የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለቀጣይ ሀገራዊ ብልፅግና ጉዞ የማይተካ ሚና አለው!

ሀገራት ዕድገታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉት የተሳለጠ የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴ ሲኖር ነው። ኮንስትራክሽን የአንድ ሀገር እድገት አመላካች ከሚባሉ መስፈርቶች አንዱ ሲሆን፤ በሚፈጥረውም የሥራ ዕድል ሆነ በሚያንቀሳቅሰው ሰፊ ካፒታል የሀገርን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ የማነቃቃት ኃይል አለው። ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥም የኮንስትራክሽን ዘርፉ የማይተካ ሚና አለው።

ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠቷ እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታም ዘርፉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ 20 በመቶ ይሸፍናል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ካለው ሰፊ የግንባታ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ አንጻር የዘርፉ ድርሻ በቀጣይ እያደገ እንደሚሄድ ይታመናል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው የተነቃቃ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ሰፋፊ ልማቶች እየተከናወኑ እንደመሆኑ መጠን እነዚህ ልማቶች ከዳር እንዲደርሱ የኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚጫወተው ሚና መተኪያ የሌለው ነው። በተለይም ከለውጡ ወዲህ የተጀመሩ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችም የኮንስትራክሽን ዘርፉን ተሳትፎ የሚፈልጉ እና ውጤታማነቱን የሚጠይቁ ናቸው።

ኢትዮጵያ ሰፊ የቆዳ ስፋት እና ብዙ ሕዝብ ያላት ሀገር እንደ መሆኗም ሕዝብን ክሕዝብ የሚያስተሳስሩ እና ኢኮኖሚን የሚያሳልጡ የመንገድ እና መሰል መሠረተ ልማቶች ያስፈልጓታል። ገጠሩን የሀገረቱን ክፍል ከከተማው የሚያስተሳስሩ፤ ወረዳን ከወረዳ የሚያቀናጁ፤ ከተሞችን የሚያዋህዱ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የግድ የሚሉ በመሆናቸውም ባለፉት ዓመታት ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል።

በተለይም ከለውጡ ወዲህ በመሠረታዊነት የኮንስትራክሽን ዘርፉን ድጋፍ እና እገዛ የሚሹ ግዙፍ የልማት እንቅስቃሴዎች ታቅደው ወደ ተግባር በመሸጋገራቸውም ዘርፉ እንደ አዲስ ተነቃቅቷል። በጥራትም ሆነ በፍጥነት ተወዳዳሪነቱን አጎልብቷል። ቀደም ሲል በዘርፉ ደካማ አፈጻጸም ሳቢያ ይከሰቱ የነበሩ የፕሮጀክቶች መጓተት ተፈትቶ ዛሬ በጥራትም ሆነ በፍጥነት አስደማሚ የሆኑ የኮንስትራክሽን ሥራዎች በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች በተያዘላቸው ጊዜ እውን ሲሆኑ መመልከት ችለናል።

ለአብነትም መንግሥት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ግንባታዎች በስፋት በማከናወንና እና ለቱሪዝም ዘርፉ መጠናከር የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። እንደ ሀገርም መንግሥት ኢኮኖሚውን ወደ ፊት ያሻግራሉ ብሎ ተስፋ ከጣለባቸው የግብርና፣ የኢንዲስትሪ፣ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ጋር በአንድነት የቱሪዝም ዘርፉን የመሪነት ሚና እንዲኖረው አድርጓል። እነዚህ ግዙፍ የልማት ትልሞችም እየዘመነ ባለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ወደ ውጤት መሸ ጋገር ጀምረዋል።

በተለይም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተጀምረው ለውጤት የበቁት ገበታ ለሸገር፣ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ በሚል ማሕቀፍ በሀገራችን የሚገኙትን የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ መልክ እንዲለሙ እና ለቀረው ዓለም እንዲተዋወቁ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ለኮንስትራክሽን ዘርፉ መነቃቃት የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።

በተመሳሳይም በ37 ከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪዶር ልማትም ለሰፊ የኮንስትራክሽን ሥራዎችን በር የከፈተ ነው። በአራቱም የሀገሪቱ ክፍሎች እየተገነቡ ያሉት የኮሪዶር ልማቶች የኮንስትራክሽን ዘርፉን አቅም ያሳዩ እና ለሀገር እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ በጉልህ ያሳዩ ናቸው።

ሆኖም ዘርፉ የበለጠ እንዲያብብ እና የሚጠበቅበትን ሀገራዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶችን ከወዲሁ መፍታት ይገባል። ከእነዚህም መካከል በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የተበታተነ አቅም አሰባስቦ እና አዋህዶ ከመጠቀም አንጻር ያሉትን ውስንነቶች መፍታት አንዱ ነው። የፋይናንስ ተደራሽነት እና የአቅም ክፍተተም እንዲሁ ዘርፉን የሚፈትኑት ችግሮች ናቸው። ስለዚህም እነዚህን ተግዳሮቶች መፍታት ለነገ ይደር ሊባል አይገባም።

በአጠቃላይ የኮንስትራክሽኑን ዘርፍ ማዘመን ፣ በቴክኖሎጂ እና በፋይናንስ መደገፍ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው። ይህ ከሆነ ዘርፉ ለቀጣይ ሀገራዊ ብልፅግና ጉዞ የማይተካ ሚናውን እንደሚወጣ ከወዲሁ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል!

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You