ኮንጎ እና ሩዋንዳ የሰላም ስምምነት በዋሽንግተን ተፈራረሙ

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን አስከፊ ግጭት ለማስቆም የሚያስችል የሰላም ስምምነት በዋሽንግተን ተፈራረሙ። በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት የተፈረመው ይህ የሰላም ስምምነት አሜሪካ ከኮንጎ ብርቅዬ ማዕድናት ተጠቃሚ እንድትሆን ሊያደርጋት እንደሚችል ተገልጿል።

በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት የተደረሰው የሰላም ስምምነት በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊከ ኮንጎ የሚዋጉ ታጣቂ ቡድኖች “ውጊያ ማቆም፣ ትጥቅ መፍታት እና ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስን ያለመ” ነው። ስምምነቱን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎች አልወጡም።

በቀጣናው አሸማጋይነት የተጀመሩ የሰላም ስምምነቶች ከዚህ ቀደም ቢከሽፉም የአሜሪካ እና የኮንጎ መሪዎች ስምምነቱን ከአሁኑ “ትልቅ ድል” ሲሉ አሞካሽተውታል። “ዛሬ ግጭቱ እና ውድመቱ ተቋጭቷል። መላው ቀጣና አዲስ የተስፋ እና የድል ምዕራፍ ጀምሯል” ሲሉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዓርብ ዕለት ተናግረዋል።

ትራምፕ፤ ምክትል ፕሬዚዳንታቸው ጄዲ ቫንስ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ማርኮ ሩቢዮ እንዲሁም ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ የተውጣጡ ልዑካን በተገኙበት ቢሯቸው በሰጡት መግለጫ የሰላም ስምምነቱን “አስደናቂ ድል” ብለውታል።

ስምምነቱ የተፈረመው በሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አማካኝነት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ነው። ትራምፕ ከዚያ በኋላ በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ባኖሩበት ወቅት “ትልቅ ስኬት ነው” ብለዋል። የኮንጎ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤትም “ለፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ በ30 ዓመት ከታዩት የበለጠ ሌላ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት” ሲል የሰላም ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት መግለጫ አውጥቷል።

ምንም እንኳን ቀኑ ባይገለጽም የኮንጎው ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ እና የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ወደ ዋሽንግተን አቅንተው ከትራምፕ ጋር እንደሚገናኙ ተነግሯል። በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት በተባባሰበት ወቅት ኳታር ይህንን ለማርገብ ከጥቂት ወራት በፊት የሽምግልና ጥረት መጀመሯን ስለ ድርድሩ የሚያውቁ ዲፕሎማት ተናግረዋል። ኳታር ወደ ሁለቱም ሀገራት ልዑካን የላከች ሲሆን፤ የኮንጎ እና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንቶች ዶሃ ላይ ከተገናኙ በኋላ በአሜሪካ የሚደገፍ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል ሲሉ እኝሁ ዲፕሎማት ገልጸዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት የኤም 23 አማጺያን የምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መዲና ጎማ፣ የቡካቩ ከተማ እና ሁለት አየር ማረፊያዎችን ጨምሮ ሰፊ ግዛት መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ለአስርት ዓመታት የዘለቀው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦርነት የበለጠ እንዲባባስ አድርጎታል። በቅርቡም በተደረጉ ውጊያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ግዛቶቹን ያጣው የኮንጎ ማዕከላዊ መንግሥት አሜሪካ ርዳታ እንድትሰጠው ጠይቋል። በዚህም አሜሪካ የደኅንነት ዋስትና የምትሰጠው ከሆነ በምላሹ ወሳኝ የሆኑ ማዕድናትን ለመስጠት መጠየቁ ተዘግቧል። የምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግዛት ኮልታን ጨምሮ በዓለም አቀፉ የኤሌክትሪክ ኢንዱስትሪ አስፈላጊ የሆኑ የማዕድን ግብዓቶች የበለፀገ ነው። ሩዋንዳ ኤም23 የተሰኘውን ታጣቂ ቡድን እንደምትደግፍ በርካታ መረጃ የቀረበባትን ክስ አትቀበለውም።

ሩዋንዳ፤ በኮንጎ ወታደሮቿን ያስገባችው በአብዛኛው ከሁቱ ብሔር የተውጣጣና በአውሮፓውያኑ 1994 የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ ግንኙነት ያለው ኤፍዲኤልአር (Democratic Forc­es for the Liberation of Rwanda) የተባለው ታጣቂ ቡድን የጋረጠውን ስጋት ለመከላከል ነው ትላለች። ሩዋንዳ በበኩሏ ኤፍዲኤልአር የተሰኘውን ቡድን ኮንጎ ትደግፋለች ስትል የምትከስ ሲሆን ኮንጎ ይህንን አትቀበለውም። የኮንጎ ተደራዳሪዎች የሩዋንዳ ወታደሮች ከኮንጎ በአስቸኳይ መውጣታቸው በስምምነቱ እንዲካተት ጫና ማድረጋቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በኮንጎ ምድር 7 ሺህ ወታደር ያላት ሩዋንዳ ይህንን ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆነች ተገልጿል። የሩዋንዳ ወታደሮች ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለቆ መውጣት ለሁለቱ ሀገራት አከራካሪ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው። ስምምነቱ ሊፈረም ጥቂት ሰዓታት ሲቀረው የትሽሴኬዲ ጽሕፈት ቤት ስምምነቱ የሩዋንዳ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ የሚያስችል ነው ብለዋል። ሆኖም የተፈረመው ስምምነት ሙሉ ዝርዝር ይፋ እስካልሆነ ድረስ በርካታ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ አያገኙም ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You