባሉ የቀድሞ የንጉሡ ባለሥልጣናት ሁሉ በጦር ፍርድ ቤት የሚዳኙ መሆኑን ደርግ በአዋጅ አስታወቀ። በእዚሁ ዕለት የንጉሡ የልጅ ልጅ እና የባሕር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ ተይዘው ከእሥረኞቹ ጋር ተቀላቀሉ። እንዲህ እንዲህ እያለ ደርግ የታሳሪዎችን ቁጥር እያበዛው መጣ። በመጨረሻም፤ ደርግን ክፉኛ ያስወቀሰው 60 የጦር መኮንኖችንና ባለሥልጣናትን የረሸነበት ድርጊት ተፈጸመ።

ደርግ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም በአራተኛ ክፍለ ጦር በይፋ ተመስርቶ፣ መስከረም 2 መንግሥት መሆኑን አውጆ፤ ሀገር ባስተዳደረበት ዘመን በጨካኝነት የተገለጸውን ያህል፤ የሀገር ዳር ድንበር በማስከበርና የውጭ ወራሪን አፈር ድሜ በማስበላት ይታወቃል። ከእዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ታሪካዊ አዋጆችን አውጇል።

በየካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም «የገጠር መሬት አዋጅ» እና ሐምሌ 19 ቀን 1967 ዓ.ም «የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ» በመባል የሚታወቁት ሁለት አዋጆች ተጠቃሽ ናቸው።

1966 ዓ.ም ተከትሎ የመጣው ለውጥ ቀደም ሲል የነበረውን የርስት ጉልት ግንኙነት በመሻር በመሬት ላይ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። የደርግ ሥርዓት ይከተል በነበረው የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም በመመራት ኢኮኖሚውን የሚመሩትን ዋና ዋና ነገሮች ከግል ባለቤትነት ወደ ሕዝብ ባለቤትነት አሸጋግሯል። መሬትም የገጠር መሬትን የሕዝብ ሀብት ለማድረግ በሚል አዋጅ ቁጥር 31/67 የሕዝብ ሀብት በሚል ታወጀ። አዋጁም መሬት አይሸጥም አይለወጥም የሚለውን ጥብቅ የሆነና የመሬት ጉዳይን ከሌሎች ንብረቶች የሚለየውን ገደብ ይዞ ብቅ ብሎ ነበር።

የገጠር መሬትን የሕዝብ ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 31/67 አንቀጽ 5 አንድ የመሬት ተጠቃሚ በይዞታ የያዘውን መብት መሸጥ፣ መለወጥ፣ በስጦታ ማስተላለፍ፣ በማስያዝ፣ በወለድ አግድ ወይም በሌላ ሁኔታ ማስተላለፍ እንደማይችል ገደብ ያስቀምጣል። ደርግ፤ ንጉሳዊ ሥርዓቱን ከመገርሰሱ ባሻገር በእነዚህና በሌሎች አዋጆች ይታወሳል።

የአብዮቱን 50ኛ ዓመት አስመልክቶ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በነበረው ቆይታ እንደገለጹት፤ የአብዮቱ መነሻ ምክንያቶች ነባራዊ ሁኔታዎች እና ሥነ ልቦናዊ ሁኔታዎች ናቸው። ነባራዊ ሁኔታዎች ማለት በንጉሣዊ ሥርዓቱ አገዛዝ ዘመን የነበሩት ኢፍትሐዊ አሰራሮች ማለት ነው። የጭሰኛና ባላባት ሥርዓት መኖሩ አንዱ ነው። ‹‹መሬት ለአራሹ›› የሚለውን የተማሪዎች እንቅስቃሴ የፈጠረውም ይሄው አሠራር ነው። አገዛዙም ፍጹም ንጉሣዊ ብቻ መሆኑ አብዮቱን ወለደ።

የሥነ ማህበረሰብ ተመራማሪው የራስ ወርቅ አድማሴ (ዶ/ር) ‹‹አብዮት›› የሚለውን ቃል ሲያብራሩ፤ የግብርና አብዮት ነበር፣ የኢንዱስትሪ አብዮት ነበር፣ አብዮት ሲባል ለፖለቲካ እንዳልሆነ ገልጸው፤ የ1966ቱ አንድ የአብዮት አይነት እንደሆነ ይናገራሉ።

ባለፈው ዓመት የአብዮቱ 50ኛ ዓመት ሲታወስ ዋናው ነገር ምን እንማር? የሚለው እንደሆነ ብዙዎች አስተያየት ሲሰጡበት ነበር። የአስተያየቶች ይዘት ሲጠቃለል፤ የ1966 አብዮተኞች ለትምህርት ወደ ውጭ ሀገራት ሲሄዱ የሰለጠኑ ሀገራትን ተመለከቱ፤ ከሀገራቸው ሁኔታ ጋር ሲያነጻጽሩት ሰማይና ምድር ሆነባቸው። ለውጡን ቢመኙትም ዳሩ ግን የሀገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነበርና ድንገተኛ ንቃት ሆነ። ከአብዮቱ በኋላ የመጣው መንግሥትም የተፈለውን ዴሞክራሲ ሳያስገኝ ቀረ። በመሆኑም ከእዚያ ስህተት በመማር ከእርስ በእርስ መጠላለፍና መጠፋፋት በመላቀቅ ወደ ሰላምና ዴሞክራሲ መሄድ እንደሚያስፈልግ ብዙዎች መክረዋል።

ወደ ታሪክ ትውስታችን ስንመለስ፤ የኢትዮጵያን ንጉሣዊ ሥርዓት ለማስወገድ የተጀመረው አብዮት እነሆ 50 ዓመት አለፈው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You