
አዲስ አበባ፡– ተመራቂ ተማሪዎች ሀገራችሁን በታማኝነት ማገልገል ይጠበቅባችኋል ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፤ ተመራቂዎች ስኬታችሁ የሚለካው ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቦቿ በምታደርጉት አስተዋፅዖ ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ75 ዓመታት ሲመራመር ሲያስተምር የኢትዮጵያ አዕምሮ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ልህቀት ብቻ ሳይሆን የጥበብ፣ የታሪክና ቅርስ ማኅደር ጭምር ስለመሆኑም አንስተው፤ ለሀገር ውስጥ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ዜጎችን በመሳብ የእውቀት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ መሆኑንም አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራውን ይበልጥ በማጠናከር ተወዳዳሪና ተመራጭ ለማድረግ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ተመርቃችሁ ወደ ሕዝቡ ስትቀላቀሉ የምትቀላቀሉት ዓለም ተለዋዋጭ ጂኦ ፖለቲካ እና ጂኦ ኢኮኖሚክ በመሆኑ ይህንን በመረዳት ተስፋ ሳትቆርጡ ሀገራችሁን ለማገልገል ዝግጁ ልትሆኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዓለም አቀፍ ችግሮች በመበራከታቸው ተስፋ ሳትቆርጡ የኢትዮጵያን ፍጎላት እና ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም ልትሠሩ እንደሚገባ አመልክተው፤ ስኬታችሁ የሚለካው ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቦቿ በምታደርጉት አስተዋፅዖ ነው ብለዋል፡፡
በጠንካራ የትምህርት ሀብት በጥበብ የተሠራችሁ ተመራቂዎች የዓመታት ድካማችሁንና ልፋታችሁን በተግባር ለማዋል ዝግጁ መሆን አለባችሁ ብለዋል።
በሥራ ዓለም የሚኖር ቆይታ የዓለምን ተለዋዋጭ ሁኔታ በመረዳት የኢትዮጵያን ፍላጎትና ብሔራዊ ጥቅም መሠረት በማድረግ ሀገራችሁን በታማኝነት ማገልገል ይጠበቅባችኋል ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ ሁሉን መርምሩ መልካሙን ግን ያዙ ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ የሚገኘውን የዘመናት መልዕክት በማንሳት ለተመራቂዎች የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዘንድሮ የተማሪዎች ምረቃ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ከሆነ በኋላ የመጀመሪያ የምረቃ በዓል መሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
በዚህ ሂደት ዩኒቨርሲቲው አሠራሩን በማሻሻል፣ የመማር ማስተማር ሥራውን ለማጠናከር ባካሔደው የሪፎርም ሥራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።ዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከልነቱን ለማስጠበቅና ለማላቅ የተማሪዎችን ስኬት የሚያግዙ እና የመምህራንን ብቃት ከፍ የሚያደርጉ ርምጃዎች በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የጀመረው የራስ ገዝ አስተዳደር የአካዳሚ ነፃነቱን የመለሰለት መሆኑን አንስተው፤ የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ እና የጥናት ጽሑፎችን በማዘጋጀት የልህቀት ማዕከልነቱን አጠናክሮ እያስቀጠለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ የትምህርት ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉ ዩኒቨርሲቲው ያለውን ላቅ ያለ አፈፃፀም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ጉልህ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲውን ዲጂታል ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም ስድስት ኪሎ የሚገኘውን ዋና ግቢ ስማርት የማድረግ እና የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልንም የዲጂታል ሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በ2017 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረቃችሁ ተማሪዎች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ስጦታዎች ናችሁ ብለዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች ለዚህ ስኬት እንድትበቁ ኢትዮጵያ ጥሪቷንና ተስፋዋን በእናንተ ላይ አውላለች ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፤ በዚህም ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጉዞ ከዳር ለማድረስ ኃላፊነት ተጥሎባችኋል ነው ያሉት።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 6ሺህ 849 ተማሪዎች ማስመረቁ ታውቋል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም